Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መውረድ ለምን አቀበት ሆነ?

እነሆ ከየረር ወደ መብራት ኃይል ልንጓዝ ነው። ተጓዥ ይታክተው እንጂ መንገድ ሁሌም አለ። ፍጡር ይደክማል እንጂ መዓልትና ሌቱ መፈራረቃቸው አይስተጓጎልም። ይመሻል ይነጋል። አበባ ያብባል። የዘሩትን ሊያጭዱ፣ ዘር የሚዘሩ የሰው ልጆች ማለዳ ተነስተው ጀንበር እስክትሸኝ እዚያና እዚህ ይረግጣሉ። ያጨዱት የቀለለባቸው፣ ያሰቡት ሰሎ የቀረባቸው እንደ ነጋበት ጅብ ማንከሳቸው በቀን ብርሃን እየታየባቸው፣ በጥቆማ ዝለው ይጓዛሉ። ያልጠበቁት የሆነላቸው ያላቀዱት የሰመረላቸው ደግሞ ከድካም ወዛቸው ይልቅ የዕምነት ተስፋ እያፍለቀለቃቸው ሲታዩ፣ ፈጣሪ እንደ ምድራዊ ዳኛ ፍትሕ የሚያባዛ አስመስለው ያስተረጉማሉ። ነገን ለመኖር ከመጓጓት ይልቅ ዛሬ ላይ ማክተም የሚቀላቸው፣ በትርጉም ብዛት የተስፋ ቆራጮችን ‘ካምፕ’ ሊያደልቡ ይሯሯጣሉ። ቀዳዳን ከመድፈን ይልቅ ቀዳዳውን ማስፋት በእልፍ ዕላፍ ትውልዶች ዕድሜ የታየ ደካማ ባህሪያችን ነው። ዝግመት ያልዳሰሳቸው እልፍ ጥያቄዎች ዛሬም ጎዳናው ላይ እንደተበተኑ ናቸው። የማንም አልፎ ሂያጅ ውዝግብ፣ ንጭንጭና አተካራ ይኼው ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ መንገዱ ሁሉን እንደ ፀባዩና እንደ አስተዳደጉ እያገናኘ ያለያያል፤ ያለያያውን ያነፋፍቃል። ቆም ብለው ካሰቡት ከሰው ልጆች ይልቅ ጎዳናው ብዙ ታሪክ ያውቃል። መሬት በሆዷ ከደበቀችው የተፈጥሮ ሀብት ይልቅ የእኛ ስንኩል ዕድሜና እንባ እንደማይበልጥ በምን እናውቃለን? ጊዜ ለማን አድልቶ ማንን እንደገደለ፣ ማንን አጉርሶ ማንን እንዳስራበ፣ ለማን አስጨብጭቦ ማንን እንዳስወገረ፣ ከተነገረውና ከተዘከረው በላይ ጎዳናው በሆዱ የቋጠረው መዓት ቢያስንቅ ማን ይነግረናል? ሕይወት ሞተሯ አላረጅ ብሎ ትውልድ ሲተካካ ይዞ የማጣት፣ ሆኖ ያለመሆን ፍዳ ከራስ እስከ ሰው፣ ከሰው እስከ ፈጣሪ ያጣላል። ዛሬም እንደ ትናንቱ እንራመዳለን። ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር ናፍቀን በአዲስ ቀን ያንኑ ዙር እንደግመዋለን። መጥኔ! ታክሲያችን ሞልታለች። ጋቢና ነጠላ ያዘቀዘቁ እናቶች አሉ። ወዲህ ደግሞ በዕድሜ ጠና ያሉ ጎልማሶች፣ ወጣቶች፣ ባለጉዳዮች፣ እንጀራ ፈላጊዎችና አፋላጊዎች ተሰይመናል። “ሾፌሩ የት ሄዶ ነው?” አብዛኞቻችን ከሰመጥንበት ትካዜ የአንዲት ተሳፋሪ ድምፅ አነቃን። “ሾፌሮቻችን በይ! ያለሽው ኢትዮጵያ እንጂ ሰሜን ኮሪያ ወይም ኤርትራ አይደለም፤” ብሎ ወያላው ያልተጠየቀውን ይቀባጥራል። አንዱ ተሳፋሪ፣ “ጥሩ የዲሞክራሲ ጠባቃ ይወጣዋል፤” ብሎ አምቶት ሳይጨርስ፣ “ደግሞ እኔ የሾፌር ጠባቂ ነኝ?” ይላታል። ዘንድሮ ከነገር በላይ ነገረኛው ሊጨርሰን ነው መሰል! የወያላው መልስ ያበሸቃቸውና ያስገረማቸው ተሳፋሪዎች ሾፌሩን ቶሎ እንዲጠራው ይረባረቡበት ገቡ። ከጩከቱ ባሻገር፣ “ቃላታዊ ምላሽ ይሉሻል ይኼ ነው!” ይላታል አቧራውን ካስነሳችው ወጣት አጠገብ የተቀመጠ ተሳፋሪ። “አይገርማችሁም? ‘እንዲያ ስንባባል አለብኝ ጭልምልም’ ያለችው እኮ ዘፋኟ ወዳ አይደለም። ለጋራ ዕድገት፣ ለጋራ ጉዞ፣ ለጋራ ሕይወት የተናጠል ዕርምጃና አስተሳሰብ በቃ አይተወንም ማለት ነው? ከቃየልና ከአቤል ጊዜ አንስቶ ሲበጠብጠን የኖረ ነገር እኮ ይኼ ነው፤” በማለት ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጠች የኮሌጅ ተማሪ መሳይ ምልልሱን ተቃላቀለች። ጓደኛዋ ፈገግ ብሎ፣ “እኔ እኮ አርፈሽ ሰባኪ መሆን ስትችይ ለምን ምህንድስና እያጠናሽ ጊዜሽን እንደምታጠፊ አይገባኝም?” ብሎ አፌዘባት። “ምናለ አንተስ ቁም ነገር ስናገር እንደ ገዢው ፓርቲ ማፌዝህን ትተህ መልካም መሬት፣ በጎ ምዕመን ብትሆን? የአገሪቷ አልበቃ ብሎ የገዛ ዕድሜህን በፉገራ ጨረስከው እኮ!” ትለዋለች። ጨዋታቸው የተመቸው አንድ ተሳፋሪ ዘወር ብሎ እያያቸው ይሳሳቃል። “ተው እናንተ ሰዎች በትንሽ ትልቁ አገርን ያህል ነገር እያነሳችሁ ልብ አታስበርግጉ። ከተጫወትን በራሳችን ዛቢያ እየተሽከረከርን መጫወት ነው እንጂ፣ አሁን በአንድ ፓርቲ ዙሪያ የምትሽከረከርን ምስኪን አገር ዛቢያ ማደናገር ግፍ አይሆንም?” ይላል አንደኛው ጎልማሳ። ትግትጉ ሲጋጋል ሾፌራችን ከሄደበት መጥቶ ታክሲያችን ማንቀሳቀስ ጀምሯል። ብንዘገይም ልክ እንደ ልማቱ ጉዟችንን ጀምረናል። ጋቢና የተቀመጡት እናቶች ይዝታሉ። “እንዲያው ይኼ ባቡር መጥቶ ተገላግለናችሁ!” ይላሉ። “እኛን ነው?” ሾፌሩ እየተቅለሰለሰ ያጨውታቸዋል። “ታዲያ ማንን ነው? ታክሲ ጥበቃ በየሄድንበት የምንገተረው አንሶ ደግሞ ተሳፍረንም ሾፌር ጥበቃ? ለመሆኑ የት ሄደህ ነው?” እየተቀባበሉ ጠየቁት። “ምን የታክሲ ሾፌሮች ስብሰባ ተጠርተን እኮ . . . ” ሳይጨርሰው ያቋርጡታል። “ይኼ የስብሰባ አባዜ ወደ እናንተ ተጋባ ደግሞ? ለመሆኑ የተቀላጠፈ የትራንስፖርት አገልግሎት የምትሰጡት በስብሰባ ነው እያሉዋችሁ ነው?” በአናት በአናቱ እያከታተሉ ይጠይቁታል። “ኧረ ስብሰባችን መጪውን አገር አቀፍ ምርጫ የተመለከተ ነው፡፡ ስለትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ችግር አልነበረም፤” ይላል። “የባሰ አታምጣ አሉ! አሁን እኛን ስታዩን የአማራጭ ችግር እንጂ የመምረጥ ወይም ያለመምረጥ ቸግር አለብን?” አሉት አንደኛዋ ተናደው። “እኔ ምን አውቃለሁ ብለው ነው? እኔስ ነገን ፈርቼ እንጂ አርፌ ሥራዬን ብሠራ አልመርጠም ብለው ነው?” ብሎ ጠጋ ጠጋውን ይያያዘዋል። እንደ ልጅ መቅለስለሱን ታዝበው ሲያበቁ ደግሞ ሊመክሩት ይጀምራሉ። “ለራስህ ብታውቅበት ይሻልሃል ልጄ! ፖለቲካ ማቡካት አይደለም ለአገር የሚበጀው። መሥራት፣ ጠንክሮ መሥራት ነው። አገር በወሬ አትቆምም፣ በተግባር ነው። ሥጋህ ባይኖር ነፍስና መንፈስህ ብቻቸውን ምን አቅም አላቸው? ንገረኝ እስኪ?” ሲሉት አንደኛዋ ሌላኛዋ ተቀብለው፣ “እውነት ነው! ምክር ስማ የዛሬ ልጆች ምክር አትወዱም። ገንዘብ ብቻ ነው የምትወዱት። አየህ እኛ ብዙ አይተናል። ትናንት ተወልደው ስሙን ከፈረንጅ ተውሰው ‘ዲሞክራሲ’፣ መደማመጥ፣ ምርጫ ይሉናል። ድሮም በአገራችን አንድ ሰው ሲያወራ አቋርጦ መዘላበድ አናውቅም። ነውር ነው። የእርጎ ዝንብ ሲባል ታውቃለህ አይደለም? አዎ! ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን የሚጋፉትን ያወገዝንበት አባባል ነው። ምርጫም ቢሆን ሽማግሌ አንቱ የተባለ አዋቂ ሰው ነው እንዲያስተባብረንና እንዲያስታርቀን ስንመርጥ የኖርነው። ሥርዓት ብቻውን ግን ምን ይረባል? ለሰው ዲሞክራሲ ከማለት በፊት የሚያሻው ፍቅር ነው። እኛ ሀብት ሳናውቅ ዕድሜ ያገኘነው በእሱ ነው። አንተ ትሻል እኔ ሲባል እንጂ በረከት ያለው፣ መብት የማስከብር ትንቅንቅ ሲገጥሙ ብቻ አይደለም፤” ሲሉት በዕውቀትና በጥበብ መሀል ያለን ልዩነት ለማይገነዘብ እነዚህን እናቶች ‘ፀረ ዲሞክራሲ’ ብሎ ሊጠቁማቸው አስቦ ‘ኔትወርክ’ እንቢ እንዳለው ማን ያውቃል? ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላው፣ “ሒሳብ ወጣ ወጣ በነፃ የሚወስደው ሞት ብቻ ነው!” እያለ ይቀልዳል። መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ ተሳፋሪዎች፣ “አፍሪካ አንድ ስትሆን ሳናይማ አንሞትም፤” ይባባላሉ። “ኤድያ የእኛ ሰው ጉራ ብቻ! እኛ አንድ ሆነን መሬታችንን የግል ማድረግ አቅቶናል፣ እናንተ ስለአፍሪካ አንድ መሆን ታወራላችሁ፤” አለ ከመሀላቸው አንዱ። “ፍሬንድ ጨዋታ አታቆርፍድ! ምንድነው እንደ ተቃዋሚ ፓርቲዎቻችን ለመልስ ምት መቸኮል? በገዛ ምኞታችን?” አለችው አጠገቡ የተቀመጠች ቀዘባ። ወያላው ሒሳቡን እየተቀበለ “ኳስ በመሬት!” ይላል። “እሱን ሂድና ለሞሪንሆ ንገራቸው! አምስት ሲገባባቸው የት ነበርክ? በአገር ጉዳይ አስተያየት ከምትሰጥ ኳስን በተመለከተ ሐሳብ ብትሰነዝር ይሰሙሃል፤” አለው የመሬት ነገር ያንገበገበው። ይኼን ጊዜ አንድ ሁለቱን ከልቡ ያላዳመጠ አጠገቤ የተቀመጠ ተሳፋሪ ጠጋ ብሎ “ሞሪንሆ የኢትዮጵያ ፓስፖርት አወጡ እንዴ?” ብሎ አፈጠጠብኝ። ምን ትሉታላችሁ? በዚህ መሀል የኮሌጅ ተማሪዎቹ ወራጅ ይላሉ። ታክሲያችን ትቆማለች። ከመውረዳቸው አንድ ትንሽ ልጅ ከአቅሙ በላይ ማዳበሪያ እንደተሸከመ ተሳፈረ። “ምንድነው እሱ?” አለው ወያላው ማዳበሪያውን እየጠቆመ። “ጤፍ!” አለው ልጁ የሞት ሞቱን ቁና ቁና እየተነፈሰ። “20 ብር ትከፍላለህ!” አለው ኮስተር ብሎ። መጨረሻ ወንበር ብዙም ሳትናገር የቆየች ወይዘሮ “እንዴ! ሕፃን ነው ብለህ ነው?” ብላ ጮኸች። “ሕፃንማ ቢሆን ጤፍን ያህል ነገር አሸክመው ብቻውን አይልኩትም ነበር። አሁን እስኪ በዚህ ጊዜ ኑሮ የሚደቁሰንን ያህል ጨዋነት ይዞን እንጂ አንዱ ነጥቆት ቢሮጥ ይኼ ልጅ ማን አለው?” ብትል ቀዘባዋ ተሳፋሪዎች ደንግጠው እርስ በርስ ተያዩ። ጤፍ እንደ ሞባይል ተመንትፎ ሊሮጥ? ኧረ የሌባ ጆሮ አይስማ! ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጃክሮስ አደባባይን ይዞ እስከ ታክሲ ማራገፊያው የትራፊክ መጨናነቁ እንዲህ ነው አይባልም። ከሾፌሩ ጀርባ ከተቀመጡት ጎልማሶች አንደኛው፣ “መንገዱ ነፃ ቢሆን አዲስ አበባ እኮ አሁንም ጠባብ ከተማ ናት!” ብሎ ወሬ ጀመረ። የወዲያኛው ተቀብሎ፣ “አንተን የሚገርምህ የከተማው ሰፍቶ አለመስፋት ብቻ ነው? የአስተሳሰባችንና የአመለካከታችንስ? ስንት ያልተነካ ስንት ያልተሠራ ሥራ እያለ ልክ እንደ መኪና መንገዱ ጥቂት የሥራ ዘርፎች ላይ መጣበባችንስ?” ይለዋል። “የሚያሠራ ሲኖር ነዋ! ሙስና መንገዱን ሁሉ ዘግቶ መልካም አስተዳድር እጦት በሥራ ተነሳሽነት ስሜታችን ላይ እየተጫወተበት፣ እጠቆር ይሆን እያልን፣ እባልን ፈርተን፣ መታማትን ተሳቀን ይኼን ያህልም መታተራችን ሊደናቅ ይገባዋል። ተሳሳትኩ? ምንድነው ‘ፌስቡክ’ ላይ ብቻ ነው ‘ላይክ’ ማድረግ የምትወዱት?” ብሎ ሁሉም እየሰሙት የሚጮኸው አጠገቤ የተቀመጠው ተሳፋሪ ነው። “ታዲያስ ጉዟችን ረጅም! የምንጠበቀው ሩቅ! ይኼው ግን እንደምትሉት በረባ ባረባው ተፋፍገንና በቢሮክራሲ ጣጣ ተተብትበን በኤሊ ፍጥነት እየተሳብን ‘ከመቆም ይሻላል’ እንላለን” ብላ ቆንጂት አስተያየቷን ሰጠች። ወያላው ወርዶ መንገዱ የተዘጋጋበትን ምክንያት አጣርቶ መጣና “ግጭት ነው። የሚቸኩል ካለ ወርዶ ማዝገም ይችላል፤” ብሎን አረፈው። አብዛኞቻችን ወረድን። እኛስ ወረድን ሌላው ግን ምነው መውረድ አቀበት ሆነበት? ምንም! መልካም በዓል! መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት