Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምተቃውሞ የበረታበት አወዛጋቢው የኬንያ ፀረ ሽብር ሕግ

ተቃውሞ የበረታበት አወዛጋቢው የኬንያ ፀረ ሽብር ሕግ

ቀን:

ኬንያ የአልሸባብ የሽብር ጥቃት ሰለባ መሆን ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የኬንያ መንግሥትም ከአሸባሪዎች እየተሰነዘረበት ያለውን ጥቃት ለመመከት በተደጋጋሚ ቃል ቢገባም አልተሳካለትም፡፡ አልሸባብም ቀድሞ ቦምብ በማፈንዳት ዘር፣ ቀለምና ሃይማኖት ሳይለይ ያደርስ የነበረውን ጥቃት አቅጣጫ በመቀየር በኬንያ ክርስቲያኖች ላይ አነጣጥሯል፡፡ በዚህም ኬንያውያን ሥጋት ውስጥ ወድቀዋል፡፡ መንግሥት የሚገባውን ያህል አልሠራም ሲሉም ኮንነዋል፡፡ የኬንያ መንግሥት በአገሪቱ በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለውን የሽብር ጥቃት ለመግታት ያግዘኛል ብሎ ሰሞኑን የፀረ ሽብር ሕግ ቢያወጣም፣ ከውጭ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ከውስጥ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ተቃዋሚዎች ሕጉ ሰብዓዊ መብቶችን ይጥሳል ሲሉ ተቃውመዋል፡፡ የፀረ ሽብር ሕጉ ሽብርተኝነትን የመከታተልና የመቆጣጠር፣ የኤሌክትሮኒክስ ግንኙነቶችን የመቆጣጠር፣ የመከታተልና የማቋረጥ መብትን ለደኅንነት አካላት ሰጥቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማንኛውንም ወንጀል ለመፈጸም ይረዳል ወይም ያገለግላል ተብለው የሚጠረጠሩ ቁሳቁሶችን መያዝ ይችላል፡፡ የማኅበረሰብ ድረ ገጾችን ጨምሮ የመገናኛ ብዙኃን የአገሪቱ የደኅንነት አካላት የሚሠሩትን ሥራ ከነቀፉ ወይም ካብጠለጠሉ፣ ከፖሊስ አካላት ፈቃድ ሳያገኙ የሽብር ጥቃት ሰላባ የሆኑ፣ የተጎዱና የሞቱ ሰዎችን ምሥል በኅትመትም ሆነ በብሮድካስት ሚዲያ ካቀረቡ፣ በሕዝቡ ላይ ፍርኃት የሚለቅ ዘገባ ከለቀቁ፣ 55 ሺሕ ዶላር ወይም የሦስት ዓመት እስራት ወይም ሁለቱንም እንዲቀጡ ሕጉ ይፈቅዳል፡፡ የፀረ ሽብር ሕጉ ከዚህ በኋላ ኬንያ የምትቀበለውን የስደተኛ መጠንም ገድቧል፡፡ ኬንያ የፖለቲካ ጥገኝነት ሚጠይቁም ሆነ ስደተኞችን ጨምሮ የምታስተናግደው 150 ሺሕ ያህል ብቻ ይሆናል፡፡ ስደተኛ መሆናቸውን ያመለከቱም ቢሆኑ እንደ ቀድሞው በዋና ከተማዋ ናይሮቢ መኖርም ሆነ መንቀሳቀስ አይፈቀድላቸውም፡፡ ይልቁንም በስደተኛ ካምፕ ብቻ ተወስነው እንዲኖሩ ይደነግጋል፡፡ ሕጉ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ለአገሪቱ ፓርላማ ቀርቦ ከመፅደቁና በማግሥቱም በፕሬዚዳንቱ ከመፈረሙ አስቀድሞ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ያስከትላል፣ ለሽብርተኛ ተብሎ ሳይሆን በኬንያ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና ሚዲያውን ለማፈን የወጣ ነው፣ መንግሥት ሥልጣኑን በብቸኝነት ለመያዝ ሆን ብሎ ያስቀመጠው ሽፋን ነው በማለት ክርክር ሲደረግበት ቆይቷል፡፡ ባለፈው ሐሙስ የፀረ ሽብር ሕጉን ለማሳለፍ ወይም ለመጣል የተሰየመው ፓርላማም በብጥብጥና በድብድብ የታጀበ እንደነበር አልጄዚራ ዘግቧል፡፡ የፓርላማ አባላት አብላጫ ድምፅን አግኝቶ የፀረ ሽብር ሕጉ ሲያልፍ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ዶክመንቶችንና መጻሕፍትን የፓርላማው አፈ ጉባዔ ላይ ሲወረውሩ፣ ወረቀት እየቀዳደዱ ሲበትኑና ሲንጫጩ፣ እንዲሁም እርስ በርስ ሲታገሉ ታይተዋል፡፡ ይህ ግን የፀረ ሽብር ሕጉን በፓርላማው ከመፅደቅ አላገደውም፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ አወዛጋቢ የተባለውን ፀረ ሽብር ሕግ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በፊርማቸው ባለፈው ዓርብ ያፀደቁት ሲሆን፣ የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደግሞ ከሕጉ ስምንት የሚሆኑ ነጥቦችን ማገዱን አስታውቋል፡፡ ይህ የፀረ ሽብር ሕጉን ለሚቃወሙ አንድ ድጋፍ ቢሆንም፣ በተግባር ላይ ሲውል የሚያመጣው አሉታዊ ተፅዕኖ በቀጣይ የሚታይ ይሆናል፡፡ የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዳስታወቀው፣ ከሕጉ ውስጥ የታገዱት ነጥቦች ከሰብዓዊ መብት ተማጋቾች፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጎባቸው ስምምነት ላይ ሲደርስ ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ኬንያታ አወዛጋቢ የተባለውን የፀረ ሽብር ሕግ ከፈረሙ በኋላ፣ ‹‹በምሥራቅ አፍሪካ ላይ የተጋረጠውን የሽብር ጥቃት ለመግታት ያስፈልገናል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ኬንያውያን ተሻሽሎ የቀረበውን ሕግ እንዲያነቡት የጠየቁት ፕሬዚዳንት ኬንያታ፣ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ከተቃዋሚዎች ሕጉ በሽብር የሚጠረጠሩትንና የመገናኛ ብዙኃንን ነፃነት ያሳጣል የሚል ትችት ገጥሟቸዋል፡፡ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ በጋራ በሰጡት መግለጫ ሕጉ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያመጣ ይችላል በማለት ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ የአገሪቱን ደኅንነት ለመጠበቅ ሕግ መውጣቱን እንደሚደግፉ የገለጹት አገሮቹ የሰብዓዊ መብት ማክበር፣ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት መጠበቅና የሲቪሎችን ነፃነትና ዲሞክራሲ ማስከበር ሰላምን ለማስፈን ወሳኝ ጉዳዮች ናቸውም ብለዋል፡፡ የኬንያ ፕሬዚዳንት ቢሮ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሙንዮሪ ቡኩ፣ በፕሬዚዳንታዊው ድረ ገጽ ላይ አሜሪካ በኬንያ ፀረ ሽብር ሕግ ላይ የሰነዘረችውን ነቀፌታ አጣጥለውታል፡፡ ‹‹በኬንያ የፀደቀው ፀረ ሽብር ሕግ ከአሜሪካው በእጅጉ የተሻለ ነው፡፡ አሜሪካ በጓንታናሞ ቤይ የእስር ማዕከል በመርማሪ ፖሊሶቿና በደኅንነት አባሎቿ ከምታከናውነው አስከፊ ተግባር የኬንያው ፀረ ሽብር ሕግ የተሻለ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በአገሪቱ ከሚገኙ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ታዋቂ የሆነው ‹‹ኮዋሊዥን ፎር ሪፎርምስ ኤንድ ዲሞክራሲ›› አዲሱ የፀረ ሽብር ሕግ ዋና ዓላማ ሽብርተኝነትን መዋጋት ሳይሆን፣ ለፖሊስ አፋኝ ሥልጣን መስጠት እንዲሁም በመንግሥት ላይ ጫና የሚፈጥሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጠራርጎ ለማስወጣት ነው ብሏል፡፡ ፖሊስ በሽብር የተጠረጠረ ግለሰብን እስከ ሦስት ወራት ድረስ ፍርድ ቤት ሳያቀርብ ምርመራ ሊያደርግበት እንደሚችል በረቂቅ ሕጉ ላይ ሰፍሮ የነበረ ቢሆንም፣ የፀደቀው ሕግ ግን ይህንን ወደ አንድ ዓመት አሳድጎታል፡፡ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብትን ይጥሳል የተባለው ፀረ ሽብር ሕግ ፖለቲከኞች ጥላቻ የተሞላበት ንግግር ውስጥ እንዲዘፈቁ አድርጓል፡፡ አሰዳድቧል፣ አደባድቧል፡፡ ሆኖም ከመፅደቅ አልቀረም፡፡ ኬንያ በተደጋጋሚ በአልሸባብ እየተሰነዘረባት ያለውን የሽብር ጥቃት ከመከላከል ጋር ተያይዞም፣ ባለፈው ሳምንት ብቻ ከ500 የሚበልጡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ፈቃድ ሰርዛለች፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 15 ያህሉ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም የገቢ ማሰባሰቢያ ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው ተብሏል፡፡ የኬንያ መንግሥት ዕርምጃውን የወሰደው በተለይ ከአልሻባብ እየተሰነዘረበት ያለውን ጥቃት ለመከላከል እንደሆነ ቢናገርም፣ ተቃዋሚዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዕርምጃውን ነቅፈውታል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆኑት ሞሰስ ዋታንጉላ፣ የፀረ ሽብር ሕጉ ኬንያውያን እያጣጣሙ የነበረውን ነፃነት የሚጨፈልቅ ነው ብለዋል፡፡ የኬንያ መንግሥት ሰላም ለማስፈን ወታደሮቹን ወደ ሶማሊያ ከላከ እ.ኤ.አ. ከ2011 ወዲህ ሰላሙን በአልሻባብ አጥቷል፡፡ ዋና ከተማዋ ናይሮቢን ጨምሮ በተለያዩ ሥፍራዎች አልሸባብ ጥቃት አድርሷል፡፡ የኬንያ ወታደሮች ከሶማሊያ እስካልወጡ ድረስም ጥቃቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ ይህንን ተከትሎ ከአገር ውስጥና ከውጭ ሽብርን መከላከል አቅቶታል እየተባለ ሲነቀፍ የከረመው የኬንያ መንግሥት ጠንካራ የተባለ የፀረ ሽብር ሕግ አውጥቷል፡፡ በተለይ ከአካባቢው አገሮች ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ነፃነት የነበራቸው የኬንያ ጋዜጠኞች፣ እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አሁን በፀረ ሽብር ሕጉ ገደብ እንደተጣለባቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡ የኬንያ መንግሥት ጠንካራ የፀረ ሽብር ሕግ መውጣቱ አገሪቱን ከሽብር ለመከላከል ነው ሲል፣ የኬንያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ደግሞ ሕጉ እንዲቀየር ወይም እንዲሻሻል እንደሚሠሩ ለኬንያውያን ቃል ገብተዋል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች ግን ሕጉ በተግባር ላይ ሲውል ውጤቱን መገምገም ይበጃል እያሉ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...