Sunday, June 23, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያና ግብፅ ከጠላትነት ምንም አያተርፉም

ልዑል ዘሩ

ግብፅና ኢትዮጵያ የወዳጅነትም ሆነ የተቃርኖ ማዕከላቸው ዓባይ መሆኑን ይህ የሁለቱ አገሮች የተፈጥሮ ገመድ ግንኙነታቸውን ወደ ሌላ ከፍታ እንደወሰደው በተከታታይ ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡ በተለይ የግብፅ ገዥዎች የኢትዮጵያ ሕጋዊና ተፈጥሯዊ ጥቅምን የሚያሳጡ የተለያዩ የፖለቲካ ደባዎችን ሲፈጽሙ እንደቆዩም ዳሰሳ ተደርጓል፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብን አገራችን በራስ አቅም ለመገንባት ስትነሳ ግብፆች ከተፋሰሱ አገሮች ስምምነት ውጪ ወደ ሌላ ድርጊትና ፈጥጫ ሲገቡ መክረማቸውንም እንዲሁ፡፡ ከዚያ በኋላ መለዘብ አሳይተው ለውይይት መዘጋጀታቸውን፣ በውይይቱ መሀል አደናቃፊ ነገሮች መሰንቀራቸውንና የተለያዩ አቋሞችን ማራመዳቸው ተወስቷል፡፡ በዚህ በኩል ኢትዮጵያ ይዛ የተነሳችው የውጭ ግንኙነት አቋም የአገሪቱን ሕዝብ በፍጥነት ከድህነት በማውጣት፣ ሰላምና ዲሞክራሲ የሰፈነባት አገር መገንባት ላይ ማተኮሩ የኃይል ሚዛኑን እየቀየረው መምጣቱም ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ የፀረ ድህነት ትግል ገና በርካታ ቀሪ ሥራዎች ያሉበት ዲሞክራሲውም ቢሆን እንጭጭና የተነደፉ ሕጎች በሁሉም በኩል በንቃት የሚፈጸሙ ባይሆንም ጅምሩ መልካም ዕድል ፈጥሯል፡፡ ነገር ግን በብርቱ ታስቦበት ሊጠናከር ይገባል፡፡ ከግብፅ መንግሥት ጋር በዓባይ ጉዳይ እየተደረገ ያለው ውይይትና ድርድር ግን አሁንም ጥልቅ ብልኃት፣ ሚዛናዊ ፖለቲከኝነትና ደፋር አመራርን መፈለጉ አይቀርም፡፡ ከወሰን ተሻጋሪ ውኃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ምንጊዜም በአገሮች መካከል አለመግባባትና ፍጥጫ ይከሰታል፡፡ በዚህ መዘዝ ወደ ግጭት የገቡ አገሮች ተሞክሮ ግን ብዙም አይደመጥም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ውኃን ብቻ መሠረት አድርጎ ጦርነት ማካሄድ አክሳሪና የማያወጣ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከውጊያ በኋላ አትራፊ ሊኖር የማይችል በመሆኑም ነው፡፡ ውኃ ግን ያለመግባባት መንስዔ መሆኑ አይቀርም፡፡ ኢትዮጵያና ግብፅም ሆኑ ሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች የናይል ውኃን በጥንቃቄ፣ በቁጠባና በትብብር ከተጠቀሙ ለረዥም ጊዜ በበቂ ሁኔታ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህ ወደ ግጭት የሚወስድ ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ግጭት መሞከርም የኋላ ኋላ ግጭት የሚቀሰቅሱትን የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ለዘለዓለም ሰለባ ሊያደርግ የሚችል አደጋ ሊከሰት ይችላል፡፡ በመሆኑም በየትኛው አግባብ ግብፃውያን ከውይይትና ከመቀራረብ ውጪ ሊመኙት የሚችል ጉዳይ አይደለም ጦርነት፡፡ ግን ከጀርባ የፖለቲካ ደባ፣ የኢኮኖሚ ጫናና የዲፕሎማቲካዊ አሻጥር ሊፈጠር አይችልም ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ የራሱ አደጋ አለው፡፡ ታዛቢዎች እንደሚገልጹት ግብፆች በአንድ ትልቅ ተፅዕኖ የፈጠረ የናይል ውኃ ጉዳይን የብሔራዊ ደኅንነታቸው አካል አድርገው መውሰዳቸው ነው፡፡ ስለዚህ ዓባይ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ልማትና ፕሮጀክት በብሔራዊ ደኅንነታቸው ላይ የተደረገ ትንኮሳ አድርገው ይወስዳሉ፡፡ በዚህ ላይ መደራደርም አይፈልጉም፡፡ ይህንን እውነታ መንግሥታትም ቢቀያየሩ ሊለወጥ ያልቻለው በሕዝቡ አዕምሮና ሥነ ልቦና ላይ ሲቀርፁ የኖሩት በመሆኑ፣ በቀላሉ የፖለቲካ ክስረት ሊያስከትልባቸው እንደሚችል ስለሚገነዘቡ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ጉዳዩን የሕገ መንግሥታቸው አካል በማድረጋቸው የበለጠ አወሳስበውታል እንጂ አላቀለሉትም፡፡ የአዲሱ የግብፅ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 44 በናይል ጉዳይ ላይ ራሳቸውን ሌላ አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት እንደሆነ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡ ይኼው ግብፃውያንን የተፋሰሱ አገሮች ስምምነትን እንዳይቀበሉ ወይም ከሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ጋር እንዳይደራደሩ እግር ይይዛል፡፡ የግብፅን ‹‹ታሪካዊ የውኃ መብት›› የመከላከልና የመጠበቅ ግዴታ በመንግሥት ላይ የጣለው ይህ አንቀጽ ተደንቅሮ አሁን ምን ዓይነት ውይይት ሊደረግ ይችላል? ሲሉ የሚጠይቁ ኢትዮጵያውያን ሥጋት በተሞላበት ስሜት ነው፡፡ በእርግጥ ግብፆች ሕገ መንግሥታቸውን በፈለጉት አኳኋን የማውጣት መብት አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ በወሰን ተሻጋሪ ወንዝ ላይ እንደዚህ ዓይነት ዓይነት ሕገ መንግሥት መቅረፅ ግብፃውያን ራሳቸውን ሌላ ተፅዕኖ ውስጥ ይከታቸዋል፡፡ የወሰን ተሻጋሪ ውኃ የአንድ አገር ሀብት አይደለም፡፡ የተፋሰሱ አገሮች የጋራ ሀብት ነው፡፡ ይህን ሀብት በዘላቂነት ለመጠቀም ደግሞ መተባበር የግድ ያስፈልጋል፡፡ ስምምነት ከሌለ መጀመርያ የሚጎዳው ተፋሰሱ ነው፡፡ በውኃው ላይ ሽሚያ ይኖራል፡፡ በጋራ ዕቅድና መንከባከብ ላይም ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ ስለዚህ የግብፅን ሕገ መንግሥት የናይል (የዓባይ) ውኃ አጠቃቀምን አሁን ባለበት ሁኔታ ማካተቱ ልዩነቶችን በስምምነት ሳይሆን፣ በሌላ ፍጥጫ እንዲቀጥሉ የሚያንደራድር እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ጥሬ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አዲሱ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ የመሪነትን ቦታ ይዘው በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በአፍሪካ ኅብረት የማላቡ ጉባዔ ላይ በተናጠል መገናኘታቸው ነገሮችን እንደቀየረ ተወስዷል፡፡ በዲፕሎማሲ ሥራ ውስጥ ዘለዓለማዊ ወዳጅ ወይም ጠላት ብሎ ፍረጃ ባይኖርም፣ ወይም ለድርድርና ስምምነት የተዘረጋ አትሮነስን የራስንን ጥቅም በማያስከብር አኳኋን ማንበቢያ ከማድረግ ውጪ አማራጭ ስለሌለ እንጂ የድርድር ጉዞው መቋጫ የሚያገኝ አይመስልም፡፡ አሁን ባለው የግብፅና የኢትዮጵያ ሁኔታ ቀጥ ያለ ድርድርና ወደ ስምምነት የመቀረራረብ አዝማሚያ አለ ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ የሁለቱም መንግሥታት ተደራዳሪዎች ከስድስት ወራት በፊት በቆሙበት አቋም ላይ እንዳሉ ናቸው፡፡ ይልቁንም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ወዳለቀ ደረጃ ለመውሰድ በሚመስል ሁኔታ የፐብሪክ ዲፕሎማሲው ሥራው ላይ ያተኮሩ መስለዋል፡፡ ከወራት በፊት በግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራ የመንግሥት ባለሥልጣናትና በለሀብቶች ልዑካን በአዲስ አበባ ተገኝቶ ምክክር አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ በቅርቡ ደግሞ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ አርቲስቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን፣ ታዋቂ ሰዎችና ጋዜጠኞች የተሳተፉበት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ካይሮ ሄዶ ተመልሷል፡፡ በዲፕሎማሲያዊ መቀራረብ እንዲህ ዓይነት ግንኙነቶች ማዳበር፣ የግብፅ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረጋቸውን ጥረት ማሻሻል፣ የኢትዮጵያ የውጭ ምርቶችን ከፍ ባለ ደረጃ ለግብፅ ገበያ ማቅረብን የመሳሰሉ ጥረቶችም ሊጎለብቱ ይገባል፡፡ ከዘህም ባሻገር በንግድ፣ በቱሪዝም፣ በሃይማኖታዊና ነባህላዊ ግንኙነቶችም አዳዲስ ግንኙነቶችን መዘርጋት፣ በድንበር የማይገናኙትን ነገር ግን በዓባይ ውኃ ምክንያት በጥብቅ የተሳሰሩትን የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ተጠቃሚነት ሊያሳድገው እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህም በላይ ግን ሁለቱም አገሮች ከየትኛውም ዓይነት የፖለቲካና የኢኮኖሚ አሻጥር መራቅ ይኖርባቸዋል፡፡ አንዱ የሌላውን የታጣቂ ተቃዋሚ በፋይናንስ፣ በፕሮፓጋንዳም ሆነ በሎጀስቲክስ ያለመደገፍ፣ አንዱ ሌላው ብድርና ዕርዳታ እንዳያገኝ አለማወክ፣ አንዱ የሌላውን ገጽታና ምሥል አለማጠልሸትን የመሰሉ ሥራዎችንም ያካትታል፡፡ እነዚህ እውነታዎች ግን ገና ወደ መደራደሪያ ነጥብነት ያመሩ አይመስሉም፡፡ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸውን መገመት ግን አያዳግትም፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በፀረ ግብፅ ዘመቻ ባትታወቅም ንፅህናን ማሳየት ጠቃሚ ነው፡፡ ወደ ዓባይ ውኃ አጠቃቀም በተለይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውይይት ስንመለስ ግን ‹‹የተጓተተው ውይይት እስከ መቼ ይቀጥላል?›› ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ወሰን ተሻጋሪ ውኃዎች ላይ ድርድር ያለና የተለመደ ቢሆንም፣ አገሮቹ ወደ ድርድር ወይም ትብብር መድረክ የሚመጡት በሁለት ቅድመ ሁኔታዎች እንደሆኑ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ የመጀመርያው ቅድመ ሁኔታ አገሮቹ በድርድር ላይ አመኔታ ሲኖራቸው ነው፡፡ ይኼውም ወሰን ተሻጋሪ ውኃዎችን በትብብርና ጥቅም ላይ ቢውሉ የተሻለ የጋራ ጥቅም እንደሚገኝ አምኖ መቀበል አለባቸው፡፡ ይህንን ከተቀበሉ ወደ እውነተኛ ትብብርም ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ይህ በማይሆንበት ሁኔታ ግን ሁለተኛው አማራጭ የሚሆነው በወሰን ተሻጋሪ ውኃዎች ላይ ትብብር ግዴታ ይሆናል፡፡ በወሰን ተሻጋሪ ውኃ ላይ ያለመተባበር የሚያስከፍለው ዋጋ አለ፡፡ የትብብርና የመደጋገፍ ጥቅም አሳምኖት ወደ መድረኩ ያልመጣን አካል ያለመተባበር የሚያስከፍለው ዋጋ አስገድዶት እንደሚመጣ ነው የዘርፉ ተንታኞች የሚገልጹት፡፡ ይህ ደግሞ የተሻለ አማራጭ አይደለም፡፡ የግብፆችም ሁኔታ ሲታይ ወደ ትብብር መምጣታቸው አይቀሬ ብቻ ሳይሆን፣ ለስምምነትና ውይይት የተፈጠሩ ዕድሎችን በበጎ ጎን ወስደው መጠቀም ይገባቸዋል፡፡ ዕድሎቹን መግፋት ግን ተገዶ ወደ ትብብር መምጣትን ያስከትላል፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ያሉ የግብፅ ሕዝብ አስተዳዳሪዎችና ፖለቲከኞች የጀመሩትን መልካም ጥረት አጠናክረው ገፍተው በመቀጠል፣ ከኖረው የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ በመውጣት ወደ እውነተኛ ትብብር መምጣት እንዳለባቸው የብዙዎቹ ታዛቢዎች አስተያየት ያስረዳል፡፡ እዚህ ላይ የሱዳን መንግሥትና ሕዝብ ከኖረው የተዛባ አስተሳሰብ በመውጣት በዓባይ (ናይል) ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላዩ የቀጣናው ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ውስጥ ብቸኛው መፍትሔ ትብብር ነው የሚል እምነት ማሳደራቸው በአርዓያነቱ ይጠቀሳል፡፡ ግብፅ በሱዳን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ይዞታ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ነበራት፡፡ ሱዳን ውስጥ ሁለት ፓርቲ ሲኖር ከሁለቱ አንዱ ዩኒየኒስት የሚባል ፓርቲ ነው፡፡ ይህ ፓርቲ የተቋቋመው በአብዛኛው ግብፅና ሱዳንን አንድ አገር የማድረግ ዓላማ በመሰነቅ ነው፡፡ የሚደገፈውም ሙሉ በሙሉ በግብፅ መንግሥት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የተወሰኑ ሚኒስትሮች ደግሞ ቢያንስ ሁለት ከዚሁ ፓርቲ ይመረጣሉ፡፡ ለምሳሌ የመጨረሻው ከዚህ ፓርቲ የውኃ ሚኒስትር ሆነው ለረዥም ጊዜ ያገለገሉትና በናይል ተፋሰስ ትብብር መድረክም በተደጋጋሚ ሲገኙ የነበሩት ኢንጂነር ከማል ዓሊ የተባሉት ሚኒስትር ይጠቀሳሉ፡፡ ታዲያ እኚህ ባለሥልጣን ለግብፅ ካላቸው የፀና ድጋፍም በላይ የግብፅን አቋም በሱዳን በኩል አጥብቀው ስለሚያራምዱ፣ በአብዛኛው ኅብረተሰብ ዘንድ ሱዳን ከግብፅ የባሰች ለትብብር ያልታመነች ተደርጎ ነበር፡፡ ይህ የአንድ ሚኒስትር የግል አቋም በሒደት የሱዳን ሕዝብና መንግሥት አቋም አለመሆኑ ሲገለጥም የናይል ትብብር ማዕቀፍ በብዙ ድካም ሲፈረም እሳቸው ከሥራቸው የተሰናበቱ መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያስረዱት፡፡ ለሱዳን የድርድርና ትብብር መንፈስ መዳበር ቀደም ባሉት ጽሑፎች እንደተገለጸው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገነቡት ግድቦች ጥቅሟን የሚነኩ አለመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ጥቅም መስጠታቸውን መገንዘባቸው አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እያረጋገጡት የመጡት ፈጣን ዕድገትና ሰላማዊ አገርነት፣ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲም ሆነ በአፍሪካ የመሪነት ሚናቸው እየጎላ መምጣቱም አላገዘም ማለት አይቻልም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በናይል ውኃ ላይ ሱዳን ሁልጊዜም ቢሆን ለግብፅ ጠበቃ ሆና ትከራከራለች እንጂ፣ ግብፃዊያን ስለሱዳን የውኃ ተጠቃነትሚነት የሚጨነቁ አለመሆናቸው ተስፋ አስቆርጧቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በቅርቡ ‹‹የናይል ጉዳይ ትብብር ወይስ ፍጥጫ›› ሲል ባወጣው አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ እንዲህ ብሏል፡፡ ‹‹በአብዛኛው የሚታየው ሱዳን ለግብፅ ጥብቅና የመቆም ነው እንጂ በግብፅ በኩል ለሱዳኖች የተደረገ ምንም ዓይነት ድጋፍ የለም፡፡ አልፎ አልፎም በውኃ አጠቃቀማቸው ላይ ከግብፅ በኩል ግፊትና ጫና እንዳለ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ማንሳት የሚቻለው የመረዌ ግድብ ተገንብቶ ሥራ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ሱዳን ግድቡን ለመገንባትና ውኃ ለመሙላት ከግብፅ ፈቃድ መጠየቅ ነበረባት፡፡ ፈቃድ ጠይቃ ግን እስከዛሬም መልስ አላገኘችም፡፡ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገኘውን የሮዝሬስ ግድብ (ኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ላይ ያለውን) ሱዳኖች ከፍታውን ለመጨመር ፈልገው ከግብፅ ፈቃድ ጠይቀዋል፡፡ እስዛሬም ፈቃድ አላገኙም፡፡ እ.ኤ.አ. በ1959 ከግብፅ ጋር በገቡት ስምምነት የተሰጣቸውን የውኃ ኮታ ድርሻ እንኳን እንዲያገኙ አልተፈቀደላቸውም፡፡ በአብዛኛው በግብፅ በኩል ከፍተኛ ጫና እንዳለባቸው በአሁኑ ወቅት ተገንዝበዋል፤›› ይላል፡፡ ታዲያ ለኢፍትሐዊ ተጠቃሚነት መወገን ይበልጣል ወይስ በፍትሐዊነትና በምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም ላይ ላተኮረው የተፋሰሱ ስምምነት መታመን!? ይህንን አንባቢያን ሊፈርዱ ይችላሉ፡፡ ማጠቃለያ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ለሦስት ዓመታት ይዣቸው የቆየሁት ሐሳቦች የጉዳዩ አሳሳቢነትና ወቅታዊነት ትኩረቴን ስለሳቡት ብቻ አይደለም፡፡ ወይም የግብፃውያን ፖለቲከኞች ቁርጥ አቋም አለመያዝና አንዳንድ የተፋሰሱ አገሮችም ፈጥነው ስምምነቱን በየምክር ቤቶቻቸው አለማፅደቃቸውም አላስጨነቀኝም፡፡ ከዚያ ይልቅ ቀን ከሌት ያለውን ሀብት፣ ዕውቀትና ጉልበት ሁሉ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ እያፈሰሰ ያለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያወያይና ግንዛቤ ሊያስጨብጥ ይችላል ብዬ በማመን ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላትና መሰል ወገኖች ከዓባይ ወንዝ የውኃ አጠቃቀምና ከመጪው የአገሮቹ ግንኙነት አኳያ ተጨማሪ ምልከታና ምርምር እንዲያደርጉ ለመጋበዝም ነው፡፡ በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ድርድሩና ትብብር ጥረቱ በጥሩ ሁኔታ እየተጓዘ ነው ቢባልም፣ የዓባይ ፖለቲካ በሴራና በፍጥጫ የኖረ እንደመሆኑ ወዴት ሊያመራ ይችላል? ብሎ ማጤን እንደ ዜጋ የሁሉም ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ረገድ በአገራችን የሚገኙ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች፣ መገናኛ ብዙኃንና ሲቪክ ማኅበራት ሁሉ ለብሔራዊ ጥቅም ከሚሰጡት ትኩረትና ወገንተኝነትና አኳያ እንደሚመዘኑ ተረድተው ከሕዝባችንና ከመንግሥት አቋም ጎን መቆም እንዳለባውም ሊዘነጋ አይገባም፡፡ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በቅርቡ ኢትዮጵያን ሲጎበኙም ከምንም ነገር በላይ እንዲነገራቸው የሚፈለገው፣ ኢትዮጵያና ግብፅ በዓባይ ውኃ ምክንያት ችግር ውስጥ መግባት እንደሌለባቸው ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ውኃን በፍትሐዊነት መጠቀምና ለበለጠ ትብብር ራስን ማዘጋጀት እንደሚበልጥ ማሳሰብ ተገቢ ነው፡፡ ከዓባይ ውኃ በላይ የሚያስተሳስሩን በርካታ የጋራ ጉዳዮች ስላሉን በውንድማማችነት ግንኙነታችንን መስመር እናስይዘው መባል አለበት፡፡ ኢትዮጵያና ግብፅ ከጠላትነት ምንም እንደማያተርፉ በግልጽ መነገር አለበት፡፡ ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles