Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የኢንተርፕሩነርሺፕ ሥርዓተ ትምህርት ቀርፀን በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለመስጠት ዕቅድ አለን››

ወ/ሮ እታለም እንግዳው የኢንተርፕሩነርሶች ልማት ማዕከል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢንተርፕሩነርሺፕ ልማት ማዕከል የተቋቋመው ባለፈው ዓመት  ነው፡፡ ቢዝነስ የመመሥረት ሐሳብ ያላቸውና ቢዝነስ የጀመሩ ግለሰቦች ስኬታማ ለመሆን የሚረዳቸውን የስድስት ቀናት ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ኢንተርፕሩሮቹ ሥራ ከጀመሩ በኋላም በተቋሙ ክትትል ይደርግላቸዋል፡፡ ከተመሠረተ ጀምሮ ለ6,891 ወንድና 3,700 ሴቶች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ወ/ሮ እታለም እንግዳው የኢንተርፕሩነርሺፕ ልማት ማዕከል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ በድርጅቱ ስለሚሰጠው ሥልጠናና አጠቃላይ ሥራዎቻቸው ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር:- ስለ ድርጅቱ አመሠራረትና ሥራዎቻችሁ ቢያብራሩልን?

ወ/ሮ እታለም፡- መንግሥት ማዕከሉን እንዲቋቁም ምክንያት የሆነው፣ የግሉ ዘርፍ ለአገሪቱ የምጣኔ ሀብት ዕድገት የሚያደርገው አስተዋጽኦ በታሰበው ፍጥነት አለመሄዱ ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ሬዚደንት ተወካይ ጋር ተወያዩ፡፡ ኢንተርፕሩነርሺፕ ማዕከል ሲቋቋም ብዙ ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ትልቁ ተብሎ የሚታሰበው ካፒታል ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ቴክኒካል የሙያ ሥልጠና ይሰጣል፤ ከዛም አልፎ የመሥሪያ ቦታ ይሰጣል፡፡ በትንሹም ቢሆን የሥራ ማስኬጃ ካፒታል ይሰጣል፡፡ ነገር ግን በታሰበው ፍጥነት ዘርፉ እያደገ አልነበረም፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው ሲባል ከካፒታል ባልተናነሰ የሰው አስተሳሰብ ላይ ክፍተት ነበር፡፡ ሰዎች በሥራ ላይ ተሰማርተው እንዲሳካላቸው ከሌሎች አገሮች የስኬታማ ኢንተርፕሩነሮች ልምድ ታይቷል፡፡  ግለሰቦች ክትትል እንዲደረግላቸው፣ የቢዝነስ ዕድገት አገልግሎት እንዲሰጥና በአገሪቱ ውስጥ ጥሩ የሆነ ኢንተርፕሩነርሺፕ ድባብ እንዲኖር ተብሎ የኢንተርፕሩነርሺፕ ልማት ፕሮግራም ተፀነሰ፡፡ ፕሮግራሙ የተጀመረው እ.ኤ.አ. ጥር 2013 ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር:- ተሞክሮ የተወሰደው ከየትኞቹ አገሮች ነው? ውጥኑ ላይ ይሳተፉ የነበሩትና አሁን ድጋፍ የሚሰጡት ተቋማት የትኞቹ ናቸው?

ወ/ሮ እታለም፡- በጋና እየሠራ ከሚገኘው ኢምፕሪቴክ ጋና ፋውንዴሽን ነው፡፡ የሥልጠና ሞጁሉ ሞዴል በዩኤን ተቀባይነት ያለውና ከ34 አገሮች በላይ በሥራ ላይ አውለውት ጥሩ ውጤት ያመጣ ነው፡፡ ያንን ተከትለን ነው ከነሱ ጋር በመተባበር ፕሮግራሙን ቀርፀን ሥራ ላይ ያዋልነው፡፡ ዩኤንዲፒ የመጀመርያው ተባባሪ ነው፡፡ የሥራውን ውጤታማነት በማየትና በተለይ በሴቶችና በወጣቶች ላይ ሊሠራ እንደሚችል በማረጋገጥ የካናዳ መንግሥትም ፕሮግራሙን ይደግፋል፡፡ ዩኤንዲፒ ትብብር  ለሦስት   የካናዳ ደግሞ ለሁለት ዓመት ይቆያል፡፡ ለወደፊት ሥራው እየታየ እንዴት እንደሚቀጥሉ ይወሰናል፡፡ መንግሥትም የኢንተርፕሩነርሺፕ ልማት አስፈላጊነቱን ትኩረት ስለሰጠው ከተባባሪዎች ጋር ያለው ፕሮጀክት ሲያልቅ የሚቆም አይደለም፡፡ ማዕከሉ በአዲስ አበባ ዋና መቀመጫውን አድርጎ በሌሎች አራት የክልል ከተሞች ቢሮዎችን ከፍቶ ሥራውን እያካሄደ ነው፡፡ አሁን ከዩኤንዲፒና ከካናዳ መንግሥት በተገኘ ገንዘብ ነው ሥራው የሚከናወነው፡፡ የከተማ ልማት ሚኒስቴርና የፌዴራል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ ተሳትፎም ትልቅ ነው፡፡

ሪፖርተር:- ወደ ማዕከሉ ለሚመጡ ኢንተርፕሩነሮች ተቋሙ በዋነኛነት የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ምን ምን ናቸው?

ወ/ሮ እታለም፡- ሥራ የመፍጠር ዝግጁነት ያላቸውን ሥራ እየሠሩ ያሉ ኢንተርፕሩነሮችንና የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው እየሠሩ ያሉ ተቋማትን ያግዛል፡፡ በብዙ አገሮች ተሞክሮ ትልቅ ለውጥ ያመጣውን ሥልጠና ለስድስት ቀናት እንሰጣለን፡፡   ሠልጣኞቹም ስድስቱን ቀን ልምምድ ያደርጋሉ፡፡ ሥልጠናው ለሥራ መነሳሳትን ያመጣል፡፡ ለምሳሌ ሥራ እየሠሩ ነገር ግን  ስለቢዝነስ ግልጽ የሆነ ሐሳብ የሌላቸውን ሥራቸውን እንዲረዱ ያደርጋል፡፡ ሥልጠናው ራሳቸውን እንዲያሻሽሉ፣ የቢዝነስ ዕቅድ እንዲኖራቸው፣ ፈቃድ እንዴት ማውጣት እንዳለባቸውና ኢመደበኛ ነገሮችን መደበኛ ለማድረግ ያግዛል፡፡ መደበኛ መንገድ በመከተል ኢንተርፕሩነሮች ራሳቸው ተጠቅመው አገራቸውን እንዴት መጥቀም እንደሚችሉ ሥልጠናው ያሳያል፡፡ የትምህርት ደረጃቸው ዝቅተኛ ለሆኑ በተለይ ሴቶች ውስጣቸው ያለው አቅም እንዲወጣ የሚያደርግ የሁለት ቀን ሥልጠናም እንሰጣለን፡፡ ሥልጠናው ሲያልቅ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት የሚቆይ ክትትል በቢዝነስ ዕድገት አማካሪዎች ይሰጣቸዋል፡፡ የቢዝነስ ዕቅድ ያዘጋጃሉ፤ ግልጽ የሆነ ግብ ያስቀምጣሉ፡፡ ይህም አሥሩን የሥራ ፈጣሪነት ብቃቶች እንዲተገብሩ ይረዳቸዋል፡፡ ቦታ ካላቸው እንዴት ማደራጀት እንዳለባቸው፣ ምርት ካላቸው እንዴት ጥራቱን ማሻሻል እንዳለባቸው፣ ገበያ ከሌላቸው ገበያ እንዴት ማፈላለግና የገበያ ትስስር  መፍጠር በሚችሉበት መልኩ አማካሪዎቹ ይረዷቸዋል፡፡ ካፒታል የሚፈልጉ ከሆነም ይጠቁሟቸዋል፡፡

ሪፖርተር:- ለሠልጣኞቹ ከሥልጠና በተጨማሪ መቋቋሚያ ገንዘብ ትሰጣላችሁ?

ወ/ሮ እታለም፡- ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ለማስተሳሰር የቀረጽነው ፕሮጀክት አለ፡፡ በኛ ሥልጠናና ክትትል እንደሚደረግላቸው እንዲሁም ገንዘብ ቢበደሩ ሠርተው እንደሚያተርፉና እንደሚከፍሉ ምስክርነት እየሰጠን ገንዘብ እንዲያገኙ እናደርጋለን እንጂ ገንዘብ አንሰጥም፡፡ ራሳቸው ሥራ ፈጥረው ለሌሎች የሥራ ዕድል የሚያመቻቹ፣ ገበያቸውን ማሳደግ የሚችሉ፣ በአገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይሆን ለውጪ ገበያም የሚያቀርቡ ኢንተርፕሩነሮችን ነው ማዕከሉ የሚደግፈው፡፡

ሪፖርተር:- ተቋሙ ቢዝነስ ለጀመሩም ሐሳቡን ይዘው ለሚመጡም ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ሥልጠናውን መውሰድ ያለባቸውን እንዴት ትለያላችሁ?

ወ/ሮ እታለም፡-  በጋዜጣና በሬዲዮ ፕሮግራሙን እናሳውቃለን፡፡ በመሥፈርቱ መሠረት የቢዝነስ ሐሳብ ያላቸውና መሥራት የሚፈልጉ ነገር ግን እንዴት አድርገው ወደ ሥራው መግባት እንዳለባቸው የማያውቁትን እናስገባለን፡፡ ሌላው ሥራ ጀምረው በሥራው ላይ ችግሮች የገጠሟቸውና የተሻለ ለመሥራት የሚፈልጉትን እንቀበላለን፡፡ ያሠለጠናቸው ሰዎች ከወጡ በኋላ የሚያመጧቸው ሰዎች ይበዛሉ፡፡ ሰዎቹን እንገመግማቸዋለን፣ ቃለ መጠይቅ እናደርግላቸዋለን፡፡ ትክክለኛ ሥልጠና የሚያስፈልጋቸው ሆነው ያገኘናቸውን እንጠራቸዋለን፡፡ ሥልጠናውን የጀመርነው በውጪ አገር አሠልጣኞች ነበር፡፡ ኢንተርፕሩነሮችን እያሠለጠንን ጎን ለጎን አሠልጣኝና የቢዝነስ ዕድገት አማካሪ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችንም እያሠለጠንን ነበር፡፡ ረዥም ጊዜ የሚወስደው ሠልጣኞቹ በቅተው እስከሚወጡ ድረስ ነው፡፡ እስካሁን 165 የአገር ውስጥ አሠልጣኞች ሠልጥነዋል፡፡ እነሱ በመኖራቸው አገልግሎታችን በየክልሉ ሊስፋፋ ችሏል፡፡ በሳምንት  ከአምስት እስከ ዘጠኝ ተከታታይ ክፍሎች ለማካሄድም አስችሎናል፡፡ ክትትል የሚያደርጉ 207 የቢዝነስ አማካሪዎች አሠልጥነናል፡፡ እያንዳንዳቸው ከ10 እስከ 15 ደንበኛ እየያዙ የምክር አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

ሪፖርተር:- ከአዲስ አበባ ውጪ የትኞቹ ክልሎች ላይ ቅርንጫፍ አላችሁ? ከተጠቀሱት በተለየ መንገድ የምትሰጡት አገልግሎት አለ?

ወ/ሮ እታለም፡- በትግራይ መቐለ፣ በአማራ ባህር ዳር፣ በደቡብ አዋሳ፣ ኦሮሚያ ደግሞ ቢሾፍቱ ውስጥ ቅርንጫፍ ተከፍቷል፡፡ ሥልጠናና ክትትል እየሰጠን ነው፡፡ ሌላው  እየሠራን ያለነው ነገር በየዓመቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ ብዙ ተመራቂዎች አሉ፡፡ እነዚህ ተመራቂዎች ወጥተው የትምህርት ማስረጃቸውን ይዘው እየዞሩ ሥራ ከመፈለግ የራሳቸውን ሥራ መፍጠር የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው፡፡ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ከመውጣታቸው በፊት መጨረሻ ዓመት ላይ ከ2 እስከ 3 ቀን ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የልቀት ተቋም እየከፈትን ነው፡፡ በተለይ ለአራቱ አስፈላጊው መሣሪያዎች ገብተውላቸው ሥራ እየጀመሩ ነው፡፡ ይኼ ተማሪው ከትምህርት ቤት ተመርቆ ሲወጣ የራሱ የሆነ ትርፋማ ፕሮጀክት ይዞ ወጥቶ የራሱን ሥራ ጀምሮ ሌሎችንም ቀጥሮ በአገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግር ይቀርፋል ብለን እናስባለን፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና ቢዝነስ ሴንተሩ ጋር ሁለት ተቋም ይኖረናል፡፡ ሌሎቹ መቐለ፣ አዳማ፣ አዋሳና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ናቸው፡፡ ከዛ ውጪ ደሴ፣ ድሬዳዋ፣ ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ሄደን ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ በሁሉም ሙያ የተሰማሩ ሰዎች የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው ለሌሎችም ሥራ መፍጠር እንደሚችሉ እናውቃለን፡፡ በመሆኑም ወደፊት የኢንተርፕሩነርሺፕ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ያንን ኮርስ ለሁሉም ትምህርት ክፍል እንዲሰጡ የማድረግ ዕቅድ አለ፡፡ ተማሪዎች አስተሳሰባቸው ይቀየራል፣ የራስን ሥራ የመፍጠር ዝንባሌ ይኖራል ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን ምን ያህል አሠልጥናችኋል?

ወ/ሮ እታለም፡- መጀመሪያ ላይ ስለ ፕሮግራሙ የሚያውቁ ሰዎች ውስን ስለነበሩ እኛም አሠልጣኞች በብዛት ስላልነበሩን በጣም በጥቂቱ ነበር የምናሠለጥነው፡፡ አሁን ግን በቂ አሠልጣኞች አሉን፤ ወደ 165 ገደማ ናቸው፡፡ ሌላው ሞጁሉ በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በትግርኛ ተተርጉሟል፡፡ ይህም የሥልጠና አሰጣጡን አመቺ አድርጎታል፡፡ በዚህ ምክንያት ከ10,000 በላይ ኢንተርፕሩነሮች ሥልጠናውን አግኝተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከድርጅታችሁ ሠልጥነው የወጡ ታዋቂ ኢንተርፕሩነሮች አሉ፡፡ ምን ያህል አስተዋጽኦ አድርገንላቸዋል ብላችሁ ታምናላችሁ?

ወ/ሮ እታለም፡-  ከሥልጠናው የወጡ ሰዎች የተሳካላቸው እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡  ክትትል በምናደርግበት ጊዜ እንዳየነው በአዲስ ሥራ የተሰማሩ ሰዎች አሉ፤ የሚሠሩትን ሥራ ያስፋፉም አሉ፡፡ አዳዲስ ሥራዎች በመጀመራቸውና የነበሩት ሥራዎችም በመስፋፋታቸው በርካቶች ሥራ አግኝተዋል፡፡ ከመንግሥት መሥሪያ ቤት ወጥተው የራሳቸውን ሥራ ጀምረው ገቢያቸውን ያሻሻሉና በሕይወታቸው ላይ ለውጥ ያመጡ አሉ፡፡ አንድ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የወጣ ልጅ ነበረ፡፡ ምን መሥራት እንዳለበትና እንዴት መሥራት እንደሚገባው አቅጣጫ ሳይኖረው ወጥቶ ከጓደኛው ጋር ሥራ እየሞከረ ነበር፡፡ ስለ ሥልጠናው ሰምተው ከመጡ በኋላ ‹‹ቤተ ሻማ›› ብለው በጣም ብዙ ዓይነት ሻማ መሥራት ጀምረዋል፡፡ ገቢያቸው ጨምሯል፤ ብዙ ሠራተኞችም አሏቸው፡፡ እኛ የሰጠናቸው ሥልጠናና ክትትል በሥራቸውና በሕይታቸው ለውጥ አምጥቷል፡፡ ባለቤቷ አራት ልጆች ጥሎባት እንደሄደና  ኪሷ ውስጥ 21 ብር ብቻ እንደቀረ የነገረችን እናት ከማዕከሉ ሥልጠና ካገኘች በኋላ ዳቦና ደረቅ ኩሲሶችን በማዘጋጀት እስከ 1.2 ሚሊዮን ብር ካፒታሏ ማደጉን ነግራናለች፡፡ እኛ አገር ንግድ የሚመራው በልምድ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ቢዝነስ ድባቡ ተቀይሯል፡፡ ከአገር ውስጥና ከውጪም ተወዳደሪነት እንዲኖር እያንዳንዱ የንግድ አነስተኛ፣ መካከለኛ ወይም ትልቅ ዕቅድ ሊኖረው ይገባል፡፡ ስለዚህ የንግድ ዕቅድ እንዲኖራቸው እናደርጋለን፡፡ ሠልጣኞች የታቀደ የሥራ ጅምር ይኖራቸዋል ማለት ነው፡፡ ገቢያቸውንና ወጪያቸው የሚቆጣጠሩበት መንገድ፣ ቦታቸውን በሚገባ እንዲጠቀሙበት፣ አገር ውስጥና ውጪ እንዴት መድረስ እንዳለባቸውና እንዴት የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚችሉ ከሥልጠናው ያገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ቢዝነስ ከተጀመረ በኋላ ለሚገጥሙ ችግሮች ተቋሙ ምን ያደርጋል?

ወ/ሮ እታለም፡- አንዳንድ ሰዎች ቢዝነስ የጀመሩት ሳያጠኑና አቅማቸውን ሳያማክሉ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምርታቸው ገበያ መኖሩን ሳያጠኑ የሚገቡም አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት  ችግሮች ሲገጥሙ በመጀመሪያ የቢዝነስ አማካሪው ቢዝነሱን ጤናማነት ያረጋግጣል፤ ችግሮቹን ይለያል፡፡ ችግሮቹ ሲለዩ ለምን እንዳልተሳካላቸው ለማወቅ ይቻላል፡፡ ስለዚህ እንዲሳካላቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው አማካሪው መፍትሔ ይዞ ይሄዳል፡፡ በጉዳዩ ሙያተኛ ከሆኑ ሰዎች ጋርም ያገናኛቸውና ወደ ስኬት እንዲሄዱ ይረዳቸዋል፡፡

ሪፖርተር:- የሥራ አጥ ቁጥር በርካታ ነው፡፡ በእርሶ አመለካከት እስካሁን ማዕከሉ ሥራ አጥነትን በመቅረፍ በኩል ያለው ሚና ምን ይመስላል?

ወ/ሮ እታለም፡- ሠልጥነው የወጡትን ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡ የተወሰኑት የራሳቸውን ሥራ ጀምረዋል፡፡ አንድ ሰው አንድ ሥራ ሲጀምር ብቻውን አይሠራም፡፡ ቢያንስ ሌላ ሰው ይቀጥራል፡፡ በኛ ፕሮጀክት የሚታሰበው አንድ ኢንተርፕሩነር ቢያንስ እስከ ሦስት ሰው ሊቀጥር እንደሚችል ነው፡፡ ሥራ የፈጠሩ ሰዎች ሥራ አጦችን መቅጠር ጀምረዋል፡፡ ቢዝነሳቸውን የሚያስፋፉም ልዩ ልዩ ምርቶችን ለማምረት ሰው ይቀጥራሉ፡፡ ሥራ አጥ በብዛት ነው ያለውና በአንድ ሌሊት ሊፈታ የሚችል አይደለም፡፡ ጅምሩ ግን ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ አሁን ከምናየው ወደፊት እየተሻሻለ የሚሄድ ነው፡፡ በተለይም ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡ ወጣቶች ሥራ ፈላጊ እንዳይሆኑ ድጋፍ ቢያገኙ ቢያንስ በየዓመቱ ከሚወጡት የተወሰኑት የራሳቸውን ሥራ እየፈጠሩ ሌሎችን መቅጠር ይችላሉ፡፡ በዚህ መልኩ የሥራ አጥ ቁጥርን መቀነስ እንችላለን፡፡ ፕሮግራሙ የተቀረፀበት አንዱ ዓላማ በአገሪቱ ላይ ያለውን ድህነት መቀነስ ነው፡፡ ሰዎች ቁጭ ብለው ለመቀጠር የሚጠብቁ ከሆነ ሁሌም ሥራ አጥነት አለ፡፡ የማንም አገር ኢኮኖሚ ሁሉንም ሥራ አጥ ሥራ ለማስያዝ አቅም ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ እያንዳንዱ ሰው በየአቅሙ የራሱን ሥራ መሥራት ቢችል ለውጥ ይኖራል፡፡ ሥራ ፈጣሪ መሆን ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋር በመተሳሰርና ሥራ የሚፈጥሩ ሰዎች ስንት ሰው ማቀፍ እንደሚችሉ በማሳየት ነው ሥራ አጥነትን ለመቀነስ የሚሞከረው፡፡ ማዕከሉም በዚህ ረገድ አስተዋጽኦ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡

 

 

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን

ቢሻን ጋሪ ፒውሪፊኬሽን ኢንዱስትሪ ወደ ውኃ የማከም ቴክኖሎጂ ሥራ የገባው በየጊዜው በኢትዮጵያ የተከሰቱ ውኃ ወለድ በሽታዎች መደጋገምን ዓይቶና ጥናት አድርጎ ነው፡፡ በ2000 ዓ.ም. ቢሻን...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...

ሕይወትን ለመቀየር ያለሙ የቁጠባና ብድር ማኅበራት

ወ/ሮ ቅድስት ሽመልስ በግሎባል ስተዲስ ኤንድ ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በፕሮጀክት ማኔጅመንት እንዲሁም በኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ ሠርተዋል፡፡ በኮርፖሬት ፋይናንስ ካናዳ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ...