Wednesday, March 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊውጥረት በምሁራን መንደር

ውጥረት በምሁራን መንደር

ቀን:

አብዛኞቹ ተማሪዎች በትምህርቱ ዓለም ሲያልፉ የአንደኛ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃ፣ እንዲሁም የመሰናድኦ ትምህርት የሚማሩት በለመዱት አካባቢና ከቤተሰቦቻቸው ሳይርቁ ነው፡፡ ስለሆነም አኗኗራቸው አዋዋላቸውና ሌሎችም ተጓዳኝ ድርጊቶቻቸውን የሚቆጣጠሩትና የሚያስተዳድሯቸው ቤተሰቦቻቸው ናቸው፡፡ የመሰናድኦ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ዩኒቨርሲቲ በሚቀላቀሉበት ጊዜ ግን ሁኔታዎች መልካቸውን ይቀይራሉ፡፡ ከትውልድ ቦታ መራቅ፣ ከዚህ ቀደም ከማይተዋወቋቸው ሰዎች ጋር አብሮ መኖር፣ የተለያየ ባህሪ፣ የተለያየ ቋንቋ፣ የተለየ የመማር ማስተማር ሒደት ከቤተሰብ መለየትና የመሳሰሉት ሁኔታዎች ከፊታቸው የሚጋፈጡት እውነታዎች ናቸው፡፡ የተወሰኑት አዳዲስ ክስተቶችን በቶሎ ሲለምዱ ጥቂት የማይባሉት ግን ውጥረት ይፈጠርባቸዋል፡፡ በመሆኑም ከአጠናን ዘዴአቸው አንስቶ ችግር ይፈጠርባቸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ብዙ ተማሪዎች ጊዜአቸውን በጥናት ለማሳለፍ ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን በቂ ዕረፍት ስለማያገኙ ውስብስብ የሆነ ችግር የሚጋረጥባቸው ጥቂት አይባሉም፡፡ ይሁን እንጂ በሚፈጠርባቸው ውጥረት ሳቢያ የሚጠበቅባቸውን ያህል ሲሠሩ እንደማይታዩ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ‹‹ገና እንደገባን ሁላችንም ፈርተን ነበር›› የምትለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮተቤ ካምፓስ የአንደኛ ዓመት የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪ ዘይነባ ሐሰን ናት፡፡ ዘይነባ የመጣችው ከባሌ ሮቤ አካባቢ ሲሆን፣ ከቤተሰቦቿ ተለይታ ራቅ ወዳለ ሥፍራ ስትጓዝ የመጀመሪያዋ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲውን በተቀላቀለችበት ዕለትም ፍርኃትና ባይተዋርነት ተሰምቷት ነበር፡፡ ‹‹ቶሎ ትምህርት አልጀመርንም ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ምንነቱ ያልታወቀ ሥጋት ለቀቀብን፤›› በማለት ከማታውቃቸው የዶርም ጓደኞቿ ጋር መፋጠጡና የከበባት የብቸኝነት ስሜት ቤተሰቦቿን አብዝታ እንድትናፍቅ እንዳደረጋት ትናገራለች፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ትምህርት ተጀመረ፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም መምህራን ገና ማስተማር አልጀመሩም ነበር፡፡ እንዲህም ሆኖ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ላይብረሪ መግባት ጀመሩ፡፡ ሁኔታው በፈጠረባት ፍርኃትም እሷም መጽሐፍ ደርድራ ላይብረሪ መዋል ጀመረች፡፡ አመሻሽ ላይ ገብታ እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ ትቆይና ታጠናለች፡፡ ትምህርት በጀመሩ በሳምንታት ዕድሜ የክፍል ፈተና (Quiz) እንደሚሰጣቸው ተነገራቸው፡፡ በሰዓቱ የነበረውን ስሜት ስትገልጽም ‹‹ሁላችንም ተደናግጠን ነበር፡፡ ቢሆንም ረጅም ሰዓት ቁጭ ብዬ ሳጠና አደርኩ፤›› በማለት በወቅቱ የነበራትን ስሜት ታስታውሳለች፡፡ ጊዜ ጊዜን እየተካ በሄደ ቁጥር የሚሰማቸው ፍርኃትና ውጥረት እየቀነሰ ቢመጣም በካምፓሱ ውስጥ እንደቆዩ ሌሎች ተማሪዎች መረጋጋት እንዳልቻሉም የሚናገሩ አሉ፡፡ ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን የመጀመሪያ ሴሚስተር ፈተና ለማለፍ ማጥናት ተያይዘውታል፡፡ ‹‹አልፍ ይሆን›› የሚለው ጥያቄም ዕረፍት ነስቷቸዋል፡፡ በቂ ዕውቀት ቢያካብቱም በዩኒቨርሲቲው የመቆየት ዕድላቸው እንደሚያስጨንቃቸውም ያነጋገርናቸው ተማሪዎች ነግረውናል፡፡ ‹‹መሥራት እየቻሉ ነገር ግን በሰዓቱ ጭንቀት ይዟቸው መሥራት ያልቻሉ ልጆች ሲጫሩ እናያለን፤›› የምትለው ፋጡማ አህመድ ናት፡፡ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት የአግሪካልቸርና ናቹራል ሪሶርስ ተማሪ ስትሆን ዩኒቨርሲቲውን በተቀላቀለችበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ስታስታውስም ‹‹የተለያየ ብሔር ብሔረሰብ፣ የተለያየ እምነት፣ የተለያየ ባህሪ ያላቸው ተማሪዎች በአንዴ ስለተሰባሰብን እርስ በርስ በቀላሉ መግባባት አልቻልንም ነበር፡፡ ይህም ከባድ የብቸኝነት ስሜት እንዲሰማን አድርጐን ነበር፤›› ትላለች፡፡ እንደ እሷ ገለጻ፣ እሷን ጨምሮ አብዛኞቹ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚሰጥን ትምህርት ከባድ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ስለዚህም ምንም ያህል ቢያጠኑና ዕውቀት ቢኖራቸውም ራሳቸውን ብቁ አድርገው አያስቡም፡፡ አብዛኛውን ጊዜአቸውን በማጥናት የሚያሳልፉ ቢሆንም በከንቱ እንደሚለፉ ይቆጥሩት ነበር፡፡ ‹‹የምናነበው ፈተና ላይ የሚመጣ ሁሉ አይመስለንም ነበር፤›› በማለት ስለፈተና በተነሳ ቁጥር ተማሪ ይደናገጥ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ‹‹ቤተሰቦቼ በጣም ይናፍቁኝ ነበር፤›› የምትለው ፋጡማ የመጣችው ወደ ዩኒቨርሲቲው በውሎ ገብ መመላለስ ከሚቻልበት ቅርብ ከሆነው ከጐንደር በመሆኑ ሲያመቻት ወላጆቿን ሄዳ ታያቸው እንደነበር ትገልጻለች፡፡ አብዛኞቹ ተማሪዎች ግን ቤተሰብ ናፍቋቸው ያለቅሱ እንደነበርና ከቤተሰብ መራቅ የሚፈጥረው ጭንቀትም ቀላል አለመሆኑን ትናገራለች፡፡ ዛሬ ላይ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የገጠሟት ሁኔታዎች ብርቱ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ቀደም ብለው ይታይባት የነበረው የመጨነቅ፣ የመደናገጥ ስሜት፣ የትምህርት አሰጣጥ ሒደቱን ስላጤነችው ፈጽሞ አይታይባትም፡፡ ‹‹እኛ ገብተን አረጋግጠናል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርትም ሆነ ሕይወት የሚከብድና የሚያስፈራ አይደለም፡፡ እንደ ከባድ አትዩት፤›› በማለት በቀጣዩ ዩኒቨርሲቲ ለመቀላቀል በዝግጅት ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች ምክሯን ትለግሳለች፡፡ አቤል ተሾመ (ስሙ ተቀይሯል) ከሁለት ዓመት በፊት በጅማ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ዲፓርትመንት ተመድቦ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ራቅ ካለ አካባቢ የመጣ ባይሆንም የዩኒቨርሲቲውን ድባብ መላመድ ተስኖት ነበር፡፡ ስለዚህም ዶርም ለመውሰድ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን ትምህርት ከተጀመረ ዕለት ጀምሮ ውሎው ላይብረሪ ነበር፡፡ ‹‹ሁሉንም ትምህርት ኤ ለማምጣት ነበር የማልመው፤›› ይላል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ሳያጠና ቢውል ጭንቀቱ ይበረታል፣ ከተማሪዎች ሁሉ ኋላ የቀረ መስሎ ይሰማዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የክፍል ፈተና እንደሚሰጥ ሲሰማም ተደናግጦ ነበር፡፡ ‹‹ያን ለሊት ላይብረሪ ሳጠና ነው ያደርኩት፤›› በማለት በወቅቱ የነበረውን ፍርኃቱን ይገልጻል፡፡ ሩጫው ግን በውጥረት የተሞላ በመሆኑ ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም፡፡ በጣም ከባድ እንደሆነ የሚነገርለት ከፊቱ የሚጠብቀው የሴሚስተር ፈተናም ይብሱኑ ያስጨንቀው ጀመር፡፡ በተለይም ‹‹ግሬድ ተሰቅሎ እወድቅ ይሆናል፤›› የሚለው ሥጋት ውስጡን ይረብሸው ነበር፡፡ ሁኔታዎች ተደማምረው ተስፋ አስቆረጡት፡፡ ‹‹የማልጨርሰውን መንገድ ለምን ጀመርኩ፤›› በማለትም እንደተጸጸተ ያስታውሳል፡፡ የጀመረውንም ትምህርቱን ከዳር ሳያደርስ ትምህርቱን በጀመረ በጥቂት ወራት አቋረጠ፡፡ ‹‹ተጭሮ መጣ›› የሚለውን ነቆራ ፈርቶ ሌላ አካባቢ ሥራ እንደጀመረ አሳውቆ ከትውልድ ቀዬው ወጥቶ እንደነበር ይናገራል፡፡ በመጀመሪያ ሴሚስተር የመደናገጥም ሆነ የመረበሽ ስሜት በአብዛኞቹ ተማሪዎች ላይ ይስተዋላል፡፡ ‹‹ፍሬሽ ጦጣው›› የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸው ከሚያሳዩት የድንጉጥነት ባህሪ ነው፡፡ ይህ ባህሪ በጊዜ ሒደት የሚቀየር ሲሆን፣ ጥቂት የማይባሉት ላይ ግን ስሜቱ ረጅም ጊዜ ይቆያል፡፡ አንዳንዴ የአዕምሮ ችግር ሲፈጥርባቸውና ትምህርት ሲያቋርጡ ይታያል፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት አካባቢን በቶሎ ያለመልመድ ችግር ነው የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፈቃደኝነት የተማሪዎች መማክርት ሆነው የሚያገለግሉት ወ/ሮ መስከረም አሰፋ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የሚከሰተው ውጥረት ተማሪዎቹ የሚመጡት ከተለያየ አካባቢ እንደመሆኑ በቀላሉ አዲስ አካባቢን መልመድ ባለመቻላቸው ነው፡፡ እርስ በርስም በቶሎ መግባባት ይቸግራቸዋል፡፡ በተለይም ደግሞ አንዳንድ ሰዎች በተፈጥሯቸው አካባቢን በቶሎ የመልመድ ችግር ሲኖርባቸው በገቡበት አዲስ ማኅበረሰብ ውስጥ ለመኖር ከሌሎቹ በተለየ ከፍተኛ ጭንቀት ይፈጥርባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ከተቃራኒ ጾታ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት፣ ኢኮኖሚያዊ ችግር በአለባበስም ሆነ በአመጋገብ ከጓደኛ ላለማነስ የሚደረግ ሩጫ፣ የአቻ ግፊትና የመሳሰሉትን ከትምህርት ጋር እንዴት አብሮ ማስኬድ እንዳለባቸው ይቸገራሉ፡፡ በዚህም ትልቅ ጫና ያርፍባቸዋል፤›› ይላሉ፡፡ እነዚህን ክስተቶች ተከትለው ሁለት ዓይነት ውጥረቶች ይፈጠራሉ፡፡ አንደኛው ጤናማ ውጥረት ሲሆን፣ በቀላሉ ሊፈቱት የሚችሉት እንደ በትምህርት ወደ ኋላ መቅረት፣ የመልመድ ችግርና በመሳሰሉት የሚከሰት ነው፡፡ ጤናማ ያልሆነው ውጥረት ግን ሊፈቱት የማይችሉት ችግር ሲሆን፣ ተማሪዎቹ ተሸክመውት ይቆዩና ለከፋ የሥነ ልቦና ችግር እንደሚጋለጡ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በአብዛኛው አዲስ ተማሪ (ፍሬሽ) ላይ የሚታየው ውጥረት በጊዜ ሒደት የሚቀረፍ ነው፤›› የሚሉት በኦሮሚያ ልማት ማኅበር የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የሥነ ልቦና ባለሙያ አቶ ሚደቀሳ ኦላና ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በአዲስ ተማሪዎች ላይ የሚፈጠረው ውጥረት ይህ ሁኔታ እስከ ስድስት ወር ብቻ የሚቆይ ሲሆን፣ የተለመደና የሚስተካከል ነው፡፡ ነገር ግን ከስድስት ወር በላይ ሆኖ ሲቆይ ያለመልመድ ችግር (Adjustment disorder) እንደሆነና ተማሪው የባለሙያ እገዛ እንደሚያስፈልገው ይናገራሉ፡፡ ብዙ ጊዜም ተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲ በተቀላቀሉ በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የሚፈጠርባቸው ጭንቀት ወይም ውጥረት ከሌሎች ማኅበራዊ ሁኔታዎች በተለየ ከትምህርት ጋር በተያያዘ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹አብዝተው የሚጨነቁት ለውጤት ነው፡፡ ነገር ግን እርስ በርስ ስለማይተዋወቁ ከማን ጋ እንደሚፎካከሩ ግራ ይገባቸዋል፡፡ የዕውቀት ደረጃውንም የሚለኩት ረጅም ሰዓት ተቀምጠው ስላነበቡ ይሆናል፡፡ ቀኑን ሙሉ ሲያጠኑ ቢውሉም ሌሎች ሲያጠኑ የተበለጡ ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህም የዕውቀት ደረጃቸውን በራሳቸው ሳይሆን በሌሎች መለካት ይጀምራሉ፡፡ እገሌ በጣም ጐበዝ ብለው ሲያስቡ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል፤›› ይላሉ፡፡ ተማሪዎቹ እርስ በርስ የሚያደርጉት መስተጋብር በራሱ የሚፈጥረው ውጥረት እንዳለ የሚናገሩት አቶ ሚደቅሳ፣ ዩኒቨርሲቲ የሚቀላቀሉ ተማሪዎች በአማካይ ዕድሜአቸው 18 ሲሆን፣ ይህ የዕድሜ ደረጃ the late adolescent (የመተላለፊያ ጊዜ) ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ማንም እንዲቀበለን እንፈልጋለን፤›› ይላሉ፡፡ ስለዚህም ተማሪዎቹ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወይም የሚሰነዝሩት ሐሳብ ውዴታን እንዲያተርፍላቸው ይሻሉ፡፡ ይሁን እንጂ ተማሪዎቹ በሚኖራቸው የእርስ በርስ ግንኙነት አንዱ ከሌላው እኩል አይሆንም፡፡ በማኅበራዊ ሕይወት ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎ ከሌላው እኩል በማይሆንበት ጊዜ ደግሞ ተቀባይነት እንዳጡና ከሌሎች ያነሱ ይመስላቸዋል፡፡ በመሆኑም ራሳቸውን ያገላሉ፣ ይህንን ተከትሎ ከመረጃ መራቅና ሌሎችም ችግሮች ይገጥሟቸዋል፡፡ ለቦታው ብቁ እንዳልሆኑ አድርገው ያስባሉ በዚህ ምክንያት የውጥረት ስሜት ይፈጠርባቸዋል፡፡ ‹‹ብቁ ካልሆንኩ ቁጭ ብዬ ምን አደርጋለሁ?›› በማለት ድንገት ተነስተው ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚመለሱበት አጋጣሚዎች እንደሚኖሩ ይገልጻሉ፡፡ የችግሮቹን መፍትሔ ሲናገሩም ‹‹ውስጣዊና ውጫዊ የሆኑ ነገሮችን ከተገቢው በላይ ግምት አለመስጠት አንዱ ነው፤›› ይላሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲ የተቀላቀሉት ባላቸው አቅምና ዕውቀት ብቁ ሆነው ስለተገኙ ነው፡፡ ‹‹ለምንድነው እዚህ የመጣሁት? አቅም ስላለኝ ነው ብለው እንዲያስቡ ያስፈልጋል፤ እንዲህ ብለው ካሰቡና ለትምህርታቸው ቅድሚያ ከሰጡ ያለምንም ውጥረት መሥራት እንደሚችሉ ይረዳሉ፤›› ይላሉ፡፡ ምክንያታዊ ሆኖ ማሰብ፣ ማንነትን አለመርሳትና አብዛኛው ሰው በሚስማማበት እውነታ ለመግባባት መሞከር ከትምህርት ውጪ ውጥረትን የሚፈጥሩ ክስተቶችን ማራቅ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...