ኮትዲቯራዊው ያያ ቱሬ የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ የእግር ኳስ ተጨዋች ተብሎ ለተከታታይ አራተኛ ጊዜ አሸናፊ ሆኗል፡፡ የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ አማካይ እ.ኤ.አ. የ2014 ምርጥ የአፍሪካ አሸናፊ በመሆን በናይጄሪያ ሌጉስ በተደረገው ሥነ ሥርዓት ላይ ሽልማት ማግኘቱን ካፍ ይፋ አድርጓል፡፡ ያያ ቱሬ እ.ኤ.አ. በ2011፣ በ2012 እና በ2013 አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ከእሱ በፊት ካሜሮናዊው ሳሙኤል ኤቶ እ.ኤ.አ. በ2003፣ በ2005 እና በ2010 ማሸነፉ አይዘነጋም፡፡ ያያ ቱሬ ከተፎካካሪዎቹ 175 ድምፅ አግኝቶ አሸናፊ መሆኑ ሲገለጽ፣ የጋቦኑ አማካይ ኦባሚያንግ 120 ድምፅ፣ ናይጄሪያዊው ግብ ጠባቂ ኢኒያማ 105 ድምፅ በማግኘት ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ በመሆን የአፍሪካ ምርጦች ሆነዋል፡፡ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች፣ የቴክኒክ ዳይሬክተሮችና ከካፍ ጋር ግንኙነት ያላቸው የስፖርት ማኅበራት መሪዎች በሰጡት ድምፅ መሠረት የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ብሔራዊ ቡድን በመባል የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን አሸናፊ ሆኗል፡፡