Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ተጠርጣሪ በነፃ ተሰናበቱ

የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ተጠርጣሪ በነፃ ተሰናበቱ

ቀን:

– ከአንድ ዓመት ከአምስት ወራት በላይ በእስር ቆይተዋል

በሥልጣን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የዲስትሪቢዩሽን ሲስተም ሥራ አስፈጻሚና የደንበኞች አገልግሎት ድጋፍ ክፍል ኃላፊ፣ የተመሠረተባቸውን ክስ በብቃት መከላከል በመቻላቸው ከተጠረጠሩበት የወንጀል ክስ ታኅሳስ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በነፃ ተሰናበቱ፡፡ የተመሠረተባቸውን ክስ በብቃት ተከላክለው ከተጠረጠሩበት ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል በነፃ የተሰናበቱት፣ ሥራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ብርሃኔና የደንበኞች አገልግሎት ድጋፍ ክፍል ኃላፊ አቶ ሞገስ በላቸው ናቸው፡፡ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ነፃ በወጡት ሁለቱ ኃላፊዎችና ሌሎች ሦስት ተጠርጣሪዎች ላይ ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ በወቅቱ ኮርፖሬሽኑ የዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመሮችን በሰፕላየር ክሬዲት ለመግዛት ጨረታ ያወጣል፡፡ ጨረታውን ጉድላክ ስቲል ቲዩብስ ሊሚትድ የሚባል የህንድ ኩባንያ ያሸንፋል፡፡ 3,520 ትራንስፎርመሮችን ወለዱን ጨምሮ 17,695,686.07 ዶላር ለማቅረብ ጥር 30 ቀን 2000 ዓ.ም. ውል በመግባት ስምምነቶችን መፈጸሙን ክሱ ያብራራል፡፡ ጉድላክ በውሉ መሠረት በሰፕላየር ክሬዲት እንደሚያቀርብ የተስማማውን በራሱ ማቅረብ እንደማይችል በመግለጽ፣ ፋይናንስ የሚያደርግለት ኮብራ ኢንስታሌሽን የተባለ ሌላ ሦስተኛ ኩባንያ ማቅረብ እንዲችል ውሉ እንዲሻሻልለት ጥያቄ ማቅረቡን ክሱ ይገልጻል፡፡ ኩባንያው ባቀረበው የውል ማሻሻያ ጥያቄ መሠረት ግንቦት 10 ቀን 2000 ዓ.ም. ጉድላክ ስቲል ቲዩብስ ትራንስፎርመር አቅራቢ፣ ኮብራ ኢንስታሌሽን የተባለው ኩባንያ ደግሞ የትራንስፎርመር ግዢውን በገንዘብ የሚደግፍ ተባባሪ ሆነው ሲቀርቡ፣ የኮርፖሬሽኑ የሕግ ክፍል ጉድላክ ኩባንያ ከሦስትዮሽ ውሉ እንዳይወጣ ማሳሰቢያ መስጠቱን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ እንደ ኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ግን አቶ መስፍን የውክልና ሥልጣን ሳይኖራቸው፣ ጉድላክ ኩባንያ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ቀደም ብሎ የገባውን ውልና የወሰደውን ኃላፊነቶች ለኮብራ ኢንስታሌሽንና ህንድ ለሚገኘው ትራንስፎርመር አምራች ለሆነው ናሽናል ኤሌክትሪክ ኢኪዩፕመንት ኮርፖሬሽን ማስተላለፉን የሚገልጽ ውል ሲቀርብላቸው፣ ውሉ ተቀባይነት ማግኘቱን የሚገልጽ ማረጋገጫ መስጠታቸውን በክሱ አካቷል፡፡ ኮብራ የተሰኘው ኩባንያ ትራንስፎርመር የማቅረብ የሕግ ችሎታው (Legal Capacity) እና አቅሙ (Supplier Qualification) ሳይገመገምና ከኮርፖሬሽኑ ይሁንታ ሳያገኝ፣ ለሪዘርቭ ባንክ ኦፍ ኢንዲያ (Reserve Bank of India) ለጻፈው ደብዳቤ ማረጋገጫ፣ መጀመሪያ ከኮርፖሬሽኑ ጋር የገባውን የውል ኃላፊነት ለሦስተኛ ወገን አስተላልፎ ጉድላክ መወጣቱን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ አቶ መስፍን መስጠታቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቦ ነበር፡፡ አቶ ሞገስ በላቸው ደግሞ በሌለበት ክስ የተመሠረተበት ሚስተር ጂስስ ማሪያ ግራሶይን ሮምዬ የተባለው የኮብራ ኢንስታሌሽንስ ዋይ ሰርቢሺዬስ ኢንዲያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዳይሬክተር፣ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ለገባቸው ውሎች የአፈጻጸም ዋስትና ውል በሚያዘው ፎርማትና ይዘት መሠረት ያልተዘጋጀ ውል እንዳቀረበላቸው ክሱ ያስረዳል፡፡ ያቀረበው ሰነድ የአፈጻጸም የባንክ ዋስትና ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው፣ ‹‹በዋስትና ሰጪው የባንክ የገንዘብ መጠየቂያ ደብዳቤ በህንድ መንግሥት ባንክ የሚሰጥ ሆኖ፣ ፓሪስ በሚገኘው የናቲክሲስ ማድሪድ ቅርንጫፍ ባንክ ተቀባይነት ካገኘበት ቀን በኋላ ብቻ›› መሆኑን አቶ ሞገስ ያውቁ እንደነበር ክሱ ይተነትናል፡፡ የኮብራ ኩባንያ ዳይሬክተር በውሉ መሠረት ሳይፈጽም ከቀረ ኮርፖሬሽኑ የአፈጻጸም ዋስትናውን መውረስ እንደማያስችለው እያወቁ፣ አቶ ሞገስ ለኮርፖሬሽኑ ማሳወቅ ሲገባቸው ዋስትናውን ተቀብለው በውስጥ ማስታወሻ ሸኝነት ለኮርፖሬሽኑ ፋይናንሻል ማኔጅመንት መምርያ በመላካቸውና ችግር በመፈጠሩ፣ ኮርፖሬሽኑ ኮብራ ያስያዘውን የአፈጻጸም ዋስትና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲወርስለት ሲጠይቅ፣ ዋስትናው በቅድመ ሁኔታ የተያዘ በመሆኑ መውረስ እንደማይቻል ባንኩ በመግለጹ፣ ኮርፖሬሽኑ 1,487,776 ዶላር ጥቅም እንዲያጣ ማድረጋቸውንና በመንግሥት ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ገልጾ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶ ነበር፡፡ ሁለቱም በነፃ የተሰናበቱት ተጠርጣሪዎች ድርጊቱን አንዳልፈጸሙና ጥፋተኛም እንዳልሆኑ በወቅቱ በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል አረጋግጠው ክርክራቸውን ሲያደርጉ ከርመዋል፡፡ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰዎችና የሰነድ ማስረጃዎችን እንዲያቀርብ በተሰጠው ብይን መሠረት፣ ምስክሮቹን አሰምቶና ሰነዶችንም አቅርቦ ነበር፡፡ ክሱን ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ክሱንና ማስረጃዎቹን መርምሮ ያጠራጥራሉ ባላቸው ነጥቦች ላይ ነፃ የተሰናበቱት ኃላፊዎች እንዲከላከሉ ፍርድ ሰጥቶ ነበር፡፡ ኃላፊዎቹ የሰውና የሰነዶች መከላከያ ምስክሮቻቸውን በማቅረብ የተጠረጠሩበትን ሥልጣንን ያላግባብ የመገልገል የሙስና ወንጀል፣ በአግባቡና በብቃት ያስተባበሉና ያስረዱ መሆናቸውን በመግለጽ፣ በእስር ላይ ከቆዩበት አንድ ዓመት ከአምስት ወራት የማረሚያ ቤት ቆይታ በኋላ ከታኅሳስ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በነፃ መሰናበታቸውን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አሳውቋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ አንድ ዓመት ከአምስት ወራት የማረሚያ ቤት ቆይታ በኋላ በነፃ መሰናበታቸው ከፍርድ ቤቱ ይፋ ሲደረግ አዛውንቶች፣ ባልቴቶች፣ ጐልማሶችና ወጣት ቤተሰቦቻቸው በእንባ ተራጭተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...