Monday, July 22, 2024

ፖለቲከኞቻችን የማኅበረሰቡ ነፀብራቅ ይሁኑ!

እኛ ኢትዮጵያውያን ከምንታወቅባቸው መልካም እሴቶቻችን መካከል በክፉና በደግ ጊዜ በሰላምና በፍቅር መተሳሰባችን፣ ከልዩነቶቻችን ይልቅ አንድ የሚያደርጉንን አጥብቀን መያዛችን፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላቶቻችንን በአንድነት ማክበራችንና አገራችንን ከምንም ነገር በላይ መውደዳችን ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተለያዩ ማኅበረሰቦች ውስጥ ትልቅ አክብሮት የሚሰጠው አለመግባባቶችን በሽምግልና የመፍታት ልማዳችንም እንዲሁ ከፍተኛ ትኩረት የሚቸረው ነው፡፡ በአገራችን በዓላት በሚከበሩበት ወቅት በተለይ የሙስሊምና የክርስትና እምነት ተከታዮች የሚያሳዩት አብሮነት ለዓለም ሳይቀር ምሳሌ መሆን የሚችል ነው፡፡ ከበዓላት በተጨማሪ ሠርግ፣ ለቅሶና ሌሎች ማኅበራዊ ግንኙነቶቻችን እጅግ ከሚከበሩት እሴቶቻችን መካከል ይመደባሉ፡፡ በባህል፣ በእምነት፣ በአኗኗር ዘይቤና በአመለካከት ብንለያይ እንኳን ተቻችለንና ተከባብረን በመኖራችን እዚህ ደርሰናል፡፡ የመከራ ቀንበር እንደ መርግ ቢከብደንም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቢያጎሳቁለንም፣ ድህነት ህልውናችንን ቢፈታተነውም፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ቢያንገላታንም፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሉንም ችለን አንድ ላይ በሰላም ኖረናል፡፡ ወደፊትም እንኖራለን፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሕዝባችን መልካም እሴቶች አሉና፡፡ ሰሞኑን የሙስሊምና የክርስቲያን እምነት ተከታዮች በአራት ቀናት ልዩነት በዓሎቻቸውን ሲያከብሩ፣ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው አብሮነት በማኅበረሰቡ ውስጥ ሲንፀባረቅ ነበር፡፡ አንዳቸው የአንዳቸውን ድግስ ከመቋደስ አልፈው በተለያዩ ጉዳዮች ያስተሳሰሩዋቸው ማኅበራዊ ክንውኖቻቸውም ይወሳሉ፡፡ በዕድር፣ በዕቁብና በመሳሰሉት ይደጋገፋሉ፡፡ አንዱ ለሌላው ደራሽነታቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ይህ ሁሉ አብሮነት ለዘመናት የዘለቀ እሴት በመሆኑ ልንንከባከብና ልናጠናክረው ይገባል፡፡ የፈለገውን ያህል የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ቢኖር እንኳ የማኅበረሰባችን ተረዳድቶና ተሳስቦ መኖር መቼም ቢሆን ጥያቄ ተነስቶበት አያውቅም፡፡ ይልቁንም ተምረናል የሚሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በብሔርና በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት የማኅበረሰቡን መልካም እሴቶች ሲንዱ ይታያሉ፡፡ በአክራሪና በጽንፈኛ አመለካከታቸው የተቃኘውን ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ብቻ እነዚህን የከበሩ እሴቶች ለማጥፋት ይታትራሉ፡፡ በአንድነት ውስጥ ልዩነት፣ በልዩነት ውስጥ ውበት መኖሩን ባለመቀበል ሁሉንም ነገር ከቡድናዊ ፍላጎት አንፃር ብቻ ማስተናገድ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ጠባብ ቡድናዊ አመለካከት አገራዊ እሴቶችን እንደሚያፈራርስ ተገንዝበው ከድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው፡፡ ላለፉት 40 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጎልቶ የሚታየው ትልቁ ችግር፣ ለዘመናት በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ የሚታወቁትን መልካም እሴቶች ለማገናዘብ አለመፈለግ ነው፡፡ በሐሳብ የሚለይን በጠላትነት በመፈረጅ ዓይንህን ላፈር ማለት ትልቁ መለያ ነው፡፡ ዞር ብለን ስናይ ግን ኢትዮጵያውያን ከሚለያዩዋቸው ይልቅ፣ ለትልቁ አገራዊ አንድነትና ክብር ቅድሚያ በመስጠት ነው የሚታወቁት፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖሩ ዜጎቻችን ልዩነታቸውን ወደጎን በማድረግ አንድነታቸው ላይ በማተኮር በመተሳሰብ ሲኖሩ፣ ፖለቲከኞቻችን ግን በተቃራኒው አቅጣጫ ይጓዛሉ፡፡ ሥልጣን ላይ የሚወጣው ቡድን የተቀናቃኙን ነፃነት ባለመቀበል ለምን እኔ የምለውን አትሰማም በማለት ያስራል፣ ያጎሳቁላል፣ ይገድላል፡፡ ለሥልጣን የሚታገለውም ተቀናቃኙን ነገ አንተን አያድርገኝ በማለት ጊዜ ሲገኝ የሚወራረድ ዛቻ ይሰነዝራል፡፡ በዚህም ምክንያት በልዩነት ላይ ተነጋግሮ ችግሮችን በማስወገድ ነፃ ኅብረተሰብ እንዳይፈጠር በጠላትነት መፈራረጁ ይቀጥላል፡፡ ያለፉት 40 ዓመታት ጉዞ በደም የጨቀየውና በጥላቻ የተበላሸው የማኅበረሰባችንን መልካም እሴቶች ማክበር ባለመቻሉ ነው፡፡ አገር የሚያውቃቸው አዛውንቶች ባሉበት አገር ውስጥ ሸምጋይ ጠፍቶ ፖለቲከኞች ለከፋ ነገር ሲፈላለጉ ማየት አስተዛዛቢ ነው፡፡ ‹‹የእብድ ገላጋይ ድንጋይ ያቀብላል›› እንዲሉ፣ አንዳንዶቹ ከመካሪነትና ከመገሰጽ ይልቅ የመጠፋፋት አራጋቢ ሲሆኑ ይታያሉ፡፡ በአጠቃላይ እከሌ ከእከሌ ሳይባል የፖለቲካው መንደር ውስጥ ያሉ የማኅበረሰባችንን መልካም እሴቶች ማየት ካልቻሉ ለአገር አደጋ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በግራም ሆነ በቀኝ ጎራ የተሠለፉ የፖለቲካ ኃይሎች ስለዲሞክራሲ ከሚገባው በላይ ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ ነገር ግን ዲሞክራሲን በተግባር ለመተርጎም ያልተቻለበት ምክንያት ምንድነው ተብሎ እንደ አገር መጠየቅ አለበት፡፡ ዲሞክራሲ የተለያዩ አመለካከቶች የሚንሸራሸሩበት የሐሳብ ገበያ እንደመሆኑ መጠን፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት መገደብ የለበትም፡፡ በዲሞክራሲ የሰው ልጅ መብት ከምንም ነገር በላይ መጠበቅ እንዳለበት ይታወቃል፡፡ የሰው ልጆች መብት በተከበረ ቁጥር ከጠብ ይልቅ ሰላም፣ ከመራራቅ ይልቅ መቀራረብ፣ ከጉልበት ይልቅ ለሐሳብ ልዕልና ትልቅ ትኩረት ይደረጋል፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣን ተብሎ እነዚህን የዲሞክራሲ እሴቶች መናድ ለአገርም ለሕዝብም አይጠቅምም፡፡ በማኅበረሰባችን ውስጥ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ተከባብሮ መኖር ዋነኛ መሠረቱ አስተዋይነት ነው፡፡ የአገራችን ሕዝብ ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በተፈራረቁት አገዛዞች ውስጥ በርካታ ችግሮችን ቢያይም፣ በፖለቲከኞች ምክንያት የተቀሰቀሱ ግጭቶችን ቢያስተናግድም፣ በአስተዋይነቱ ምክንያት ለአንድነቱ ቅድሚያ ሰጥቷል፡፡ ይህንን የመሰለ መልካምና ታላቅ እሴት ባለበት አገር ውስጥ ግን ፖለቲከኞቻችን ጥላቻቸው ወደር የለውም፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ተቃዋሚዎቹን አላስተነፍስ ብሎ መውጪያ መግቢያ ሲነሳ፣ በተቃራኒው ያሉት ደግሞ በይደር የያዙት የመረረ ጥላቻ ውስጥ ናቸው፡፡ ፖለቲካዊ ልዩነት ያለ፣ የነበረና ወደፊትም የሚኖር መልካም ፀጋ መሆኑ እየተዘነጋ አገሪቱ እየተጎዳች ነው፡፡ የነገር እሳት እየቆሰቆሱ መልካም እሴቶችን ከመናድ ይልቅ መቀራረብና መነጋገር ይበጃል፡፡ ቀናውን ጎዳና እየተው ጠመዝማዛውን መምረጥ ጠቃሚ አይደለም፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም እሴቶች ይከበሩ፡፡ ሁለት ፀጉር ያወጡ ፖለቲከኞቻችንም ሆኑ በዙሪያቸው ያሉ ሁሉ ለእነዚህ መልካም እሴቶች መከበር ይትጉ፡፡ ጎራ ለይቶ እሳት መቆስቆስ ለማንም አይበጅም፡፡ የሕዝባችን የዘመናት የአብሮነት ፀጋዎች አቅጣጫውን ለሳተው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በመፍትሔነት ይቅረቡ፡፡ በፖለቲካው መንደር ውስጥ የነገሡት ጥላቻዎች፣ አሽሙሮች፣ ሐሜቶችና መፍትሔ አልባ ቧልቶች ለአገራችን አይበጁም፡፡ ከፖለቲካዊ ሥልጣን በላይ አገር ትቅደም፡፡ ሕዝብ ይከበር፡፡ በአገር ስም፣ በሕዝብ ስም፣ በዲሞክራሲ ስም መቀለድ ይብቃ፡፡ የአገራችን ሕዝብ መልካም እሴቶች አርዓያ ይሁኑ፡፡ ፖለቲከኞቻችን የማኅበረሰባችን ነፀብራቅ ይሆኑ ዘንድ ዓይናቸውን ይክፈቱ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...