Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ካርዲናል ሆኑ

ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ካርዲናል ሆኑ

ቀን:

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳትና የኢትዮጵያ ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚዳንት ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል የካርዲናልነት ማዕረግ አገኙ፡፡ ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስን ጨምሮ ለ15 ሊቃነ ጳጳሳት የካርዲናልነት ማዕረግና ለአምስት ሊቀ ጳጳሳትና ጳጳሳት ድምፅ አልባ (የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት የሌላቸው) የካርዲናልነት ሹመት ባለፈው እሑድ ረፋድ ላይ በቫቲካን በመስጠት ይፋ ያደረጉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ናቸው፡፡ ቫቲካን ሬዲዮ ታኅሣሥ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. እንዳስታወቀው፣ የአዲሶቹ 15 ካርዲናሎች በዓለ ሲመት በቫቲካን የሚፈጸመው የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው፡፡ 20ዎቹ ተሿሚዎች ከሁሉም ክፍለ ዓለም ከሚገኙ ከ14 አገሮች የተውጣጡ ሲሆን፣ ስብጥሩም የሮም ካቶሊካዊ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዙሪያ ካሉት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላትን ትስስር የሚገልጽ መሆኑን አቡነ ፍራንሲስ አስታውቀዋል፡፡ ሁለተኛው አፍሪካዊ ካርዲናል የሆኑት የኬፕቨርዴው ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ፣ ከተመረጡት አምስቱ አረጋውያን ጳጳሳት መካከልም የሞዛምቢኩ ጳጳስ ይገኙበታል፡፡ አዲሶቹ ካርዲናሎች አብዛኛዎች ከ80 ዓመት በታች ሲሆኑ፣ በተሰጣቸው አዲስ ሹመት መሠረት በመንበረ ጴጥሮስ የሚቀመጠውን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት (ፖፕ) ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ ይችላሉ፡፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ከተለያዩ አገሮችና አኅጉሮች አዲሶቹን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ይፋ ሲያደርጉ እንዳስታወቁት፣ ፍላጎታቸው በዓለም ዙሪያ የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ከሮም ቤተ ክርስቲያን ጋር ያላቸው የማይነጣጠል ትስስር ለማሳየት ነው፡፡ በመጪው የካቲት በአዲሶቹ ካርዲናሎች በዓለ ሲመት አጋጣሚም ለቫቲካን አስተዳደር ህዳሴን ለማምጣት ሁሉም ካርዲናሎች በዋዜማው እንደሚመክሩ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ የአቡነ ብርሃነየሱስ ካርዲናል መሆንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ደስታዋን የገለጸች ሲሆን፣ በተለይ የቤተ ክርስቲያኒቷ ሊቀ ጳጳሳት ጽሕፈት ቤት ጸሐፊ አባ ተስፋዬ ወልደማርያም ለቫቲካን ሬዲዮ እንደተናገሩት፣ የካርዲናልነት ሹመቱ ለአገሪቱ ትልቅ ክብርና ኩራት መሆኑንና ለኢትዮጵያ መንፈሳዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያለው አስተዋጽኦ ትልቅ ነው ብለዋል፡፡ ሊቀ ጳጳሳቱ ለካርዲናልነት ሹመት የበቁት ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ባደረጉት ከፍተኛ መንፈሳዊና ሁለንተናዊ ሰብዓዊ ዕድገት አስተዋጽኦ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ብፁዕ እምብፁዓን ካርዲናል ብርሃነየሱስ ደምረው ሱራፌል ገጸ ታሪካቸው እንደሚያመለክተው፣ የተወለዱት ሐምሌ 7 ቀን 1940 ዓ.ም. በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ከሐረር ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ጨለቅለቃ ነው፡፡ የነገረ መለኮት (ቲኦሎጂ) እና የፍልስፍና ትምህርታቸውን በአገር ውስጥና በእንግሊዝ ሲያጠናቅቁ፣ ከኢጣሊያ ግሪጎሪያን ዩኒቨርሲቲም በሶሲዮሎጂ የማስትሬት ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም ሰኔ 27 ቀን 1968 ዓ.ም. ማዕረገ ክህነትን ሲቀበሉ፣ ጥቅምት 28 ቀን 1990 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ረዳት ጳጳስ፣ ጥር 17 ቀን 1990 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ጳጳስ ሲሆኑ፣ የመጀመርያው የኢትዮጵያ ካርዲናል ጳውሎስ ፃድዋ (1913-1996) ተተኪ በመሆንም ሰኔ 30 ቀን 1991 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ሊቀ ጳጳሳት ሆነዋል፡፡ ከሲመተ ጵጵስናቸው በፊት በ1982 ዓ.ም. የላዛሪስት ማኅበር፣ እንዲሁም በ1986 ዓ.ም. የጂማ ቦንጋ ሀገረ ስብከት ጠቅላይ አለቃ የነበሩት ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ በአዲስ አበባ በሚገኘው የካፑቺን ፍራንቼስካና የፍልስፍናና ነገረ መለኮት ተቋም ከመሠረቱት አንዱና መምህርም ነበሩ፡፡ ከመንፈቅ በፊት በማላዊ ሊሎንግዌ ከተማ በተካሄደው የ17ቱ የምሥራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ኅብረት (አመሲያ) ሊቀመንበር ሆነው በመመረጥ በማገልገል ላይ ሲገኙ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለርም ናቸው፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጳጳሳት ምክር ቤትንም በሊቀመንበርነት ይመራሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ የታሪክ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በኢትዮጵያ የካቶሊክ እምነት በተንሰራፋበት ከ16ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ 71 ጳጳሳት ያለፉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ከ20 በታች የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ አልፎንስ ሜንዴዝን ጨምሮ ሦስት የፖርቱጋልና የስፔን ሊቃነ ጳጳሳት በተለያዩ ጊዜያት ‹‹የኢትዮጵያ ፓትርያርክ›› የሚል ሥልጣን ነበራቸው፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመርያ አጋማሽ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ መንበር በሊቀ ጳጳስነት ከ1953 ዓ.ም. እስከ 1969 ዓ.ም. የተቀመጡት አቡነ አሥራተ ማርያም የምሩ ሲሆኑ፣ ተከታያቸው ደግሞ ካርዲናል ጳውሎስ ፃድዋ ከ1969 ዓ.ም. እስከ 1991 ዓ.ም. ተቀምጠው ነበር፡፡ አቡነ ጳውሎስ ፃድዋ በቫቲካን ካርዲናል በሆኑ (ግንቦት 17 ቀን 1977 ዓ.ም.) በ30ኛው ዓመት ካርዲናል የሆኑት አቡነ ብርሃነየሱስ፣ የአዲስ አበባ ሜትሮፖሊታንን በሊቀ ጳጳስነት መምራት ከጀመሩ 16 ዓመታት ሞልቷቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከቫቲካን ጋር ዲፕሎማቲክ ግንኙነት በሌጋሲዮን ደረጃ የጀመረችው በ1949 ዓ.ም. ሲሆን፣ ወደ ኤምባሲ ደረጃ ያደገው ከ12 ዓመታት ቆይታ በኋላ መሆኑ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...