Saturday, June 10, 2023

‹‹እናንተስ በምርጫ ትተኩ ይሆን?››

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ወደ ጄኔራሉ የተወረወረው የአርቲስቷ ጥያቄ

ብዙዎቹ ባለፉት ሁለት ቀናት ባዩትና በታዘቡት ነገር ተደምመዋል፡፡ የሰው ልጅ ሆኖ በዚህ በረሃ ውስጥ ሠፍሮ ለዚያውም ያኔ ሰው ባልነበረበትና አካባቢው የተለያዩ ሽፍቶች በሚንቀሳቀሱበት ሥፍራ፣ ከአሥር የማይበልጡ ሰዎች ባረጁና ጊዜያቸው ባለፈባቸው ጠመንጃዎች ትግሉ ከአርባ ዓመት በፊት በደደቢት ተጀምሮ ዛሬ የደረሰበትን ማመን ያቃታቸው ይመስል ነበር፡፡ ሕወሓት በተመሠረተበት ደደቢት በምትገኝ አንድ አነስተኛ የሐውልት ምልክት አካባቢ አቶ ስብሐት ነጋን ጨምሮ በአንጋፋ የሕወሓት (ኢሕአዴግ) አመራሮች በተደረገ ገለጻ የአካባቢውን አስቸጋሪነትና ሙቀት አይተዋል፡፡ እዚህ ቦታ ላይ የታጋዮች ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር ያኔ የ30 ዓመት ወጣት የነበሩት ወያናይ ካህሳይ በቀጥታ ትዝታቸውን አካፍለዋል፡፡ ወያናይ ካህሳይ የዱር አራዊት እያደኑ ይመግቧቸው እንደነበር፣ ምግብ ማብሰያውም ሆነ እንደ ሰሀን የሚያገለግለውም ድንጋይ እንደነበር የተናገሩት ለጐብኚዎቹ በጭንቅላታቸው ውስጥ እያቃጨለ ውሏል፡፡ እሱም ብቻ አይደለም፡፡ ከደደቢት መልስ በሁለተኛው ቀን ከሽረ እንደሥላሴ በተደረገው የግማሽ ቀን አስቸጋሪ ጉዞ ደጀን በተባለው አካባቢ የሚገኘው ‹‹ሚስጥራዊ›› ዋሻ መመልከትም የሚታመን አልነበረም፡፡ ይህ ተደጋጋሚ በደርግ አውሮፕላኖች ድብደባ ተደርጐበት ምንም ጉዳት ሳይደርስበት፣ አንድም ታጋይ አደጋ ሳያጋጥም ድርጅቱን የታደገ ዋሻ፣ በውስጡ ጽሕፈት ቤቶችም ያካተተ ሲሆን፣ የዋሻው የመጀመሪያ ክፍል አነስተኛ የስታዲየም ቅርፅ ኖሮት ለስብሰባ እንዲመች ተደርጎ የተሠራ ነው፡፡ ድርጅቱ ለመጨረሻ ጊዜ ከውድቀት ራሱን የታደገበትና አዳዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ የቀረፀበት እንዲሁም ከፍተኛ የእርስ በርስ ግምገማ የተደረገበት ሥፍራ መሆኑም ይነገራል፡፡ እዚያ ለመድረስ አስቸጋሪ ቢሆንም ከጥቂቶች በስተቀር በዕድሜ የገፉ የሥነ ሥርዓቱ ተሳታፊዎች ሳይቀሩ ገደሉን አልፈው ሄደው ተደግፈው ለማየት ችለዋል፡፡ ወደ አካባቢው ለመድረስ ከትግል የማይተናነስ ፅናት የሚጠይቅ ነበር፡፡ የፕሮግራሙ መጨናነቅ ታክሎበት ብዙዎችን ያማረረ ረጅም ጉዞ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ሥፍራውን አይተው ከተመለሱ በኋላ ግን በትዝታቸው ውስጥ የሚቀረው ጥቂቱ ብቻ ይመስላል፡፡ በየአካባቢው ሕዝቡ ባሳያቸው ከፍተኛ ፍቅርና በእነዚህ ሚስጥራዊ ሥፍራዎች ባዩዋቸው ታሪካዊ ሁነቶች ባይመሰጡ፣ ምናልባት ወደ መጣንበት መልሱን ማለታቸው የሚቀር አይመስልም፡፡ በሕይወት ከሌሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በስተቀር የሕወሓት መሥራችና አንጋፋ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ጐብኚዎቹን አጅበው ታሪካቸውን ሲነግሩ ሲያስነግሩና ሲያሳዩ ሰነባብተዋል፡፡ አብዛኛው በመኪና ጉዞ የሚያልፈው ጊዜ በፈጠረባቸው ድካምና መሰላቸት የሚታይባቸው ጐብኚዎች በሦስተኛው ቀን ካደሩበት ከሽረ እንደሥላሴ እምብዛም ርቀት ሳይኖረው አንድ ታሪካዊ ቦታ ለማየት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የደርግ መንግሥት 604ኛ ኮር የተደመሰሰበት ሥፍራ ነው፡፡ አንዳንድ ጸሐፊዎች እንደገለጹት፣ ሕወሓትን ከመላ ትግራይ ጠራርጐ ለማጥፋት በአራትና በአምስት ግንባሮች ከኤርትራም አቅጣጫ ሳይቀር የዘመተበትና በመጨረሻም ሕወሓት በደርግ ወታደሮች ላይ የውጊያ የበላይነቱን የተቆጣጠረበት ‹‹የሞት ሽረት›› ውጊያ የተደረገበት ሥፍራ ነበር፡፡ ከዚህ አንድ ተራራ ጫፍ በመሆን የሽረ ከተማን ሙሉ ማየት በሚቻለው ቦታ ላይ አጭር ገለጻ ከተደረገላቸው በኋላ ስብሰባ ወደተዘጋጀበት አዳራሽ ነበር ያመሩት፡፡ ቀደም ብሎ ደደቢት ላይ በተደረገው ውይይት አቶ ስብሐት ነጋ፣ አቶ ዓባይ ፀሐዬና አምባሳደር ሥዩም መስፍን በወያናይ ካህሳይ ታጅበው ስለሕወሓት አመሠራረት፣ ሕወሓት ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ስለነበረው ግንኙነት፣ እንዲሁም የሕወሓት ፖለቲካዊ አስተሳሰብና አኅጽሮት ጋር በተያያዘ መድረክ ላይ ተቀምጠው እየተጋገዙ ነበር ገለጻ ያደረጉት፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ወታደራዊ ዕዝ መቀመጫ በሆነው በዚሁ ሥፍራ ግን አንድ ሰው ብቻቸውን ተቀምጠው ይታያሉ፡፡ ቀስ በቀስም ከፊት ያሉት ወንበሮች የትግራይ የቀድሞ ፕሬዚዳንትን አቶ ፀጋይ በርሃንና የትግራይ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኪሮስ ቢተውን ጨምሮ አቦይ ስብሐት ነጋ፣ አምባሳደር ሥዩም መስፍን፣ አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ አቶ አዲሱ ለገሰ፣ አቶ በረከት ስምኦን እንዲሁም አቶ ካሱ ኢላላ የፊት ወንበሮች በረድፍ ተቀምጠዋል፡፡ ‹‹መደመር አልቻልንም ነበር›› ከመድረኩ በስተጀርባ ከነበሩት በርከት ያሉ የቀድሞው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ምሥሎች ከያዘው ሸራ ውጪ ብቻቸውን ተቀምጠው በእጅ የተጻፉ በርከት ያሉ ማስታወሻ የያዙ ወረቀቶች የሚያገላብጡ የቀድሞ ታጋይ፣ የአሁኑ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዥር ሹም ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ ነበሩ፡፡ ያቀረቡት ጽሑፍ ጠቅለል ተደርጐ ሲቀርብ ድርጅቱ ለአሥር ዓመታት ያህል የሽምቅ ውጊያ ላይ የነበረ በመሆኑ ‹‹መደመር አልቻልንም ነበር›› የሚለውን ነው፡፡ ይኼውም አንድ ቦታ ላይ አጥቅተው ሲመለሱ ቦታው በደርግ ይዞታ ሥር መልሶ የሚወድቅበት አጋጣሚ ይበዛ ነበር ከሚል ነው፡፡ ይኼ ታሪክ የተቀየረው ወታደራዊ እንቅስቃሴው እንደ ሳይንስ ተቆጥሮ በደጀና ላይ ከፍተኛ ጥናት ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ የዚሁ ዋነኛ የትግል መገለጫም የ604ኛ ኮር መደምሰስ ነበር፡፡ አንጋፋ ፖለቲከኞቹ ምንም ዓይነት የፕሮቶኮል አለባበስ ያልነበራቸው ሲሆን፣ ‹‹ሻዕቢያ ጉድጓድ መቆፈር ይችላል፣ እኛ ደግሞ ከጉድጓድ አውጥተን መቅበር እንችላለን፤›› በሚለው ንግግራቸው በስፋት የሚታወቁት ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ ደግሞ ቀለል ያለ ሹራብ ጣል አድርገው ምንም ዓይነት ወታደራዊ ፕሮቶኮል አልበራቸውም፡፡ አቀራረባቸውም ቢሆን ለብዙዎች የተመቸና የጉብኝቱ ተሳታፊዎች የሕወሓት ወታደራዊ ሥልትና ታክቲክን በቀላል መንገድ እንዲረዱ የረዳ ነበር፡፡ በሦስት ምዕራፍ ከፋፍለው ያቀረቡት ይኼው የሕወሓት የትግል ታክቲክ ከ500 ሺሕ በላይ ጦር የነበረውና በአፍሪካ ወደር ያልነበረው የደርግ ጦር ሠራዊትን ያሸነፈበት ‹‹ሕዝባዊና ወታደራዊ›› ሳይንስ ካብራሩ በኋላ አንዳንዶቹ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የመጀመሪያው ጠያቂ አርቲስት አበበ ባልቻ ሲሆን፣ በዚህ የ604ኛ ኮር ጦርነት የሻዕቢያ ሚና ምን ነበር የተነገረው? ወታደራዊ ፍፃሜዎችስ ምን ያህል በጽሑፍና በምሥል ተሰንደዋል? የሚል ነበር፡፡ ጄኔራሉ ሲመልሱ በነበራቸው በወታደራዊ ትብብሩ መሠረት ‹‹የሕወሓት ታጋዮች በሳህል ተራሮች ጦርነት እንደተሳተፉ ሁሉ ሻዕቢያም በትንሹም ቢሆን ተሳትፏል፤›› ብለዋል፡፡ እነሱ በሚያወሩት ደረጃም ባይሆን፡፡ አቶ ሳምሶን ማሞ አስተያየትም ጥያቄም አቅርቧል፡፡ ‹‹ባለፉት 23 ዓመታት ያየሁት የደርግ ወታደሮች በሚጽፉት ድርሰት ምክንያት እነሱ አሸናፊ መስለው እስከመታየት ደርሷል፡፡ ምናልባትም ትንሽ ቆይተን አቶ ለገሰ አስፋው ‘እኔና ሐውዜን’ የሚል መጽሐፍ ሊጽፉ ይችላሉ፤›› በማለት ታዳሚዎችን ፈገግ አሰኝቷል፡፡ ታሪካቸውን እንዲጽፉ ወታደራዊ ሚስጥሮቻቸውን ሳይቀር ለጸሐፊዎች ክፍት እንዲያደርጉ አርቲስቶችን በመወከል ነበር የተናገረው፡፡ ‹‹ይኼ ታሪክ የትግራይ ሕዝብ ብቻም አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ሆኗል፡፡ መብታችን ነው ፍቀዱልን እንጻፈው፡፡ ሥርዓቱ እንዲቀጥል እንፈልጋለን፡፡ ከፋም ለማም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሥርዓቱ ተጠቃሚ ነው፤›› ሲል በታዳሚዎቹ ከፍተኛ የድጋፍ ጭብጨባ ታጅቧል፡፡ ‹‹ማንንም ለማዳን ብዬ ሳይሆን ለራሴ ስል ነው፡፡ አገሬን አሳልፌ አልሰጥም፡፡ የአገር መፍረስ ማለት እነዚህ ኃይሎች የራሳቸውን የፈጠራ ታሪክ እየጻፉ የሕዝቡን አስተሳሰብ መቀየር ሲችሉ ብቻ ነው›› ሲል አስተያየቱን ቋጭቷል፡፡ ‹‹እናንተን የሚተካ አዲስ መሪ›› በመጨረሻ ዕድሉ የተሰጣት አርቲስት አስቴር በዳኔ ከተቀመጠችበት ወደፊት ወጥታ ማይኩን ስትጨብጥ ፍርኃት ቢጤ እንደወረራት ከመጀመሪያው ያስታውቃል፡፡ ‹‹በጣም ነው የሚያስፈራው፤›› በማለት የጀመረችውን አስተያየቷን የያዘችውን ማስታወሻ እያነበበች አስተያየት መስጠት ቀጠለች፡፡ ‹‹ይህንን ዕድል ተመቻችቶልን በቴሌቪዥን ስናየው የኖርነው ታሪክ ለማየት ስለቻለን እጅግ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ በፊት የነበረኝ ያልተጨበጠ አመለካከት በመረጃ የተደገፈ ሆኗል፤›› በማለት ሐሳቧን ቀጠለች፡፡ ‹‹እውነትን መናገር እወዳለሁ፡፡ የሐሳብ ነፃነትም አለ፡፡ በእርግጥ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም፤›› በማለት ታዳሚዎችን ፈገግ ያሰኘች ሲሆን፣ በሒደትም የፍርኃቷ መጠን እየቀነስ የመጣ ይመስላል፡፡ ‹‹ዛሬ ባልናገረው የሚቆጨኝ የተከፈለው መስዋዕትነት እጅግ በጣም ከባድ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ የሕወሓት ታሪክ አንድ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው፡፡ በጆሮ ስሰማው ደርግ ተደምስሶ ታጋይ እንዲህ ሆኖ ሲባል ከሁለቱም ወገን የተሰዉት በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው፡፡ የሞቱት፣ እግራቸው የተቆረጠ፣ ዓይናቸው የጠፋ ስላሉ ለሁለቱም ‹ጠላት› የሚለው ቃል ተገቢ አይመስለኝም፡፡ የወንድማማቾች ደም በመፍሰሱ ቤተሰቦቻቸው ዘንድ ሄደን ስናይ ልብ የሚሰብር ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የጦርነትና የትግል ታሪክ ዘመኑ የፈጠረው ነው፡፡ በወቅቱ መንግሥታዊ ለውጥ ለማምጣት የትጥቅ ትግሉ አማራጭ አልነበረውም፡፡ አሁንስ?›› አርቲስት አስቴር ትንፋሿን ዋጥ በማድረግ ቀጠለች፡፡ ‹‹የትግሉ ዋና ሐሳብ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በአገሪቱ ለማምጣት ነው፡፡ የመንግሥትም ሆነ የሥርዓት ለውጥ በጦርነት ሳይሆን በዲሞክራሲ እንዲሆን ነበር ያ ሁሉ ከባድ መስዋዕትነት የተከፈለው፡፡ አሁን ላይ ሲታሰብ የሚመጣው ግንቦት ላይ 24 ዓመት የሚሆነው ሥልጣን ላይ ያለው አንድ ፓርቲ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ላይ ልባችሁ ምን ይላል? ያኔ ለሥልጣን ሳይሆን ለሕዝብ ስትታገሉ በጦርነት ሳይሆን በዲሞክራሲ ለውጥ እንዲደረግ ነበር፡፡ አይለደም?›› በማለት ጠየቀች፡፡ ‹‹በእርግጥ የድሮን አስተሳሰብ መናፈቅ አዲስ አስተሳሰብ ለመቀበል ይከብዳል፡፡ አሁን ዝም ብዬ ሳስበው ራሱ ተቃዋሚ የሚለው ቃል ራሱ ጥሩ አይደለም፡፡ ተፎካካሪ ቢባል፡፡ አዲስ አስተሳሰብና ፍልስፍና ያለው ተተኪ መሪ ሊፈጠር አይችልም የሚል አቋም ነው ያላችሁ?›› በማለት ሐሳቧን ያልቋጨችው አርቲስት አስቴር፣ ሐሳቧ በብዙዎች ተጠብቆ የነበረ አይመስልም፡፡ ‹‹አመሰግናለሁ›› የሚለው የመጨረሻውን ቃል እስክትናገር ከአጠገቧ የተቀመጡ ኢትዮጵያን እየመሩ ያሉት አንጋፋ ታጋዮች ጥያቄው እስኪያልቅ የተጨነቁ ይመስላል፡፡ እርስ በርስ አየት ተደራርገው የተለዋወጡት ፈገግታ ጥያቄውን የጠበቁት እንዳልሆነ ያሳብቃል፡፡ በእርግጥም በምርጫ ዋዜማ ሆነው ለጥያቄው ምን ተብሎ ምላሽ እንደሚሰጥ ሳያስጨንቃቸው አልቀረም፡፡ ‹‹እውነት መናገር እውዳለሁ›› በሚል የጀመረችው ፍርኃት እየፈጠረባትም ቢመስል የመጨረሻ ማጠናቀቂያ ሐሳቧ እንዲህ ነበር የሚለው፡፡ ‹‹ምክንያቱም እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፡፡ ቁርጠኛ የሆነ ታሪክ ያፈራ በኢትዮጵያ አይደለም በዓለም የሚደነቅ የትግል ታሪክ ነው ያላችሁ፡፡ ‘So, next time’ ምን ያህል አዲስ ታሪክ አዲስ አስተሳሰብ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተለውጦ እናያለን?›› የሚለው ፈራ ተባ እያለች የጨረሰችውን ጥያቄ ‹‹ውርድ ከራሴ›› ይመስል ድምጿ እየተቆራረጠ ‹‹አመሰግናለሁ›› ብላ፣ ‹‹እናንተስ በምርጫ ትወርዱ ይሆን?›› ብላ ነበር ጥያቄዋን የቋጨችው፡፡ አቶ በረከት ስምኦን ሁለት እጆቻቸውን ወደፊት ወስደው እንደማፍተልተል ሲያደርጉ፣ ሌሎች ብዙዎቹ አንጋፋ አመራሮች በግርምት ጉንጫቸውን ደገፍ አድርገው ይዘው ታይተዋል፡፡ ጄኔራል ሳሞራ መልሳቸውን በመጨረሻውና ጠንከር ባለው ጥያቄ ላይ የጀመሩ ሲሆን፣ ‹‹ተቃዋሚ የሚለው ችግር ያለው አይመስለኝም፡፡ አንቺ ያመጣሽውም ቢሆን የሚጠላ አይደለም፡፡ ተቃዋሚ የሚጠላ ድርጅት ያለ አይመስለኝም፡፡ ኢሕአዴግ ተቃዋሚ የሚጠላ ቢሆን ኖሮ እንደ ሻዕቢያ በሩን መዝጋት ይችል ነበር፤›› ብለዋል፡፡ የኤርትራ መንግሥት የሚጠቀመውን ‹‹ሓደ ልቢ፣ ሓደ ሥርዓት፣ ሓደ ሕዝቢ›› የሚለውን አገላለጽ ተርጉመው ‹‹አንድ ልብ፣ አንድ ሕዝብ፣ አንድ ሥርዓት›› የሚለውን አስቀምጠው እጆቻቸውን እያወናጨፉ፣ ‹‹ኢሕአዴግ ተቃዋሚ የማይቀበል አመለካከትና አስተሳሰብ ቢኖረው ኖሮ የዲሞክራሲ መንገድም አይታይም ነበር፡፡ ጋዜጦችን መዝጋት ይቻላል፡፡ የኢሕአዴግ ዓላማ ራሱ ይኼ አይመስለኝም፤›› በማለት ወደ ተቃዋሚዎች ጣታቸውን ቀስረዋል፡፡ ‹‹አንድ ነገር ልጨምር፡፡ በአስተሳሰብ ወይም በፖሊሲ የሚቃወም ተቃዋሚ የሚጠላ አይመስለኝም፡፡ የሚፈለግ ይመስለኛል፡፡ እኛ ጋ ያለው ተቃዋሚ ግን ብሔራዊ ጥቅምን ለሌላ አሳልፎ እየሰጠ የሚቃወም ተቃዋሚ ነው፤›› የሚለው ንግግራቸው በከፍተኛ ጭብጨባ የታጀበ ነበር፡፡ ‹‹አገሩን ለሌላ እየሰጠ የሚቃወም ተቃዋሚ ለምሳሌ የዚህች አገር መከላከያ ቢበተን ደስ ይለዋል፡፡ እንዲበተንም የሚሠራ ነው፡፡ አገር እየተተራመሰች እንድትኖር የሚፈልግ ተቃዋሚ ተቃዋሚ አይደለም፡፡ አንቺ ባልሽው በዚህ እስማማለሁ፡፡ ተቃዋሚ እንደዚህ ከሆነ፡፡ ለማንኛውም እኔ ምድብተኛ ወታደር ነኝ፤›› በማለት ሐሳባቸውን ቋጭተው በፈገግታ የውይይቱ ተሳታፊዎችን ተሰናብተዋል፡፡ በሌሎች ጥያቄዎች ላይ ምልልሱ ቢቀጥልም፣ ነገር ግን ሌሎች የፖለቲካ አመራሮች በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየት ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -