ላብሲን ኢንተርናሽናል ኤክስፖ የተባለ ኩባንያ ከታኅሳስ 10 እስከ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ያዘጋጀው የገና ባዛር በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ሲካሄድ ነበር፡፡ በዚህም ዝግጅት ላይ 3,400 ያገለገሉ የእሽግ ውኃ ፕላስቲኮችን በማሰባሰብ ቁመቱ 12 ሜትር የሆነ ትልቁ የገና ዛፍ ለዕይታ አቅርቧል፡፡ ከታኅሳስ 10 እስከ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ የምሽቱን ሳይጨምር ከ200 ሺሕ በላይ ሰዎች መጎብኘታቸውን አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡ ፎቶ በታምራት ጌታቸው * * * ኑሮዬ ጣም ካጣ ልሒድ ልነሳ፣ ብር ልበል ልጥፋ፣ ራሴን ልሰዋ፣ ፈቅ ካላለልኝ የምኖረው ኑሮ፣ ልዩነት ከሌለው ድሮና ዘንድሮ፤ ምኑ ያጓጓኛል፣ ምኑ ይረባኛል፣ በድኔ ተገሽሮ፡፡ ጭንቅላት ጠንብቶ፣ አፍላነት ጠንዝቶ፣ የሚቀር ከሆነ በሰው መንገድ ጠፍቶ፤ ዓይን ይሉት ገላ አዲስ ቀን ካላየ፣ ሰማይ ኖርኩ ምድር፣ ገነት ገባሁ ሲዖል፣ ምን ያጋጥመኛል ከዚህ የተለየ፡፡ ከእርቅይሁን በላይነህ ‹‹እርቃንሽን ቅሪ›› (2007) * * * የታችኛውና የላይኛው ግብፅ ምድሪቱ ለሁለት የተከፈለች ነች፡፡ የታችኛው ግብፅ የሚባለው የዓባይ ወንዝ ወደ ሜዲትራንያን ባህር ሲቃረብ ረግረጋማና ደለላማ ባህር ገብ መሬት (ዴልታ) ያለውን ምድር ያጠቃልላል፡፡ የላይኛው ግብፅ የሚባለው ደግሞ ከዴልታው አንስቶ እስከ መጀመሪያው የዓባይ ፏፏቴ ድረስ 930 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚደርሰውን ምድር ያካትታል፡፡ የላይኛው ግብፅ በጥንቱ ዘመን ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የተሞላ ነበር፡፡ በጥንቶቹ ሐውልቶች ላይ ተቀርፀው የተገኙት ምሥሎች የሚያሳዩት፣ አንገታቸው ያጠረ፣ ራሰ ሞላላ፣ ግምባራቸው ጠባብ፣ አፍንጫቸው አጭርና ደፍጣጣ፣ ከናፍራቸው ትልቅና ወፍራም፣ አገጫቸው አጠር ያለና ወደ ኋላ የዘመመ ሰዎችን ነው፡፡ የእነዚህ ሕዝብ ገዥዎች ሙሉ በሙሉ ኩሽ ኢትዮጵያውያን ስለመሆናቸው የቀደምት ፈርኦኖቹን ገጽታና የተሳሉባቸውን የሸክላ ሳህኖችንና ጥንታውያን ቅርሶችን መመልከት ይበቃል፡፡ ታላቁ የስፊንክስ ሐውልት፣ የአንድ ጥንታዊ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ገጽታን የሚያሳይ ሲሆን፣ የዛሬውን ኢትዮጵያዊ መልክና ገጽታ በሐውልቱ ላይ ካለው የኬዎፕስ መልክ ጋር ስናነፃፅር ተመሳሳይነቱ ቁልጭ ብሎ ይታያል፡፡ ይህም ዘመን ያልሻረው የኩሽ ኢትዮጵያዊን ዘር የሚወክል ማስረጃ ነው፡፡ የታችኛው ግብፅ (ዴልታው ክፍል) በለም አፈር የተሞላ፣ እርሻ በብዛት የሚታይበት፣ የቴምር ዛፎች የሚበቅሉበት ሲሆን፣ ዝናብና ጤዛ ከዴልታው ይልቅ ወደ ባህሩ ጠረፍ ይበዛል፡፡ በአሌክሳንድሪያ ከተማ ጀንበር ስትጠልቅ፤ ከአየሩ እርጥበት የተነሳ በውጭ የተሰጡ ልብሶች ዝናብ እንዳረሰረሰው ረጥበው ይገኛሉ፡፡ ዝናብ ብርቅ ስለሆነ፣ በዝናብ ጊዜ ሕዝቡ በየጐዳናው ወጥቶ ሲደሰት ይታያል፡፡ ከፀደይ ወራት አጋማሽ በኋላ ግን በዚህ ክልል ከተሰነጣጠቀ መሬትና እንደ ግራጫ ከመሰለ ምድር በስተቀር ሌላ ነገር አይታይም፡፡ በመጸው ወራት፣ ውኃው የደፈረሰ ቀይማ መልክ ሲኖረው የቴምር ዛፍ ማደጊያ ወቅት ነው፡፡ በክረምት ደግሞ መላው የታችኛው ግብፅ በቆንጆ ልምላሜ ተውባ የምትታይበት ወቅት ነው፡፡ የላይኛው ግብፅ በተራሮች መካከል የሚገኝ ጠባብና ለም ሸለቆ የሚታይበት ምድር ሲሆን፣ ከታችኛው ግብፅ ጋር ሲነፃፀር ደረቃማ የአየር ንብረት ያለውና ለጤናም ተስማሚ የሆነ ክልል ነው፡፡ ሰማዩ በብርሃን ፀዳል የተሞላና ሙቀቱ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ይህን ሙቀት መቋቋም ለሚችል የሰው ዘር ሥፍራው እንደ መልካም የመኖሪያ ሥፍራ የሚቆጠር ነው የሚሉ አሉ፡፡ ዝናብ በዚህ አካባቢ የተለመደ ስላልሆነ የእርሻ ሥራዎች በመስኖ አማካይነት የሚካሄዱ ናቸው፤ በክልሉ ትልቁ ትኩረት ውኃን እንዴት ከወንዝ መሳብ ወይም መጥለፍ ይቻላል የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ በሁለቱ አካባቢዎች ከሚታየው የአየር ንብረት ልዩነት የተነሳ በሕዝቦቹ መካከል የአካልና የቆዳ ቀለማት ልዩነቶች እስከ መከሰት ደረጃ አድርሷል፡፡ በታችኛው ግብፅ የነዋሪዎቹ ቆዳ ነሐሳማ ሲሆን፣ በላይኛው ግብፅ ደግሞ ጥቁር የቆዳ ቀለም መለያ ሆኗል፡፡ – ድሩሲላ ዱንጂ ሒውስተን ‹‹ፒራሚድ ገንቢዎቹ ጥንታዊ ኢትዮጵያውያን›› (2002 ዓ.ም.) * * * ፖሊስ ደፋሪ ሲሆን የህንድ ሴቶች በወንዶቻቸው የሚደርስባቸው በደል የከፋ ነው፡፡ ከዘመድ ጐረቤት አንስቶ በማያውቁት ሰው ሁሉ ይደፈራሉ፡፡ ሰሞኑን ቢቢሲ ይዞት የወጣው ዘገባ ደግሞ ሁለት ፖሊሶች ታዳጊ ወጣት መድፈራቸውን ነው፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ ፖሊሶቹ ታዳጊ ወጣቷን የደፈሯት፣ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው ነው፡፡ * * * በአይጥ ምክንያት የአውሮፕላን በረራ በስድስት ሰዓት ዘገየ ከጥቂት ቀናት በፊት የኳታር አየር መንገድ አውሮፕላን ከስፔን ማድሪድ ወደ ኳታር ዶሪ ያደርግ የነበረው በረራ አውሮፕላኑ ውስጥ አይጥ በመግባቱ ለስድስት ሰዓታት መዘግየቱ ተዘግቧል፡፡ ዘገባው እንደሚያመለክተው አይጥ አውሮፕላኑ ውስጥ የገባው አውሮፕላኑ በማድሪዱ አዶሎፍ ሱዋሬዝ ባራጃስ አየር ማረፊያ ባረፈበት ወቅት ነበር፡፡ የአይጥ አውሮፕላኑ ውስጥ መግባት ተሳፋሪውን አደናግጦም ነበር፡፡ አይጧን ለመግደል ሙሉ አውሮፕላኑን ኬሚካል መርጨት የግድ ሆኖ የነበረ ሲሆን፣ በአውሮፕላኑ ተሳፍረው ወደ ዶሪ ለመሄድ በአየር ማረፊያው ይጠባበቁ የነበሩ ተጓዦች የኬሚካሉ ሽታ ሙሉ በሙሉ እስኪጠፋ ድረስ ባሉበት እንዲቆዩ ተደርጐ ነበር፡፡ በመጨረሻ አይጧ ሞታ ብትገኝም ስድስት ሰዓታት በወሰደው በዚህ አጋጣሚ ምክንያት ወደ ታይላንድ፣ ሲንጋፖርና ኢንዶኔዥያ ቀጣይ በረራ የነበራቸው ተጓዦች አውሮፕላን ያመለጣቸው ሲሆን፣ ኳታር አየር መንገድ የደረሰውን ኪሳራ እንደሚሸፍን አስታውቋል፡፡ * * * ከ2014 ትልልቅ የዓለም ሁነቶች በጥቂቱ – በምዕራብ አፍሪካ የተቀሰቀሰውና ብዙዎችን ለህልፈት የዳረገው የኢቦላ ወረርሽኝ – ለዘመናት ተቋርጦ የነበረው የአሜሪካና የኩባ ግንኙነት መለሳለስ – የነዳጅ ገበያ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ መቀነስ – 200 ተጓዦችን ያሳፈረው የማሌዥያ አውሮፕላን መጥፋት – አይኤስ አይኤስ ጥቃትና በሰሜናዊ ኢራቅ የተለያዩ ቦታዎችን መቆጣጠር – በናይጄሪያ የ200 ሴት ተማሪዎች በቦኮሀራም መጠለፍ – ሩሲያንና ምዕራባውያኑን ፍጥጫ ውስጥ የከተተው የዩክሬን ቀውስ – የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫን ማንሳት – የኦስካር ፒስቶሪየስ የፍርድ ቤት ውሎ – የጥቁር አሜሪካዊቷ ደራሲና ገጣሚ ማያ አንጀሎ ህልፈት * * * ከ43 ዓመታት በኋላ የቀድሞ ፍቅረኛቸውን ፍለጋ የገቡት አዛውንት የቋንቋ መምህር የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በጡረታ ላይ የሚገኙት ፕሮፌሰር በኢንተርኔት የቀድሞ ፍቅረኛቸውን በማፈላለግ ላይ ሲሆኑ፣ ፍቅረኛቸውን ለመጨረሻ ጊዜ ያዩአቸው እ.ኤ.አ. 1971 ነበር፡፡ ፕሮፌሰሩ በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ሆነው ከስኰትላንዳዊ ፍቅረኛቸው ኬት ሞሪስ ጋር የተነሱትን ፎቶግራፍ ዩቲዩብ ላይ ፖስት አድርገዋል፡፡ እንዴትና የት እንደተገናኙ በማስታወስ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ እየጻፉ ያሉት ፕሮፌሰሩ በወቅቱ እሳቸው ለሥራ ወደ ስፔን ከዚያም ጀርመን ሲሄዱ ፍቅረኛቸውም ወደ ስኮትላንድ መጓዟንም ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳ ዛሬ ሁለቱም በስልሳዎቹ ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም የዛኔዋ ፍቅረኛቸው ዛሬም ከሐሳባቸው እንደማትጠፋ የሚገልጹት ፕሮፌሰር ኬስ ሞሪስ የት እንደምትገኝ መረጃ ያለው ሁሉ እንዲረዳቸው ተማጽነዋል፡፡
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -
ፌርማታ ፅሁፎች
ትኩስ ፅሁፎች
- Advertisement -
- Advertisement -