‹‹ኔትወርክ የለም›› እና ‹‹ሲስተም የለም›› የሚሉት ሃረጎች የእንግሊዝኛ ቃላትን የያዙም ቢሆን እንግሊዝኛ ለማያውቁትም የአገራችን ሰዎች የተለመዱ ሆነዋል፡፡ ገንዘብ ለማስቀመጥ፣ ገንዘብ ለማውጣት፣ ገንዘብ ለማስተላለፍ፣ ለመላክ፣ ለመቀበል፣ ቼክ ለመመንዘር፣ የተለያዩ ግብይቶችን ለመፈጸም ወደ ባንክ የሚሄድ ሰው በየዕለቱ የሚሰማቸው ሆነዋል፡፡ በዚህ ሰሞን አንድ ባልንጀራዬ ገንዘብ ከባንክ አውጥቶ ያለበትን የመንግሥት ግብር ለመክፈል ወደ ግብር ሰብሳቢው አካል ለመሄድ ባሰበ ጊዜ ያጋጠመውን ሲነግረኝ የ‹‹ኔትወርክ የለም›› ጉዳይ እጅጉን አሳሳቢ መሆኑን ተረዳሁኝ፡፡ ልጁ እንደነገረኝ ገንዘቡን ከባንክ ሒሳቡ ለማውጣት በሄደበት አንድ የግል ባንክ ብዙ ደንበኛ አገልግሎት ለማግኘት ባንኩን ቢሞላውም፣ ‹‹ኔትወርክ›› ባለመኖሩ ሁሉም ለረዥም ሰዓት ተቀምጠዋል፡፡ ወደ መክፈያ መስኮቱ ተጠግቶ ባንከሯን ‹‹ኧረ ያስቀመጥኩትን ገንዘብ ለማውጣት ረዥም ሰዓት ተቀምጥኩ አንድ መፍትሔ ስጢኝ?›› ብሎ ሲያናግራት፣ የሰጠችው መልስ እንደገረመው ገለጸልኝ፡፡ ‹‹ኔትወርክ የለም›› ‹‹ሲስተም የለም›› ታዲያ እኛ ምን ማድረግ እንችላለን? በማለት ኔትወርክ አለመኖሩ ያስደሰታት በሚመስል መልኩ መልስ ሰጠችኝ ይላል፡፡ ሁለት ሦስት ጊዜም ቢመላለስ እርሱ ከኔትወርክ የተጣላ ይመስል በሄደ ቁጥር መልሱ ተመሳሳይ ሆኖበት መገረሙን አጫወተኝ፡፡ ‹‹ኔትወርክ የለም›› የሚለው ቃል መደበኛ የባንከር ሥራ ይመስል በየባንኩ መስኮቶች በከፍተኛ የመተማመን ስሜትና በደስታ በባንከሮች የሚነገር ሁሉም ደንበኛ በየዕለቱ የሚሰማው መርዶ ሆኗል፡፡ የአገራችን ኔትወርክ ጥሩ አለመሆኑን የሦስተኛ ወገን ነጋሪ ባይፈልግም፣ ባንከሮቹ ግን በገቡት የባንክ አገልግሎት ወይም ግብይት የመስጠት የሕግ ግዴታ የሚጠበቅባቸውን ላለመወጣት ‹‹ኔትወርክ የለም›› የሚለው ዘይቤ መከላከያ እንደሚሆናቸው ወይም እንደማይሆናቸው መመርመር ተገቢ ነው፡፡ በሕግ ሙያ አንድ ኩነት መከላከያ /Defence/ የሚሆነው በሕግ ወይም በውል በግልጽ ተመልክቶ ግዴታ ፈጻሚው ያለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችለው ነገር በተከሰተ ጊዜ በሕግ (በፍትሐ ብሔር) እንዳይጠየቅ ምክንያት የሚሆንለት ከሆነ ነው፡፡ በኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት መስጠት እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ በአሜሪካ ጀምሮ በዓለም ሁሉ ላይ በመስፋፋት ላይ ያለ ሲሆን፣ እኛም አገር ባለፉት አሥር ዓመታት በባንኪንግ ኢንዱስትሪ በተደረጉ ለውጦች የሚታይ ነው፡፡ የኢንተርኔት ባንኪንግ የተለመደውን የባንክ አገልግሎት (Traditional Banking Services) ከመስጠት በተጨማሪ የባንክ ሒሳብ ለመጠየቅ፣ የቼክ ግብይቶች ለመፈጸም፣ ገንዘብ ለማስተላለፍ፣ ሒሳብ ለመክፈት፣ ከሱቆች ግብይት ለመፈጸም ወይም ዕዳ ለመክፈል ወዘተ. አገልግሎት ላይ ይውላል፡፡ የባንክ ግብይትን ፈጣን፣ ወጪ ቆጣቢና ለደንበኛው የተመቸ ያደረገ በመሆኑ ጠቃሚነቱ አከራካሪ አይደለም፡፡ የጠቃሚነቱ ያህል ግን ለደኅንነት ሥጋት የተጋለጠ መሆኑ የባንክ ግብይት ተዓማኒ እንዳይሆን፣ ሊያደርገው እንደሚችሉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በአገራችን ያለውን የደኅንነት ሥጋት (በኢንተርኔት ማጭበርበር፣ የምስጢር ቁልፍ መስበር፣ ባንክ መዝረፍ ወዘተ.) የኢንተርኔት ባንክ አገልግሎት ሲዳብር የምናስተውለው ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የ‹‹ኔትወርክ›› አለመኖር ቀዳሚ አነጋጋሪ ጉዳይ በመሆኑ እዚሁ ነጥብ ላይ ብቻ ማተኮር ተገቢ ነው፡፡ የባንኮችን ኃላፊነት ከኔትወርክ አለመኖር ጋር በምሳሌ ለማስረዳት እንሞክር፡፡ አንድ ሰው በባንክ በተላከለት ገንዘብ፣ ከተቆረጠለት ቼክ ወይም ካስቀመጠው ገንዘብ በማውጣት ያሸነፈውን ጨረታ ክፍያ ለመፈጸም፣ የበሰለውን ዕዳውን ለመክፈል ወይም የግብር ክፍያውን ለመወጣት የባንክ አገልግሎት ፈልጎ ባንክ መጣ፡፡ ባንኩም ‹‹ኔትዎርክ የለም›› በማለት ደንበኛው በፈለገበት ሰዓት አገልግሎቱን ሳይፈጽምለት ቢቀር ለደረሰበት ጉዳት ከባንኩ ካሳ የመጠየቅ መብት ይኖረዋልን? ወይም ደንበኛው ባንኩን ገንዘቤን እንድጠቀም ስላላደረከኝ በዚህ ምክንያት የደረሰብኝን ጉዳት ልትክሰኝ ይገባል በማለት ለመሠረተበት የፍትሐ ብሔር ክስ ‹‹ኔትወርክ ባለመኖሩ ክፍያ አልፈጸምኩም›› በማለት ኃላፊነቱን ሊከላከል ይችላል ወይ? የዚህ ጽሑፍ ጭብጥ በእነዚህ ቁልፍ ጭብጦች ላይ ያጠነጥናል፡፡ የኤሌክትሮኒክ ባንክ አገልግሎት የሕግ መሠረት አብዛኛው የባንክና የደንበኛ ግንኙነት የሚተዳደረው በውልና ውልን በሚገዙ ሕግጋት ነው፡፡ ለአብነት የአደራ የቁጠባ ሒሳብ፣ ቼክ፣ ብድር፣ ለአብነት ሊጠቀሱ ይችላል፡፡ ውሉ የሚመሠረተው ደንበኛው የባንኩ ተጠቃሚ በመሆን በሚገባው ውል በሚመሠረት የባንክና የደንበኛ ግንኙነትና የባንክ አገልግሎቱን ልዩ ሁኔታ በሚገዛ ውል ነው፡፡ አንድ ደንበኛ በባንክ ውስጥ የባንክ ሒሳብ በመክፈት ገንዘብ ሲያስቀምጥና ሲያወጣ ከባንኩ ጋር የውል ግዴታ ይገባል፡፡ ባንኩ በደንበኛው ወይም በሦስተኛ ወገን ለደንበኛው የሚመጣ ወይም የሚላክ ገንዘብን ለመቀበል በመስማማት፣ ይህንኑ ገንዘብ ደንበኛው በፈለገ ጊዜ ወይም በተወሰነ ቀን ከወለድ ጋር ወይም ያለወለድ ለደንበኛው ወይም ደንበኛው እንዲከፈል ላዘዘለት ሦስተኛ ወገን የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ በደንበኛው ሒሳብ ከማንኛውም ምንጭ የሚመጣው ገንዘብ ባለቤት ደንበኛው ቢሆንም፣ ባንኩ ገንዘቡን እንደተበደረ ሰው ለሚፈልገው የባንክ አገልግሎት የመጠቀም መብት ይኖረዋል፤ በተጠየቀም ጊዜ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ ከውል ግንኙነት አንፃር ገንዘብ በቁጠባ መቀበል በባንኩና በደንበኛው መካከል የባለገንዘብና የባለዕዳ (Creditor – debtor) ግንኙነት ይፈጥራል፡፡ የአገራችን የንግድ ሕግ ይህንን በንግድ ሕግ ቁጥር 896 በዝርዝር ደንግጓል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት በአደራ ገንዘብ የሚያስቀምጥ ባንክ ለደንበኛው ከማንኛውም ምንጭ የሚላክ ገንዘብን የመቀበልና የማስተዳደር ደንበኛው በጠየቀ ጊዜም በውሉ በሰፈረው ግዴታ መሠረት የመክፈል/የማስተላለፍ ግዴታ አለበት፡፡ ኢንተርኔት የደንበኛውን ትዕዛዝ ለመፈጸም፣ ገንዘብ ለማስገባትና ለማውጣት፣ ለማስተላለፍ ጥቅም ላይ የዋለ አማራጭ ዘዴ በመሆኑ በውል ያለውን የባንኩንና የደንበኛውን የሕግ ግንኙነት የሚያጠናክር ነው፡፡ በኢንተርኔት ባንኪንግ ገንዘብ ከደንበኛው ሒሳብ በኢንተርኔት አማካኝነት ለሌላ የባንክ ባለ ሒሳብ ተጠቃሚ ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ባንኩ ከደንበኛው የገንዘብ ማስተላለፍ ትዕዛዝ በደረሰው ጊዜ የደንበኛውን ሥልጣን፣ የሒሳቡን ሁኔታ እንዲሁም በቂ ገንዘብ መኖሩን በማረጋገጥ በደንበኛው ትዕዛዝ መሠረት አገልግሎቱን ይፈጽማል፡፡ በአገራችን በብዛት የተለመደ ባይሆንም ደንበኛው በራሱ ኮምፒውተር ወይም ሞባይል የኢንተርኔት ኔትወርክን በመጠቀም ትዕዛዙን ለባንኩ ሥርዓት ሊያደርስና ግብይቱን ሊፈጽም ይችላል፡፡ ሆኖም አሁን ባለው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ደንበኛው ባንክ ሄዶ በሚሰጠው ትዕዛዝ ባንከሮች በራሳቸው ኤሌክትሮኒክስና ኔትወርክ ትዕዛዙን ይፈጽሙለታል፡፡ ከውል ደንቦች አንፃር ባንኮች የደንበኛቸውን ትዕዛዝ በመፈጸም ረገድ ሙያው የሚጠብቀውን ጥንቃቄና ክህሎት ሊያከናውኑ ይገባል፡፡ ደንበኛውም በጥንቃቄ ትዕዛዙን በማስተላለፍ ባንኮች እንዳይሳሳቱ ወይም እንዳይጭበረበሩ ሊያደርግ ይገባል፡፡ የባንክ አገልግሎት በኢንተርኔት ማግኘት ቀደም ሲል ከላይ የተመለከትነው የባንክና የደንበኛ ግንኙነት የሚመሠረትበት ውል አካል ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡ በሌሎች አገሮች የኢንተርኔት ተደራሽነትና አገልግሎት በተለየ ውል የሚገዛ ሲሆን፣ ከኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት ጋር የተያያዙ ልዩ መብትና ግዴታዎች የሚካተቱበት ይሆናል፡፡ እንዲህ በሆነ ጊዜ የኢንተርኔት አገልግሎት ውሉና በቀዳሚነት የነበረው የባንክና የደንበኛ ግንኙነት የተመሠረተበት ውል በጣምራ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡ የኢንተርኔት አገልግሎት ውል በተደራሽነት መብት፣ የሒሳብ ባለቤትን የመለያና የማረጋገጫ ሁኔታ፣ የደኅንነት መጠበቂያ ሥርዓትና መሣሪያዎች፣ ሥርዓቱ በተቋረጠ ጊዜ ተፈጻሚ ስለሚሆን አማራጭ (Contingency) ሥርዓት እንዲሁም መጭበርበር በተከሰተ ጊዜ ሊኖር ስለሚችል ኃላፊነት ወዘተ. በዝርዝር ይደነግጋል፡፡ በእኛ አገር የባንክ ሥርዓት የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2003 አንቀጽ 19 ባንኮቹ ለደንበኞቻቸው ተፈጻሚ የሚያደርጉትን ውሎች አዘጋጅተውና በብሔራዊ ባንክ አፀድቀው ሥራ ላይ እንደሚያውሉ ቢደነግግም፣ ምሉዕ የኢንተርኔት አገልግሎትን የሚገዛ ወጥ ውል የላቸውም፡፡ የኤቲኤም አገልግሎት የሚጠቀም ደንበኛ ከሚሞላው ፎርም ውጭ በኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት የደንበኛው ግዴታ፣ የባንኮቹ ኃላፊነት፣ ኔትወርክ በማይሠራ ጊዜ ባንኩ ወይም ደንበኛው ሊኖረው የሚችለው ግዴታን የሚያመለክት ውል የለም፡፡ ከዚህ አንፃር በአሁኑ ወቅት ባንኮች የሚሰጡት የኢንተርኔት ባንክ አገልግሎት እስካሁን ተፈጻሚነት በሚኖረው የባንክ አሠራር (Traditional Banking Practice) የሚተዳደርና በባንኩና በደንበኛው መካከል በተገባው የአደራ ገንዘብ የማስቀመጥ ውል የሚተዳደር ነው፡፡ የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎትም ሆነ ብድር እስከአሁን ለዘመናት ተፈጻሚነት ባላቸው ሕግጋትና ውሎች የሚተዳደር ይሆናል፡፡ ቼክም እንዲሁ፡፡ በዚህ አውድ ከተረዳነው ባንኩ ደንበኛው በፈለገ ሰዓት ደንበኛው ባዘዘው መሠረት ያስቀመጠውን ገንዘብ የመክፈል ወይም የማስተላለፍ ግዴታ ስላለበት የኢንተርኔት አማራጭንም ሲተገብር የደንበኛውን መብት በጥንቃቄ ለማስፈጸም የሚያስችል ሥርዓት የመዘርጋት ግዴታ ይኖርበታል፡፡ በዚሁ መሠረት ባንኩ ፈጣንና አስተማማኝ ኔትወርክ የመዘርጋትና አገልግሎቱን በፍጥነት የመስጠት ግዴታው ከደንበኛው ጋር የገባው ውል አካል እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ የባንኮቹ ኃላፊነት የኢንተርኔት መቋረጥ ወይም የኔትወርክ አለመኖርን ተከትሎ የሚኖር የባንኮችን ኃላፊነት የሚገዙ ወጥ ዓለም አቀፋዊ ሕግጋት የሉም፡፡ ስለዚህ የባንኮቹ ተሞክሮ ከአገር አገር፣ እንዲሁም ባንኮችን የሚያስተዳድረው አካል ከሚወስደው ዕርምጃ ልዩነት፣ አልፎ አልፎም ከባንክ ባንክ ይለያያል፡፡ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው ከኔትወርክ መቋረጥ ጋር የሚኖር ኃላፊነት በዋናነት በውል የሚገባ ሲሆን፣ ባንኮች ኃላፊነታቸውን የተመለከቱ ማግለያ አናቅጽ የማካተት ልማድ አላቸው፡፡ የሲስተም አለመሥራት ወይም መቋረጥ ባንኩ ሊቆጣጠረው በሚችለው ምክንያት ወይም ከባንኩ አቅም በላይ በሆነ ምክንያት ሊከሰት ይችላል፡፡ የባንኩ ግዴታ ደንበኛው አድርግልኝ ያለውን ትዕዛዝ መፈጸም ነው፡፡ ደንበኛው የጠየቀውን የባንክ ግዴታ ለመፈጸም የሚወስደው ጊዜ እንደ ግብይቱ ባህርይ ይለያያል፡፡ የአልግሎት መዘግየት ወይም መቋረጥ ኢንተርኔትን በሚያስተላልፈው በኮምፒውተር ወይም የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ምክንያት ወይም በኢንተርኔት የባንክ ሥርዓት መቋረጥ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ መዘግየቱ ወይም ስህተቱ የተፈጸመው በተጠቃሚው ኮምፒውተር ወይም ሞባይል ወይም ኢንተርኔት ምክንያት ከሆነ ባንኩ ደንበኛው ለሚደርስበት ኪሳራ ተጠያቂ ላይሆን ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ የባንክ የኢንተርኔት አገልግሎት በባንኮቹ ቅርንጫፎች፣ ኮምፒውተሮችና የኢንተርኔት ሲስተም በሚሠራበት በእኛ አገር ሁኔታ ተፈጻሚነቱ አነስተኛ ነው፡፡ በሌላ በኩል ባንኮቹ ከደንበኛው ጋር በሚገቡት ውል ከአቅም በላይ በሆኑ ጉዳዮች ምክንያት ኢንተርኔት ቢቋረጥ ደንበኛው ለሚደርስበት ጉዳት ኃላፊ እንደማይሆኑ የሚደነግጉበት አጋጣሚ አለ፡፡ በታይላንድና በእንግሊዝ እንዲህ ዓይነት ልማድ በስፋት ይታያል፡፡ ከአቅም በላይ የሚለው ምክንያት የባንኩ መሣሪያ ወይም የመገናኛ ሥርዓት (Communication System) መሥራት እንደማይችል የመገናኛ አመልካች ሲኖር፣ በኮምፒውተር ቫይረስ፣ የኢንተርኔት ሰርቨር መሰበር ወይም ተፈጥሮዓዊ ችግር፣ ጦርነት፣ የሽብር ጥቃት ወዘተ. ዓይነት ያልታዩ፣ ለማራቅም ያልተቻሉና በተጨባጭ አስቸጋሪ ምክንያቶች ሲያጋጥሙ ባንኮቹ ተጠያቂ የማይሆኑበት ሁኔታ አለ፡፡ እነዚህ የባንክ ኃላፊነቶች መነሻ የሚያደርጉት አገሮች ጥራት ያለውና አስተማማኝ የኢንተርኔት አገልግሎት መኖራቸውን ሲሆን፣ ልዩ ሁኔታዎቹ በአጋጣሚ ካልተከሰቱ በቀር የኢንተርኔት መቋረጥ ወይም የኔትወርክ አለመኖር ስለማይከሰት ነው፡፡ የእኛ አገር ሁኔታ ግን ኢንተርኔቱ በልዩ ሁኔታ ካልሆነ በቀር ስለማይሠራ የኔትወርክ አለመኖር ጉዳይ ባንኮቹ በዘረጉት ሥርዓትና አስተማማኝነቱ ላይ የሚወሰን ነው፡፡ በአውስትራሊያ ባንኮች ከደንበኞቻቸው ትዕዛዝ ከተቀበሉ በኋላ በኔትወርክ ላይ ወይም በባንኮቹ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ላይ በደረሰ ችግር ትዕዛዙን ሳይፈጽሙ ከቀሩና ደንበኛው ጉዳት ከደረሰበት ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡ ባንኮች ኔትወርክ አልነበረንም በማለት ከኃላፊነት ሊሸሹ እንደማይችሉ ሕጉ በግልጽ ይደነግጋል፡፡ የተለያዩ ባንኮች የክፍያ ሥርዓት መፈጸሚያ ኔትወርክ ቢጋሩና ክፍያ ያልተፈጸመው የባንኮቹ የኅብረት ኔትወርክ ባለመሠራቱ ቢሆን እንኳን ከኃላፊነት ነፃ አይሆኑም፡፡ በአገራችን ያሉ ባንኮች የኔትወርክ ችግር ምንጭ ሁለት ሊሆን ይችላል፡፡ በአንድ በኩል የባንኮቹ የውስጥ የኢንተርኔት ሥርዓት መበላሸት (ሰርቨር ብልሽት፣ ሥራ ላይ የዋለው ሶፍትዌር ጥራት አለመኖሩ፣ ከሠራተኛ አጠቃቀም ጉድለት፣ ጄኔሬተር ካለመኖር ወይም በኮምፒውተር ቫይረስ) ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የኢንተርኔት አገልግሎቱን ከሚሰጠው አካል ኢትዮ ቴሌኮምና አጋዥ የመንግሥት ድርጅት (የኤሌክትሪክ ኃይል ባለሥልጣን) ምክንያት የሚመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ችግር አገራዊና በዕለት ተዕለት ኑሮአችን ቋሚ ምስክር የሆንለት ነው፡፡ በሁለቱም ምክንያት ለሚከሰት የኔትወርክ አለመኖር ምክንያት ባንኮች ያለባቸውን ኃላፊነት የሚገዛ ዝርዝር ሕግ ባለመኖሩ ለኃላፊነት ምንጭ የሚሆነው በባንኩና በደንበኛው መካከል የተገባው ውል ነው፡፡ ይህ ውል ደግሞ ባንኮች በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት ያለባቸውን ግዴታ የማያስቀር በመሆኑ ባንኮቹ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡ ከባንኩ ጋር የተፈጸመ ውል ባይኖር ደግሞ ባንኩ ከውል ውጭ ኃላፊነት ሊጠየቅ ይችላል፡፡ ባንኮቹ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1792 መሠረት ከአቅም በላይ የሆነ ኃይልን /Force majeure/ እንደ መከላከያ በመጠቀም ከኃላፊነት ሊድኑ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም በአገራችን የኔትወርክ መቋረጥ፣ ብልሽት ወይም አለመኖር እንኳን በኢንተርኔት ባንኪንግ ለሚሠሩት ባንኮች ሙያው ላልሆነ መንገደኛም የታወቀ፣ ዱብ ዕዳ ሊባል የማይችል ነው፡፡ ባንኮቹ ችግሩን ከሕዝቡ በተሻለ በመረዳት አማራጭ ሊያበጁለት፣ በዕቅድም ሊፈቱለት የሚችሉት ነው፡፡ ቢጠፋ ቢጠፋ ለዘመናት በተለመደው ትውፊታዊ የባንክ አሠራር መሠረት ደንበኛውን ሊያስተናግዱት ይችላሉ፡፡ የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ በረቂቅነት በነበረበት ጊዜ የአዋጁን የተፈጻሚነት ወሰን በአንቀጽ 2 ደንግጎ ነበር፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት አዋጁ በባንኮችና ፋይናንስ ተቋማት ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን የገለጸ ሲሆን፣ የኢንተርኔት ባንኪንግ አጋዥ ተቋማት (ቴሌና መብራት ኃይልን የመሰሉት) በአዋጁ ኃላፊነት እንደማይኖርባቸው ተደንግጎ ነበር፡፡ ድንጋጌው ‹‹It does not directly govern the rights and duties of third parties, such as operators issuing access methods who are not financial institutions nor their parties in an electronic fund transfer network such as merchants›› በሚል አስቀምጧል፡፡ ይሄም ለኢንተርኔት ባንኪንግ መቋረጥ ወይም ኔትወርክ አለመኖር ምክንያቱ ኢትዮ ቴሌኮም ቢሆን እንኳን ኃላፊነት እንደማይኖርበት ለመግለጽ ነው፡፡ በአዋጁ የመጨረሻ ይዘት ላይ ድንጋጌው ባይቀመጥም ሦስተኛ ወገኖችን ኃላፊ የሚያደርግ ምንም ዓይነት ድንጋጌ የለም፡፡ ከዚህ አንፃር ደንበኞች በኔትወርክ አለመኖር ለሚደርስባቸው ጉዳት ኃላፊነቱ የባንኮቹ ስለመሆኑ በቂ አስረጅ ነው፡፡ ከኢትዮ ቴሌኮም ውጭ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጥ ተቋምም ባለመኖሩ ባንኮች ኃላፊነታቸውን ሊጋራ የሚችል አካል እንደሌላቸው ልብ ይሏል፡፡ ባንኮቹ ከቴሌ ጋር የአገልግሎት ስምምነት (Service level agreement) በመፈጸም ኃላፊነታቸውን ኢትዮ ቴሌኮም እንዲሸፍንላቸው ያደረጉትም ጥረት የተሳካ አይመስልም፡፡ ከቴሌ በተጨማሪ መብራት ኃይልም በጉዳዩ ስላለበት የኃላፊነት መጋራቱን ለመፈረም ፈቀደኛ አይሆንም፡፡ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው የሞባይልና የባንክ አገልግሎት በውክልና ለመስጠት የሚያስችለው መመርያ ባንኮቹ የኢንተርኔት መኖርን፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን፣ የአንቲ ቫይረስ ጥበቃ ወዘተ. በማጠናከር አገልግሎቱን እንዲሰጡ ያስገድዳል፡፡ ይህም ባንኮቹ የኢንተርኔት ባንኪንግ ከመጀመራቸው በፊት ሰፊ ጥንቃቄ በማድረግ ኔትወርክ በማይኖር ጊዜ ደንበኞችን በተሻለ ስለሚያገለግሉበት ሁኔታ ሥርዓት ማበጀት እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው፡፡ እንደ መፍትሔ ባንኮቹ የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት ለመስጠት የተነሳሱት በብሔራዊ ባንክ መመርያ አስገዳጅነት በመሆኑ ለሥርዓቱ በቂ ዝግጅትና ተቋማዊ አቅም አልነበራቸውም፡፡ አንዳንዱ ባንክ እንዲያውም በውድድር መንፈስ ኢንተርኔት አገልግሎቱን በብዙ ገንዘብ ከመግዛት ውጭ ለቀጣይ ሥራ የሚያድግበትን፣ ደኅንነቱን ጠብቆ የሚሠራበትን፣ ችግርም ሲያጋጥም በምትክ ደንበኛን ለማገልገል የሚያስችል ሥርዓት አልቀረጹም፡፡ ለዚህም ነው በየቅርንጫፉ ብዙ ደንበኛ ታቅፈው ኔትወርክ ጠባቂዎች የሆኑት፡፡ ደንበኞች በኔትወርክ አለመኖር ምክንያት በየፍርድ ቤቱ ወይም በሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ክስ እየመሠረቱ ባንኮች ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት ባንኮቹ የተወሰኑ ችግር መቀነሻ ዘዴዎችን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ አንደኛ የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት ውል ማዘጋጀትና ከአቅማቸው በላይ በሆኑ ኔትወርክ መቋረጦች እንዳይጠየቁ የውል ቃል ማስፈር፡፡ እንዲህ ዓይነት ይዘት ያለውን ውል ለመፈረም ለማይፈቅድ ደንበኛ እስከ ዛሬ በሚሠራበት የወረቀትና የታይፕ አገልግሎት ማስተናገድ ተገቢ ነው፡፡ ባልቻልነው ቴክኖሎጂ ከመጨነቅ ከዕድገታችን ብዙም ያልራቀውን አስተማማኙን ልማዳዊ አሠራር መቀጠል ይችላል፡፡ ሁለተኛው ኔትወርክ በተቋረጠ ጊዜ በየመስኮቱ በኩራት ‹‹ኔትወርክ የለም›› ብሎ ደንበኛን ከማስቀየም አማራጭ የአገልግሎት ዕቅድ (Contingency Plan) አዘጋጅቶ ለደንበኛ አገልግሎት መፈጸም፡፡ ቢያንስ ሒሳብ በከፈቱበት ቅርንጫፍ በወረቀት ወይም በመተማመኛ እንዲስተናገዱ በማድረግ ኔትወርክ በመጣ ጊዜ ወደ ሲስተሙ ማስገባት፡፡ በመጨረሻም ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የባንኮችን ሥርዓት በተሻለ ፍጥነትና ደኅንነት አገልግሎት የሚሰጥ የኢንተርኔት ኔትወርክ እንዲኖር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር መሥራት፣ መንግሥትን በብሔራዊ ባንክ በኩል መወትወት እንዲሁም ሁለተኛ የኢንተርኔት አቅራቢ ተቋም የሚኖርበት ሁኔታ እንዲፈጠር መታገል ያስፈልጋል፡፡ ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡