Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅያመጣል መንገድ ያስቀራል መንገድ ወሊሶ ከተማ መግቢያ አካባቢ ከጥቂት ወራት በፊት

ያመጣል መንገድ ያስቀራል መንገድ ወሊሶ ከተማ መግቢያ አካባቢ ከጥቂት ወራት በፊት

ቀን:

ፓስፖርት ተከልክዬ

ሳልሾም

ሳልሸለም

ሳልሰየም

መሬት ሳልገዛ

ቪላ ሳልሠራ

ኒሻን ሳላንጠለጥል

ጉቦ ሳልበላ

ለታሪክ ሳልሠራ፣

እንኳን አሽከር

ለማኝ ሳልገፈትር

ሳልበቃ ለማስገረፍ

ታላቆቼን ውስጥ እግር፣

ሳላስነቅል

አንዲት እንኳ የጣት ጥፍር፣

ሳልመቻች ለማቃጠር

ረሽኜ በድብቅ ሳልቀብር

በሙት እናት በሬዲዮ ሳልሸልል፣

ኢትዮጵያን ሳላስቀድም

ይዤ ሳልሸሽ ወርቅ ቀርቶ ብር

እንኳ ለፈረንጅ ለኢትዮጵያ ሳልሰልል

ሳይኖረኝ የሚያጋድል ያገር ፍቅር

ለኢትዮጵያዊነቴ ማን ሊመሰክር?

  • ሰለሞን ዴሬሳ፣ ዘበት እልፊቱ (1991 ዓ.ም.)

ወንፈል

በገጠሩ የአማራ ክልል ነዋሪዎች የሚዘወተሩና የተለመዱ፣ የተጻፈ ደንብና መመርያ ሳይኖራቸው በጋራ ስምምነትና በመረዳዳት ላይ የተመሠረቱ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፋይዳ ካላቸው ማኅበራት ወይም ተቋማት አንዱ ደቦ ወይም ወንፈል ነው፡፡ ወንፈል ወይም ደቦ አገር በቀልና ነባር የኅብረት ሥራ ማኅበር ነው፡፡

ደቦ እንደ እድርና እንደ እቁብ በተወሰኑ ቋሚ አባላት አይመሠረትም፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ወዳጅነትና ቀረቤታ ወይም ዝምድናና አግባብ ያላቸው ሰዎች አንድን በርከት ያለ የጉልበት ኃይል የሚጠይቅ ተግባር ለአንድ የማኅበረሰቡ አባል በጋራ የሚያከናውኑበት ተቋም ነው፡፡ በማኅበረሰብ አባላት መካከል ካለው መጠቃቀም አንፃር ደቦ ልዩ ልዩ መልኮችና አፈጻጸሞች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ከእነዚህ ዋና ዋናዎቹ መገለጫዎች፣ ደቦ እንደ ጉልበትና አገልግሎት ልውውጥ እንዲሁም እንደ ማኅበራዊ የጉልበት ድጋፍ አሰጣጥ ሥርዓት የሚኖረው ጠቀሜታዎች ናቸው፡፡

ደቦ እንደ ጉልበት ልውውጥ ሥርዓት በሚያገለግልበት ጊዜ ሰዎች ወረፋ ገብተው በቅደም ተከተል ለአንድ የቡድኑ አባል ጥቅም የሚሠሩበት ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በዚህ ሁኔታም ውስጥ እጅግ በጣም አድካሚና አሰልቺ የሆነውን የግብርና ሥራ በመተጋገዝና በመተባበር ለማከናወን ብዙ የሰው ኃይል በሚፈልጉ የሥራ ተግባራት አጨዳ፣ አረም ወዘተ የተወሰነ ቡድን በማቋቋም ወረፋ ገብተው ይሠራሉ፡፡ እያንዳንዱ የቡድኑ አባልም ለሌሎች አባላት የሰጠውን አገልግሎት በተመሳሳይ ሁኔታ ከእያንዳንዱ አባል መልሶ ስለሚጠይቅና ስለሚያገኘው ደቦ ማኅበራዊ የጉልበትና የአገልግሎት ልውውጥ ሥርዓት ተቋም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዓላማቸው በጋራ መሥራት ሆኖ የሴትና የወንድ ማኅበራት የሚቋቋሙበት ሁኔታ አለ፡፡ ወንዶች ብዛት ባላቸው ጥንድ በሬዎች መሬታቸውን ለማረስ፣ ለመዝራት፣ ቤት ለመሥራት፣ አጥር ለማጠር፣ ሰብል ለማረም ደቦ በመጥራት እርስ በእርስ ይጠቃቀማሉ፡፡ ሴቶች ደግሞ ጥጥ ለመፍተል፣ ቤት ሲሠራ ውኃ ለመቅዳት፣ የማኅበር፣ የሰንበቴ የሰርግ ድግስ ለመደገስ ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ማኅበሮችን በማቋቋም በኅብረት ይሠራሉ፡፡

ደቦ እንደ ማኅበራዊ መረዳጃ ተቋም በሚያገለግልበት ጊዜ በአባላቱ መካከል ከሚኖር እርስ በእርስ የጉልበትና የአገልግሎት ልውውጥ ይልቅ ለማኅበረሰብ አባላት ደኅንነትና ጥቅም ሲባል ግለሰቦች በፈቃዳቸው በአጸፌታው ምላሽ ሳይጠብቁ የሚያከናውኑት ማኅበረሰባዊ ነፃ አገልግሎት ይሆናል፡፡ ግለሰቦች ከማኅበረሰባቸው አባላት የጉልበት አገልግሎት የሚጠይቁባቸውና የሚያገኙባቸው ሁኔታዎች አያሌ ናቸው፡፡ እጅግ ከሚዘወተሩት ውስጥ አቅመ ደካሞች፣ በዕድሜ የገፉ አዛውንቶችና ባል የሌላቸው ሴቶች ቤታቸውን ለመጠገንና ለማደስ፣ አጥር ለማሳጠር፣ አረም ለማሳረም፣ ሰብል ለማሰባሰብ ወይም እነዚህን ለመሳሰሉት የኅብረት ሥራን ለሚጠይቁ ተግባራት ወዳጅ፣ ዘመድ፣ ጐረቤት ማኅበራዊ የነፃ ጉልበት አገልግሎቶች የሚሰጡባቸው ሁኔታዎች ይገኙበታል፡፡ ለዚህም ነው ወንፈል ወይም ደቦ ከኢኮኖሚ ጠቀሜታ ባሻገር ማኅበራዊ ፋይዳ አለው የሚባለው፡፡ ወንፈል ወይም ደቦ ሰዎች እምነታቸው፣ ቋንቋቸው፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ደረጃቸው ሳይገድባቸው በመረዳዳት የሚጠቃቀሙበት ነባርና አገር በቀል የቡድን ወይም የኅብረት ሥራ ማኅበር ነው፡፡  

– የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የአማራ ሕዝብ ባህልና ቋንቋ (2001 ዓ.ም.)

* * *

የህንድ መንግሥት መፀዳጃ ቤት አጠቃቀምን በሞባይልና ታብሌት ሊቆጣጠር ነው

የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በገጠሪቱ የህንድ ክፍል የሚኖሩ ህንዳውያን በአግባቡ መፀዳጃ ቤት እየተጠቀሙ መሆን አለመሆናቸውን መከታተል የሚያስችል ብሔራዊ የኢንተርኔት ፕሮግራም በይፋ መክፈታቸውን ሮይተርስ ከቀናት በፊት ዘግቧል፡፡

ከዚህ ወዲህ የመንግሥት ኃላፊዎች ሞባይል ስልክ፣ ታብሌትና አይፓድ በመጠቀም የገጠር ነዋሪዎች መፀዳጃ ቤት እየተጠቀሙ መሆን አለመሆናቸውን በኢንተርኔት ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት ጥናት እንደሚያመለክተው በህንድ የመፀዳጃ ቤት እጥረት አገሪቱን በዓመት ከሃምሳ ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስወጣታል፡፡ አገሪቱ በይበልጥ ለወጪ የምትዳረገው ከንፅህና ጉድለት ከሚመጡ በሽታዎች ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በጥቅሉ በዚህ ምክንያት ህንድ ከየትኞቹም የእስያ አገሮች ለከፍተኛ ወጪ የተዳረገች ናት፡፡

ጥናቱ በንፅፅር እንደሚያሳየው 626 ሚሊዮን ህንዳውያን የትም የሚፀዳዱ ሲሆን፣ በቻይና በተመሳሳይ መንገድ የሚፀዳዱ 14 ሚሊዮን ናቸው፡፡ በግንቦት ወር ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ ሞዲ በአገሪቱ በከፍተኛ የንፅህና ጉድለት የኅብረተሰብ ጤና እየተጐዳ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ይህን ከባድ የአገሪቱ ችግር በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ እንደሚፈቱትም ቃል ገብተዋል፡፡ ለዚህም የአገሪቱ መንግሥት የመፀዳጃ ቤት ግንባታ በጀቱን በእጥፍ ያሳደገ ሲሆን፣ ከትልልቅ ኩባንያዎችም የገንዘብ ድጋፍ መጠየቁ ሪፖርት ተደርጓል፡፡

ሞዲ ጥቅምት ወር ላይ የመንግሥት ኃላፊዎች በበዓል ቀን ከሥራ ገበታቸው ተገኝተው በየቢሯቸው የሚገኙ መፀዳጃ ቤቶችን እንዲያፀዱ ማድረጋቸው ኃላፊዎቹን አስቆጥቶ ነበር፡፡

* * *

ሚስቶች ባሎችን ደበደቡ

የሚስቶች በባሎቻቸው መደብደብ የተለመደ ወግ ነው፡፡ ከኡጋንዳ ሰሞኑን የወጣ መረጃ ደግሞ ሚስቶች ባሎቻቸውን ደበደቡ ሲል አስነብቧል፡፡ በኡጋንዳ ኢጋንጋ ከተማ ፆታዊ ጥቃትን አስመልክቶ በተደረገ ሕዝባዊ ውይይት ላይ እንደተገለጸው፣ በ2014 ብቻ 98 የሚጠጉ ባሎች በሚስቶቻቸው ተደብድበዋል፡፡ በኢጋንጋ ፖሊስ ጣቢያ የቤተሰብ ጥቃት ክፍል ኃላፊ በሆኑት ሚሊ ናብሪዬ እንደተናገሩት፣ በሚስቶቻቸው ጥቃት የሚደርስባቸው አብዛኛዎቹ ወንዶች በሕዝብ ዘንድ መሳለቂያ ላለመሆን ክስተቱን ሪፖርት አያደርጉም፡፡  በመሆኑም ድብደባ የሚፈጽሙት ሴቶች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ችግር ፈጥሯል፡፡

ለአብዛኞቹ ድብደባ መንስኤው፣ የወሲብ ጥያቄን ያለመቀበል፣ ሌላ ሴት መደረብ፣ የቤተሰብን መሠረታዊ ፍላጎት ያለማሟላት እንደሆኑም ተነግሯል፡፡

ባሎች ማታ ላይ ከሌሎች ሴቶች ጋር በስልክ ማውራታቸውና ይህም በሚስቶች ዘንድ ጥርጣሬ መፍጠሩ ሌላኛው የጥቃቱ መንስኤ ነው ተብሏል፡፡ በ2013፣ 13 ሚስቶች በባሎቻቸው ላይ ጥቃት በማድረሳቸው ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር፡፡ በ2014 ደግሞ ቁጥሩ አሻቅቧል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...