Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርመዘመን ከሥርዓት ጋር ይሁን

መዘመን ከሥርዓት ጋር ይሁን

ቀን:

በይበይን ተግባሩ

ባሕል፣ ልማድ፣ የአነጋገር ዘይቤዎችና መሰል የሰዎች ባህርያት እንዲሁም ቋንቋና የመሳሰሉት የኅብረተሰብ እሴቶች ሁኔታዎች መለዋወጥ፣ በተለይም ከሕዝቦች መቀላቀልና መተሳሰር ጋር እየተገናዘቡና እየተዳቀሉም መሻሻል፣ መዳበር አንዳንዴም እየተዋጡ መመንመንም የተለመደ ነው፡፡ ይልቁንም ባለንበት ከፍተኛ የመረጃ ልውውጥ (ኮሙዩኒኬሽን) እና ሉዓላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ዘመን፣ በአንድ አገር ሕዝቦችና ማኅበረሰቦች ብቻ ሳይሆን በአገሮችም መካከል ያለው መስተጋብር በፍጥነትም ሆነ በጥልቀት እየጨመረ መሄዱ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በዚህ ሒደት ተወራራሽ ሁኔታዎች መከሰታቸው የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይልቁንም የአንዱ ማኅበራዊ እሴት፣ ኢኮኖሚያዊ አቅም ወይም ፖለቲካዊ ተሰሚነት የሚያመዝን ከሆነና እሴቱም ይበልጥ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ለአኗኗርና ለአሠራር የቀና ሆኖ ከተገኘ ሌላው በተለያየ መንገድ እየቀዳ፣ እያዳቀለ ወይም እንዳለ ወስዶ የራሱን በመተካት የሚያንፀባርቅበት ወይም የሚኖርበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ የዚህ ዓይነት ሒደቶች ይበልጡን በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በአጠቃላይም በዘመናዊ አኗኗር ረገድ የጎሉ ናቸው፡፡ በእነዚህ መስኮች በዕውን የላቁና የመጠቁ ከሚባሉ ኅብረተሰቦች ብዙ መማር ወይም በተለያዩ የግንኙነት ዘዴዎች እየወሰዱ ከራስ ፍላጎትና እውነታ እያገናዘቡ መጠቀም ደግሞ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ በስተቀር አንድ ኅብረተሰብ የራሱ የሆኑ መገለጫዎች እያሉትና እነዚህም ከሌላው ተወዳዳሪ ብቻ ሳይሆኑ በተሻለና በቀላሉ ሊያግባቡ የሚችሉ ሆነው ሳለ የባዕድን ቋንቋ፣ ባህል ወይም ወግ ሳያመዛዝኑ መቃረም የማይገባ ብቻ ሳይሆን የሚያስገምትም ይሆናል፡፡ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት አገራችን ባሏት አያሌ ብሔረሰቦችና ማኅበረሰቦች ውስጥ ለዘመናት የዳበሩ አባባሎችና አጠራሮች ሞልተውን አንዳንድ ጥራዝ ነጠቆች የራሳቸውን አባትና እናት ጨምሮ አዛውንቶችን ‹‹ፋዘር ማዘር›› ማለት የሚመርጡት በምን ሳቢያ እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ዕውን አማርኛውስ ቢቀር በየራሱ ብሔረሰብ ለእነዚህ የሚሆኑ ቃላት ጠፍተው ነው? አንዳንዴ ደግሞ ከራሳችን ቋንቋዎች ትክክለኛውን ቃል ባለመምረጥ አገባቡን ስናዛባው ይስተዋላል፡፡ ምግቡን ወደዱት ወይም ተስማማዎት ለማለት፣ ተመቸዎት ወይ የሚሉ አስተናጋጆች አሉ፡፡ ይህ እንግዲህ አማረ ተብሎ የጣዕምና መሰል የስሜት እርካታን ከአካላዊ ምቾት ጋር በማምታታት የሚፈጸም ግድፈት ነው፡፡ ምናልባት ምግቡ ጣፈጠዎት ወይም ጣመዎት ወይ ቢባልና መቀመጫው ወይም አልጋው ተመቸዎት ወይ ቢባል የተሻለ አገላለጽ ይሆን ነበር፡፡ ሌላው ጉልህ ስህተት የአማርኛ ቃላትን ግዕዛዊ በማስመሰል በዚህም ጊዜ በአስጸያፊ ማባዛት ቃላትን መደረት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ መምህር ብሎ መምህራን ማለት ሲገባ መምህራኖች ይባላል፡፡ ቃልን በቃላት በማባዛት ፈንታ ቃላቶች የሚሉም አሉ፡፡ ነጠላና ብዙ ባለቤቶችን ከተገቢው ግስ ጋር የማዛመድም ችግር ይታያል፡፡ ለአብነት አንድ የኤፍኤም ራዲዮ ጣቢያ ‹‹ቃላት ያንሰኛል›› የሚል የጠዋት ፕሮግራም አለው፡፡ እንግዲህ ችግሩ የሚጀምረው ከስሙ ከራሱ ነው፡፡ ይህንን አባባል ብዙ ጊዜ እየደጋገመ የሚያስተዋውቀው አቅራቢ ርዕሱ የአግባብ ጉድለት እንዳለበት ጨርሶ የተገነዘበው አይመስልም፡፡ እኔ እንኳ በስልክ ወዲያውኑ እንዲያርመው ለማገዝ ሞክሬ ነበር፡፡ ግን በመስመር መጣበብ የተነሳ አልተሳካልኝም፡፡ የየትኛውም ቋንቋ የዓረፍተ ነገር መሠረት የባለቤትና ግስ መስማማት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ነጠላና ብዙን መለየት ዋነኛ ሰዋሰዋዊ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ሐረግ ለማስተካከል ወይ በነጠላው ቃል ያንሰኛል፤ አልያም በብዙ ቃላት ያንሱኛል መባል ይገባዋል፡፡ የሚዲያን ነገር ካነሳን ሌላው ትዝብት ‹‹ዜና እወጃ›› የሚሉት ፈሊጥ ነው፡፡ አዋጅና ዜና የተለያዩ ጉዳዮች መሆናቸው እንዴት እንደሚሳታቸው አይገባኝም፡፡ ምናልባት የመንግሥት ራዲዮና ቴሌቪዥን የሚያቀርቡትን ዜና ሁሉ እንደ አዋጅ ካልቆጠሩት በስተቀር? በዚህ ርዕስ ሥር መነሳቱ ተገቢ የሚመስለኝ አንድ መጥፎ ሒደት የአንቱታ መናድ ነው፡፡ በአገራችን ከሥልጣንና ከኃላፊነት ወይም ከማዕረግ ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ ማኅበረሰቦች ባህልና ወግ ላይ የተመሠረቱ የአክብሮት ሥርዓቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚሰጠው አክብሮት ነው፡፡ ይህም አክብሮት አንቱታን የሚገልጽ ነው፡፡ በዕድሜ ከፍ ያለን ሰው በቅርበት ወይም በዝምድና የተነሳ ያለ አንቱታ መጥራት የሚስተዋል ቢሆንም፣ ታላላቆችን በ‹‹አንቱታ›› ማክበር የቆየና አስመስጋኝ የጋራ ባህላችን ነው ለማለት ይቻላል፡፡ አሁን አሁን ግን (በተለይ በአዲስ አበባ) ነጭ ሽበታቸው በጉልህ የሚታይ አዛውንትን ሳይቀር ‹‹አንቺ››፣ ‹‹አንተ›› እያሉ መጥራት (መዘርጠጥ ቢባል ይሻላል) እየበዛ መጥቷል፡፡ እናም አዛውንት ተስተናጋጆችንና ደንበኞችን ‹‹አንቺ፣ አንተ›› የማለት ነገር እንደ ሬስቶራንት በመሳሰሉ የአገልግሎት መስጫ ቦታዎችም ጭምር የተለመደ ወግ እየሆነ ይታያል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ዘመናዊ ነን ባይ የዕድሜ ባለፀጎች አንቱታን ጊዜው እንዳለፈበት ሥርዓት በመቁጠር ላይወዱት ይችላሉ፡፡ ደግሞም የሰው ባህርይ የተለያየ እንደመሆኑ፣ ዕድሜያቸውን ብቻ ሳይሆን ማንነታቸውንም የማይቀበሉ ጥቂት ግለኞች አይጠፉም፡፡ ግን በአጠቃላይ በዕድሜም ሆነ በሥራ ኃላፊነት አክብሮት መስጠት ወይም መቀበል የሚነቀፍበት ምክንያት ሊገባኝ አልቻለም፡፡ በመገናኛ ብዙኃንና (ሚዲያ) መሰል መድረኮችም በዕድሜያቸው የገፉ፣ እንዲሁም በትምህርትና በዕውቀታቸው የላቁ ባለሙያዎችና አንጋፋ የሥራ ኃላፊዎች ጭምር ሲያነጋግሩ ‹‹አንተና አንቺ›› እየተባሉ ለሕዝብ የሚቀርቡበት አዝማሚያ እየጎላ መጥቷል፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ አቅራቢዎቹ በዕድሜም ሆነ በሌላ መመዘኛ ከእንግዶቹ ያነሱ መሆናቸው ነው፡፡ በተለይም በተዋናይነት፣ ሙዚቀኝነት፣ ስፖርተኝነትና አልፎ አልፎም በመምህርነት ያገለገሉ አዛውንቶች ሳይቀሩ ‹‹አንቱ›› እንዳይባሉ የተወሰነ ይመስል፣ በብዙ ብሔረሰቦቻችን ቋንቋና ባህል የተለመዱና የተመሰገኑ የአክብሮት መገለጫዎች የሚነፈጓቸው ለምን እንደሆነ ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡ የተወሰኑ ፕሮግራም አቅራቢዎች ጋሼ፣ እትዬ፣ በሚሉት ሲጠቀሙ የቅርበት ስሜታቸውንም ለመግለጽ ያህል ከመሆኑ ጋር፣ ባህልንም ተከትሎ አክብሮትና ፍቅርንም የሚያሳይ ነውና በጎ ይመስለኛል፡፡ ያም ቢሆን እንደ እንግዶቹ ዕድሜና ደረጃ በአንቱታ ቢደገፍ የተሟላ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንዲህ ቢደረግ ደግሞ የሚዲያ ሰዎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች፣ በተለይም ለወጣቶች ጥሩ ምሳሌ በመሆን ለበጎ ወጎቻችንም መጠበቅ ያግዛሉ፡፡ እናም ትህትናና አክብሮት የለመደውን ኅብረተሰባችንን ባናደናብረውና ከሞላ ጎደል በሁሉም ብሔረሰቦችና ማኅበረሰቦች ዘንድ በጎ ተብለው የቆዩትን እሴቶቻችንን እየጠበቅን ብንኮራባቸው፣ እንዳስፈላጊነቱ እየዳበርንም ብንጠቀምባቸው ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ከእነዚህም አንዱ ‹‹አንቱታ›› ነውና ያለጥፋቱ እንዳይጠፋ እንጠብቀው እላለሁ፡፡ ሲጃራ ሲሆን ጎጂ ነውና ባይለመድ፣ ቢያንስ ግን የማያጨሱ ሰዎች በተለይም ሕፃናትና ሕሙማን ጭምር በሚገኙባቸው በሕዝብ መገልገያ አካባቢዎች እንዳይጨስ የሚደረገው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር የመንገዱና የመዝናኛ ቦታዎች ሲገርመን ይባስ ብሎ ትላልቅ ስብሰባዎችንና የደስታና የሐዘን ሥነ ሥርዓቶችን ለመታደም ብዙ ሕዝብ በከተማቸበት ቦታ ጭምር ጫት መቃምና ማስቲካ ማመንዠግ ተገቢ ስላይደለ ቢተው ጥሩ ነው፡፡ ቢያንስ ግን ትራፊ ውዳቂዎችን በየቦታው ማዝረክረክ አስፀያፊና ለፅዳትም የማያመች መጥፎ ልማድ ስለሆነ ሊታረም ይገባል፡፡ ከዚህም ተያይዞ የተጠቀሙበትን ቆሻሻ ወረቀት፣ የምግብና የመጠጥ ትራፊ ሆነ መያዣ አውራ መንገድ ላይ መወርወር፣ መስኮት ከፍቶ መትፋትና ዘፈንና መንፈሳዊ መዝሙሮችን በከፍተኛ ድምፅ መልቀቅ የመሳሰሉት ሊነቀፉና ሊስተካከሉ የሚገቡ ናቸው፡፡ ጉዳይ ለመፈጸምና አገልግሎት ለማግኘት ተራ በሚጠበቅበት ወቅት ብልጥነት እየመሰላቸው መስመር የማያከብሩ ወይም አቋራጭ እየፈለጉ ሥርዓት አክባሪውን ወገን ማወክ፣ ለሌሎች ደንታ ቢስነት ብቻ ሳይሆን የቀልጣፋ አሠራር እንቅፋትም ነው፡፡ በዚህ ረገድ አሁን በታክሲ ጥበቃ አካባቢ የሚታዩ በጎ ጅምሮች ተጠናክረው ሊለመዱ ይገባል፡፡ በመኪና ማሽከርከር ረገድ በርካታ የሥነ ሥርዓት ጉድለቶች እንደሚታዩና መታረምም እንደሚገባቸው በተለያዩ መንገዶች ይነገራል፡፡ አንዳንዴ መሣሪያዎቹን እንጂ አብሯቸው የሚሄደውን ተገቢ አሠራርና አጠቃቀም የምናጤን አይመስልም፡፡ ተሽከርካሪዎችን በአግባቡና በጥንቃቄ አለመጠቀም የራስንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት ጭምር አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል በመሆኑ ተሯሩጦ መሪ መያዝ ብቻ ሳይሆን፣ ከአሽከርካሪዎች የሚጠበቀውንም ሥነ ሥርዓት በትዕግሥትና በኃላፊነት ማሟላት ይገባል፡፡ በተለይም ለእግረኞች ቅድሚያ አለመስጠት፣ ከሌሎች አሽከርካሪዎች ጋር አለመተሳሰብ፣ የትራፊክ ፖሊስ ካላየኝ በሚል ሕግና ደንብን መጣስ ለቅጣትና ለችግር የሚያጋልጥ፣ ቢያንስ ለህሊና ወቀሳ የሚዳርግ ነው፡፡ በአለባበስም በኩል ሰው እንዳቅሙ ማድረጉ ባያስነውርም እያላቸው ወቅትና ሁኔታዎችን የማያገናዝቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ አስገዳጅና አጣዳፊ ካልሆነ በስተቀር በሠርግና በሐዘን ላይ የስፖርት ቱታና ቲሸርት መልበስ ቅሬታ የሚፈጥር ነው፡፡ አለባበስ ከተነሳ በተለይ ወጣቱ አካባቢ አንዳንዶቹ ከወገባቸው ወርዶ መቀመጫቸውን የሚያሳይ፣ እንዲያውም በቅጡ አላስኬድ የሚላቸውን ሱሪ መልበስ ከዝርክርክነት ውጪ የሚታይ አይደለም፡፡ ፋሽንና አጋጌጥ የግል መብትና ምርጫ (ቴስት) መሆኑን ብናምንና ሌሎች ቁምነገሮች እያሉብን ለጌጥና ቄንጥ መጨነቅ የማያስፈልግ ቢመስልም፣ ፀጉሯን ማስረዘም ወይ ማስመሰል የምትሻ የአገሬ ልጅ ከገጽታዋ ጋር የሚሄድ እንጂ በጥቁር መልኳ ላይ ወርቅማ (ብሎንድ) የግዥ ፀጉር ባትጭንበት፣ ለሽሩባውም ተጨማሪው ገመድ ባይበዛ የሚያምር ይመስለኛል፡፡ ሽቶና ቅባቱም እንደቆዳው ሁኔታ እየታየ ከታጠቡ በኋላ እንጂ ውኃን እንዲተካ ባይደረግ፡፡ ለወንዱም ሆነ ለሴቱ የፀጉር ‹‹ስታይል›› እንደ ባለቤቱ ምርጫ ሆኖ፣ የማይፈለጉ ነገሮችን እንዳይጋብዙ በተቻለ መጠን ያልተንጨባረሩና የፀዱ ቢሆኑ ለዓይን ማስደሰት ብቻ ሳይሆን ለጤናም ጥሩ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ጥቃቅን የሚመስሉ ግን ጉዳት ሊያመጡ የሚችሉ፣ ቢያንስ የራስን ምቾት የሚቀንሱና ከሌላውም ጋር የሚደረገውን ግንኙነት የሚያዛቡ፣ በአመዛኙም ካለመተሳሰብና ለሌላው ደንታ ከማጣት የተነሳ የሚደርሱ ሁኔታዎችን በጥሞና በማስተዋል ማረምና መታረም ለሁሉም የሚበጅ ነው፡፡ እነዚህን ደግሞ ያለብዙ ጥረትና የራስን ምቾት መስዋዕት ሳያደርጉ እየዘመኑ ማስተካከልና መራመድ ይቻላል፡፡ በተለይም ዕውቀቱና ክህሎቱ ኖሯቸው የነገሮችን አግባብና የተገቢ ሥነ ሥርዓትን ጠቀሜታ ማገናዘብ የሚችሉ ወገኖች፣ የተዛቡ ሁኔታዎችን እያዩና እየሰሙ ቸል ማለት ወይም በግዴለሽነት ማለፍ፣ አልፎም እንደ ወረት መከተል ሳይሆን፣ በሚቻላቸውና በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ በምሳሌነትም ጭምር በማሳየት ለማረምና ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ይገባል እላለሁ፡፡ ይልቁንም መዘመን የሚያምረው አበላሽቶ በማፅዳት ወይም አጥፍቶ በመቆጨት ሳይሆን፣ መጀመርያውኑ በመጠንቀቅ ነውና የነገሮችን አንድምታ እያስተዋሉ መራመድ ለራስም ሆነ ለማኅበራዊ ኑሮ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው፡፡ ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...