በኬንያ ከሁለት ወራት በፊት የተካሄደውና ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አሸንፈውበታል የተባለው ምርጫ ከተሰረዘ በኋላ የኬንያ ሰላም ደፍርሷል፡፡ በወቅቱ የኬንያታ ተቀናቃኝ ራይላ ኦዲንጋ ከምርጫው በፊት ጀምሮ ምርጫው እንደሚጭበረበርና እንደማይቀበሉት ሲናገሩ የነበረ ሲሆን፣ ከምርጫው በኋላም ሽንፈታቸውን ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት ባለመቀበላቸውና ጉዳዩ ፍርድ ቤት በመሄዱ ምርጫው ተሰርዟል፡፡
ዳግም ምርጫውን ለማካሄድ ለሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የተቀጠረ ቢሆንም፣ ምርጫው ፍትሐዊ አልነበረም ሲሉ የነበሩት የ72 ዓመቱ ኦዲንጋ ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህም በኦዲንጋና በኬንያታ ደጋፊዎች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ኦዲንጋ ከምርጫው ራሳቸውን ያገለሉት የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ፍትሐዊ አይደለም፣ መቀየር አለበት በማለታቸው ነው፡፡ ለደጋፊዎቻቸውም፣ ‹‹ከምርጫው ራሴን ማግለሌ የምርጫ ኮሚሽኑ ዳግም እንዲዋቀር ጊዜ ይሰጣል፤›› ብለዋል፡፡ ተከታዮቻቸው ምርጫውን እንዲቃወሙ በምርጫው ዕለትም የተቃውሞ ሠልፍ እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በቀዳሚው ምርጫ ማሸነፋቸው የተነገረላቸው ኬንያታ ዳግም ለደጋፊዎቻቸው ቅስቀሳ እያደረጉ ሲሆን፣ ኬንያ ወደ ብጥብጥ እንዳትገባም እንዲፀልዩ አሳስበዋል፡፡ ኬንያታ ለዳግም ምርጫው የምረጡኝ ዘመቻ ሲያጧጥፉ፣ ኦዲንጋ በተቃራኒው ራሳቸውን ማግለላቸውና ደጋፊዎቻቸውን ለተቃውሞ መጥራታቸው፣ በኬንያ ካለፈው ምርጫ መሰረዝ ጀምሮ እዚህም እዚያም እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችን አባብሷቸዋል፡፡ ምዕራባውያን ዲፕሎማቶችም የሐሙሱ ምርጫ ከመካሄዱ አስቀድሞ በአገሪቱ የደኅንነት ሥጋት እያየለ ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የኦዲንጋ ከዳግም ምርጫው ራሳቸውን ማግለል ግጭቱን ያባብሰዋል ያሉት ዲፕሎማቶች፣ ነገር አቀጣጣይ የሆኑ ንግግሮችና ዛቻዎች በምርጫ ኮሚሽኑ ላይ እየተሰነዘረ መሆኑም፣ ተቀባይነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ እንቅፋት ይሆናል ብለዋል፡፡
በኬንያ የአሜሪካ አምባሳደር ቦብ ጎዴክን ጨምሮ 20 የልዑካን ቡድን አባላት ያሉት የዲፕሎማቶች ቡድንም፣ በምሥራቅ አፍሪካ ትልቅ ኢኮኖሚ ያላት ኬንያ አስፈሪ ወደሆነ የፖለቲካ ምዕራፍ ውስጥ ገብታለች ብሏል፡፡
ሚስተር ኦዲንጋ ዳግም ምርጫው በሚካሄድበት ዕለት ደጋፊዎቻቸውን ለተቃውሞ ሠልፍ የጠሩ ሲሆን፣ ምርጫውን እንዲያደናቅፉም ጠይቀዋል፡፡ በምዕራብ ኬንያ የምትገኘው ኪሲሙ ምክትል ገዥ የነበሩት እህታቸው ሩት ኦዲንጋ ደግሞ በከተማዋ ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል ተከሰው ታስረዋል፡፡
የቀድሞው ምርጫ ሕገወጥና የተዛባ ነበር በማለት የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውጤቱን ሰርዞ ምርጫው ዳግም እንዲካሄድ ቢወሰንም፣ በወቅቱ በምርጫ የተሸነፉት ኦዲንጋ ከዳግም ምርጫው ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ ‹‹ምንም የተለወጠ ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡ በኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ወሳኝ መዋቅር ለውጥ ካልተደረገና ባለሥልጣናቱ ከሥራ ካልተወገዱ ምርጫውን አልቀበልም፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
በቀዳሚው ምርጫ የኬንያታን ማሸነፍ ተከትሎ በተቀሰቀሰ ብጥብጥ 70 ያህል ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ዳግም ምርጫው በሚካሄድበት ቀን በተጠራው የተቃውሞ ሠልፍ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ሞት ሊኖር ይችላል ተብሏል፡፡
ምዕራባውያኑ ዲፕሎማቶችም፣ ‹‹ከመገንባት ማፈራረስ ቀላል ነው፣ በኬንያ ያለው አካሄድ አደገኛ ስለሆነ መቆም አለበት፤›› ብለዋል፡፡
በኬንያውያን ዛቻና ማስፈራራት እየደረሰበት ያለው የምርጫ ኮሚሽኑንም በገለልተኝነት ውሳኔ መስጠት ከማይችልበት ሁኔታ ደርሷል እየተባለ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት የኮሚሽኑ ባለሥልጣን ሮዝሊን አኮምቤ ወደ አሜሪካ ተሰደዋል፡፡
ኦኮምቤ እንደሚሉት፣ የምርጫ ኮሚሽኑ በምርጫ ውጥንቅጥ ውስጥ ገብቷል፡፡ እሳቸውም በደረሰባቸው የግድያ ዛቻ ወደ አሜሪካ ለመሸሽ ተገደዋል፡፡ የምርጫ ኮሚሽኑ እንዲህ በዛቻ በተወጠረበት የምርጫ ወረቀቶችና ቴክኖሎጂዎች ለዳግም ምርጫው ተዘጋጅተዋል፡፡ ምርጫው በአግባቡ ስለመካሄዱና ተቀባይነት ስለማግኘቱ ግን ጥርጣሬ አለ፡፡
በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት ምርጫው ከጥቅምት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ወዲህ መከናወን አለበት፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤት በድንገተኛ ጉዳዮች ችግር ውስጥ መግባቱ፣ የምርጫ ኮሚሽኑ ሹም ከሥራ መልቀቃቸው፣ እንዲሁም አወዛጋቢ የተባለው አዲስ የምርጫ ሕግ መፅደቁ አለመመቻቸትን ፈጥረዋል፡፡
የምርጫ ኮሚሽን ሊቀመንበር ዋፍላ ቺቡካቲ ያነጋገሩት ፕሬዚዳንት ኬንያታ፣ የሐሙሱ ምርጫ ይካሄዳል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለኮሚሽኑ ገንዘብ አቅርበናል፣ ሥራቸውን መሥራት አለባቸው፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
የኮሚሽኑ አባላት ግን ጥቃት እየተፈጸመባቸው ነው፡፡ የአሜሪካ አምባሳደር ጎዴክ ይህንን አስመልክተው እንደተናገሩት፣ በምርጫ ኮሚሽን ሠራተኞች ላይ የሚፈጸም ጥቃት መቆም አለበት፡፡ ማንም ሰው ያለፍላጎቱ ቢሮ ገብቶ እንዲሠራም ሆነ በምርጫ እንዲሳተፍ አይገደድም፡፡
የምርጫ ኮሚሽኑ የሚስተር ኦዲንጋን ስም በምርጫ ወረቀቱ ያሠፈረ ሲሆን፣ በነሐሴው ምርጫ አንድ በመቶ ያህል ድምፅ ያገኙት ስድስት ዕጩዎችም ይገኙበታል፡፡ ነሐሴ 2009 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ፕሬዚዳንት ኬንያታ ተቀናቃኛቸውን ሚስተር ኦዲንጋን በ1.4 ሚሊዮን ድምፅ ልዩነት አሸንፈው እንደነበር ይታወሳል፡፡
የኬንያ ዳግም ምርጫ ይካሄድ ይሆን?
በኬንያ ዳግም ምርጫ እንዲካሄድ ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡ ቀነ ቀጠሮም ለሐሙስ ተይዟል፡፡ ሆኖም የግድያ ዛቻ የሚሰነዘርባቸው የምርጫ ኮሚሽኑ ባለሥልጣናት ገለልተኛነታቸው አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ወደ አሜሪካ የተሰደዱት ሚስ አኮምቤም፣ ኮሚሽኑ ምርጫውን ለማካሄድ አቅም ይኖረዋል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡
የኮሚሽኑ ባለሥልጣናት በፖለቲከኞችና በግለሰቦች ዛቻና ማስፈራራት እየደረሰባቸው ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ኮሚሽኑ ተቀባይነትና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ ዋስትና የለውም፤›› ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኬንያታ ደግሞ ዳግም ምርጫው እንደሚከናወን ተስፋ ሰንቀዋል፡፡
በምርጫው ዕለት ብጥብጥ ይከሰት ይሆን?
የሰብዓዊ መብት ቡድኖች የነሐሴ 2009 ዓ.ም. ምርጫ ከተሰረዘ ወዲህ 70 ሰዎች መገደላቸውን ከእነዚህ ውስጥ 30 በናይሮቢ እንደሆነ አሳውቀዋል፡፡ አሁን በኬንያ እየታየ ያለው ብጥብጥ እ.ኤ.አ. ከ2007 ወዲህ ከታየው ለየት ያለ ነው፡፡ የሚስተር ኦዲንጋ ደጋፊዎች ይበዙበታል በሚባለው ምዕራብ ኬንያ የምርጫ አስፈጻሚዎች ማስፈራሪያ እየተዘነዘረባቸው ነው፡፡ ይህ በምርጫው ዕለት የበለጠ ብጥብጥ ሊኖር እንደሚችል ማሳያ ነው፡፡ በሌላ በኩል ተቃውሞዎች ቀጥለዋል፡፡ ምርጫው የሚካሄድበት ሐሙሰት ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ደግሞ ከሁሉም የላቀ ሠልፍ የሚወጣበት ይሆናል ሲሉ ሚስተር ኦዲንጋ ተናግረዋል፡፡ ይህም በዕለቱ ዋና ከተማዋን ናይሮቢን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ብጥብጥ ሊኖር እንደሚችል ያሳያል ተብሏል፡፡