Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊነፃ ‹‹Wifi›› አሰሳ

ነፃ ‹‹Wifi›› አሰሳ

ቀን:

ምሽት ለሦስት ሰዓት ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ቀርተዋል፡፡ የድንጋይ ንጣፍ አቋራጭ መንገዱ ግን በሰው ተሞልቷል፡፡ የመንገዱ መግቢያ ጨለም ያለ መሆኑን አስተውሎ ሰው በብዛት ሊታይ ይችላል ብሎ መገመት ሊከብድ ይችላል፡፡ ከሚተላለፉ ሰዎች ቁጥር ይልቅ ግራና ቀኝ ጥግ ጥግ፣ ይዘው በስልካቸው ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ብዙ ናቸው፡፡ ጥግ ላይ ደገፍ ወይም አንዱ ጋር ቁጭ ብለው ለመመቻቸት ሳይሞክሩ፣ ይጓዙ የነበረበትን አቅጣጫ እንኳን ሳይቀይሩ ዕርምጃቸውን ድንገት ቀጥ አድርገው ስልካቸውን በማውጣት ኢንተርኔት የሚጠቀሙም አሉ፡፡ በተወሰኑ ዕርምጃዎች ርቀት ደግሞ መንገድ ላይ እንዳሉ ሳይሆን ከተመቻቸ ቦታ ላይ ተደላድለው እንዳሉ ያህል ከጆሯቸው ላይ ሄድ ሴታቸውን አድርገው በስካይፕ የሚያወሩም አሉ፡፡ ከመንገዱ አጋማሽ ግራና ቀኝ እንደ ውኃ ልክ ተደርጎ ከተሠራ ቦታ ላይ ደግሞ ላፕቶፕ በጋራ የሚጠቀሙ ይታያሉ፡፡ ጎን ለጎን ተቀምጠው ‹‹ይሄንን ላውርደው ያን›› በማለት የሚጠያየቁ በተቃራኒው ምንም እንኳ ከሁኔታቸው እንደሚተዋወቁ መገመት ቢቻልም ምንም ሳይባባሉ ስልካቸው ላይ የተመሰጡ የሚመስሉም ነበሩ፡፡ ካፍቴሪያ ውስጥ እንዳሉ ያህል እየተሳሳቁ ኢንተርኔት የሚጠቀሙም አሉ፡፡ ብዙዎቹ በሃያዎቹ መጀመርያ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን መገመት ሲቻል በሰላሳዎቹ አጋማሽ የሚመስሉም ነበሩ፡፡ መንገዱ አራት ኪሎ ቅድስት ማርያም አቅራቢያ ከሚገኝ አንድ ረዥም ሕንፃ ጀርባ የሚገኝ ሲሆን፣ ሰዎች በዚያ ምሽት ስፍራው ላይ የተገኙት ነፃ (Wifi) ዋይፋይ ለማግኘት ነበር፡፡ ሁሉም ማለት ይቻላል በትምህርትና በሥራ ምክንያት ወይም በመኖሪያቸው አቅራቢያ መሆን እዚያ ቦታ ላይ ነፃ ዋይፋይ መኖሩን አውቀው ደንበኝነት ያጠነከሩ መሆናቸውን በስፍራው ያገኘነው አቶ ፋሲል አልታዬ ይናገራል፡፡ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ አምስተኛ በር፣ ስድስት ኪሎ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ አራዳ ጊዮርጊስ አዲስ ሬጀንሲ ሆቴል፣ አራት ኪሎ ቅድስት ማርያም፣ ቤልየርና ካዛንቺዝ አካባቢ ነፃ ዋይፋይ በተለያየ ጊዜ የተጠቀመባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ ሥራውም መኖሪያውም አራት ኪሎ አካባቢ በመሆኑ የነፃ ዋይፋይ ደንበኝነቱ በይበልጥ አራት ኪሎና ስድስት ኪሎ ካሉ ነፃ ዋይፋዮች መሆኑን ይናገራል፡፡ አንድ ቦታ ላይ ሁለት ሰዓት ያህል እንደሚያጠፋና እሱ በብዛት በሚጠቀምባቸው ቦታዎች ላይ ሰዎች ኢንተርኔት ለማግኘት ከቦታው የሚገኙት ከምሽቱ 11 ሰዓት በኋላ መሆኑን ገልጾልናል፡፡ ለምሳሌ ቅድስት ማርያም አቅራቢያ በሚገኘው አቋራጭ መንገድ ነፃ ዋይፋይ ማግኘት የተቻለው መስከረም 2007 ዓ.ም. ላይ የትልቁን ሕንፃ አገልግሎት መስጠት መጀመር ተከትሎ ሲሆን ሰዎች ዋይፋይ ለመጠቀም ከ11 ሰዓት ጀምሮ ምሽት አራትና አምስት ሰዓት ድረስ እንደሚቆዩ ይናገራል፡፡ ‹‹ሕንፃው ላይ ብዙ መሥሪያ ቤቶች አሉ፡፡ ከሥራ ሰዓት በኋላ ግን ውስጥ የሚጠቀም ስለማይኖር ኮኔክሽኑ ጥሩ ይሆናል የሚለው›› አቶ ፋሲል፣ ቦታው ላይ ሁለት ነፃ የዋይፋይ አድራሻዎች መኖራቸውንና በጥሩ ፍጥነት የፈለገውን ነገር ዳውን ሎድ አፕሎድ ማድረግም እንደሚችል ይናገራል፡፡ ቦታው ላይ ከጓደኛው ጋር ያገኘነው ሌላው የአካባቢው ነፃ ዋይፋይ ደንበኛ ወጣት አቤል አበራ፣ ሠፈሩ እዚያው አካባቢ እንደሆነና ቀን በቀን ምሽት ላይ አብሮት ከነበረው ጓደኛው ጋር ጎራ እንደሚሉ ገልጾልናል፡፡ ዘወትር ምሽት ላይ ከዚህ ጓደኛው ጋር ቤተ ክርስቲያን እንደሚሳለሙና ትንሽም የእግር ጉዞ እንደሚያደርጉ የሚናገረው አቤል፣ ፌስ ቡክ በማየትና አንዳንድ የሚያስፈልጓቸውን መረጃዎች ዳውን ሎድ በማድረግ ጥቂት ደቂቃዎችን ማሳለፍም የምሽት ፕሮግራማቸው አካል ከሆነ ጥቂት ወራት መቆጠሩን ገልጾልናል፡፡ ብዙም ሳይርቅ በዚያው አካባቢ አቅራቢያ ተመሳሳይ ነፃ ዋይፋዮች ያሉበት አካባቢ መኖሩን ቢያውቅም ጭር ያለና መኪና ብዙም የማያልፍበት መንገድ በመሆኑ የሚመቸው አቋራጭ መንገዱ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ አቶ ፋሲል ደግሞ በአቅራቢያው ከሚገኘው ቤተክርስቲያን ውስጥ ተቀምጦ ለመጠቀም ምቹ ስለሚሆንለት ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ አምስተኛ በር አካባቢ ያለው ነፃ ዋይፋይን መጠቀም የመጀመርያ ምርጫው ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የብዙ ሰዎችን ስማርት ፎን መያዝና የተጠቃሚዎችን የኢንተርኔት ፍላጎት በመረዳት በዚያውም ተወዳዳሪ ካፌዎችን ለመብለጥ በሚመስል መልኩ ዋይፋይ በትልልቅ ሆቴሎች ብቻም ሳይሆን በአነስተኛ ካፍቴሪያዎች ጭምር ማግኘት ተችሏል፡፡ በመሆኑም ለአቶ ፋሲል መሀል ከተማ አዘውትሮ የሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ላይ ዋይፋይ በመኖሩ ለኢንተርኔት ሲል ካፍቴሪያና ሆቴል መሄድ ምክንያታዊ አይደለም፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በተለይም ትልልቅ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አካባቢ በነፃ ዋይፋይ በቀን ኢንተርኔት ይጠቀሙ የነበሩ ሰዎች ሁለት ሦስት ጊዜ በሕግ አስከባሪዎች ቦታውን እንዲለቁ ሲደረጉ በማየቱ በቀን የትም ለመጠቀም እንደማይሞክር ያስረዳል፡፡ ነገር ግን ተቋማቱ የዋይፋይ ሲግናሉ በቅርብ ርቀት ላይ ሊደርስና ሰዎችም ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ እያወቁ ዋይፋዩን ክፍት እስካደረጉት ድረስ የእሱና የሌሎች በነፃ መጠቀም ችግር ነው ብሎ አያስብም፡፡ ‹‹ቢሆንም ሰው ደግሞ ነፃ ነው ብሎ ያንንም ይኼንንም ዳውንሎድ ሳያደርግ ኃላፊነት በተሞላ መንገድ መጠቀም እንዳለበት አምናለሁኝ፤›› ይላል፡፡ ስሟ እንዲገለጽ ያልፈለገች ያነጋገርናት ሌላ ሴት፣ መንግሥተዊ ባልሆነ አንድ ዓለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅት ፕሮጀክት ኦፊሰር ነች፡፡ የሥራዋ ፀባይ አንዳንድ ጊዜ ከሥራ ሰዓት ውጭ፣ ቅዳሜና እሑድም ኢንተርኔት መጠቀም ግድ ስለሚል ኢንተርኔት ፍለጋ አዘውትራ የምትሄድባቸው ሆቴሎች ነበሩ፡፡ ለኢንተርኔት ብሎ መሄድ ብቻም ሳይሆን፣ እግረ መንገዷን ሻይ ቡና እያለች በዚያ መሥራቱንም አትጠላውም ነበር፡፡ ከምትሄድባቸው ሆቴሎች በአንዳንዶቹ አገልግሎት በመጠቀም ብቻ የዋይፋይ የምስጢር ቁልፍ ማግኘትና ኢንተርኔት መጠቀም ሲቻል በሌሎቹ ደግሞ እንደ ሻይ ቡና አገልግሎት ሁሉ ለዋይፋይም ሌላ ክፍያ ይጠየቃል፡፡ ከምትሄድባቸው ሆቴሎች አንዱ መኖሪያ ቤቷ አቅራቢያ እንደነበርና የእዚያን የምስጢር ቁልፍ ካወቀች በኋላ ግን መሄዷን አቁማ ከቤቷ ሆና የሆቴሉን ዋይፋይ ለረዥም ጊዜ መጠቀሟን ነግራናለች፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በፊት ግን ሆቴሉ የምስጢር ቁልፉን በመቀየሩ እንደ በፊቱ በነፃ መጠቀም አቁማለች፡፡ ገርጂ ሰንሻይን አካባቢ የሚገኝ አንድ በርገር ቤት ባለቤት እንደገለጸልን፣ ለተጠቃሚዎች ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ የዋይፋይ የምስጢር ቁልፍ በመስጠት ኢንተርኔት እንዲጠቀሙ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ከእሱ ዘንድ ደንበኛ የሆኑ፣ ከበርገር ቤቱ አጠገብ ባሉ ካፍቴሪያዎችና ሬስቶራንቶችም የዘወትር ተጠቃሚ በመሆናቸው የእሱን አገልግሎት ባልገዙበት አጋጣሚ ሁሉ ዋይፋዩን በነፃ እየተጠቀሙ መጨናነቅ በመፈጠሩ በተደጋጋሚ የምስጢር ቁልፍ ለመቀየር መገደዱን ያስረዳል፡፡ ካዛንቺስ፣ ቦሌ ኦሎምፒያ፣ አራት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎና እንጦጦ ኪዳነምሕረት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ስለጉዳዩ የጠየቅናቸው ሰዎች ከተማ ውስጥ ነፃ ዋይፋይ እናገኝባቸዋለን ካሉን ቦታዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በከተማው ኢንተርኔት ብርቅ በነበረበት ወቅት ትልልቅ ጥናት የሚያደርጉ ምሁራን ኢንተርኔት ፍለጋ ጐራ የሚሉት ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) ነበር፡፡ ዛሬ ላይ በአገሪቱ የኢንተርኔት ተጠቃሚ በጣም ትንሽ (1.9 በመቶ እ.ኤ.አ. የ2013 መረጃ እንደሚያሳየው) ቢሆንም ከቀድሞ ጋር ሲነፃፀር ይኼም ቦታ የሚሰጠው ለውጥ ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ በተለይም አይፎን ብዙ ሰዎች እጅ መግባትን ተከትሎ ምንም እንኳ ብዙዎች ስልኮቻቸው የተለያዩ አፕልኬሽኖች ያሏቸው ቢሆንም አፕልኬሽኖቹን ባለመጠቀማቸውና ከኢንተርኔት ጋር ያላቸው ትውውቅም ጥያቄ ውስጥ የሚወድቅ በመሆኑ ‹‹አይፎን ተጠቃሚ ነው ተሸካሚ›› እየተባለ የሚቀለድበት ጊዜ ሩቅ ካለመሆኑ አንፃር፣ በአሁኑ ወቅት ኢንተርኔት ሰዎች ብርድ ጨለማ ሳይሉ እዚህም እዚያም የሚፈልጉት ነገር መሆን መጀመሩም ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የነፃ ዋይፋይ ሲግናል አሰሳም የዚሁ አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ላይ የተለቀቀ፣ በዓለም አቀፍ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ዩኒየን (ITU) ተሠርቶ ይፋ የሆነና ሌሎችም ጥናቶች በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቁጥር በጣም ትንሽ መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡ በአገሪቱ በብዛት በሚታዩ ድረ ገጾች ደግሞ በደረጃ ፌስ ቡክ፣ ዩ ቲዩብና ጉግል ሲሆኑ ከአገር ውስጥ ድረ ገጾች ደግሞ በደረጃ ድሬ ቲዩብ ፣ ኢትዮ ቲውብና ኢትዮ ጆብስ መሆናቸው በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...