Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉከምርጫው ተዋናዮች ምን ይጠበቃል?

ከምርጫው ተዋናዮች ምን ይጠበቃል?

ቀን:

በጉተማ ዘለዓለም ‹‹በ2007 ዓ.ም. በአገራችን የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ነፃና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንዲሠሩ መንግሥት የሚጠበቅበትን ሁሉ ያደርጋል፡፡ ሁሉም ተዋናይ ወገኖችና ዋናው ፈራጁና ወሳኙ ሕዝብ በአገራችን የተፈጠረውን ሰፊ የሐሳብ ግብይት ዕድል በመጠቀም ደረጃ በደረጃ እየጐለበተ የመጣውን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን ኃላፊነት በተሞላት መንፈስ ወደ ሌላ ከፍታ ማሸጋገር ይጠበቅብናል፤›› ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በመስከረም 2007 ዓ.ም. የፓርላማና ፌዴሬሽን ምክር ቤት የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የተናገሩት ሐሳብ ነበር፡፡ 2007 ዓ.ም. ግንቦት ወር አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄድበት ጊዜ ነው፡፡ አገሪቱ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በመገንባቱ ሒደት ውስጥ የተለያዩ የዲሞክራሲ ውጣ ውረዶችን አሳልፋ ልምዶችን የቀመረች እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይሁንና ከታሪካችንም ሆነ ከአኗኗራችን የሚቀዳው የፖለቲካ ጉዟችንና የዲሞክራሲ ግንባታ ሥርዓቱ እያደገ የመጣ ነው ሊባል አይችልም፡፡ በጣም ብዙ ይቀረዋል፡፡ የመንግሥት ሕግ የማውጣት፣ የማስፈጸም አቅም፣ የሕዝቡ የግንዛቤ ደረጃና ዓለም አቀፉ ሁኔታ ዲሞክራሲን ለማሻሻል ምቹ ሁኔታ ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የምርጫ ፖለቲካ ቁልፍ ባለድርሻ የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን ያደጉት በቁጥር ብቻ ነው፡፡ ሰባ ደርሰዋል መሰለኝ፡፡ በፖሊሲ አማራጭ አቀራረብ፣ በትግልና በዓላማ ፅናት መገለጫዎች፣ ወደ ሕዝቡ ወርዶ አባልና ደጋፊ እንዲሁም የፋይናንስ እገዛ በማሰባሰብ የተስተዋለ ዕድገት የለም፡፡ እንዲያውም እንደ ምርጫ 97 ካሉ የምርጫ ፉክክር ከፍታዎች (Climax) አንፃር ሲታይ ወርደው የታዩ ይመስላሉ፡፡ በአገራችን ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕድገት ያላሳዩበት ሌላው ሀቅም የሕዝቡን የዘመናት ‹‹ተባበሩ ወይም ተበታተኑ›› መፈክር አዳምጠው ዘወትር መበታተንን መምረጣቸው ነው፡፡ በፖሊሲና በስትራቴጂ ቅርርብን ፈጥሮ በታዳጊ አገር ውስጥ ያለ ጠንካራ የፖለቲካ ተወዳዳሪ ከመሆን ይልቅ፣ በትንሽ በትልቁ መለያየትና መነጣጠልን እንደገፉበት ነው፡፡ ቅንጅት፣ ኅብረት፣ መድረክ፣ ጥምረት … የሚሉ የፓርቲ ጥረቶች ደርሰው ፍሬ አፍርተው አልታየም፡፡ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በኩልም ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው የሚያግዙ ለውጦችን በማምጣት ላይ እመርታ ሊታይ አልቻለም፡፡ እንዲያውም ‹‹ሕግና ሥርዓት›› ዘረጋሁ በሚል የፖለቲካ ምኅዳርን የማጥበብ፣ የሐሳብ ነፃነትና የመደራጀት ሒደቶችን የመጋፋት ተግባር ውስጥ እየገባ መምጣትን ተደጋግመው በሚነሱ አስተያየቶች እየተደመጠ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ዲሞክራሲን የሚቃኝበት ሥነ ሐሳብ በራሱ ችግር አለበት፡፡ አንዱ ጉድለት የፓርቲና መንግሥታዊ መዋቅሩ መለያትና የመንግሥት ገለልተኛ ሚና ባለመታየቱ ዜጐች ነፃ አስተሳሰብ እንዲያራምዱ ከማድረግ ይልቅ ‹‹ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት›› በሚለው የነቻይና ተሞክሮ ፓርቲና መንግሥቱን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም በአንፃሩ ግዙፍ የሆነውን የመንግሥት የሰው ኃይል፣ ግብዓትና የሎጂስቲክስ ሥርዓት ኢሕአዴግ በስፋት እየተጠቀመበት ነው፡፡ በዚህም ሲቪል ሰርቨሱ ውስጥም ሆነ በሌላው መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ከኢሕአዴግ አስተሳሰብ ውጪ የሆኑ አማራጮች የማይተነፈሱበትና የማይታዩበት ሆኗል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ ከሰፈሩት መብቶች ጋር በእጅጉ ይጣረሳል፡፡ ኢሕአዴግ በፓርቲነቱ የራሱ አባላትና ደጋፊዎች፣ ሊግን የመሳሰሉ የሚተኩት ወጣቶችና ሴቶችን ማደራጀቱ መብቱ ብቻ ሳይሆን ኃላፊነቱም ነው፡፡ ነገር ግን ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው እንዲመለምሉና እንዲያደራጁ በመደገፍ ረገድ አልተሳካለትም፡፡ እንዲያውም እንደ ሶሻሊስታዊ ፓርቲዎች በገለልተኛ የሙያና የሲቪክ ማኅበራት ውስጥ ሳይቀር እጁን ለመስደድና አሻራውን ለመጣል የሄደበትን ርቀት የሚተቹ አሉ፡፡ ወደ ገጠርና ክልል ዝቅ እየተባለ ሲመጣም በሕጋዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ በሚንቀሳቀስ ፓርቲ አባልነትና ደጋፊነት መጠርጠር አይደለም መገመት እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍልና በፀረ ኢሕአዴግነት የሚያስፈርጅ ሆኗል፡፡ እንግዲህ የምርጫ ተዋናዮችን ድክመትና ጥንካሬ እያሳየን ብንሄድ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ ማኅበራትና የምርጫ ታዛቢ አካላት፣ የዳኝነትና የፀጥታ አካሉ፣ ራሱ ሕዝቡን እየመዘዙ ማየት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መቀጠል ያለፈውን ድክመት ደግሞ ደጋግሞ ከመውቀጥ ይልቅ ምርጫ 2007ን በማሰብ ከወዲሁ ከምርጫ ተዋናዮች የሚጠበቁ ተግባራትን በመጠቃቀስ ለውይይት በር መክፈት የሚሻል ይመስለኛል፡፡ በዚህ በኩል ሪፖርተር ጋዜጣም የተለያዩ አስተያየቶችን ብናራምድበት ቅር የሚሰኝ አይመስለኝም፡፡ ባለትልቅ ሸክሙ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ዘወትር ተቃዋሚዎች ገለልተኛ ካለመሆኑም በላይ የመፈጸም አቅሙ አልዳበረም ሲሉ ይተቹታል፡፡ መንግሥትም ሆነ ራሱ ቦርዱ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ልምድ እያካበተ መመጣቱ፣ በሰው ኃይልና በሎጂስቲክስ ዕድገት እንዲመጣ ያስረዳሉ፡፡ በእርግጥም ተስፋ ሰጪ ለውጦች የመጣባቸው መስኮች አሉ፡፡ አንደኛው ከምርጫ 2000 የክልልና የማሟያ ምርጫ በኋላ በመቀጠልም ምርጫ 2002 ላይ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችን አሻሽሎ በመንደፍ፣ እዚህ ላይ በአንዳንዶቹ ሰነዶች ላይ ፓርቲዎችም ተሳትፎ ስለነበራቸው ሥራ ላይ አውሏል፡፡ ከሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ፣ ከፓርቲዎች የምርጫ ምልክትና ምዝገባ፣ ከመገናኛ ብዙኃን የምርጫ ዘገባ ሥነ ምግባር፣ ከምርጫ ቅስቀሳና ዕጩ ማስተዋወቅ ጋር በተያያዘ ግልጽ የሕግ ማዕቀፎችን አውጥቷል፡፡ አተገባሩ ላይ ግን አሁንም ስምምነት አለመኖሩም ይታያል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ የመጣው ያልተሻሻለ ‹‹የአፈጻጸም ችግር›› እየረገጠው እንጂ መመርያዎቹ ፓርቲዎችን፣ ሕዝቡንም ሆነ መንግሥትን የሚያስገድዱም ናቸው፡፡ በገለልተኝነትም ሆነ ከሌላው ዲሞክራሲ አራማጅ አገር የምርጫ የሕግ ማዕቀፎችም የተለዩ ናቸው ብሎ መውሰድ ያስቸግራል፡፡ እነዚህን ሰነዶች በስፋት ወደ ሕዝቡና የሚመለከታቸው አካላት ለማድረስም የኅትመትና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው ላይ መግፋት ይገባል፡፡ ሁለተኛው የቦርዱ መልካም ጅምር የዘንድሮውን ምርጫ አስመልክቶ የሎጂስቲክስ፣ የሥልጠናና የምርጫ ትግበራ ሥራዎችን በመለየት ከአምስት ወራት ቀድሞ መርሐ ግብር አውጥቶ እንቅስቃሴ መጀመሩ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹‹አፋጣኝ ምላሽ አላገኘንባቸውም›› የሚሉዋቸው የምርጫ ምልክት፣ የስያሜና የመቀናጀት ፈቃዶች ቢኖሩም ለመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍና ቅስቀሳ ለማካሄድ ተቸገርን ሲሉ ይሰጣሉ፡፡ ምርጫ ቦርድ ሕጉ በሚፈቅድለት አኳኋን ፈጥኖ ጥረት ሲያደርግ ባይታይም ጅምሩ በበጐ መታየት አለበት፡፡ ነገር ግን በጣም ብዙ ይቀረዋል፡፡ በምርጫ ወቅት ብቻ ሳይሆን በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ቁልፍ ሚናና ከባድ ሸክም ያለበት ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ግን አሁንም ካለፈው ጊዜ ትምህርት በመውሰድ ማስተካከል ያለበት ጉዳዮች አሉ፡፡ እነሱን ወደ መመልከት መግባት ይሻላል፡፡ ቦርዱ ከምርጫ ጣቢያ እስከ ቦርዱ ዋና ጽሕፈት ቤት ድረስ የሰው ኃይሉን ማሟላቱ ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ ይህ ሲባል ደግሞ በዝውውር ወይም በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች እንደሚታማው ‹‹በኔትወርክ›› ባለሙያና አሠራር መሰብሰብ አይደለም፡፡ ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ ማስታወቂያ ወጥቶ፣ ተፈትኖና ተወዳድሮ አገር ማገልገል የሚሻ ገለልተኛ ኃይል እንዲገባበት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የአገራችን ፖለቲካ ከብሔር ማንነት ጋር ይበልጥ እየተቆራኘ እንደ መምጣቱ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን የሚወክሉ ሰዎች በገለልተኝነት በተቋሙ ቢሰባሰቡ ይበልጥ ይበጃል፡፡ የገዥውም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባልና ደጋፊ በቦርዱና በጽሕፈት ቤቱ ውስጥ መኖርም ገለልተኝነቱን ጥያቄ ውስጥ እንደሚከት ለአፍታም ያህል መዘንጋት የለበትም፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ‹‹ጥርስ›› ያለውና ማንንም የሚገስጽ መሆን አለበት፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት እንደታየው የአገሪቱ የዲሞክራሲ ባህል አዲስና ለጋ መሆኑ እየታወቀ፣ ምርጫ ቦርድ ቅጣትም ሆነ ማስጠንቀቂያ የሚሰጠው ለተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ብቻ ነው፡፡ የገዥው ፓርቲም ሆኑ የመንግሥት አካላት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለሚፈጽሙት ስህተት ተግሳጽም ሆነ ቅጣት መወሰኑ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ ይህም ‹‹ከሳሽም ዳኛም›› መንግሥት ነው ለሚል መላምት በር ከፍቷል፡፡ ስለዚህ ከየትኛውም ወገን ለሚታይ ጉድለት አስተማሪ ዕርምጃ በመውሰድ ፈጣንና የተደራጀ ውሳኔ ማሳለፍ የቦርዱ ድርሻ መሆን አለበት፡፡ ለምርጫ ሥራ ዋነኛ አጋዥ መሣሪያ መገናኛ ብዙኃን ሲሆን፣ በመረጃና በሐሳብ ነፃነት ላይ መመሥረትን ግድ የሚል ነው፡፡ በዚህ በኩል ተከታታይ ጋዜጣዊ መግለጫዎች መስጠት፣ በራሪና የኅትመት ውጤቶችን ማድረስ፣ ዘመኑ በፈጠራቸው ማኅበራዊ ድረ ገጾች መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ለመገናኛ ብዙኃን ሙያተኞች አመቺ የሆነ የመረጃ ቋት የመፍጠርና የግልጽነት ባህልን ማዳበርም ይኖርበታል፡፡ በዚህ በኩል ጥረቶች ቢኖሩም መጠናከር ግን ግድ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፍትሐዊነት የመገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ የሐሳብ ነፃነታቸው እንዳይገደብ፣ እንዲሁም መገናኛ ብዙኃንም በምርጫ አዘጋገብ ሥነ ምግባሩ መሠረት እንዲሠሩ ማድረግን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ መሥራትም ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ሲሆን ነው ከአንድ የምርጫ ዘመን ባለፈ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው የሚበጅ አሻራ ማሳረፍ የሚችለው፡፡ የምርጫው ሒደት ተጀምሯል፡፡ ባለፉት ሳምንታት አንድ እሑድ አገር አቀፍ የሕዝብ የምርጫ ታዛቢዎች ምርጫ ተካሂዷል፡፡ ከ200 ሺሕ በላይ የሕዝብ የምርጫ ታዛቢዎችም ተመርጠዋል፡፡ በሒደቱ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ አንስተዋል፡፡ የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ በግልጽነት ባለመካሄዱ እንዲደገም ጥያቄ እየቀረበ ነው፡፡ በዚህ መሀል የሚመረጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቃለ መሀላ ፈጽመው፣ ለዲሞክራሲና ለአገር ጥቅም የሚበጅ አስተዋጽኦ ለማበርከት የፈጸሙትን ስምምነት ጠብቀው በቃላቸው እንዲገኙ የምርጫ ቦርድም ኃላፊነት አለበት፡፡ በተለያዩ ሰነዶችና መመርያዎች ላይ ግልጽነት ከመፍጠር አንስቶ፣ በራስ መተማመን እንዲኖራቸውና የሕዝቡን ድምፅ እንዲያከብሩ አርዓያ ሆኖ ማስገንዘብ አለበት፡፡ እንዲህ ያለ ተግባር ‹‹የእናቴ መቀነት›› አደናቀፈኝ ብሎ ሰበብ ለሚደረድርም ሆነ ኮረጆ ሰርቆ የሕዝብ ድምፅን ለመስረቅ ለሚመኝ ኃይል ዕድል አይሰጥም፡፡ ለጫጫታና ለግርግርም በር ካለመክፈቱም ባሻገር ውጤቱንም ሕዝቡ በፀጋ እንዲቀበል ያስችለዋል፡፡ በቀጣይም የፓርቲዎቹ ታዛቢዎች፣ የዕጩዎች ምዝገባ፣ የፓርቲ ምልክቶች፣ የፓርቲ ውህደትና መነጣጠል ጥያቄ ጉዳዮች ከፊቱ ይገጥሙታል፡፡ የመራጭ ምዝገባ፣ የድምፅ መስጠትና የካርድ ቆጠራ ትልልቅ ሥራዎችንም በገለልተኝነትና በግልጽነት መሥራት ይኖርበታል፡፡ የተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሁኔታ የተለያዩ ጸሐፊዎች እንደሚገልጹት 70 የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቱ አሉ ማለት ለዓለም እንግዳ ነገር ይመስለኛል፡፡ የጥንካሬ ምልክትም አይደለም፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የአገራችን ፖለቲካ ዛሬም ድረስ ከብሔርና ከጐሳ ጀርባ ላይ አልወረደም፡፡ በዚህም በግልጽ ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ በዕውቀትና በዓላማ ከሚፎካከሩ ፓርቲዎችና የፖለቲካ መሪዎች ጋር መገናኘት አልተቻለም፡፡ እንዲሁም በአገሪቱ ሁሉም በብሔሮች ስም የተቋቋሙ ናቸው ባይባልም የብሔረሰቦቹን ቁጥር የሚተካከል ‹‹ፓርቲ›› ለምርጫ ሊወዳደር እየሞከረ ነው፡፡ በመነሻው ላይ እንደተጠቀሰው ከ20 ዓመታት በኋላ ይህን ማየት ‹‹ለውጡ መቼ ሊመጣ ይሆን?›› ቢያስብልም፣ ለዘንድሮው ምርጫ ከፓርቲዎች የሚጠበቁ ተግባራትን ማንሳት ግን ተገቢ ይመስለኛል፡፡ እውነት ለመናገርም ሆነ የአብዛኛውን ሕዝብ ግንዛቤ በጽሑፌ ለማስቀመጥ አሁን በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ‹‹አገር ለመምራት ይችላሉ›› የሚል እምነት ያለ አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ ለዚህ ያፈጠጠ ችግር ፓርቲዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ራሱ ሕዝቡ፣ መንግሥትና ኢሕአዴግም ከወቀሳ አይድኑም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ተፎካካሪዎቹ ቢቻል በዓላማና በፖሊሲ ከሚቀራረቧቸው ጋር መቀናጀትና መጣመር ይበጃቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁን ለአንዳንዶች ከሚታየው የሥልጣን ስግብግብ ፍላጐት፣ ፀረ ዲሞክራሲያዊ ባህርያትና መበጣበጥ መውጣት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከዚሁ ተነጥሎ የማይታየው ለምርጫው የሚሳተፉበትን ዓላማም በግልጽ አስቀምጠው መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ በእኔ እምነት የሚያስቀምጡት ግብ እንደ በፊቱ ቅንጅት በጣም የተለጠጠ (Over Ambitious) መሆንም የለበትም፡፡ በ1997 ዓ.ም. ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ያገኘው ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ በሦስት ወራት ጊዜ ተሰባስቦ ያውም በመተማመን እንኳን ውህደት ሳይፈጽም ውስጥ ውስጡን እርስ በርስ እየተባላ ግብ አድርጐ የተነሳው ኢሕአዴግን ከሥልጣን ለማንሳት ተወዳደሮ ማሸነፍ የሚል ነበር፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ወደ ሥልጣን ለሚመጣውም ሆነ ከሥልጣን ይወርዳል ለሚባለው በቂ ዝግጅት ያልተደረገበትና ግብታዊነት የተጫጫነው በመሆኑ መጨረሻው የዜሮ ድምር ፖለቲካ (Zero Sum Game Politics) ሆኗል፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን ባለው ደረጃ ጠንክሮ የሕዝብ ድጋፍን በማሰባሰብ አምስትም፣ አሥርም፣ ሃምሳም ሆነ አንድ መቶ የፓርላማ ወንበር ማግኘትና በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ውስጥ አንድ ደረጃ ከፍ ባለ ተፎካካሪነት ለመቀጠል መዘጋጀት ያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በተናጠልም ተወዳድሮ ፓርላማ ከተገባ በኋላ መጣመር ስለሚቻል፣ ግልጽና ተደራሽ የሆነ ዕቅድ ይዞ በክልልም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ መወዳደሩ ጠቃሚ ነው፡፡ የተፎካካሪው ፖለቲካ ኃይል ዘወትር እርግጠኛ መሆን ያለበት ሕጉና የዲሞክራሲ መርሁ የሚፈቅደውን ተግባር ብቻ እየፈጸመ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ነው፡፡ ለመቻቻልና ለውይይት እንዲሁም ለዲሞክራሲ ባህል ግንባታ የሚረዱ የመደማመጥና የፖለቲካ ጨዋነትም ሊርቁት አይገባም፡፡ ይህን በማድረግ በአንድ በኩል መንግሥት ‹‹ሕገ ወጥነትና ሕጋዊነትን እየደበላለቁ ነው›› ለሚለው ትችቱና ክሱ የሚከፍቱት በር አይኖርም፡፡ በሌላ በኩል እያደገ ለሚሄደው የአገር ግንባታና የዲሞክራሲ ሥርዓት የሚጠቅምም አይደለም፡፡ እዚህ ላይ መንግሥት አብላጫ ድምፁን ተጠቅሞ በሕጋዊ መንገድ ያፀደቃቸውና የአገር መመርያ ያደረጋቸው ሕጐችን ዋጋ መስጠትና እንደሌሉ መቁጠርም የሚበጅ አይደለም፡፡ ሥራ ላይ በዋሉ ሕጐች የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችና አነስተኛ ቀዳዳዎችም ቢሆን ለቅሞ መጠቀም እንጂ ሕግን አለማክበርና መጣስ መቼም ቢሆን ማስጠየቁ አይቀርም፡፡ ከዚህ ውጪ ‹‹ተፎካካሪ የፖለቲካው ጐራ አማራጭ የለውም መንግሥትን ብቻ ነው የሚተቸው›› ለሚለው የአንዳንዶች አስተያየት ፓርቲዎች ግልጽና የራሳቸው ለሆኑ ቁልፍ ፖሊሲዎች ቢያንስ የምርጫ ማኒፌስቶ ማውጣት አለባቸው፡፡ የመንግሥትን አፈጻጸምና ድክመት ወይም የፖሊሲ ክፍተትን እየመዘዙ መተቸት ግን የተፎካካሪው ብቻ ሳይሆን የሕዝቡም መብት ነው፡፡ በየትኛውም አገር ቢሆን ተቃዋሚ ፓርቲ የመንግሥትን ክፍተት አይደል እንዴ የሚተቸው? እሻላለሁ ለማለት እኮ የተፎካካሪን ጉድለት ማጋለጥና በመረጃ ላይ ተመሥርቶ ‹‹መጠዝጠዝ›› አንድ ሥልት ነው እንጂ መተቸት ሊያሸማቅቃቸው አይገባም፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ የተፎካካሪ ፖለቲካው ኃይል ሁሉንም በአንድ ጨፍልቆ ሲታይ የጀማመራቸው ጥረቶች አሉ፡፡ ጠቅላላ ጉባዔ፣ የምርጫ ምልክት፣ ተከታታይ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የሰላማዊ ሠልፍ ሙከራ፣ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ ወደ ሕዝቡ ወርዶ የፖለቲካ ፕሮግራምን ማስተዋወቅ፣ እስከ ገጠርና ክልል በመሄድ ደጋፊን ማናገርና አባላትን ማፍራት ግን በድፍረት ሊጀመር የሚገባው ነው፡፡ ትግሉ ምንም ያህል ቢኖር እስከ መጨረሻው መታገል ተገቢ ነው፡፡ በአገሪቱ መዲና ብቻ የሚደረግ እንቅስቃሴ እንደ አገር ሲታይ ኢምንት መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለሆነም በየአካባቢው ያለውን ዝምታ ማፍረስ፣ በዲሞክራሲያዊ መንገድ አማራጭ ሐሳብ ማንፀባረቅ መብት መሆኑን ማሳየት፣ በብሔራዊ ጥቅም ባለመደራደር ቀዳሚና አርዓያ ሆኖ መታየት ይገባቸዋል፡፡ በዚህ በኩል የፋይናንስ፣ የሰው ኃይል እጥረትና የመገናኛ ብዙኃንና የማኅበራዊና ድረ ገጾችን ለመጠቀም አቅም ላይኖር ቢችል እንኳ፣ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ አቋማቸውን ማሰራጨትና ወደ ሕዝቡ መድረስ ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብን ወደ ግጭትና ትርምስ በሚያስገቡ ድርጊቶችና ሕገወጥ ተግባራት ውስጥ እስካልገቡ ድረስ አስፈላጊውን መስዋዕትነት እየከፈሉ፣ የዜግነት ግዴታን መወጣት ለመጪው ጊዜ ዲሞክራሲ የሰፈነባት አገር ለመፍጠር ይረዳል፡፡ ጉዳዩ በብዕር እንደሚጻፈውና በንግግር እንደሚንበለበለው ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን ወደ ፖለቲካው መስክ ሲገባ የሚያስከፍለውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ተዘጋጅቶ ነውና በፅናት፣ ከጥላቻና ከፖለቲካ ጽንፈኝነት የወጣ የፖለቲካ ትግል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ ምርጫ 2007ን በተመለከተ ወደፊት የሚነሳውና የሚጣለው ጉዳይ ብዙ ነው፡፡ እኔም በአንድ ክፍል ብቻ የምርጫ ተዋናዮችን አሳስቤ በቃኝ ማለት አልቻልኩም፡፡ ስለሆነም ቀሪዎቹን ጉዳዮች በሚቀጥለው ሳምንት ተመልሼ ብነካካቸው ቅር የምትሰኙ አይመስለኝም፡፡ ለዛሬ እንሰነባበት፡፡ ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...