Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊቅንጨራን ለመከላከል ባለድርሻዎች ተናበው እንዲሠሩ ተጠየቀ

ቅንጨራን ለመከላከል ባለድርሻዎች ተናበው እንዲሠሩ ተጠየቀ

ቀን:

በሥርዓተ ምግብና በንፅሕና ላይ የሚሠሩ ተቋማት ቅንጨራን ለመከላከል ተናበው መሥራት ካልቻሉ ለውጥ ማምጣት አይቻልም ተባለ፡፡

መቀንጨርንና የሥርዓተ ምግብ ችግርን ለመቅረፍ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ኃላፊነት ወስደው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች እርስ በርስ ተረዳድተው መሥራት ካልቻሉም መቀንጨርን ለማጥፋት የተያዘውን የሰቆጣ ስምምነት እ.ኤ.አ. በ2030 እንዳይሳካ ምክንያት እንደሚሆን የሰቆጣ ስምምነት የሴክተር ማጠናከር ኃላፊዋ ወ/ሮ ጽጌረዳ አብርሃም ገልጸዋል፡፡

‹‹አብረን አለመሥራታችንን በ2030 የተያዘውን መቀንጨርን የማጥፋት ዕቅድ እንዳይሳካ ያደርጋል፤›› የሚሉት ወ/ሮ ጽጌረዳ፣ ተቋማት ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመው፣ ትብብራቸው ትኩረት አድርገው የሚሠሩበትን ማኅበረሰብ አንድ እንዲሆን ከማድረግ ጀምሮ በፖሊሲ ደረጃም መደጋገፍን እንደሚጨምርም ተናግረዋል፡፡

ስለሥርዓተ ምግብ ያለው ግንዛቤ እያደገ ቢሆንም፣ ከውኃ እጥረትና ከአካባቢና የግል ንፅሕና መጓደል ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎች 30 በመቶ ለሚሆነው መቀንጨር ምክንያት እንደሆኑ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶችና ሕፃናት ጤና ዳይሬክተር ኤፍሬም ተክሌ (/) መናገራቸውን ከወራት በፊት ባወጣነው ዕትም መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡ በአገሪቱ ለጤና ጠቃሚ በሆኑ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ምግቦችን የሚመገቡ፣ ከስድስት እስከ 23 ወራት ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሕፃናት ከሰባት በመቶ አይበልጡም፡፡

መቀንጨርን ለማጥፋት ‹‹የፖሊሲ ሰነዶቻችን በተለይም ውኃ ላይ ያሉ ነገሮች ስለ ሚልኒውትረሽን ምንም የሚሉት ነገር አልነበረም፡፡ አሁን ግን በሰቆጣ ስምምነት ላይ “ወሽ” እንዲገባ ተደርጓል፤›› ይላሉ፡፡ የቀነጨረ ዕድገትን ለመቀነስ የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገቡ ማድረግ ብቻ ዋጋ የለውም፡፡

ስለዚህም ሥርዓተ ምግብን ለማስተካከል በሚሠራበት ማኅበረሰብ ላይ እንደ ወሽ ያሉ ፕሮግራሞች የውኃ አቅርቦት፣ የመፀዳጃ ቤት መኖር፣ የግልና የአካባቢ ንፅሕና አጠባበቅ ሥራዎችን መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ አለዚያ ግን የሚመገቡት የተመጣጠነ ምግብ በንፅሕና ጉድለት ምክንያት በሚከሰቱ በሽታዎች በተቅማጥና በትውከት መልክ እንዲወጣ፣ በሥርዓተ ምግብ ላይ የተሠራው ሥራም ዋጋ እንዲያጣ እንደሚያደርገው ወ/ሮ ፅጌረዳ ይናገራሉ፡፡

ለሕፃናት መቀንጨር ዋነኛው ምክንያት ከፅዳትና ከሥርዓተ ምግብ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሲሆኑ፣ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2017 ባወጣው መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ 38.4 የሚሆኑ ከአምስት ዓመት በታች የሚገኙ ሕፃናት የቀነጨሩ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ 9.9 በመቶ የሚሆኑ ከአምስት ዓመት በታች የሚገኙ ሕፃናትም የመነመኑ ናቸው፡፡

በአገሪቱ 57 በመቶ ብቻ የሚሆኑት ዜጎች የተሻለ የውኃ አቅርቦት ያገኛሉ፡፡ የተሻለ የፅዳት ተደራሽነት ያላቸው ዜጎች ደግሞ 28 በመቶ የሚሆኑት ናቸው፡፡ ችግሩን ተናብቦ በመሥራት እንዴት መቅረፍ ይቻላል? በሚለው ጉዳይ ዙሪያ መሰንበቻውን በሐርመኒ ሆቴል በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡  

መረጃዎች እንደሚያሳዩት 30 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ በአመጋገብ ችግሮች ተጠቂ ነው፡፡ ይህ ቁጥር ... 2035 ወደ 50 በመቶ ከፍ ይላል፡፡ 7 ቢሊዮን ከሚሆኑ የዓለም ሕዝቦች መካከል ሁለት ቢሊዮን የሚሆኑት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ይጠቃሉ፡፡ አምስት ቢሊዮን ከሚሆኑ አዋቂዎት መካከልም ሁለት ቢሊዮን የሚሆኑት ከአመጋገብ ችግር ጋር በተያያዘ ከመጠን ባለፈ ውፍረት ይጠቃሉ፡፡

 በአሁኑ ወቅት ትልቁ የጤና ሥጋትም ከአመጋገብ ችግር ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ በሽታዎች ናቸው፡፡ በቂ ምግብ ባለማግኘትና በረሀብ  ምክንያት የዓለም 1.4 እስከ 2.1 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዓመታዊ የምርት ፍጆታ እንደሚጠፋ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ... 2009 በረሃብ ምክንያት 55.5 ቢሊዮን ብር ወይም 16.5 ከመቶ የሚሆነው አገራዊ የምርት ፍጆታ ማጣቷን የሥርዓተ ምግብ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በሥርዓተ ምግብ ችግር ዙሪያ ... 2016 በተሠራ አንድ ጥናት፣ በኢትዮጵያ 67 በመቶ የሚሆኑት አዋቂዎች ዕድገት እንዲቀጭጭ ሆኗል፡፡ በጥናቱ መሠረት፣ ከአምስት ዓመት ዕድሜ በታች በሆኑ ሕፃናት የመቀንጨር ችግር በስፋት የሚታየው በአማራ ክልል ነው፡፡ በክልሉ የመቀንጨር ችግር 46.3 በመቶ ሲሆን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 42.7 በመቶ፣ በአፋር ክልል 41.1 በመቶ ችግሩ ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ የተሻሉ የተባሉት አዲስ አበባ 14.6 በመቶና ጋምቤላ ክልል 23.5 በመቶ መሆኑን ከጥናቱ መረዳት ተችሏል፡፡

ይህንን አገራዊ ችግር 2022 .. ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ሲሆን፣ ይህን ዕውን ለማድረግም ለሕፃናቱ ዕድገት ትልቁን ድርሻ በሚይዙት በመጀመሪያዎቹ አንድ ሺሕ ቀናት ውስጥ ብዙ መሠራት ይኖርበታል፡፡ ይህም ማለት ሕፃኑ(ኗ) ከተረገዘ ወይም ከተረገዘችበት ጊዜ እስከ ሁለት ዓመቱ(ቷ) ድረስ ባሉት ቀናት የሚደረግ እንክብካቤ ነው፡፡ ይህም የሆነው በሕፃናት አካላዊና አዕምሯዊ ዕድገት ላይ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ትልቁን ሚና ስለሚጫወቱ ነው፡፡ የሰቆጣ ስምምነትም ይህንን ዕውን ለማድረግ የተጀመረ ፕሮግራም ነው፡፡

በአገሪቱ ለጤና ጠቃሚ በሆኑ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ምግቦችን የሚመገቡ፣ ከስድስት እስከ 23 ወራት ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሕፃናት ከሰባት በመቶ እንደማይበልጥ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...