Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበአዲስ አበባ ከተማ ፍጻሜ ጨዋታ 39 ተመልካቾች ለጉዳት ተዳርገዋል

በአዲስ አበባ ከተማ ፍጻሜ ጨዋታ 39 ተመልካቾች ለጉዳት ተዳርገዋል

ቀን:

  • ዘጠኙ ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ከፍተኛ ሆስፒታል አምርተዋል

በ12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ በደጋፊዎች መካከል በተከሰተ አለመግባባት ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ተመልካቾች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡

ጥቅምት 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በቅዱስ ጊዮርጊስና በኢትዮጵያ ቡና  ክለቦች መካከል በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ ከተጠናቀቀ በኋላ በተከሰተው የተመልካቾች እንካ ሰላንትያ በተፈጠረው ግብግብ በበርካታ ተመልካቾች ላይ ጉዳት በመድረሱ በተለያዩ ሆስፒታሎች ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የክለቦች የቅድመ ዝግጅት አንድ አካል በሆነው በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ የተከሰተውን ብጥብጥ ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛል፡፡

በሁለቱ ቡድኖች ግጥሚያ ወትሮም እክል የማያጣው ጨዋታ ለቀጣዩ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ‹‹በእንቅርት ላይ. . .›› እንደሚሆንበት እየተነገረ ይገኛል፡፡

ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ምንም ዓይነት ችግር እንዳይፈጠር በሚል የተመልካቾችን ሰላም ለማስከበር በዙሪያው የነበሩት የሁለቱም ክለቦች የደጋፊ ማኅበር ኃላፊዎች፣ ድካም መና አድርጎታል፡፡ የመጀመርያ አጋማሽ ከመጠናቀቁ አንድ ደቂቃ በፊት አዲሱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ፈራሚ የሆነው ኢብራሒም ፎፋና ያስቆጠራት ጎል የጨዋታውን ድባብ ቀይራዋለች፡፡ በተለይ በሁለቱ የከተማ ቡድኖች መካከል ጠብ የማያጣው የካታንጋ መቀመጫ ጎሏ መቆጠሯን ተከትሎ የጠላትነት ስሜት ባለው መንፈስ ወደ ትርጉም አልባ የእርስ በርስ ሁከትና ብጥብጥብ ለመለወጥ ብዙም ጊዜ አልፈጀበትም፡፡

ለ45 ደቂቃዎች ያህል በተቋረጠው በዚህ ጨዋታ በ39 ተመልካቾች ላይ ጉዳት ደርሶ ዘጠኙ ከፍተኛ አደጋ ስላጋጠማቸው አምስቱ ወደ ቤተዛታ ሆስፒታልና ቀሪዎቹን አራት ተመልካቾች ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል ለከፍተኛ ሕክምና እንዲወሰዱ ተደርጓል፡፡

ረብሻው ከተከሰተ በኋላ የጠብታ አምቡላንስ ባለሙያዎች ከወትሮው በተለየ የነርሶችንና የአምቡላንስ ቁጥራቸውን ለመጨመር የተገደዱበት ሁኔታ እንደነበርም የጠብታ አምቡላንስ ባልደረባ ሲስተር ምኞት ዘሪሁን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ከተጎጂዎች መካከል አራቱ የፀጥታ ኃይሎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ረብሻ ከተከሰተ በኋላ ሪፖርተር በተለያዩ ሆስፒታሎች ባደረገው ማጣራት፣ ቤተዛታ ሆስፒታል ከተወሰዱት ታካሚዎች መካከል የተወሰኑት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለተጨማሪ የሕክምና ዕርዳታ እንደተላኩ ተረጋግጧል፡፡

ሪፖርተር በዘውዲቱ ሆስፒታል ባደረገው ቆይታም መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ተመልካቾች አስተያየት ለመቀበል ባደረገው ጥረት፣ ብጥብጡ ከተከሰተ በኋላ ጉዳቱ ከስታዲየም ውጪ እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡ ተጎጂዎቹ ለረብሻው የተቃራኒ ክለብ ደጋፊዎችና የፀጥታ ኃይሎች ምክንያት መሆናቸውን ጭምር ይናገራሉ፡፡  

ሪፖርተር በረብሻው ወቅት አደጋ የደረሰባቸው ተመልካቾች መካከል በግፊት በጀርባው ወድቆ የዋለው በራስ ቅሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት እንዲሁም እግሮቹና እጆቹ ላይ ተመሳሳይ ጉዳት የደረሰበትን ተመልካች ተመልክቷል፡፡

የሁለቱም ክለቦች አመራሮችና የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነት ባልወሰዱበት በዚህ ረብሻ የተለያዩ የስፖርት ባለሙያዎች አስተያየታቸውን እየሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡

ከነዚህ አስተያየት ሰጪዎች መካከል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወቅታዊ ደረጃ እያሽቆለቆለ በመጣበት በዚህ ጊዜ፣ የተመልካቾች ቁጥር  እየጨመረ መምጣት አግራሞት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ስታዲየሞች የድብድብና የስድብ መናኸሪያ እየሆኑ ከመጡ ሰነባብተዋል፡፡ በአንፃሩ የተለያዩ ፈጠራዎችን ያካተቱና ይበል የሚያስብል ያደጋገፍ ሥርዓት በመከተል ጥሩ ጥዕመ ዜማ ያላቸውን ዝማሪዎች በመያዝ ሁለቱም የከተማ ክለቦች ምስጋና ሲቸራቸው ሰንብቷል፡፡ በዕለቱም ከጨዋታው በፊት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታዎች ወቅት የተከሰተውን ረብሻ ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ሲሆን፣ በካታንጋ መቀመጫ ቦታ ላይ ደጋፊዎችን የሚለይ አጥር ይሠራ የሚለው አስተያየት በዋናነት ይጠቀሳል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአልኮል መጠጦችን ጠጥተው ወደ ስታዲየም የሚገቡትን ተመልካቾች እንዳይገቡ ማድረግ ሌላኛው አማራጭ እንደሆነ እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች ያክላሉ፡፡  

በአዲስ አበባ ስታዲየም እግር ኳስ በመመልከት ሃያ ዓመታትን ያስቆጠረው አቶ ሰለሞን ተሾመ፣ ‹‹ከዚህ የባሰ ችግር ከመከሰቱ በፊት የክለቦቹ ደጋፊ አባላት ተገናኝተው መወያየትና ለችግሩ መነሻ የሚሆኑትን አካላት በአፋጣኝ መፍትሔ መስጠትና ለደጋፊዎቻቸው የመታወቂያ ካርድ በመስጠት መቆጣጠር ይኖርባቸዋል፤›› በማለት አስተያየቱን ለሪፖርተር ሰጥቷል፡፡

በተከታታይ ለሚደርሱ ረብሻዎች፣ ‹‹የእኛ ትክክለኛ ደጋፊዎች›› አይደሉም በማለት መከራከሪያ የሚያቀርቡት የደጋፊ ማኅበራቱ፣ በቀጣይ አባሎቻቸውን እየለዩና መታወቂያ እየሰጡና እያጣሩ ማስገባት እንዳለባቸው ከባለሙያዎች የተሰነዘረ አስተያየት ነው፡፡ ከመስከረም 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም በሁለት የክልልና ስድስት የከተማው ቡድኖች በአዲስ አበባ ዋንጫ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በዘጠኝ የውድድር ቀን ቆይታ ውስጥ ከ128,000 በላይ ደጋፊዎች የተለያዩ ጨዋታዎችን ለመመልከት መታደማቸው ተገልጿል፡፡

የዘንድሮውን የአዲስ አበባ ዋንጫ በ1 ለ0 ውጤት ያነሳው ቅዱስ ጊዮርጊስ የአሸናፊነቱን ክብር ለአምስተኛ ጊዜ ተቀዳጅቷል፡፡ ለደረጃ በተደረገው ግጥሚያ ተጋባዡ ጅማ አባ ጅፋር ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1 ለ0 በመርታት ሦስተኛ ሆኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...