Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹ልጃችንን በነጠቀን ካንሰር ሕፃናት እንዳይሞቱ ከሁሉም ጋር ተባብሬ መሥራት እፈልጋለሁ››

  አቶ ወንዱ በቀለ፣ የማቲዎስ ወንዱ – የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ

  ማቲዎስ ወንዱ – የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ከተቋቋመ 14 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የተቋቋመው ማቲዎስ የተባለውን የአራት ዓመት ልጃቸውን በካንሰር ሕመም ባጡት አቶ ወንዱ በቀለና ባለቤታቸው እንዲሁም በሌሎች 13 መሥራች አባላት ነው፡፡ ሶሳይቲው ከተቋቋመ ወዲህ ለካንሰር አጋላጭ ከሆኑ ነገሮች መከላከልን ጨምሮ ሕክምና በሚገኝበት ዙሪያ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡ ለካንሰር ሕክምና አዲስ አበባ መጥተው መጠለያና ገንዘብ ያጡትንም ሕሙማን የሚያስጠልልና ሕክምና የሚያገኙበትን ሁኔታ የሚያመቻች ማዕከል አቋቁመዋል፡፡ ለዚህ በጎ ሥራቸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኒውዮርክ ከተማ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ኢንብለር ቪዥን አዋርድ መስከረም 11 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲሁም አሜሪካ በሚኖሩ ከ5000 በላይ ኢትዮጵያውያን የሕክምናና የተለያዩ ሙያ ባለሙያዋች ከተቋቋመው ፒፕል ቱ ፒፕል መስከረም 13 ቀን  2010 ዓ.ም. እጅግ የላቀ የማሕበረሰብ አገልግሎት የዕውቅና ሽልማት በዋሽንግተን ዲሲ አግኝተዋል፡፡ በተለይ ሁለተኛውን ሽልማት ያገኙት ማቲዎስ ከ14 ዓመት በፊት በተለየበት ቀንና  ሰዓት መሆኑ ቤተሰቦቻቸውን እንዳስገረመ ይናገራሉ፡፡ የሶሳይቲው መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ  አቶ ወንዱ በቀለ በካንሰር ዙሪያ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

  ሪፖርተር፡- ከዛሬ 14 ዓመት በፊት ማቴዎስ የተባለውን የአራት ዓመት ልጅዎን በደም ካንሰር ካጡት በኋላ በብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት የነበረዎትን የሥራ ኃላፊነት በራስዎ ፈቃድ በመተው የእኔን ልጅ የገደለው ካንሰር የሌሎችን እንዳይነጥቅ በማለት በካንሰር የታመሙ ሕፃናትና አዋቂዎች ግንዛቤና ዕርዳታ እንዲያገኙ መሥራት ጀምረዋል፡፡ በወቅቱ በየመሥሪያ ቤቱ እየተዘዋወሩ በካንሰር የተጠቁ ልጆች የሚረዱበትን ሁኔታ ለማመቻቸትም ብዙ ተንከራተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው ሥራዎት ከምን ደረሰ?

  አቶ ወንዱ፡- ማቲዎስ ወንዱ – የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የተቋቋመው ማቲን ለሕክምና ወደ አሜሪካ ይዘን ለመጓዝ ዝግጅት አድርገን ሳይሳካ ቀርቶ ከዚህ ዓለም በተለየ ከስድስት ወራት በኋላ ነው፡፡ ሐዘኑን መቋቋም የቻልነው ማቲ ቢሞትም የእኛም ጊዜ ደርሶ ከዚህ ዓለም ስንለይ እንደገና እንገናኛለን የሚለው እምነታችንና እስከዚያው ሌሎች ሕፃናት በካንሰር እንዳይሞቱ በዓለም አቀፍም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ እንቅስቃሴዎችን እንደግፍ ብለን በመነሳታችን ነው፡፡ ማቲን ለማዳን የነበረንን ጥረት እሱ ሲሞት ለምን እናቆማለን? ሌሎችን ለመርዳት መነሳት አለብን ብለን ነው ወደ ሥራው የገባነው፡፡ ማቲ የተቀበረበት ቦሌ ሚካኤል ያለው ፉካም የተጻፈበት ‹‹ከምወዳችሁ ውድ ቤተሰቦቼ በፈጣሪ እጅ ስለሆንኩ እስክንገናኝ ድረስ ለኔ አታስቡ›› ይላል፡፡ ስንሞት እናገኘዋለን ብለን ነው የምናስበው፡፡ የብሔራዊ ትምባሆ አስተዳዳሪ ሆኜ ጥሩ ደመወዝ ስለነበረኝ ከባለቤቴ ጋር ተመካክረን መኖሪያ ቤታችንን ወደ ቢሮ ቀይረን ለስድስት ዓመት ያለአንዳች ደመወዝና አስተዳደራዊ ወጪ ሠራን፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ባለቤቴ እንደ ፀሐፊ እኔ እንደ ሥራ አስኪያጅ ሆነን ስንሠራ ቆይተናል፡፡ ኦዲተር ሲመጣ የቤት ኪራይ የለም እንዴ? ደመወዝ አይከፈልም? እንባል ነበር፡፡ በኋላ ላይ የዓለም ካንሰር ድርጅት አባል ስንሆን ከካንሰር አምጪ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛ በሆነው ትምባሆ የፀረ ትምባሆ ዘመቻ እንድናካሂድ ሁኔታ ተመቻቸ፡፡ ምክንያቱም ትምባሆ የካንሰር ዋናው አምጪ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ አምስት ከመንግሥት አምስት ከግል ት/ቤቶች ጋር ሆነን ፀረ ትምባሆ ዘመቻ ስናካሂድ በአንድ በኩል ትምባሆ እያመረትኩ በሌላ በኩል ትምባሆ አታጭሱ ማለቱ አብሮ ስለማይሄድ ሥራውን በገዛ ፈቃዴ አቆምኩ፡፡ በወቅቱ ችግር ላይ ነበርን፡፡ ልጃችንን ለማሳከም ብዙ አውጥተናል፡፡ በዛ ላይ ልጃችን ሞቷል፡፡ ልጃችንን ለማዳን የጀመርነውን ጥረት ቀጥለንበት አሁን ላይ ጥሩ ለውጥ እያየን ነው፡፡ ዛሬ 91 የሕፃናት ካንሠር ሕሙማንን እንረዳለን፡፡ መድኃኒት በውድ ዋጋ እስከ ብር 30 ሺሕ እንገዛለን፡፡ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልም መድኃኒት ካለው በነፃ ይሰጥልናል፣ ከሌለው ግን በውድ ዋጋ ከውጭ እንገዛለን፡፡ በተጨማሪም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የላቦራቶሪ መሣሪያዎች እክል ሲገጥመው የግል ጤና ተቋማት ጋር በውድ ከፍለን ኤምአርአይ፣ ሲቲ ስካንና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ ሕሙማኑ ከትውልድ ቀያቸው ሲመጡና ሲመለሱ የትራንስፖርት ክፍያ አብረዋቸው ከሚመጡ ቤተሰብ ጋር እንከፍላለን፣ ሆስፒታል ሲተኙ ብር500.00 እንሰጣለን፡፡ ይህንን ሳይ ልጄን ያስታመምኩ ያህል ይሰማኛል፡፡ ከቢሮዋችን ጎን ለጎን ማዕከል አቋቁመን ሕሙማን እዚሁ እያሳረፍን ሕክምናቸውን  እንዲከታተሉ እናደርጋለን፡፡ በአሁኑ ወቅት 76 በጡትና ማህፀን ጫፍ ካንሰር የታመሙ ሴቶችን እንረዳለን፡፡ ሕሙማኑን ይዘው የሚመጡ ቤተሰቦችም በማዕከሉ ይረዳሉ፡፡ ባለው ሁኔታም እየተበረታታን ነው፡፡

   

   ሪፖርተር፡- እናንተ ከምታደርጉት ጥረት በተጨማሪ ከበፊቱ በተለየ እንድትበረታቱና ተስፋ እንዲኖራችሁ ያደረገው ምንድነው?

  አቶ ወንዱ፡- በፊት ከመላ ኢትዮጵያ የሚመጡ የካንሰር ሕሙማን ጥቁር አንበሳ ብቻ ነበር የሚታከሙት፡፡ አሁን የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና በቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ የቅርብ አመራር ብሔራዊ የካንሰር መቆጣጠሪያ ዕቅድ እ.ኤ.አ. በ2015 ከተዘጋጀ ወዲህ መንግሥት በጀት መድቦ መቐለ፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ሐዋሳና ሐሮማያ ላይ የካንሰር ማዕከሎች እየተቋቋሙ ነው፡፡ ስድስት የጨረር ሕክምና መሣሪያዎች ግዢም ተፈጽሟል፡፡ አንዱ የጨረር ሕክምና መሣሪያ እስከ አራት ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ የሐሮማያ፣ የጅማና የጥቁር አንበሳ ሥራ መጀመር ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ የጅማን ብናነሳ የሬዲዮ ቴራፒ (ጨረር ማዕከሉ) የሚያስፈልገው የኤሌክተሪክ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ሥራ አልጀመረም፡፡ ከፍተኛ የባለሙያ እጥረትም አለ፡፡ ስለሆነም ከኩባ፣ ከግብፅ እና ከህንድ ባለሙያዎች እየተፈለጉ ነው፡፡ የካንሰር መድኃኒት አቅርቦትና ዋጋ እንደሚፈለገውም ባይሆን እየተሻሻለ ነው፡፡ ዋና ገዳይ ከሚባሉት የካንሰር ዓይነቶች አንዱ በሆነው የማሕፀን ካንሰር ላይ 118 የመንግሥት ጤና ተቋማት ውስጥ የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ማከሚያ (ክራዮቴራፒ) ገብቶላቸዋል፡፡ አንዳንድ ቦታ ከ5 እስከ 50 ብር የሚያስከፍሉ ቢሆንም አብዛኛው ነፃ ነው፡፡ ሆኖም መጥቶ የሚመረመር የለም፡፡ ባለፉት ሶስት ዓመታት በመንግሥትም በግልም በአገር አቀፍ ደረጃ የተመረመሩት 80 ሺሕ ያህል ሴቶች ናቸው፡፡

  ሪፖርተር፡- በአገር አቀፍ ደረጃ ምርመራ ከተጀመረ ሦስት ዓመት ሆኖታል፡፡ በዚህ ዓመት ነው 80 ሺሕ የተመረመሩት?

   

  አቶ ወንዱ፡- አዎ? ቁጥሩን ለመጨመር በደቡብ ክልል ኦሮሚያና አዲስ አበባ ውስጥ ዘመቻ በማካሄድ ላይ እንገኛለን፡፡ መንግሥትም 1,500 ተጨማሪ የማሕፀን ጫፍ መመርመሪያና ማከሚያ መሣሪያ ለመግዛት የግዢ ትዕዛዝ አውጥቷል፡፡ ዕቅዱም አንድ ክሪዮቴራፒ በአንድ ወረዳ እንዲኖር ነው፡፡ በሆስፒታል ወይም በጤና ጣቢያ መሣሪያው ገብቶ በሠለጠኑ ባለሙያዎች አገልግሎት ለመስጠት ታቅዷል፡፡ ይህን ሳይ በመንግሥት በኩል ያለው ዝግጅት መልካምና የሚበረታታ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገር ደረጃ አራት የካንሰር ሐኪሞች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ ይህንን ለመለወጥ በየዓመቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ማዕከል የሚመረቁ ተማሪዎች ይኖራሉ፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልም የካንሰር የልቀት ማዕከል እየተሠራለት ነው፡፡ ግንባታው ሲያልቅ ወደ ስድስት የጨረር መሣሪያ ይኖረዋል፡፡ የቦንማሮው ትራንስፕላንትም የማድረግ አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ ሐኪም ሳልሆን በልጄ ምክንያት ገብቼበት እንደታዛቢ ስናገር በካንሰር ሕክምና ላይ ባለሙያ ከተሟላ፣ መመርመርያና ማከሚያ መሣሪያዎቹ ከገቡ፣ የሚያስፈልገንን ዓይነት መድኃኒት በበቂ ሁኔታ ካገኘን የምንፈልገውን ለውጥ እናመጣለን፡፡ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከቀዳማዊት እመቤት ጋር ከተባበርን ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞችን በአጠቃላይ በተለይ ካንሰር ላይ ቀድመን ከሠራን ከፍተኛ ለውጥ ይመጣል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡

  ሪፖርተር፡- የማቲዎስ ወንዱ-የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ከተቋቋመ 14 ዓመት ሆኖታል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ካንሰርን ቀድሞ በመከላከሉ ረገድ ምን ሠራ?

  አቶ ወንዱ፡- በብዙ አገሮች ብሔራዊ የካንሰር መከላከያ ዕቅድ አለ፡፡ ዕቅዱ ግን በሲቪል ሶሳይቲው የሚወጣና የሚታወቅ እንጂ በመንግሥት የሚታወቅ አይደለም፡፡ በመንግሥትም በጀትም የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የካንሰር ዕቅድ ከሌሎች የሚለየው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚመራ የተዘጋጀና በጀት የተመደበለት ሲሆን እኛም ጥረቱን ለመርዳት ባለሙያ ቀጥረን በሚኒስቴሩ ዕውቅና እንዲሠራ አድርገናል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያም የካንሰር ዕቅድ ነድፋለች፡፡ ዕቅዱ ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ አስቀድሞ መከላከል፣ ማከምና አክሞ ማዳን የማይቻለውን ክብካቤ ማድረግ የሚቻልበትን ያካተተ ነው፡፡ አስቀድሞ መከላከሉ ላይ ከክልል ጤና ቢሮዎችና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር እንሠራለን፡፡ ለምሳሌ ትምባሆ ላይ ሁለት ፕሮጀክቶች አሉን፡፡ ከኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን (ኤፌማካ) ጋር የምንሠራው ነው፡፡ አንደኛው ሥራችን የትምባሆ ማዕቀፉ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሕግ ወጥቶ ሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ ሲሆን፣ ይህ ከባለሥልጣኑ ወጥቶ ጤና ጥበቃን አልፎ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ደርሷል፡፡ አሁን በረቂቅ ደረጃ ያለው ተወካዮች ምክር ቤት ገብቶ ከፀደቀ ለእኛም ሆነ ለአገራችን ትልቅ ነገር ነው፡፡ ተግባራዊ ማድረጉ ላይ እንረባረባለን፡፡ ሁለተኛው ሐሮማያ፣ አዳማ፣ ባሕር ዳር፣ ሐዋሳና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ትምባሆ እንዳይጨስ የሙከራ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ስንሠራ የነበረውን ነው ወደ ዩኒቨርሲትዎች ያመጣነው፡፡ ከፌዴራል ኤፌማካ እና ከአዲስ አበባው ኤፌማካ ጋር በመሆን ከተሞች ራሳቸው ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታዎች ትምባሆ የማይጨስባቸው እንዲሆኑ እየሠራን ነው፡፡ የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ላይ በዕድር፣ በሴቶች ማኅበር፣ በአባቶች በኩል በጋራ ጥረት  እያደረግን ሴቶች እንዲመረመሩ እየሠራን ነው፡፡ የጡት ካንሰር ላይም እንሠራለን፡፡ ከፊታችን ሳምንት ጀምረን በተመረጡ አሥር ጤና ጣቢያዋች ሴቶች የጡት ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ እናደርጋለን፡፡ አቅማችን ትንሽ ስለሆነ ባሉን 22 ሠራተኞች ሰባት በካንሰር ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶችን እየሠራን ነው፡፡

   

  ሪፖርተር፡- እርስዎ ልጅዎትን ሲያሳክሙ ከነበረው ጊዜ አሁን ላይ ያለውን አገልግሎት አሰጣጥ ቢያነፃፅሩልኝ?

  አቶ ወንዱ፡- ማቲን ስናሳክም አብዛኞቹ መድኃኒቶች አገር ውስጥ አልነበሩም፡፡ ማቲ መድኃኒት በሚወስድበት ቀን የየብልቃጡን ሙሉ ስለማይወስድ ተጨማሪ ልጆች አብረው ይወስዱ ነበር፡፡ አሁን ላይ ዋጋውም አቅርቦቱም እየተሻሻለ ነው፡፡ ሆኖም በቂ አይደለም፡፡ በግል ፋርማሲም እየተሸጠ ነው፡፡ ልጄ ሲታከም በቂ የሕፃናት ካንሰር ሐኪም አልነበረም፡፡ አሁን ጥቁር አንበሳ ሁለት የሕፃናት ሐኪሞች ነበሩት፡፡ ሆኖም አንዱ ካናዳ ለትምህርት ሄዷል፡፡ ኢትዮጵያን የሚያክል አገር ውስጥ በዓመት ስድስት ሺሕ ሕፃናት በካንሰር እየተያዙ በቂ ሐኪም አለመኖሩ የሚያሳዝን ነው፡፡ አጠቃላይ ካንሰርን ለማከም እየተደረገ ያለው ኢንቨስትመንት ግን የሚበረታት ነው፡፡ ትኩረትም አግኝቷል፡፡ ሆኖም መንግሥት ብቻውን የሚያደርገው አይደለም፡፡ መረዳዳት ያስፈልጋል፡፡ የካንሰር የልቀት ማዕከል የለንም፡፡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተያያዥ የሆኑ ሕክምናዎችን ይፈልጋሉ፡፡ አንድ ሰው ለምሳሌ ካንሰር ተመርምሮ ቢገኝበትና ማከም ባይቻል ይህ ሌላ ጉዳት ነው፡፡ ስለዚህ ከምርመራ ጀምሮ ሕክምናው የተሟላ መሆን አለበት፡፡

   

  ሪፖርተር፡- ላለፉት 14 ዓመታት ካንሰር ላይ በሠራችሁት ሥራ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲሁም መቀመጫው አሜሪካ በሆነው ፒፕል ቱ ፒፕል የዕውቅና ሽልማት መስከረም 2010 ዓ.ም. ላይ ተቀብላችኋል፡፡ ስለዚህ ቢያብራሩልን?

   

  አቶ ወንዱ፡- የተባበሩት መንግሥታት በያመቱ መስከረም ጠቅላላ ጉባኤውንና የፀጥታው ምክር ቤትን ስብሰባ በአሜሪካ ያካሂዳል፡፡ የሥርዓተ ጾታና የልማት ግቦችን የሚመለከት ስብሰባም ከዚሁ ጎን ለጎን ተካሂዷል፡፡ በዚህ ስብሰባ በአብዛኛው የተሳተፉት ቀዳማዊት እመቤቶች፣ ጐትጓቾችና የልማት አጋሮች ናቸው፡፡ በስብሰባው ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ ተገኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ማምጣት ከቻሉ አራት ድርጅቶች አንዱ የእኛ የሆነው በካንሰር ላይ የሠራነውና ያመጣነው ለውጥ መሠረት ተደርጎ ነው፡፡ በዚህም የዕውቅና ሽልማት አግኝተናል፡፡ ሽልማቱ የእኔ ብቻ ሳይሆን አባሎች የሶሳይቲው ቦርድ፣ ሠራተኞች፣ አጋሮች ጭምር ነው፡፡ ይህንን ዕውቅና ባገኘን ከሁለት ቀን በኋላ በፒፕል ቱ ፒፕል ተጋብዤ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን በዋሽንግተን ከተማ ሲያካሂዱ በካንሰር ላይ የሠራነውን ሥራ አቀረብኩኝ፡፡ በኋላ ጥቆማ ሰብስበው ‘አውትስታንዲንግ ኮሚዩኒቲ ሰርቪስ አዋርድ’ የሚባል የዕውቅና ሽልማት ሰጡን፡፡ ሁለቱም ሽልማት ገንዘብ የለውም፡፡ የፒፕል ቱ ፒፕል ሽልማትን ያገኘሁት ልክ ልጄ ከዛሬ 14 ዓመት በፊት በሞተበት ቀንና ሰዓት መሆኑ ገርሞኛል፡፡ የፒፕል ቱ ፒፕል አባላት በኢትዮጵያ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት ስላላቸው አገራቸው መጥተው ከእኛ ጋር የሚሠሩበትን ለማመቻቸት ተነጋግረናል፡፡ እኔም ከመሞቴ በፊት ማቲን በነጠቀኝ ሕመም ሕፃናት እንዳይሞቱ ከሁሉም ጋር ተባብሬ መሥራት ነው የምፈልገው፡፡ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የካንሰር ኢንስቲትዩት የላትም፡፡ ስለዚህ ብዙ አጋሮች ስላሉን ማንኛውንም ዓይነት የካንሰር ሕክምና የሚሰጥ ተቋም ለመገንባት አቅደናል፡፡ ገንዘብ የሌለው የሚታከምበትና ከሕመሙና ስቃዩ የሚገላገልበት ተቋም እንዲሆንም እፈልጋለሁ፡፡ ልጃችን በካንሰር በመታመሙና በመሞቱ እኔና ቤተሰቤ ያየነውን ዓይነት ስቃይ ሌላው እንዲያየው አልፈልግም፡፡ ካንሰር ያለውንም ደሃ የሚያደርግ ስለሆነ አስቀድሞ ከመከላከል ጀምሮ ችግሩ ሲከሰት እስከማከም ያለውን ለመሥራት እየጣርን ነው፡፡

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች