Monday, July 22, 2024

መፍትሔ የታጣላቸውን ችግሮች የማስታመም ፈተና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በሾፌርነት ከ15 ዓመት በላይ ማስቆጠሩን የሚናገረው ተሾመ በላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየገጠሙት ያሉት ነገሮች በጣም እያሳሰቡት መሆኑን ይናገራል፡፡ ‹‹በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባደረኳቸው ጉዞዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ፍርኃት እየተጫነኝ ነው፡፡ ሁለት ልጆቼን ለማሳደግ የሚያግዘኝ ሥራዬ ሕይወቴን ለአደጋ እያጋለጠ ሲሆን፣ ጓደኞቼ ሳይቀሩ የእኔን ፍርኃት ይጋራሉ፤›› ይላል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ እየገጠሙት ያሉትን ተቃውሞዎችና ብጥብጦች ከራሱና ከቤተሰቡ አልፎ ለአገር አሥጊ እየሆኑ መምጣታቸውን የሚናገረው ተሾመ፣ ይኼ ሁሉ ሁከት መቼ ነው የሚያበቃው ሲልም ይጠይቃል፡፡

ከወራት በፊት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት ከመቶ ሺሕ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፣ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሕይወታቸው ጠፍቷል፡፡ ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በቡኖ በደሌ ዞን ዴጋና ጮራ ወረዳዎች ሁከት ተቀስቅሶ የሰው ሕይወት መጥፋትና የነዋሪዎች ቤት መቃጠል፣ የመሰንበቻው ያልተጠበቀ ክስተት ነበር፡፡

የዩኒቨርሲቲ መምህርና የፖለቲካ ተንታኙ ንጋት አስፋው (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ  ይስማማሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከብሔር ጋር የተያያዘ ግጭት በመፈጠሩና እየተፈጠረ በመሆኑ የበርካታ ዜጎች ሕይወት ማለፉን ጠቅሰው፣ እንደዚህ ዓይነት ድርጊት ሰምተውና ዓይተው እንደማያውቁ ይናገራሉ፡፡

አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለችበት ሁኔታ የወደፊት መፃኢ ዕድሏ ላይ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ብዙዎች በሥጋት ይናገራሉ፡፡ አንዱ ችግር በቅጡ ሳይፈታ ሌላ ችግር እየተፈጠረና እየተደራረበ በመሄዱ ምክንያት፣ ብዙዎችን ከፍተኛ ፍርኃት ውስጥ እየከተተ እንደሆነ ሲነገር ይሰማል፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ግጭት  በቅጡ እልባት ሳያገኝ፣ ዳግምኛ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሰው ሕይወት የቀጠፈ ተቃውሞ መከሰቱ የአደጋውን አሳሳቢነት ማሳያ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡

የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሸን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ሰሞኑን በቡኖ በደሌ ዞን ጮራና ዴጋ ወረዳዎች ሲደረግ የነበረው ሠልፍ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዲያመራ በማድረግ በሰዎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በተቀሰቀሰ ሁከት 14 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው በዚህ ግጭት 14 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጸው፣ 52 መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውንም ተናግረዋል፡፡ የሁከቱን መፈጠር ተከትሎ ጉዳት እንዳይደርስባቸው በመፍራት ከ1,500 በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው እንደተፈናቀሉም አቶ አዲሱ ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት ሳቢያ የአሥር ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጥሎ ነበር፡፡ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ማግሥት በባህር ዳር ከተማ ተደጋጋሚ የሆነ የቦምብ ፍንዳታ ከመድረሱ በተጨማሪ፣ ከቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተቃውሞዎች ተካሂደው ነበር፡፡ በወቅቱም ንብረት ወድሟል፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት ደግሞ የበርካቶች ሕይወት ሲጠፋ፣ ከመቶ ሺሕ ላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ይህ ችግር ዳግመኛ እንዳይከሰትና የተፈናቀሉ ወገኖች በሚቋቋሙበት ሁኔታ ላይ መንግሥት እየሠራ ነው ሲባል፣ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተቃውሞ ሠልፎች ተካሂደዋል፡፡ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ተደርገው በነበሩ የተቃውሞ ሠልፎች የአሥር ሰዎች ሕይወት ሲጠፋ በርካታ ንብረት ወድሟል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ትልልቅ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችና የጭነት ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ደግሞ በኢሉአባቦራና በቡኖ በደሌ ዞኖች ውስጥ በተቀሰቀሰቀ ሁከት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡

አሁን አገሪቱ ረጋ ብላ የምታስብበት ጊዜ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ የቀደሞው የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) በዚህ ጉዳይ  ይስማማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከዜግነት ወደ ጎሳ የወረደ እንደሆነ የሚናገሩት ኢንጂነሩ፣ ሁሉም ዜጋ በጎሳ ከረጢት እየገባ እኛና እነሱ የሚባል ክፍፍል በመፈጠሩ የተነሳ አገሪቱ አደጋ እንዳንዣበበባት ያስረዳሉ፡፡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አገልግሎቱ በዚህ መነጽር ስለሚታይ፣ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ደሃ አገር ውስጥ ይህ ዓይነቱ ነገር አደገኛ ጣጣ እንሆነ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ንጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ ለመጣው ሕዝባዊ ብሶትና አመፅ ከበስተጀርባው የሚገፋፉ ምክንያቶች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ ከበስተጀርባ ሆነው እያቀነቀኑ ያሉ አካላት የችግሩ አመንጭዎች መሆናቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ንጋት፣ ፊት ለፊት እየተቃወመ ያለውን ሕዝብ ችግር ለመፍታት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ከመንቀሳቀስ  እስከ ሕገ መንግሥት ማሻሻል ድረስ ሊሄድ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡

የፖለቲካ ተንታኝና ‹‹የዲስኮርስ› መጽሔት ዋና አዘጋጁ አቶ ዳደ ደስታ በበኩላቸው፣ አንዴ ረገብ ያለ የሚመስል በሌላ በኩል ደግሞ እንደገና እየተለኮሰና ብዙ ሰው እያሳተፈ ንብረትና ሕይወት እየጠፋ ላለው ችግር ምክንያቱ በቀላሉ ይህ ነው ብሎ መናገር ይከብዳል ይላሉ፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት ሙሉ በሙሉ በአካባቢውና በክልሎች ባለሥልጣናት እንዝህላልነት ወይም አባባሽነት የተፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህ እንዳይሆን የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ተግተው ሊሠሩ ይገባ ነበር ብለዋል፡፡ ‹‹በድንበር አካባቢ እንደዚህ ዓይነት ችግር እንደሚፈጠር የሚታወቅ ቢሆንም፣ መንግሥት የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን ቢያከናውን ኖሮ ችግሩ ዕድገት አይኖረውም ነበር፤›› ብለዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ አላከናወነም ብሎ ተጠያቂ ማደረግ እንደሚቻልም አስረድተዋል፡፡

አቶ ዳደ በኦሮሚያ ክልል እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ግልጽ እንዳልሆኑላቸው ያስረዳሉ፡፡ የጥያቄው ባለቤት አልባነትና የመጨረሻ ግብ በግልጽ አለመታወቅ የሁከቱን ሁኔታ ለመረዳት እንዳስቸገራቸው ጠቁመዋል፡፡ ኢንጂነር ይልቃል ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ በኦሮሚያ ክልል ከዚህ በፊት ደግሞ በአማራ ክልል ተፈጥረው የነበሩ ግጭቶችና ሕዝባዊ ጥያቄዎች፣ ዋነኛ መነሻቸው አገር በጎሳ እየተከፋፈለች በመምጣቷ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡

የተቃውሞው ባለቤቱም ግቡም እንደሚታወቅ ያስረዳሉ፡፡ የዚህ ሁሉ ተቃውሞ ባለቤቱ ሕዝቡ እንደሆነና የመጨረሻ ግቡም በአገሪቱ ውስጥ እኩልነት፣ ፍትሐዊነትና ግልጽነት ማስፈን ላይ ያተኮረ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ለዚህ ሁሉ ተቃውሞ ዋነኛ መነሻ ደግሞ ሕገ መንግሥቱ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ አገሪቱ ውስጥ ሥልጣን ያለው ዜጋ ሳይሆን ብሔር ብሔረሰቦች መሆናቸው ደግሞ ለዚህ የችግሩ መንስዔ ነው ይላሉ፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ የሙስና እየተስፋፋ መምጣት፣ የወጣቶች ሥራ አጥነት መጨመር፣ የግዴለሽነት መባባስ፣ ዝርክርክነትና አባካኝነት ከመንግሥት እስከ ግለሰብ ድረስ እየበዛ መምጣቱ አሳሳቢ እንደሆኑ ኢንጂነር ይልቃል ይናገራሉ፡፡ በፀረ ሽብር ዘመቻው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ የሆነ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ድጋፍ እንደምታገኝ የጠቀሱት ኢንጂነሩ፣ ይሁን እንጂ አገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ ማምጣት አልቻለችም ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቃውሞው እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳዩ  ምክንያቶች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአገሪቱ ብሎም በክልሉ ከዚህ በፊት የነበረው የመልካም አስተዳደር ችግርና የሙስና መንሰራፋት ሁነኛ የችግሮች መንስዔ ሆነው ሲገለጹ ቢሰማም፣ የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) መሥራችና ታጋይ አቶ አባዱላ ገመዳ ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረብ ሌላው ለተቃውሞው መስፋፋት አንዱ ምክንያት ሆኖ ተቆጥሯል፡፡ አቶ ዳደ በዚህ ሐሳብ  ይስማማሉ፡፡ በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣው የተቃውሞ እንቅሰቃሴ ግን ማን እንደሚያደራጀው እንደማይታወቅ ገልጸው፣ በመላምት ደረጃ የአቶ አባዱላ ከአፈ ጉባዔነት ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረብ አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ የሚሞተው ተራው ሰው ቢሆንም የተለየ ጥቅም አገኛለሁ ብለው የሚንቀሳቀሱ አካላት ሊኖሩ ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተከፋፈለና ጽንፍ የያዘ እንደሆነ የገለጹት አቶ ዳደ፣ ‹‹ሥልጣን ያልያዘ ተቃዋሚ በማኩረፍ ውጭ ሆኖ የመተኮስ ልማድ አለው፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ውጭ ያሉ ከፖለቲካው ተገለናል፣ ተዋክበናል፣ ታስረናል፣ ተገርፈናል ስለዚህ ይህንን መንግሥት መጣል እንፈልጋለን የሚሉ ኃይሎች አሉ፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ይህንን እንደ ጥሩ አጋጣሚና አቅም የሚያዩ የተለያዩ ፖለቲካዊ ምክንያቶች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ትምህርት ጥራት ከፍተኛ አደጋ ላይ እንዳለ የጠቆሙት አቶ ዳደ፣ ዩኒቨርሲቲዎች በአጠቃላይ ለማኅበራዊ ሚዲያ በሚያግዝ መንገድ የተቀረፁ እንደሚመስሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ምርምርና ጥልቅ ትንታኔ ለማድረግ ሳይሆን እነዚህን መረጃዎች ለመቀባበል የተቀረፁ ነው የሚመስሉት፤›› ብለዋል፡፡

አገሪቱ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች ዕድገት እያስመዘገበችና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቷ ከፍ እያለ ቢመጣም፣ በማኅበራዊ ትስስርና የጋራ የሚለውን እሳቤ በቁሳዊ የመለወጥ አዝማሚያ እየታየ ነው ይላሉ፡፡ ችግሩን ለመቋቋምና አንድ ነን የሚለውን መንፈስ የሚያጠናክር ማኅበረሰብ ከመፍጠር አኳያ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ንጋት በልመናና በድጋፍ መጥቶ የተገነባ መሠረተ ልማትንም ሆነ በውጭ ምንዛሪ የተገዛ ተሽከርካሪን ማቃጠል ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ድርጊት ምክንያት ኢንቨስትመንት በአገሪቱ ከመቆሙ ባሻገር የውጭ ኢንቨስትሮች ዘግተው የሚሄዱበት ዕድል ሰፊ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በስንት ልፋትና ውጣ ውረድ የተገነቡ መሠረተ ልማቶችን ማቃጠል ኪሳራው ለመንግሥት ሳይሆን ለሕዝብ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታትም መንግሥት ከሕዝቡ ጋር ውይይት ማድረግ አለበት ሲሉ በአፅንኦት አስረድተዋል፡፡

አቶ ዳደ በበኩላቸው ችግሩን ለመከላከልና ዘላቂ ሰላም በአገሪቱ እንዲሰፍን ለማድረግ፣ በመጀመርያ በሕግና በሕጋዊነት ላይ አለመደራደር ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ወንጀል የሠራ ሰው ካለ ተጠያቂነት ማስፈንና እሱን ወደ ሕግ ማቅረብ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ አንድ ችግር ሲፈጠር እንፈታዋለን በማለት ማለፍ ሳይሆን፣ ከሥር ከሥር እየፈቱ መሄድ ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ መፍትሔ ያላገኙ ቅሬታዎችና ችግሮች ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ብዙኃኑን ሕዝብ ማዕከል በማድረግና ውይይት በማካሄድ መፍትሔዎችን ማምጣት ይገባል ብለዋል፡፡

ኢንጂነር ይልቃል በበኩላቸው፣ ‹‹ዋንኛው መፍትሔ ኢሕአዴግ ሁሉን ነገር ጨምድዶ ይዞ ሊሻሻል ስለማይችል ሰፊ የሆነ አገራዊ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያለው የአገሪቱ ችግር ከአንድ ፓርቲና ከኢሕአዴግ በላይ ነው፡፡ ስለዚህ የሚመለከታቸው  የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሲቪክ ማኅበራትና የአገር ሽማግሌዎችን ያሳተፈና ሁሉንም ያማከለ ብሔራዊ ውይይት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ አዲሱ በቡኖ በደሌ ዞን የተከሰተውን ሁከት አስመልክተው፣ ‹‹ሲደረጉ የነበሩ ሠልፎች ወደ ሁከትና ብጥብጥ አምርተው በሰዎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን በተለያዩ ሚዲያዎች መግለጻችን ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት የወረዳዎቹ ሕዝቦች፣ የክልሉ የፀጥታ አካላትና የአገር ሽማግሌዎች ባደረጉት ርብርብ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር ሥር ውሎ በአካባቢው መረጋጋት ተፈጥሯል፡፡ በሁከቱ የተሳተፉና በሰው ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ በርካታ ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ  እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአካባቢው መረጋጋት እንዲፈጠርና ተመሳሳይ ችግሮች በድጋሚ እንዳይከሰቱ ለማድረግ ጠንክሮ እየሠራ ነው፡፡ የሁከቱን መፈጠር ተከትሎ ጉዳት እንዳይደርስባቸው በመፍራት 1,500 የሚጠጉ ዜጎች በጮራ፣ ዴጋና በደሌ ከተሞች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ሕዝቡም ለእነዚህ ዜጎቻችን ምግብ፣ ውኃና አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአገር ሽማግሌዎች፣ የፀጥታ አካላትና የመንግሥት አመራሮች ከሕዝብ ጋር በመረባረብ  ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ንጉሡ በበኩላቸው፣ ‹‹የፀጥታ አካላትና የአገር ሽማግሌዎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ቀሪ ሀብትና ንብረት በመጠበቅና አካባቢውን በማረጋጋት ላይ መሆናቸውን ከሥፍራው መረጃውን አድርሰውናል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ በተለይም በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት መንግሥት ከላይ ታች እያለ መሆኑ ሲነገር ቢሰማም፣ አፋጣኝ መፍትሔ ከመስጠት አኳያና ችግሮች ይደርሳሉ ብሎ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ረገድ አርኪ ተግባር አለመከናወኑ የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ከሚኖሩ ወገኖች ጋር የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ነው በሚባልበት ወቅት፣ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መታየታቸው የመንግሥትን የቁጥጥር መላላት ማሳያዎች እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

ለሾፌሩ ተሾመም ሆነ ለፖለቲከኞች፣ እንዲሁም የክስተቶችን ተከታታይነት ለሚታዘቡ መፍትሔ ያልተገኘላቸው ችግሮች ያሳስባሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል ሲባልም ከሕዝብ ጋር በግልጽ ከመነጋገር ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ይስማማሉ፡፡ ችግሮችን እያስታመሙ መዝለቅ እንደማይቻልም በአፅንኦት ያስረዳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -