በአንድ ሳምንት ውስጥ ተከታትለው የመጡትን የእስልምናና የክርስትና የልደት በዓላትን ተከትሎ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት መደመጥ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ የዐውደ ዓመት ግብይትም እንዲሁ ተጧጡፏል፡፡ በኤግዚቢሽን ማዕከል ከተከፈተው ባዛር አንስቶ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ዳስ በመጣልና ለዐውደ ዓመት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን በማቅረብ የበዓል ግብይቱ ዓይን እንዲስብና ፉክክር የበዛበት ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ በከተማዋ የሚገኙ አንዳንድ የገበያ አዳራሾችም መግቢያቸው ላይ ስለ አቅርቦታቸው ጥራትና የዋጋቸው ተመጣጣኝነት በማስታወቂያ ያስነግራሉ፡፡ አብዛኛው ማስታወቂያውን እየሰማ ቢያልፍም ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ወደ ማዕከሉ ጎራ ይላሉ፡፡ እኛም ወደ አንዱ የገበያ አዳራሽ ሸዋ ሃይፐር ማርኬት ጎራ አልን፡፡ በዓይነታቸው ከተደረደሩት ዕቃዎች መካከል፣ ሰዎች ጋሪ እያሽከረከሩ የሚፈልጉትን ዕቃ ወደጋሪያቸው እየጨመሩ ይተላለፋሉ፡፡ የተደረደሩትን ሸቀጦች አልፈው ወደ ውስጥ ሲዘልቁ የአካባቢው ጠረንም እየተለወጠ ይመጣል፡፡ ሰፋ ባለ ባለማቀዝቀዣ መስታወት ውስጥ የሚታዩት የበግ፣ የበሬ፣ የአሳና የተበለተ የዶሮ ሥጋ ይታያል፡፡ ከመስታወቱ ፊት ለፊት ከቆሙት ገበያተኞችም፣ አንዳንዶቹ የታሸገውን የተበለተ የዶሮ ሥጋ ሲወስዱ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በዓይነቱ የተደረደረውን የበሬ ሥጋ እያስፈጩ ይወስዳሉ፡፡ ወ/ሮ ገነት ዓለማየሁ (ስማቸው ተቀይሯል) ስናገኛቸው የተበለተ ዶሮ እየገዙ ነበር፡፡ ወ/ሮ ገነት ከውጭ አገር ከመጡ ወራት ያስቆጠሩ ሲሆን፣ ወደ መርካቶ ወይም ደግሞ ሌሎች መሰል ገበያዎች ገብተው ለመሸመት ብዙም እንደማይደፍሩ ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም ያለቀለትና የተበለተ ዶሮ መግዛት ከድካም እንደሚገላግላቸው በመግለጽ የበዓሉ ዕለት ‹‹በዓል እንደመሆኑ ሳልጨናነቅ ማሳለፍ ነው የምፈልገው›› በማለት ጊዜና ጉልበት ስለሚቆጥብላቸው ከሱፐር ማርኬት መሸመት እንደሚመርጡ ይናገራሉ፡፡ ተጨማሪ የሚያስፈልጓቸውን የባልትና ውጤቶች እንደ በርበሬ፣ ቅቤ፣ ቅመማ ቅመምና የመሳሰሉትን ከባልትና እንደሚገዙ ድፎ ዳቦን በተመለከተ ግን አድካሚ ስላልሆነ እንደማያስጨንቃቸው ይገልጻሉ፡፡ የሸዋ ሀይፐር ማርኬት ባለቤት ወ/ሮ ሰሚራ ሸረፋ እንደሚሉት፣ ከገና በዓል ጋር በተያያዘ በብዛት ፍጆታ ላይ የሚውሉት እንደ ቸኮሌት፣ ከረሜላ፣ የሻማ ማብሪያና ኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች ላይ ከአምስት በመቶ እስከ አሥር በመቶ ቅናሽ ተደርጎባቸዋል፡፡ ‹‹ምግብ ነክ ነገሮች ግን ካለው የአቅርቦት እጥረት አንፃር ዋጋውን መቀነስ አልቻልንም›› የሚሉት ወ/ሮ ሰሚራ፣ ባለፈው ዓመት ማንኛውም ዶሮ በ85 ብር ይሸጥ እንደነበረና በአሁኑ ዓመት በ106 ብር በመሸጥ ላይ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ የሽንኩርት፣ የበርበሬና የቅቤ ዋጋም በገበያ ላይ ባለው ዋጋ እንደሚሸጥ ገልጸዋል፡፡ በዓሉን ተከትሎ አንዳንድ ሱፐር ማርኬቶች በልዩ ልዩ ጌጣ ጌጥ ያሸበረቁ ሲሆን፣ የገና ዛፍ፣ የገና አባት፣ መግቢያቸው ላይ አስቀምጠዋል፡፡ እንዲሁም ቀይ ሪቫንና ብልጭ ልጭ ነገሮች በየጥጋጥጉ በመስቀል በዓሉን አድምቀውታል፡፡ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የያዙ ፖስት ካርዶችና የመልካም ምኞት መግለጫዎች በየመደርደሪያው ተቀምጠዋል፡፡ በተጨማሪም በዓሉን በማስመልከት የዋጋ ቅናሽ ማድረጋቸውን በትንንሽ ካርዶች አትመው መበተን ይዘዋል፡፡ ቀደም ባሉ ጊዜያት የዐውደ ዓመትን መምጣት ተከትሎ እናቶች ለምግብነት የሚውሉ እንደ ጠላ፣ ጠጅ፣ ዶሮ ወጥና ሌሎችንም የዐውደ ዓመት ጣጣዎች ለመወጣት ከቀናት በፊት ደፋ ቀና ማለት ይጀምራሉ፡፡ ሥራውም አድካሚ በመሆኑ የበዓሉ ዕለትም ሊቀጥል ይችላል፡፡ ስለዚህም ሥራ ያላቸው እናቶች እረፍት በመውሰድ ሽር ጉድ ማለት ይጀምራሉ፡፡ ዶሮ በወጉ መገነጣጠል የማያውቁ ጀማሪ ባለትዳሮችም ጭንቀታቸው ይበረታል፡፡ በጊዜ ሒደት ግን እነዚህ ሁሉ ችግሮች እየተቀረፉ መጥተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ማንኛውም የባልትና ውጤቶች ክሽን ተደርገው በየባልትና መሸጫ መደብሩ ይገኛሉ፡፡ የተነጠረ ቅቤ፣ ድፎ ዳቦ፣ በርበሬ፣ ቅመማ ቅመም፣ ሚጥሚጣ፣ አዋዜ፣ ቆሎ፣ የተበለተ ዶሮ፣ አልፎ አልፎም የተቁላላ ዶሮ ጩኮና ሌሎችም የባልትና ውጤቶች በትዕዛዝ መቅረብ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በዚህም የብዙዎቹን እናቶች የጊዜ እጥረት ሲገታ ጉልበታቸውንም ከመቆጠብ አንፃር ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ አራት ኪሎ አካባቢ የሚገኘውን የሺ ባልትና መጥቀስ ይቻላል፡፡ በየሺ ባልትና የተነጠረ ቅቤ፣ ድፎ ዳቦ፣ በርበሬ፣ ዳጣ፣ ቅመማ ቅመምና የመሳሰሉት በየዓይነቱ ተደርድረዋል፡፡ በድፎ ዳቦ አቅራቢነት የሚታወቀው የሺ ባልትና ሱቅ ውስጥ ቁጥራቸው በርከት ያለ በኮባ ቅጠል የተጠቀለሉ ድፎ ዳቦች ተደርድረዋል፡፡ መጠናቸው የተለያየ ሲሆን፣ ዋጋቸውም እንደዚሁ ይለያያል፡፡ አቶ ቴዎድሮስ መኩሪያ በየሺ ባልትና ተቆጣጣሪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ መደብሩ ሙሉ ለሙሉ ባህላዊ ምግቦችን ይይዛል፡፡ በበዓል ወቅት ግን ምርቶቹ በብዛት የሚቀርቡ ሲሆን፣ ‹‹ማንኛውም ሰው ይገዛናል›› ይላሉ፡፡ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች በተለይም ወንደ ላጤዎች፣ ሠራተኞች ወደ ውጭ የሚልኩ ሰዎችና የኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች አብላጫውን ቁጥር እንደሚይዙ ይናገራሉ፡፡ በየሺ ባልትና በራሳቸው የሚያዘጋጁት ዳቦ፣ ሽሮ፣ በርበሬ፣ አጥሚት እህል፣ ቆሎና የመሳሰሉት ሲሆኑ የተነጠረ ቅቤ፣ ዳጣና የመሳሰሉትን ከሌሎች አቅራቢዎች እንደሚያመጡ ይገልጻሉ፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በገና በዓል ልዩ የዋጋ ጭማሪ አልተደረገም፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ ምርቶች ላይ ቅናሽ ታይቷል፡፡ በርበሬ ከቀናት በፊት በኪሎ ከ60 እስከ 70 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ቀንሶ በኪሎ ከ50 እስከ 55 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡ 900 ግራም የተነጠረ ቅቤ 143 ብር ከ75 ሳንቲም ይሸጣል፡፡ የዳቦ ዱቄት ላይ መጠነኛ ጭማሪ የታየ ሲሆን፣ አንድ ኪሎ ዱቄት ከ14 እስከ 15 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡ ስለሆነም በድፎ ዳቦ ሽያጭ ላይ መጠነኛ ጭማሪ የተደረገ ሲሆን፣ ሦስት ኪሎ ዳቦ በ88 ብር ይሸጣል፡፡ የሸቀጦች ዋጋ የተረጋጋ ነው የሚሉት አቶ ቴዎሮስ፣ የተበለተ ዶሮና የተቁላላ ዶሮ ማቅረብ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡ ዐውደ ዓመት ይበልጥ እየተጠጋ በመጣ ቁጥር በአንዳንድ ሸቀጦችና የእርድ እንስሳት ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደሚኖር በማሰብ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ለበዓል የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት ቀደም ብለው መሸመት ለምደዋል፡፡ አብዛኛው የሸመታ ሒደቱም የሚያጠነጥነው ከሱፐር ማርኬት ውጪ በሚደረግ ግብይት ነው፡፡ ወ/ሮ አስቴር በየነ ከነዚህ መካከል አንዷ ሲሆኑ፣ በአሁኑ በዓል ግን ቀድመው አልሸመቱም፡፡ ይሁን እንጂ ስለገበያው ዋጋ ቀደም ብለው ከማጣራት አልተቆጠቡም፡፡ ‹‹በብዛት የምገዛው በዓሉ ሳምንት ወይም ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ትንሽ ተዘናግቻለሁ›› ይላሉ፡፡ ወ/ሮ አስቴር የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ከመርካቶ መግዛት እንደሚመርጡ ይናገራሉ፡፡ በተለይም የዕርድ ሥርዓቱን ከተለመደው ውጪ የሚያደርግ አካሄድ አይመቻቸውም፡፡ ‹‹በዓል በዓል የሚመስለው ዕርድ ቤት ውስጥ ሲከናወን ነው፤›› ይላሉ፡፡ ምንም እንኳ ሥራው አድካሚ ቢሆንም፣ የባልትና ውጤቶችንና የተበለቱ የሥጋ ውጤቶችን ከሱፐር ማርኬት ከመሸመት ቤት ውስጥ ማዘጋጀቱን ይመርጡታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሱፐር ማርኬት የሚገዙ ዕቃዎች ዋጋቸው ውድ እንደሆነ ስለሚያስቡ ከሱፐር ማርኬት መግዛቱን አይመርጡትም፡፡