የ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክ ሻምፒዮና ዝግጅት ቀጥሏል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየካቲት ወር መጨረሻ በአዲስ አበባ ለሚከናወነው 12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዝግጅት መቀጠሉን አስታወቀ፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ባለፈው ዓርብ ታኅሣሥ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. በብሔራዊ የአፍሪካ ሆቴል በሰጠው መግለጫ፣ ከየካቲት 25 እስከ 29 ቀን 2007 ድረስ ለሚደረገው የወጣቶች ሻምፒዮና ብሔራዊ አትሌቶች ምርጫና የውድድሩን ዳኞች ሥልጠና ዝግጅት እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ 90 ዳኞች የሁለተኛ ደረጃ ሥልጠና እየሰጠ ከመሆኑም በላይ፣ ከነዚህ ውስጥ 50 ዳኞች ለዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) ሥልጠና እንደተመረጡ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ለዚሁ ለ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌክስ ሻምፒዮና አገሪቱን ወክለው የሚወዳደሩ ብሔራዊ አትሌቶች ምርጫ ከጥር 7 እስከ 10 ባለው ጊዜ ውስጥ ለማከናወንም እንዳቀደም ተናግሯል፡፡ እስካሁን 33 የአፍሪካ አገሮች በሻምፒዮናው መሳተፍ የሚያስችላቸውን ምዝገባ እንዳጠናቀቁም ገልጿል፡፡