Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የምርት ገበያው አዲሱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሥራ ጀመሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ምርት ገበያን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ የተሾሙት አቶ ኤርሚያስ እሸቱ አዲሱ ቢሮዋቸውን በይፋ ተረክበው ሥራቸውን ጀመሩ፡፡ የዘመን ባንክ የማርኬቲንግና ኮርፖሬት ሰርቪስ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ኤርሚያስ፣ የምርት ገበያውን ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ተረክበው በይፋ ሥራ የጀመሩት ባለፈው ሐሙስ ታኅሣሥ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው፡፡ አቶ ኤርሚያስ የዋና ሥራ አስፈጻሚነቱን ቦታ የተረከቡትም ካለፈው ዓመት ጀምሮ ምርት ገበያውን በተጠባባቂ ሥራ አስፈጻሚነት ሲመሩ ከቆዩት ከአቶ ሽመልስ ሀብተወልድ ነው፡፡ አቶ ኤርሚያስ የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለመሆን የቻሉት ደግሞ ለቦታው ከታጩ ግለሰቦች መካከል ኃላፊነቱን ለመረከብ ይመጥናሉ ተብሎ በመታመኑ ነው፡፡ እንደ ምርት ገበያው መረጃ ባለፈው አንድ ዓመት ለቦታው ይመጥናሉ የተባሉ ባለሙያዎችን ለማግኘት የተለያዩ ግለሰቦችን በዕጩነት አቅርቦ ሲመዝን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከሁለት ሳምንት በፊት የአቶ ኤርሚያስን መሾም አስመልክቶ ልኮት በነበረው መግለጫ፣ በምርት ገበያው የኃላፊነት ቦታ ላይ ሊኖቸው የሚችለውን ሚና በአጭሩ ገልጾ ነበር፡፡ በዚሁ መግለጫው አቶ ኤርሚያስ፣ ‹‹ቴክኖሎጂን በመተግበር በሥራ ላይ ለማዋልና በገበያ ተኮር ተቋማት አማካይነት በግብርና ላይ የተመሠረተውን ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን በማምጣት ላይ እምነት አለኝ፤›› ማለታቸውን ጠቅሷል፡፡ አያይዞም ‹‹ከዚህ አኳያ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማጎልበትና የዓለም አቀፍ መልካም ተሞክሮን በመጠቀም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአዲስ ፈጠራዎች ኢኮኖሚው ላይ በጎ ተፅዕኖ ለማምጣት የጀመረውን የጎላ ሚና በቀጣይነት በማረጋገጡ ላይ አተኩራለሁ፤›› ማለታቸውንም መግለጫው ይጠቁማል፡፡ ምርት ገበያው ሥራ ከጀመረ ወዲህ አቶ ኤርሚያስ አራተኛው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ የመጀመርያው የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር እሌኒ ገብረመድኅን ሲሆኑ፣ እሳቸውን የተኩት ደግሞ የቀድሞው የአቢሲኒያ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አንተነህ አሰፋ ነበሩ፡፡ አቶ አንተነህ ኃላፊነቱን ተረክበው ሲሠሩ ቢቆዩም፣ በግል ምክንያታቸው ኃላፊነቱን በመልቀቃቸው አቶ ሽመልስ ሀብተወልድ ተተክተው ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ቆይተው ነበር፡፡ አቶ ሽመልስ ኃላፊነታቸውን ለአዲሱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲያስረክቡም እሳቸው በቀድሞው የኃላፊነት ቦታቸው፤ በዋና የሕግ ማስከበሪያ ኦፊሰርነታቸው እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡ አዲሱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከማንችስተር የሥራ አመራር ትምህርት ቤት በዓለም አቀፍ ንግድ ወስደዋል፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ደግሞ እንግሊዝ ከሚገኘው ከማንችስተር የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም በኮምፒውቴሽን ትምህርት ወስደዋል፡፡ የሥራ ልምዳቸውን በተመለከተ የምርት ገበያው መረጃ እንደሚያሳየው አቶ ኤርሚያስ ባለፉት 20 ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁት በአይቢኤም፣ በአልካቴል፣ በኦሬንጅና በማክሮስትራቴጂ ኩባንያዎች ውስጥ በተለያየ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግለዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስ ከከፍተኛ የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግና በቢዝነስ ኢንተለጀንስ የማማከር ልምድ ያላቸው መሆናቸውንም መረጃው ጠቅሷል፡፡ ከዚህም ሌላ የመረጃ ቴክኖሎጂና ግብዓትን አቀናጅተው ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችል አመራር ለመስጠት ክህሎት አላቸው ብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች