Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአሁንም ሹመት

አሁንም ሹመት

ቀን:

በበቀለ ወዮ

በአንድ ወቅት በአገራችን የአብዮቱ ማለዳ (በ1966 ዓ.ም. መጋቢት 18 ቀን) ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ (ዛሬ ፕሮፌሰር) የተባሉ ሰው ‹‹ሹመት›› በሚል ርዕስ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ አንድ ጽሑፍ ማቅረባቸውን አስታውሳለሁ፡፡ በጽሑፉ በዋንኛነት መግለጽ የተፈለገው በጊዜው ተጧጥፎ ይታይ የነበረውን የሹም ሽረት ጉዳይ ነበር፡፡ ነጋ ጠባ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ‹‹ሹመት›› እየሰጠ ዕድሜውን ለማራዘም ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ ለዘመናት ሲጨቆን የኖረው ሕዝብ ግን ‹‹ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም›› በማለት ተቃውሞውን ቀጥሏል፡፡ በሌላ በኩል በዚያ ጽሑፍ የተካተተው በዚያ በአብዮት ወላፈን ወቅት ጸሐፊው የታያቸውን አገሪቱ የምትገኝበትን ሁኔታና ወደፊት ሊያጋጥማት የሚችለውን አደጋ በመገመትና በማመዛዘን እንደ ህልም ታይቷቸው የነበረውን ክስተት በግልጽ አሳውቀው ነበር፡፡ እሳቸው እንደ ህልም ታይቷቸው አገራችንን ኢትዮጵያን እንደ አንድ የተበላሸች መኪና አስመስለዋት ነበር፡፡ መኪናዋ ላይ ተሳፍረው የነበሩት ሦስት ሰዎች እንደነበሩና ከሦስቱ አንዱ ሲያሽከረክራት እያለ መበላሸቷን በህልማቸው እንደታያቸው ገልጸዋል፡፡ የመጀመሪያው አሽከርካሪ እንቢ ያለችውን መኪና ከሾፌሩ ጎን ተቀምጦ የነበረው ሰው መኪናዋን ለመሥራት ነካክቶ ለመንዳት ሲሞክር ብዙም ሳትነዳ አሁንም እንደተበላሸች ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁለቱም ሰዎች መኪናዋን አስተካክለው መንዳት ሳይሆንላቸው ሲቀር ሦስተኛው ሰው ከኋላ መቀመጫ ዘልሎ ይነሳና ‹‹ሁለታችሁም መንዳት ስላልቻላችሁ ተነሱና ከኋላ ተቀመጡ እኔ አሽከረክራታለሁ›› በማለት ማሽከርከር ሲጀምር መኪናዋን በማንኮትኮት ይነዳታል፡፡ ይኼን ጊዜ ጸሐፊው (ዶ/ር ጌታቸው) ስጋታቸውን እንደትንቢት ይናገራሉ፡፡ ይኸውም ሦስተኛው ሰው ወታደር እንደነበርና በወታደር አነዳድ የዚያች መኪና ዕጣ ፈንታ ምን መሆን እንደሚችል በቅሬታ ይገልጻሉ፡፡ አልፈው ተርፈው ጸሐፊው እንዳመለከቱት ወታደሩ በወቅቱ መንጃ ፈቃድ የሌለው ቢሆንም ተለማምዶባት መንጃ ፈቃድ ሊያወጣባት እንደሚችልም ሥጋታቸውን በግልጽ ያስቀምጣሉ፡፡ ያሉት አልቀረም በወቅቱ በመጀመሪያው አሽከርካሪ የሚመሰለው የአክሊሉ ሀብተ ወልድ ካቢኔ፣ በሁለተኛው አሽከርካሪ በተመሰለው በእንዳልካቸው መኮንን ተተካ፡፡ ብዙም ሳይቆይ በሦስተኛው አሽከርካሪ በወታደር በተመሰለው ተተክቶ ጊዜያዊ ወታደራዊ አገዛዝ አገሪቱን መምራት ጀመረ፡፡ ውሎ አድሮም ተለማመደና አገሪቱን የመምራት ሥልጣን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን (ኢሕዲሪ) በመመሥረት በትረ መንግሥቱን መጨበጡን አረጋገጠ፡፡ መንጃ ፈቃዱን አወጣ ማለት ነው እንደ ዶ/ር ጌታቸው ትንበያ፡፡ ዶ/ር ጌታቸው በዚያን ጊዜ ‹‹ወዮላት ያች መኪና በወታደር አነዳድ ወይ ትጋጫለች ወይ ገደል ትገባለች፤›› ሲሉ ፍርኃታቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል›› እንዲሉ፣ ዶ/ር ጌታቸው የፈሩት ደረሰና በወታደር አመራር ሥር አገራችን ወደቀችና መቼውንም መወጣት የማትችለው ፈተና ውስጥ ገብታ ትገኛለች፡፡ እኔ ዛሬ ‹‹አሁንም ሹመት›› ብዬ የእርሳቸውን ርዕስ የተጋራኋቸው በአንድ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ ገጠመኝ ስለታየኝ ነው፡፡ ይኸውም የህልም ጉዳይ ነው፡፡ የእኔ ትንሽ ከእሳቸው ለየት የሚለው እንደ እርሳቸው ልብ ወለድ ህልም ሳይሆን የእውን የእንቅልፍ ውስጥ ህልም መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ የእርሳቸው ልብወለድ ህልም የትንቢት ያህል የተፈጸመና እየተፈጸመ ያለ ድርጊት መሆኑ በገሃድ የታየ ነው፡፡ የእኔን የእውን ህልም ልንገራችሁ፡፡ አገራችን አሁን የምትገኝበት መላ ቅጡ የጠፋበት የተከፋፈለ የፖለቲካ አደረጃጀትና አመራርን የሚያመለክት ነው፡፡ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ይመስሉኛል፡፡ ሁለቱም የፖለቲካ ድርጅቶች ከአንድ ብሔረሰብ ቢሆኑም በሐሳብ ስለሚለያዩ የተለያየ የፖለቲካ ድርጅት አቋቁመው በየፊናቸው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ከፊትና ከኋላ እኔ ከመሀል ሆነን ስንጓዝ እየተከራከሩና እየተጨቃጨቁ ይሄዳሉ፡፡ እኔ የሁለቱንም ክርክር እየሰማሁ ስለነበር የአንዳቸውንም ሐሳብ ሳልነቅፍ ወይም ሳልደግፍ በራሴ እምነት ወደፊት የቀደመው ዘንድ ፈጥኜ በመድረስ የባላጋራውን ሐሳብ ለማስረዳትና ለማስማማት የምሞክር ይመስለኛል፡፡ የሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች የመጨረሻ ግብ (End Result) አንድነቷና ዳር ድንበሯ የተከበረ እናት ኢትዮጵያን መገንባት እንደሆነ በፕሮግራማቸው ተቀርጿል፡፡ የሚጣሉትና የሚለያዩት ግን የአካሄድ ዘዴ (Means) በሆነው ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ ይህ ልዩነት ሊያጨቃጭቅና ሊያጣላ ባልተገባው ነበር፡፡ ምነው ቢባል የአካሄድ ዘዴ ሐሳቦች መቼውንም ቢሆን አንድ ወጥ ሊሆኑ አይችሉምና ነው፡፡ የድሮ ነው ተብሎ ባይጣል ‹‹የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው›› ይባል አልነበረም? በሌላ በኩል ደግሞ ፈረንጆች እንደሚሉት ‹‹ሁሉም መንገድ ወደ ሮም ያደርሳል፤›› የተለያዩ ሐሳቦች ሊፋጩና ሊጋጩ ይችላሉ፡፡ ከዚያ አልፎ ተርፎ ግን ሰዎችን ሊያፋጩና ሊያጋጩ አይገባም እላለሁ፡፡ ሰው ለሰው ሊፋጭ ወይም ሊጋጭ የሚችለው ምናልባት የአውሬነት ባህሪያችን ከውስጣችን ተቀርፎ አላበቃ እንደሆነ ይመስለኛል፡፡ የሰው ልጅ ከሌላው አራዊት የሚለይበት መንገድ ቢኖር በሁለት በኩል ማየት እንችላለን፡፡ ይኸውም አንደኛ በእምነት አኳያ በፈጣሪ አምሳል መፈጠሩና ሕሊና የሚገዛውና የሚመራው ፍጡር መሆኑ ነው፡፡ በሁለተኛነት ደግሞ በሳይንስ መንገድ ስንመለከት ሰው ሊማር፣ ሊያውቅ፣ ሊሠለጥን የሚችል ፍጡር ሆኖ እናገኛለን፡፡ እነዚህን የሰው ልጅ ባህሪያት ያልተከተለ ሰብዓዊ ፍጡር ግን ሰብዓዊነቱ ጥርጣሬ ውስጥ ይገባል እላለሁ፡፡ የአውሬነት ባህሪይ (Brutality) የሚያንፀባርቅ አይኖርም ብሎ መደምደምም ፍጹም የዋህነት ነው፡፡ ብልህነት መሆን የሚችለው ያንን አውሬያዊ ባህሪይ በመማር፣ በማወቅና በመሠልጠን መቅረፍ መቻል ነው እላለሁ፡፡ አገር የምትመራው በአንድ ፓርቲ ግንባር ቀደምትነት ከሆነ ወደ ፈላጭ ቆራጭነት ወይም አምባገነናዊነት አመራር እያመራች መሆኗ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡ የተለያዩ ሐሳቦችን በማራመድ ወደ ጋራ ግብ ለመድረስ ጥረትና ብርታት ማሳየት ይጠይቃል፡፡ ይህም ሲሆን ነው ዲሞክራሲ ‘የዛሬ አበባ የነገ ፍሬ’ ሊሆን የሚችለው፡፡ አለበለዚያ በዚያው በአበባነቱ ጠውልጎ ሊቀር ይችላልና እጅግ በጣም ጠንቀቅ ማለት ይገባል፡፡ ልዩነታችን ውበታችን፣ አንድነታችን ኃይላችን ሊሆን ይገባል እንጂ ልዩነታችን ማፈሪያችን፣ መከፋፈላችንና ደካማነታችንን ማስተል አይገባውም፡፡ ይኼ ሐሳብ የማን ነው? ይኸ አባባል የማን ነው? ብሎ ነፃ ሐሳብን ከሰዎች ወይም ከፓርቲዎች ጋር ማያያዝና በጭፍን መጥላት ወይም በጭፍን መውደድ ከመደነቃቀፍ በስተቀር የትም አያደርስም፡፡ ይልቅስ ከማንም ይምጣ ከማንም ለአገር ጠቃሚና ለወገን የሚበጅ ከሆነ መቀበልና ማራመድ እንጂ፣ እገሌ ያቀረበው ወይም ያመጣው ሐሳብ ስለሆነ አዕምሮ (ህሊና) ባይቀበለውም መከተል አይገባም፡፡ የቀረበው ሐሳብ ለግል አዕምሮ (ህሊና) ደግሞ ለአገር የማይጠቅምና ለሕዝብ የማይበጅ መስሎ ከታየ የቀረበን ሐሳብ ከየትም ይምጣ ከየት ከታችም ይሁን ከላይ ከግራም ይሁን ከቀኝ አጥብቆ መቃወምና መታገል ያስፈልጋል፡፡ በአንድ የታሪክ ወቅት በፊደል ልዩነት ምክንያት የበርካታ ሕይወት መጥፋት እንዳስከተለ በዘመኑ ለነበርነው የዕድሜ ባለፀጎች ስላለፍንበት እናውቀዋለን፡፡ ከዚያ ወዲህ የተፈጠረውም ትውልድ ከተጻፉት መጻሕፍት አንብቦ ይረዳል፡፡ ያኔ ‹‹እናሸንፋለን›› የሚሉና ‹‹እናቸንፋለን›› የሚሉ ወገኖች ጎራ ለይተው አንዱ ወገን በሽጉጥ ሌላው ወገን በታንክ ፍልሚያ ውስጥ ገብተው የነበረበት ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ሆኖ አልፏል፡፡ መደገም የለበትም፡፡ የሐሳብ ልዩነት ለአገር የሚበጅ ፀጋ (Virtue) ሆኖ መወሰድ አለበት እንጂ እንደሳንካ (Vice) መታየት የለበትም፡፡ የሐሳብ ልዩነት ለችግሮች መፍቻ አማራጭ መንገድ ይፈጥራል እንጂ ጉዳት ያመጣል ተብሎ በቀና ህሊና ሊታሰብ አይገባም፡፡ ልዩነቶች አይኑሩ ብሎ ከማሰብ ይልቅ በተቻለ መጠን ልዩነቶችን ማጥበብ ወይም ማክበር ያስፈልጋል፡፡ አገር በአንድ ፓርቲ ከምትመራ በመድበለ ፓርቲ ብትመራ የሚመረጥበትም ምክንያት ይኼንኑ የሐሳብ ልዩነቶችን (አማራጮችን) ለመጠቀም ወይም ለማስተናገድ ሲባል ነው፡፡ መጨው ጊዜ (ግንቦት 2007 ዓ.ም.) የምርጫ ወቅት እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ወገን ልዩነቶችን በማክበር አንዱ የሌላው ጫና ወይም አንዱ የሌላው ጥገኛ ሆኖ ባለመታየት ወይም ባለመገኘት፣ ምርጫው የተሳካ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ ከመመዝገብ ጀምሮ እስከ መምረጡ ድረስ እንዲሳተፍና የበኩሉን መብትና ግዴታውን አውቆ እንዲጠቀም ዝግጁ ሆኖ መገኘት የወቅቱ ጥያቄ ነው እላለሁ፡፡ ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...