Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊ‹‹ሰሚያጡ›› እሪታዎች

‹‹ሰሚያጡ›› እሪታዎች

ቀን:

የኢቦላ ደም አፍሳሽ ትኩሳት ክፍል 2 በአሸናፊ ዋቅቶላ፣ (ሕ/ዶ) መግቢያ ‹‹እኔ የእከሌ ልጅ፣ አትበል እባክህ፣ እኔ የጎበዝ ልጅ፣ አትበል እባክህ፣ ደጋ ተገኝተሀል፣ ከነስልቻህ›› “ኦራን! ኦራን!” ምንም እርባና ላይኖረው ጥሪው ከውቅያኖስ ባስተሻገር ያስተጋባል፤ ምንም ላይጠቅም ሪህዩ በተስፋ ያዳምጣል። ሁልጊዜ የቀና አንደበታም ንግግር ማዕበል መፍሰስ ይጀምርና በግራንድና በተናጋሪው መሀል ሊገደብ የማይችለውን ገደል ያስመለክታል። ‹‹ኦራን፣ አብረናችሁ ነን!›› እያሉ በስሜት ገንፍለው ይጣራሉ። ነገር ግን፣ ዶክተሩ ለራሱ እንደነገረው፣ አብሮ ለማፍቀር ወይም አብሮ ለመሞት አልነበረም፣ ብቸኛው መንገዱም ያ ነው። በጣም ርቀዋል።›› ይህ ፅሑፍ ታኅሳስ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ኢቦላ ቫይረስ በሽታ (ኢቦላ ደም አፍሳሽ ትኩሳት) ከፍተኛ ትኩረት የሚያስፈልገው እጅግ አደገኛ ሁኔታ በሚል ርዕስ ካቀረብኩት ጽሑፍ የቀጠለ ነው። ርዕሱ የተገኘው ደግሞ በዶ/ር ፈቃደ አዘዘ የሰሜን ሸዋ ረሃብን አስመልክቶ የተዘጋጀው የገበሬው የቃል ግጥሞች ስብስብ ነው። የምዕራብ አፍሪካ የኢቦላ ቫይረስ እጅግ በፍጥነት መስፋፋቱ ብቻ ሳይሆን ቀስ በቀስ ርቆ በመሄድ ለዓለም በጠቅላላው አደገኛነቱን በግልፅ እያሳየ ነው። በትልቅ የሕክምና ጆርናል ርዕሰ-አንቀፅ ውስጥ የኢቦላ ቫይረስ ወደ ምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ የመግባቱ ዕድል ዝቅተኛ መሆኑ (‹በኢቦላ ከሚያዝ ሰው የአይሮፕላን ቲኬት የመግዛት አቅም ያለው ጥቂቱ ነው› የተባለበትን ጆርናል ምንጭ በመጀመሪያው ጽሑፍ አቅርቤያለሁ።) ከተጻፈ ወር ሳይሞላ በተግባር ተስተባበለ። ይኸው በኢቦላ ቫይረስ በሽታ የተጠቁት አገሮች ስም ዝርዝር ውስጥ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ (ዩ፣ኤስ፣ኤ) ተመደበች፣ ስፔንም ተከተለች። ይህ መንገድ ሌሎች ብዙ አገሮችንና ሌሎች ጉዶችን እንደሚያሳየን ጥርጥር የለኝም። የኢቦላ ቫይረስ በሽታ ማከሚያ ቦታዎች እየተከፈቱ አንዳንዶቹ ደግሞ ግንባታቸው ከመሬት ገና ከፍ ባይልም ፎቶግራፎቻቸው የተስፋና የዓለም ምላሽ ቀርፋፋነት ምልክቶች ሆነው ታዩ። በበሽታው የሚያዙና የሚሞቱት ቁጥር ማደጉን አላቋረጠም። ከበሽታው ጋር ከመጀመሪያው ጀምሮ ሲፋጠጡ የከረሙት ድርጅቶችና መሪዎች እሪታ ቀጥሏል። ዶ/ር ጆዓንሉ የኤም፣ኤስ፣ኤፍ ዓለም አቀፍ ፕሬዚዳንት በሴፕቴምበር 25 ቀን 2014 ለተባበሩት መንግሥታት ድርጀት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ንግግር ሲያደርጉ በመጀመሪያው ዓረፍተ-ነገር ላይ እንዲህ ብለው ነበር፤ ‹‹ክቡራትና፣ ክቡራን፣ ለጋስ የዕርዳታ ቃል ኪዳኖችና ወደር የሌላቸው የተባበሩት መንግሥታት ውሳኔዎችን በደስታ እንቀበላለን። ነገር ግን አሁኑኑ ወደ ድርጊት የማይቀየሩ ከሆኑ የሚሰጡት ጥቅም እጅግ አነስተኛ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኦክቶበር 3 ቀን 2014 ባወጣው መግለጫ የቫይረሱ በሽታ መስፋፋት የዓለም ዓቀፍ ምላሹን በፍጥነት እየቀደመ መሆኑን አስታውቋል። የዋና ዋና ክስተቶች ቅደም ተከተል ዲሴምበር 2013 ወረርሽኙ በጊኒ ውስጥ ጀመረ። ማርች 23 ቀን 2014 የጊኒው የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ ለዓለም ጤና ድርጅት በኦፊሴል ተገለጠ። ማርች 30 ቀን 2014 ዓለም ጤና ድርጅት በላይቤሪያ ውስጥ የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽ መኖሩን አረጋገጠ። ሜይ 25 ቀን 2014 ሴራሊዮን የኢቦላ ቫይረስ በሽታ ወረርሽኝን ለዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀች። ጁላይ 25 ቀን 2014 ናይጄሪያ የመጀመሪያውን የኢቦላ በሽታ ተጠርጣሪን አስታወቀች። በኦገስት 8 ቀን 2014 ዓለም ጤና ድረጅት የኢቦላ ቫይረስ በሽታ ዓለም ዓቀፍ ትኩረት የሚያስፈልገው አጣዳፊ የሕዝብ ጤና ሁኔታ እንደሆነ አወጀ። ኦገስት 29 ቀን 2014 ሴኒጋል የመጀመሪያውን የኢቦላ ቫይረስ በሽተኛ አስታወቀች። ሴፕቴምበር 30 ቀን 2014 በተባበሩት የአሜሪካ መንግስታት (ዩ፣ኤስ፣ኤ) ውስጥ በቴክሳስ ስቴት የጀመሪያው የኢቦላ ቫይረስ በሽተኛ ታወቀ። ኦክቶበር 6 ቀን 2014 ከአፍሪካ ውጪ የመጀመሪያው ነው የተባለለት የስፔይን የነርስ ረዳት በኢቦላ መያዝ በአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ተገለፀ። ኦክቶበር 8 ቀን 2014 በአሜሪካ ዳላስ ከተማ ውስጥ ሕክምና ሲደረግለት የቆየው ከላይቤሪያ የመጀመሪያውን የኢቦላ ቫይረስ በሽታ ያመጣው ሰው ሕይወቱ አለፈ። ኦክቶበር 12 ቀን 2014 በአሜሪካ ዳላስ ሆስፒታል የሚሠራና በኦክቶበር 8 ቀን 2014 እዚያ ሆስፒታል በኢቦላ ቫይረስ በሽታ ሕይወቱ ላለፈው የኢቦላ ቫይረስ በሽተኛ ሕክምና የሰጠች ነርስ በኢቦላ ቫይረስ በሽታ መያዟን የመጀመሪያ ምርመራ እንዳሳየ የቴክሳስ የጤና ዲፓርትመንት አስታወቀ። ተጨማሪ ምርመራ በተከታይ ተደርጎ በሽታው ተረጋግጧል። እስካሁን የተጠቁ አገሮች እንደወረርሽኙ ክፋት ከባሰው ወደ ቀለለው ቅደም ተከተል 1 -ላይቤሪያ 2- ጊኒ 3- ሴራሊዮን 4- ናይጄሪያ፣ 5- ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ (ዩ፣ኤስ፣ኤ) 6- ስፔይን 7-ሴ ኔጋል አዲስ አስፈሪ ቁጥሮች በቅርቡ ሁለት ትንተናዎች ወጥተው እጅግ አስፈሪ ቁጥሮችን አሳይተዋል። አንደኛው ከአሜሪካው የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል (ሲ፣ዲ.ሲ) በሳምንታዊ ሕመምና ሞት ዘገባ (ኤም፣ኤም፣ደብልዩ፣አር) በሴፕቴምበር 23 ቀን 2014 ታትሞ የወጣው ሲሆን ሁለተኛው በዓለም ጤና ድርጅት የኢቦላ ምላሽ ቡድን በኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ ሜዲሲን (ኤን፣ኢ፣ጄ፣ኤም) ውስጥ በሴፕቴምበር 23 ቀን 2014 ታትሞ የቀረበው ነው። ምን ያህል ሰው ታሟል፣ ወደፊትስ ይታመማል? በላይቤሪያና በሴራሊዮን ብቻ የቫይረሱን በሽታ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ርብርቦሽ ካልተደረገ በጃኑዋሪ 15 ቀን 2015 ግድም 1,400000 (አንድ ሚሊዮን አራት መቶ ሺ) ሰዎች በበሽታው ሊያዙ እንደሚችሉ በአሜሪካው የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከያ ጥናት ተደግፎ ቀርቧል። በሳምንታዊ የሕመምና ሞት ዘገባ ዊክሊ ሞርቢዲቲ ኤንድ ሞርታሊቲ ረፖርት ውስጥ እንደተብራራው፣ የተጠቆመው አደገኛ የበሽታው መስፋፋት ሊመጣ የሚችለው የዓለም ዓቀፉ ምላሽ እንዲህ በዝቅተኝነት ከቀጠለ ብቻ ነው። ለዚህ ግምት የደረሱባቸውን ምክንያቶችና ስሌቶች ዘርዝረዋል። የወረርሽኙ እጥፍ መሆን (ደብሊንግታይም- የአዳዲስ በሽተኞች ቁጥር እጥፍ የሚሆንበት ጊዜ) በአማካይ ሃያ ቀን እንደሆነ አሳይተዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ መሠረታዊ የመራቢያ ቁጥርና (ቤዚክሪፕሮዳክሽን ነምበር) የተጣራ የመራቢያ ቁጥር (ኔትሪ ፕሮዳክሽን ነምበር) ግምት ውስጥ አስገብተዋል። ያም ሆነ ይህ ፍሬ ነገሩ ዓለም ተባብሮ ይህንን ወረርሽ ካልተቆጣጠረው ስብስቦሹ ከምዕራብ አፍሪካ አልፎ ለሁላችንም እንደሚሆን ነው። ከታመመው ከመቶ ስንቱ ይሞታል? በቅርቡ የወጡት ትንተናዎች እንደሚያሳዩት፣ ከታመሙት ውስጥ የሞት ዕድል የሚያገኛቸው ዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው 53 በመቶ ገደማ ሳይሆን 70.8 በመቶ ገደማ ነው። ለዚህ ግድፈት ምክንያት የሆነው በሽታቸው ታውቆ ሰዎች ከተቆጠሩ በኋላ ይሙቱ ይዳኑ በሚታወቅበት ጊዜ መሀል ያለው ዝግየታ ነው ተብሏል፡፡ ዓለም ጤና ድርጅት በድረ-ገፁ ላይ 47 በመቶ ሕሙማን ይተርፋሉ የሚለውን ማስተማሪያ አንስቶታል። ይበልጥ ተጠቂ የዕድሜ ክልል በኢቦላ ቫይረስ በሽታ ከተያዙት አብዛኛዎቹ (60.8 በመቶ) በ15 እና 44 ዕድሜ መሀል ያሉ ናቸው። በዚህ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ከጠቅላላው ሕዝብ 44 በመቶ ግድም ናቸው ተብሏል። የወንዶችና ሴቶች በበሽታው የመያዝ ክፍፍል ከዚህ ቀደም እንደሚነገረው ከጤና ባለሙያዎች ውጪ የሴቶች ይበልጥ በበሽታው መያዝ ይታመን ነበር። አሁን ግን አዳዲሶቹ ጥናቶች የሚያሳዩት በወንዶችና ሴቶች መሀል ልዩነት እንደሌለ ነው። የበሽታው መገለጫዎች ከቀድሞ ወረርሽኞች ጋር ሲወዳደሩ ተመሳሳይነት አላቸው። ደም አፍሳሽነት፣ በዚህ ወረርሽኝ ውስጥ ከወትሮው ዝቅ ባለ ተከስቷል። ትኩሳት (87.1 በመቶ)፣ ድካም (ፋቲግ-76.4 በመቶ)፣ ምግብ ማስጠላት (64.5 በመቶ)፣ ትውከት (67.6 በመቶ)፣ ተቅማጥ (65.6 በመቶ) ራስ ምታት (53.4 በመቶ)፣ ሆድ ሕመም (44.3 በመቶ) ለኢቦላ ቫይረስ በሽታ መለያ የሆነ ደም አፍሳሽነት ምልክት የታየው ከ1 በመቶ በታች እስከ 5.7 በመቶ ብቻ ሲሆን ምክንያቱ ሊገለጥ ያልቻለ መድማት ደግሞ በ18.0 በመቶ በሽተኞች ውስጥ ታይቷል። የኢቦላ ቫይረስ ሕይወት በሌላቸው ነገሮች ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ይቆያል? የአሜሪካ በሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል ድረ-ገፅ አንድ ጥናትን ጠቅሶ የሚጠቁመው ቫይረሱ በሚመቸው አካባቢ እስከ ስድስት ቀናት መቆየት እንደሚችል ነው። ነገር ግን በዚህ ጉዳይ የተደረጉ ጥናቶች በጣም ጥቂት ናቸው። ቢሆንም ፋይሎ ቫይረሶች (ኢቦላና ማርበርግ) በደም ውስጥ ለሳምንታት ሊቆዩ እንደሚችሉና በተበከሉ ዕቃዎች ላይ ለመሰንበት ብቃት እንዳላቸው ይታወቃል። ይህ ይበልጥ የሚሆነው በቀዝቃዛ አካባቢዎች (አራት ዲግሪ ሴንቲግሬድ) ውስጥ ነው ተብሏል። አንድ ጥናት፣ በአማካይ የክፍል ሙቀት ውስጥ ኢቦላ ቫይረስን ሊያገኝ እንዳልቻለ ተገልጿል። በማጥኛ አካል ናሙናዎች ውስጥ በአራት ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት ላይ እስከ 50 ቀናት እንደሚቆይ ተዘግቧል። ስለ ጤና ሙያተኞች በበሽታው የመያዝ አደጋ የኢቦላ ቫይረስ በሽታ ከተቀሰቀሰበት እ.ኤ.አ. ከ1976 ጀምሮ የጤና ሙያተኞች ጠር ሆኖ ቆይቷል። አሁንም ወደ አሜሪካና ምዕራብ አውሮፓ ጎራ ባለበት ጊዜም ይኸው ክፋቱ ቀጥሎ አንድ ሁለት በሽተኛ ያከሙ፣ ቫይረሱን ያጠለቁት ዘመናዊው የመከላከያ ትጥቅ ሳይበግረው የጤና ሙያተኞችን መያዙ አስደንጋጭነቱን ይበልጥ አጉልቶታል። በጣም የሚያሳዝነው ነገር ይህ መቀጠሉ የማይቀር መሆኑ ነው። ፀረ-ብከላና (ዲስ ኢንፌክታንት) ጨረሮች የኢቦላን ቫይረስ ሊያጠፉ የሚችሉ ኬሚካሎች ብዙ ናቸው። ሦስት በመቶ አሰቲክ አሲድ፣ አንድ በመቶ ግሉተራል ደሃይድ፣ አልኮል መሠረትነት ያላቸው ምርቶች፣ 5.25 በመቶ የቤት ብሊች (ሶዲየም ሃይድሮ ችሎራይት) ብሊች ዱቄት (ካልሲየም ሃይፖክሎራይትን) ይጨምራሉ። የኢቦላ ቫይረስ ከ30 ደቂቃ እስከ 60 ደቂቃ በ60 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ለአምስት ደቂቃ በማቆየትና በጋማ ጨረርና አንድ በመቶ ግሉታራል ደሃይድ በጋራ ሆነው ሊያጠፉት እንደሚችሉ ይታወቃል። እንዲሁም አልትራ ቫዮሌት ጨረር በበቂ ካገኘው ሊያጠፋው እንደሚችል በጥናት ይታወቃል። በሰውነት ፈሳሾች ወይም ከቁሳቁሶች የኢቦላ ቫይረስ በሽታ የመተላለፉ መጠን ክዚህ ቀደም ከተደረጉ ጥናቶች ውስጥ በአብዛኛው የሚጠቀሰው በ2000 በዩጋንዳ ጉሉ አካባቢ በሽተኛ ማግለያ ክፍሎች ውስጥ የተደረገው ጥናት ነው። ማግለያው ክፍል ወለል በየቀኑ በ0.5 በመቶ ብሊች ከመፅዳቱ በተጨማሪ ማናቸውም የሚታይ ነገር በተጨማሪ በብሊች እንዳስፈላጊነቱ እየተፀዳ ነበር። በዚህ ጥናት የተገኘው በኬሚካሎች የተፀዱ ማግለያ ቤቶች ውስጥ ቫይረሱን መቆጣጠር እንደሚቻል እንጂ በሌላ ስፍራዎች ያለውን ሁኔታ አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ ይህ ጥናት በጥራዝ ነጠቅነት ወይም ሆነ ተብሎ እየተጠቀሰ ቫይረሱ በቀላሉ ሊተላለፍ እንደማይችል ሲፃፍ ይነበባል። ስለ ክትባቶች ብዙ ክትባቶች በሙከራ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ዓለም ጤና ድርጅት ይበልጥ ተስፋ የጣለባቸው ሁለት የክትባት ዕጩዎች አሉ። ሁለቱም በቅድመ-ፈቃድ ማግኘት ሙከራ የመጀመሪያው ደረጃ ላይ (phase 1 pre-licensure clinical trials) ይገኛሉ። አንደኛው (cAd3-ZEBOV) ከዝንጀሮ የተገኘ አዲኖ ቫይረስ ተሸካሚነት የኢቦላ ቫይረስን ጂን በማስገባት የሚሠራ ሲሆን፣ ሁለተኛው (rVSV-ZEBOV) የሚጠቀመው የተመረዙ ወይም የደከሙ ከብቶችን የሚያሳምም ቬዚኩላር ስቶማቲቲስ ቫይረስ የሚባለውን ሲሆን አንዱን ጂኑን በኢቦላ ቫይረስ ጂን በመተካት ነው። ሙከራ ላይ ያሉ ፀረ-ኢቦላ ቫይረስ መድኃኒቶች በጥናት ላይ ከሚገኙት ፀረ-ኢቦላ መድኃኒቶች ይበልጥ የሚታወቀው ዝማፕ (Zmapp) የተሰኘው ነው። መድኃኒቱ የሦስት ሞኖክሎናል አንቲቦዲስ የሚባሉ ፀረ-አካሎች ቅንብር ሲሆን የሚሠራው የኢቦላ ቫይረስ ፕሮቲን ላይ በመጣበቅ ነው። ይህ መድኃኒት ምንጩ ፀረ-አካል ቢሆንም የሚሠራው እንደ ክትባት ሳይሆን እንደመፈወሻ ነው። ለአገጋሚ ሕክምናዎች (ኮንቫለሰንትቴራፒስ) ዓለም ጤና ድርጅት ከሴፕቴምበር 4 እስከ 5 ባደርገው የተመራማሪዎች ስብሰባ ዕጩ ክትባቶችና ሙከራ ላይ ያሉ ሕክምናዎችን በተመለከተ መክሮ ነበር። በኢቦላ ቫይረስ በሽታ ተይዘው ከዳኑ ሰዎች የሚገኘው ያገጋሚ ሙሉ ደምና ፕላዝማ ትኩረት ከተሰጣቸው ዋናዎቹ ሕክምናዎች ውስጥ ነበሩ። በእነዚህ ሕክምናዎች ላይ ያለው ጥናትና ተሞክሮ ውሱን መሆኑ ይታወቃል። ያገጋሚ ሕክምና በኢቦላ ቫይረስ በሽታ ላይ በመጀመሪያ ጊዜ የተሞከረው በዛየር (አሁን የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ) በ1976 ማለትም የቫይረሱ የመጀመሪያ ወረርሽኝ የተነሳበት ጊዜ ሲሆን ለአንድ የታመመች ሴት ኢቦላን መሰል ከሆነ በሌላ ደም አፍሳሽ ቫይረስ (ማርበርግ ቫይረስ) ተይዞ ከዳነ ሰው የተገኘ ፕላዝማ ተሰጥቷት ነበር። ሴትዬዋ አንዳንድ የመሻል ምልክቶች ብታሳይም ከመሞት አልተረፈችም ነበር። በ1995 በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ኪክዊት በተነሳው ወረርሽኝ ጊዜ ከበሽታው ከዳኑ ሰዎች የተገኘ ሙሉ ደም ለስምንት ሰዎች ተሰጥቶ ሰባቱ ተርፈው ነበር። ቢሆንም ጥናቱ መቆጣጠሪያ ቡድን (ኮንትሮል ግሩፕ) ስላልነበረው ሕክምናው ብቻ ይህን ውጤት ያምጣ ወይም አያምጣ በእርግጥ አይታወቅም። ነገር ግን ጥቅም እንደነበረው አሌ አይባልም። በአሁኑም ወረርሺኝ ጊዜ ሕክምናው ለጥቂት ሰዎች ተሰጥቷል፣ እየተሰጠም ነው። ያም ሆነ ይህ፣ ከበሽተኛው የዳነ ሰውን ለታማሚ ደም መስጠት ብዙ ትኩረት እየተደረገበት ቢሆንም አሁንም በሙከራ ደረጃ ላይ ያለ ብቻ ነው። የኢቦላ ቫይረስ በሽታ የመተላለፍ ችሎታ አንዳንድ ሰዎች ሲናገሩና ሲጽፉ የኢቦላ ቫይረስ የመተላለፍ ዕድሉ ዝቅተኛ እንደሆነ ይገልፃሉ። ሕዝቡንና ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ከሚደረግ ጥረት እንደሆነ መገመት ይቻላል። ቢሆንም ትክክል ያለሆነና ዘላቂ ጥቅም የሌለው ልፋት ነው። ወደ ሌሎች አገሮች የመስፋፋቱ አደጋ በአሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘውን የኢቦላ ቫይረስ በሽተኛ ዜና የአሜሪካ በሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ማዕከልና የቴክሳስ ሕዝብ ጤና ዲፓርትመንት በሴፕቴምበር 30 ቀን 2014 አስታውቀው ዜናው በዓለም በሙሉ ተሰራጭቷል። ሰውዬው የተነሳው በምዕራብ አፍሪካ የኢቦላ ቫይረስ እጅግ ከተጠቁት አገሮች አንዷ ከሆነችው ከላይቤሪያ ሲሆን ሴፕቴምበር 19 ቀን ከላይቤሪያ ተነስቶ ሴፕቴምበር 20 ቀን አሜሪካ ገብቶ፣ በአራተኛው ቀን ሴፕቴምበር 24 ቀን እንደታመመ ተገልጧል። በጉዞው ላይ የበሽታው ምንም ምልክቶች አልነበረውም ማለት ነው። ሴፕቴምበር 26 ቀን የጤና እንክብካቤ በቴክሳስ ሄልዝ ፕሬስስ ቢተሪያን ሆስፒታል ጀምሮ በሴፕቴምበር 28 ቀን 2014 በሆስፒታል ውስጥ እንዲተኛ ተደርጓል። በሴፕቴምበር 30 ቀን 2014 የሰውዬው ደም ናሙና በበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል ተመርምሮ በኢቦላ ቫይረስ በሽታ መያዙ ተረጋግጧል። ይህ የአሜሪካ የዜና መገናኛ አውታሮች በድንገት አንቅቷል። ሁለት ሦስት፣ ወይም አራት ስድስት፣ ወይም ስምንት አስራ ሁለት፣ ወይም አስራ ስድስት ሃያ አራት፣ ወይም…. ቁጥሮች ሲመጡ የሚሆነውን አሁን ማንም ሊያውቅ አይችልም። በሌሎች አገሮችም እንደዚሁ ቀስ በቀስ መታየት ሲጀምር የተነገረለትን የጤና አውታር ጥንካሬ ይፈትናል። ቢሆንም አሁንም ዞሮ ዞሮ እጅግ ከፍተኛው አደጋ የሚኖረው የጤና ሥርዓቶቻቸው ባልዳበሩ አግሮች በሚገባበት ጊዜ ነው። የአሜሪካ የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል የኢቦላ ቫይረስ በሽታን አስመልክቶ የሚሰጡ ምክሮችን ደረጃ አውጥቷል። ሀ) ደረጃ 3 – ወደ ላይቤሪያ፣ ጊኒና ሴራሊዮን አስፈላጊ ያልሆኑ ጉዞዎች እንዳያደርጉና ራሳቸውንም በኢቦላ ቫይረስ በሽታ ከታመሙ ሰዎች የአካል ፈሳሾች እንዲጠብቁ ያስጠነቅቃል። ለ) ደረጃ 2-ወደ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ የሚጓዙ ሰዎች ተጨማሪ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያሳስባል። ሐ) ደረጃ 1- ወደ ናይጄሪያ የሚጓዙ በማስተዋል እንዲጓዙ ይመከራል። በተጨማሪም ከኦክቶበር 8 ቀን 2014 ወረርሽኙ ካጠቃቸው አገሮች ወደ አሜሪካ ከሚያስገቡት 94 በመቶ የሚሆኑትን ሰዎች በሚቀበሉት 5 አየር ጣቢዎች የተጠናከረ የኢቦላ ቫይረስ ምርመራ ተጀምሯል። ምንም እንኳ አንዳንድ አገሮች የበረራ ዕገዳዎችን ዕርምጃ ቢወስዱም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ዓለም ጤና ድርጅትና ሌሎችም ታዋቂ ድርጅቶች የወሰዱት አቋም ማናቸውም የመገናኛና የበረራዎች ዕገዳዎችን ማድረግ በመቃወም ነው። በዚህ ላይ ያለው አቋም በሚገርም ሁኔታ አንድ ወጥ የሆነና ለየት ያለ ሐሳብ ሲነገር አይሰማም፤ ወይም ተፅፎ አይነበብም። ትልቁ መከራከሪያ ገደብ መጣል የዓለም አቀፉን የኢቦላ ምላሽ ያስተጓጉላል ነው። ካለው አደጋ አንፃር የሚታየው የዓለም አቀፍ ምላሽ እጅግ ደካማ ሆኖ ሳለ ይህንኑ ደግሞ ለምክንያትነት መጠቀሙ ላይ ያለው የአስተሳሰብ ውህደት እንዴት እንደሆነ ማሰብ ያስፈልጋል። የአገሩን ብሔራዊ ደኅንነት የመጠበቅ የመጀመሪያው ኃላፊነት የየአገሩ መንግሥት ነው። መደምደሚያ ያለው ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን ይበልጥ እየከፋና እየተስፋፋ እየሄደ ነው። የኢቦላ ቫይረስ በሽታ እስከዚህ ድረስ ሊዛመት የቻለበት ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም ከሁሉ በቅድሚያ መጠቀስ ያለበት የዓለም-አቀፍ ምላሹ እጅግ ዝቅተኛና እጅግ ቀርፋፋ መሆኑ ነው። በተጨማሪም ቀና ሐሳቡ ቢኖር በአጭር ጊዜ መለወጥም የሚቻለው ይህን ነው። ነገሩማ ድሮም ቢሆን ወደ ደሃ አገሮች መግባት የሚያስፈልገው ዕርዳታ የሚገባው እጅግ ተንቀራፎ እንደሆነ ይታወቃል። ለምሳሌ ፔፕፋር የተባለውን ትልቁን የዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ መንግሥት ዕርዳታ ብንወስድ የደረሰው የኤች፣አይ፣ቪ /ኤይድስ ቫይረስ በሽታ ከታወቀና ውጤታማ ሕክምናው ከተጠናከረ ከብዙ ዓመታት በኋላ ነበር። በዚህ መሀል ያለዕርዳታ የረገፈውን ሰው የሚቆጥረው የጎደለበት ቤቱ ብቻ ነው። ስለ ኢቦላ ቫይረስ የሰሞኑ የታዋቂ ዜና አውታሮች ትኩረት ወደ አደጉ አገሮች መግባቱ ላይ ቢሆንም፤ ማንም ሊያውቀው እንደሚችለው ወይም እንደሚገባው እጅግ አስፈሪው አደጋ ወደ ደሃ አገሮች የመግባቱና የመስፋፋቱ አደጋና የሚከተሉት መዘዞች ናቸው። የየአገሩን ዘላቂ ደኅንነትና ህልውና የመጠበቁ ኃላፊነት በመጀመሪያ ደረጃ የየአገሩ በተለይም የየመንግሥታቱ ሲሆን ይህም ኃላፊነት እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ ሌላም ተጠያቂነት ያለበት ነው። በሌላ በኩል የትኛውም ኅብረተሰብ አባል የግሉን ማድረግ መጀመር ካለበት ቆየት ብሏል። የሚያሳስበው የውጪ ዕርዳታ እያልን ስናንቀላፋ ከነጭራሹ በዛው እንዳንጠፋ ነው። ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...