Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልድሬ ቲዩብ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር በሮያሊቲ ለመሥራት መዋቅር ዘረጋ

ድሬ ቲዩብ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር በሮያሊቲ ለመሥራት መዋቅር ዘረጋ

ቀን:

ድሬ ቲዩብ የተመሠረተበትን ስድስተኛ ዓመት ሲያከብር ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሚሰነዘረውን የኮፒ ራይት ጥያቄ ለመመለስ፣ በሮያሊቲ ክፍያ ሕግ ለመሥራት መዋቅር መዘርጋቱን አስታወቀ፡፡ የድረ ገጹ መሥራች አቶ ቢኒያም ነገሱ፣ ያለ ባለሙያዎች ፈቃድ የሚጫኑ ፊልሞችም ይሁን ሌሎች ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ባለሙያውን ጥቅም እያሳጡ መሆኑን በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ድሬ ቲዩብ ከፊልም ሠሪዎች ጋር በመስማማት ሁለቱም እየተጠቀሙ ለተመልካች ጥበባዊ ሥራዎች በድረ ገጽ የሚተላለፉበትን መንገድ እያመቻቸን ነው፤›› ብሏል፡፡ የሮያሊቲ ክፍያ ሕግን መሠረት በማድረግ ድሬ ቲዩብ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከድረ ገጹና ከዩ ቲዩብ ጋር የሚሠሩበትን መንገድ አዘጋጅቷል፡፡ አሠራሩ ማንኛውም ሰው የኪነ ጥበብ ሥራዎቹ በድሬ ቲዩብ እንዲተላለፉለት ሲፈልግ ከድሬ ቲዩብ ጋር ተስማምቶ የተጠቃሚ አካውንት ይሰጠዋል፡፡ በድረ ገጹ የተለቀቀውን ቪዲዮ በተመለከቱት ሰዎች ቁጥር በየሦስት ወሩ ባሙያው ይከፋለውና የተቀረውን ዩ ቲዩብና ድሬ ቲዩብ ይወስዳሉ፡፡ ቪዲዮዎች ሲጫኑ ተመልካች እንዲኖራቸው ዩ ቲዩብ ማስታወቂያ ይሠራላቸዋል፤ ከዚህ በተጨማሪም ባለሙያዎች ባለቤትነት ይኖራቸዋል፡፡ አሠራሩ ባለሙያዎች በሕጋዊ መንገድ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ይሆናል የሚሉት አቶ ቢኒያም፣ ማንኛውም በዘርፉ ያለ ባለሙያ ቢጠቀምበት መልካም እንደሆነም ይናራሉ፡፡ ድሬ ቲዩብ ኪነ ጥበባዊ ይዘት ያላቸውንና በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከወኑ አዳዲስ መረጃዎችን በድምፅ፣ ጽሑፍና ቪዲዮ እያቀረበ ላለፉት ስድስት ዓመታት ቆይቷል፡፡ ድሬ ቲዩብ፣ ስድስተኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ታኅሣሥ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ሸራተን አዲስ ሆቴል ባከበረበት ዕለት እንደተገለጸው፣ ድረ ገጹ የሚለቀውን ክንውኖችና ጥበባዊ ሥራዎች የሚከታተሉ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ ድረ ገፁ በአሁኑ ወቅት በቀን ወደ 150 ሺሕ ጎብኝዎች አሉት፡፡ ድረ ገጹን የሚጎበኙ በኢትዮጵያ 33 በመቶ፣ ሰሜን አሜሪካ 25 በመቶ፣ እንግሊዝና የዓረብ አገሮች 28 በመቶ፣ ካናዳ አምስት በመቶ፣ ኖርዌይ አራት በመቶና ኢንዶኔዥያ ሦስት በመቶ ደርሰዋል፡፡ የድረ ገጹን ምሥረታ በማስመልከት ድርጅቱ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን አወዳድሮ ሽልማት ሰጥቷል፡፡ ሽልማቱ 14 ዘርፎችን ያካተተ ነበር፡፡ በሙዚቃ፣ ቪዲዮ ክሊፕ፣ ግጥምና ዜማ እንዲሁም የቴሌቪዥንና የሬዲዮ መርሐ ግብሮች ከመወዳደሪያዎቹ ጥቂቱ ናቸው፡፡ አቶ ቢንያም እንደተናገሩት፣ ለየዘርፉ ከቀረቡት ዕጩዎች አሸናፊዎቹን ለመለየት 80 በመቶ በተመልካችና የተቀረው በዳኞች ምርጫ የተወሰነ ነው፡፡ በየዘርፉ ለቀረቡ ዕጩዎች ድምፅ የተሰጠውም በድረ ገጽ ነበር፡፡ አቶ ቢኒያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ውድድሩ ውስጥ የተካተቱ ዕጩዎች የተመረጡት ድረ ገጹ ላይ የበለጠ ተመልካች ያላቸው ናቸው፡፡ ብዙ ተመልካች ያፈሩት ለውድድር ቀርበው ከመካከላቸው የበለጠ ድምፅ የተሰጣቸው አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ምርጫው ውስጥ የገቡ ዕጩዎች በሙያው ካስቆጠሩት ጊዜና ከሠሯቸው ሥራዎች አንፃር እኩል ለውድድር መቅረብ አልነበረባቸውም የሚል አስተያየት የሰነዘሩ ነበሩ፡፡ እንደ አቶ ቢኒያም ምላሽ፣ አንጋፋ ባለሙያዎች ከጀማሪዎች ጋር መቅረባቸው ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ የውድድር ኮሚቴው ግን ለኢንተርኔት ተጠቃሚው የቀረቡና የበለጠ ተመልካች ያገኙት ላይ አተኩሯል ብለዋል፡፡ ለዕጩዎቹ ድምፅ ከሰጡ አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት ውጪ አገር የሚገኙ ተመልካቾች መሆናቸው ሌላው ምክንያት ነው፡፡ እንደ አቶ ቢኒያም፣ ከኢትዮጵያ ውጪ ላለው ሰው በድረ ገጽ ተደራሽ መሆን የቻሉ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ብቻ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ምርጫው የተካሄደው በ192 አገር ባሉ ኢትዮጵያውያን ነው ያሉት አቶ ቢኒያም፣ ውድድሩ በድረ ገጽ በቀረቡ ሥራዎች ላይ ማተኮሩ ምናልባትም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን በኢንተርኔት ተደራሽ እንዲያደርጉ የሚያበረታታ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ በኢንተርኔት ተጠቃሚው ምልከታ ላይ ብቻ ሲተኮር አንጋፋና አማተሮች በአንድ ቡድን ገብተው ያልተጠበቀው ባለሙያ ሊያሸንፍ የሚችልበት ዕድል አለ የሚሉት አቶ ቢኒያም፣ በቀጣይ የሚኖረው አካሄድ በየዓመቱ እንደሚቋቋመው ኮሚቴ የሚወሰን እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በሙዚቃ ከነበሩት ዘርፎች የሕይወት ዘመን ሽልማት አንዱ ሲሆን፣ በዕጩነት ከቀረቡት አሊ ቢራ፣ ሙላቱ አስታጥቄ፣ መሐሙድ አህመድ፣ ጌታቸው መኩሪያ ዓለማየሁ እሸቴና አስቴር አወቀ ሲሆኑ፣ አስቴር አሸንፋለች፡፡ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውና ስሜት ቀስቃሽ ዘፈኖች በሚለው ዘርፍ የጋሽ አበራ ሞላ (ስለሺ ደምሴ) ‹‹ያምራል ሀገሬ›› አልበም ላይ ያለው ‹‹ያምራል ሀገሬ›› አሸናፊ ሆኗል፡፡ ዕጩዎቹ የየኛ (ጣይቱ)፣ አዲስ ሙላት (ቼ በለው)፣ ቴዲ አፍሮ (ጥቁር ሰው)፣ ዘለቀ ገሠሠ (ሀገሬ) እና የጃኪ ጎሲና ቴዲማን (ፍም እሳት) ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለዓለም ያስተዋወቁ ሌላው ዘርፍ ሲሆን፣ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ፣ መሐሙድ አህመድ፣ ሙላቱ አስታጥቄ፣ ተሾመ ምትኩ፣ ግርማ ይፍራሸዋ፣ ምንይሹ ክፍሌና ሳሙኤል ይርጋ ታጭተዋል፡፡ ከሰባቱ ዕጩዎች ሙላቱ አስታጥቄ አሸንፏል፡፡ የምንጊዜም የዘፈን ግጥም ደራሲና የምንጊዜም የዜማ ደራሲ በተሰኙት ዘርፎች ይልማ ገብረአብ (በግጥም) አበበ መለሰ (በዜማ) አሸናፊ ሆነዋል፡፡ በግጥም ዘርፍ ተወዳዳሪ የነበሩት ፀጋዬ ደቦጭ፣ አብርሃም ወልዴ፣ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)፣ ቴዲ አፍሮና ሐብታሙ ቦጋለ የታጩ ሲሆን፣ በዜማ ነዋይ ደበበ፣ አበበ ብርሃኑ፣ ቴዲ አፍሮ፣ ሞገሥ ተካ፣ አቤል ሙሉጌታ፣ ጌታነህ መናና ጎሳዬ ተስፋዬ ተካተዋል፡፡ በርካታ ዕጩዎች ያሉት ባህል ዘመናዊ የሙዚቃ ቪዲዮ ዘርፍ ነበር፡፡ አብርሃም በላይነህ፣ መስፍን በቀለ፣ ጃኪ ጎሲ፣ ኤደን ገብረሥላሴ፣ ተመስገን ገብረእግዚአብሔር፣ አቤል ሙሉጌታ፣ ሚሌ ዋሴ፣ ታደለ ሮባ፣ ሚኪያስ ቸርነት፣ በኃይሉ ካሳሁን፣ ቢኒ ላስታ፣ ወንዴ ማክና እመቤት ነጋሲ መካከል ጃኪ ጎሲ በ‹‹ፊያሜታ›› ለማሸነፍ ችሏል፡፡ በምርጥ የዘመናዊ የሙዚቃ ክሊፕ ዘርፍ ሸዋንዳኝ ኃይሉ ዕጩ ከነበሩት ከታደለ ገመቹ፣ ራስ ብሩክ፣ ማይክ ሶሎ፣ ዚጊ ታፈሰ፣ ሲያምረኝ ተሾመና ኃይሌ ሩትስ መካከል አሸናፊ ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ ምርጥ የሙዚቃ ክሊፕ አዘጋጅ በተሰኘ ዘርፍ አይዳ አሸናፊ፣ ስንታየሁ ሲሳይ፣ ቴድሮስ ተስፋዬ፣ አብርሃም ወልዴና ቴድሮስ ጫላ ተወዳድረው ስንታየሁ ሲሳይ አሸንፏል፡፡ ምርጥ የሙዚቃ ክሊፕ ኬሮግራፈር ተብሎ የተሸለመው ደግሞ አብዮት ደመቀ ነው፡፡ በዘርፉ ሜሮን ፀጋዬ፣ ልጅ ተመስገንና ያዕቆብ ዓለማየሁ ታጭተው ነበር፡፡ ሌላው ምርጥ የሙዚቃ ሐያሲ ዘርፍ ነበር፡፡ ለዕጩነት የቀረቡት ሰርፀ ፍሬስብሀት፣ ተስፋዬ አበበ፣ ዳግማዊ ዓሊ፣ አብርሃም ወልዴ፣ ሱልጣን ሩሪ (ሶፊ)ና አረጋኽኝ ወራሽ ሲሆኑ፣ አብርሃም ወልዴ አሸንፏል፡፡ የቴሌቪዥን ቶክ ሾውና ድራማ ከመወዳደሪያ ዘርፎች መካከል ይገኙበታል፡፡ ከዕጩዎቹ ከአርሒቡ፣ እንጨዋወት፣ ዓርአያ ሰብ፣ ሚት ኢቲቪና ጤናዎ በቤትዎ ጆሲ ኢን ዘ ሐውስ ሾው አሸንፏል፡፡ ከዳና፣ ጎረቤታሞቹና ቤቶች ጋር ታጭቶ የነበረው ሰው ለሰው ምርጥ ድራማ ተብሏል፡፡ ባላገሩ አይዶል፣ ኮካ ኮላ ሱፐር ስታርና ኢትዮ ታለንት ሾው ከተሰጥኦ ውድድሮች መካከል ተወዳድረው ባላገሩ አይዶል ለማሸነፍ ችሏል፡፡ ተወዳዳሪ ከነበሩት የሬዲዮ መርሐ ግብሮች ለዛ፣ አዲስ ጣእም፣ እንዳልክና ማህደር፣ ኢትዮፒካሊክ፣ ሰምና ወቅርና ታዲያስ አዲስ ውስጥ የቅዳሜ ጨዋታ አሸንፏል፡፡ የመጨረሻው ዘርፍ በብዛት የታየ የሙዚቃ ቪዲዮ ነው፡፡ በድረ ገጹ ላይ ከተጫነ አንስቶ ከሌሎች ቪዲዮዎች በበለጠ ተመልካች ያገኘው የነፃነት መለሰ ‹‹ባይ ባይ›› ሙዚቃ ለማሸነፍ ችሏል፡፡ እንደተገለጸው ዘፈኑን እስካሁን 325 ሺሕ ሰው ተመልክቶታል፡፡ በዕለቱ በተካሄደው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ አንዳንድ መስተጓጉሎች ነበሩ፡፡ በአንዳንድ ዘርፎች የነበሩ ዕጩዎች ስክሪን ላይ ሲቀርቡ ስክሪኑ ላይ የሚታየው የሌላ ዕጩ ስም ነበር፡፡ ለአሸናፊዎች ሽልማት እንዲያበረክቱ ወደ መድረክ ከተጠሩ እንግዶች መካከል ትክክል ባልሆነ የሥራ ድርሻ የተጠቀሱም ነበሩ፡፡ በአንድ የውድድር ዘርፍ ዕጩዎች ከተዘረዘሩ በኋላ አሸናፊ ተብሎ ወደ መድረክ የተጠራው በቀጣይ የነበረው ዘርፍ አሸናፊ ነበር፡፡ ለዕለቱ ዝግጅት ተገቢው ጥንቃቄ ተደርጓል ለማለት አያስደፍርም፡፡ የመድረኩ የድምፅ ጥራት ጉድለት ሌላው ነው፡፡ የመድረኩ አሠራር ማራኪና ሥነ ሥርዓቱን እንዲገልጽ ታልሞ የተዘጋጀ ቢሆንም የዕጩዎቹ ዝርዝር ከመድረኩ ምስል እንጂ ድምፅ አልባ መሆኑ ተመልካችን ያወከ ነበር፡፡ በዕለቱ ስለተከሰቱ ስህተቶች ያነጋገርናቸው አቶ ቢኒያም ‹‹አንዳድ የመርሐ ግብሩን አካሄዶች እንዲከታተሉ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካሎች ግዴታቸውን ባለመወጣታቸው የተፈጠረ ነው›› ብለዋል፡፡ አብዛኛው ሥራ ተሠርቶ ትንንሽ የተባሉና ለሚመለከታቸው ሰዎች የተሰጡ ሥራዎች በአግባቡ አለመሠራታቸው ስህተቱ ጎልቶ እንዲወጣ ማድረጉን እስማማበታለሁ የሚሉት አቶ ቢኒያም፣ በቀጣይ መሻሻል እንደሚኖር አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...