Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትኢትዮጵያ የነቃ አገር ወዳድነት ንቅናቄ ያስፈልጋታል

ኢትዮጵያ የነቃ አገር ወዳድነት ንቅናቄ ያስፈልጋታል

ቀን:

አገር መውደድ ማለት ምንድነው?

በበቀለ ሹሜ

ሃያ ሦስት ዓመት ያለፋቸው አዲሶቹ የኢትዮጵያ ገዥዎች የኢትዮ ኤርትራ ግጭት መጥቶ እስኪያባንናቸው ድረስ ታዳጊዎችን እንኳ በአገር ወዳድነት ስሜት የማነፅ እይታ ጠፍቷቸው ነበር፡፡ እንዲያውም አገር ወዳድነትን ከነፍጠኝነት ጋር አንድ አድርገው የሚፀየፉም ነበሩ፡፡ እስከ ዛሬ ያለው የቅርስ ስርቆትና የደኖችና የመናፈሻዎች ውድመት ሁሉ አገራዊ ተቆርቋሪነት የማጣት ጎን እንዳለው ልብ የተባለ አይመስልም፡፡ በክብረ በዓላት ወይም በሕዝባዊ ኮንፈረንሶች ላይ ለይምሰል የባህል ልብስ ለብሰው የባህል ምግብ ሲቀምሱ የሚታዩት ክቡራን ራሳቸው የውጭ ባህልና ሸቀጥ ቀለብተኛ የሆኑ አስመሳዮች ናቸው፡፡ የምናወራለት የአገር ፍቅር በደፈናው በባዕድ ባህልና ሸቀጥ ላይ በቅዋሜ የሚነሳ ወይም ‹‹እምዬ ኢትዮጵያ የነፃነትና የጀግንነት አምባ›› በሚል ወገንተኝነት ብቻ መወጠርን የሚሰብክ አይደለም፡፡ የምናወራለት አገር ወዳድነት ከዚህ ያለፈና እየተጠቃለለ ባለው ዓለም ውስጥ ለማደግ የሚገጥመንን ፈተና አሸንፎ ለመውጣት መሣሪያ የሚሆን ነው፡፡ ይህ አገር ወዳድነት፡- • የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዕድገት ዕጣ የተሳሰረ መሆኑን የተረዳ፣ የአንዱን አካባቢ ዕድገት በአጠቃላዩ ውስጥ፣ የአጠቃላዩን ዕድገት ደግሞ በአካባቢዎች ተያያዥ የልማት ቅንብር የሚያስተውል፣ በአንዱ አካባቢ ያለን ኋላቀርነትና ጉዳት የሁሉም ወይም የአገር አድርጎ የሚቆረቆርና የሚተጋገዝ አመለካከትና ተግባር ማልማት ነው፡፡ • በድህነት፣ በረሀብና በምፅዋት መታወቃችን አቃጥሎን እውነታውን ለመቀየር በሩቅም በቅርብም ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ልማት ወታደር ሆኖ መዋደቅ ነው፡፡ ባለን መኩራትና ባፈራነው መጠቀም ለዕድገት ያለውን እርባና የተገነዘበ የአኗኗር ዘይቤ ማዳበር ነው፡፡ እንግሊዞች ለረዥም ጊዜ የገዟቸው ህንዶች የማንነት መለያዎቻቸውን ይብዛም ይነስ አትርፈው ማቆየት ሲችሉ እኛ ነፃነታችንን አስከብረን ኖረናል የምንለው ግን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገር እያጣን ነው፡፡ ‹‹መዘመን››፣ ‹‹መሰልጠን›› የራስን ከማሳደግ ጋር የማይገናዘብና የፈረንጅ አኗኗርና አምሮት መቅዳት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ አገራዊ የሆነ ነገር፣ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ ሙዚቃ፣ ውዝዋዜ፣ ወዘተ ሁሉ ከቶ ዘመናዊ መሆን የማይቻለው ይመስል ምን ቢዘምን ‹‹ባህላዊ›› ከመባል አይዘልም፡፡ ተራው ሰው ብቻ ሳይሆን ምሁራኑና የየሙያው ጠበብት የሚባሉት ሰዎች ሁሉ የዚህ አመለካከት ተገዥዎች ናቸው፡፡ የውጭ የሙዚቃ መሣሪያና ምት ያልገባበት ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ፣ ዘመናዊ እስክስታ፣ ጭፈራ፣ ወዘተ ብሎ ማለት ግርታ የሚፈጥር እንግዳ ነገር ነው፡፡ ዛሬማ የራስን ምንነት ፍቆ በፈረንጅ ቅጅነት ለመተካት የሚደረገው እንቅስቃሴ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የጠነከረ ይመስላል፡፡ የመንግሥት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሳይቀር ‹‹ሥልጣኔውን›› እያስፋፋ ይገኛል፡፡ የአውሮፓውያንን አዲስ ዓመትና የልደት በዓል አከባበር ተምረን ጨርሰን እነ ‹‹ቫላንታይን›› እነ ‹‹ምሥጋና ቀን›› ውስጥ ገብተናል፡፡ ‹‹እንወዳችኋለን›› ማለትን ተለማምደናል፡፡ የአውሮፓ አሜሪካ ምርጥ ዘፈኖችና የፊልሞች ዝርዝርና በየጊዜው የሚያገኙት የተወዳጅነት ደረጃ የፋሽን፣ የፊልም፣ የዘፈን ውድድርና የሽልማት ሥነ ሥርዓታቸው ሁሉ ይቀርብልናል፣ ይወሳልናል፡፡ የፋሽን (የልብስ የፀጉር) የዳንስ፣ የቁንጅና ውድድር ሁሉ (እዚያም ውስጥ በሙስና እየተጨማለቅን አልሳካልን አለ እንጂ) ተያይዘናል፡፡ ወዘተ. ወዘተ ከእነዚህ ቀላል ምሳሌዎች በመነሳት የለየላቸው የአመንዝራነትና የውንብድና ፊልሞች በከተማ ወጣቶች ላይ ምን ያህል የመራዥነት ሥራ እንደሚሠሩ መገመት አያዳግትም፡፡ በዳዴ ደረጃ ላይ ያሉት የአገራችን (የቪዲዮም ጭምር) የፊልም ሥራዎችም ስንት ያልተነካ አገራዊ የሕይወት ገጽታ እያለ ሆሊውዳዊ የስሜት አገላለጽ፣ የአነጋገርና የአካሄድ፣ የፍቅር ትሽሽት ዘይቤን፣ የስር፣ የግድያ ፍልስፍና፣ የካራቴ ድብድብ መዋቅርን ለመኮረጅ ሲጥሩ ይታያሉ፡፡ በቴሌቪዥንና በቪዲዮ የሚቀርበው ‹‹ባህላዊ›› ተብየው ሙዚቃ ሁሉ በወሲብ አነቃቂ አለባበስና እንቅስቃሴ እየተፈተፈተ መጥቷል፡፡ የከተማው ወጣት በወሲባዊ ሥራዎች፣ በጫት፣ በመጠጥና በሐሽሽ እየቄለ የኤድስ ቫይረስ መዛመቻ ቢሆን አያስገርምም፡፡ የከተማው ሰደድ በተለያየ መንገድ ከገጠሩ ጋር ይጣቃሳል፡፡ አዲሱ ትውልድን ከዕልቂት ማትረፍና ማልማት ያልቻለ ኅብረተሰብ ዕድገትን ሊያገኛት አይችልም፡፡ ኤድስ በኮንዶምና በስብከት አይሸነገልም፡፡ ዋና መሸነፊያው በወጣቱ አካባቢ ያለውን ሙያና ዕውቀት የለሽነት፣ ተስፋ ቢስነትና ቦዘንተኛነት በመምታት ወጣቱ በተሻለ ሕይወት እንዲታገል ማስቻል ነው፡፡ በዚህ በኩል እየተስፋፋ ያለውን የሥልጠናና የትምህርት ዕድል በመደበኛም ይሁን በልዩ ፕሮግራም ትርጉም ያለው የሙያ ክህሎትና ዕውቀት እንዲያስጨብጥ አድርጎ ማሳካት ዋነኛ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር አላሻቂ ሁኔታዎችን፣ በቤተሰብ ላይ ሐሳብ የመጣልን ዝንባሌና ዝቅተኛ ሥራ ተፀያፊነትን በሚያዳክሙ በራስ መተማመንን ተፍጨርጫሪነትንና ኃላፊነትን በሚያለማምዱ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ወጣቱን መምራት ነው፡፡ ይህም በገንዘብና በቁሳቁስ፣ በዕውቀትና በሙያ እገዛ ምክርና ልምድን በማካፈል፣ በጋዜጣ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንም ሆነ በመድረክ በሚቀርቡ ሥነ ጽሑፎች፣ ተውኔቶችና ፊልሞች እስከ መኮርኮር ሁሉን አቀፍ ርብርብን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህን የወጣቱን ዕምቅ ኃይል ሥራ ላይ ማዋል ከቻልን በእርግጥ ለልማት እየሠራን ነው ማለት ይቻላል፡፡ የፈረንጅ አምላኪነት መገለጫው ብዙ ነው፡፡ ዘናጭ የቢሮ ወይዛዝርት የውጭ ውራጅ ጫማ ሲገዙ የነበሩት ድህነት አስገድዷቸው አይደለም፡፡ የሚሻል የአገር ውስጥ ምርት እያለ ‹‹የውጭ እኮ ነው›› ለማለት ሲባል የውጭ አይረቤ ምርት ሲያጣሩ የሚውሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ነጋዴዎችም ፈረንጅ ሲቀምም፣ አገልግሎት ሲሰጥ ወይም ሲገዛና ሲያደንቅ የሚያሳይ ማስታወቂያ ማሠራትንና ‹‹ከውጭ አገር የተመረተ›› ብሎ ማስተዋወቅን በገበያ መሳቢያነት ይጠቀሙበታል፡፡ ለንግድ ድርጅቶች (ለምርቶችና አገልግሎቶች ጭምር) የፈረንጅ መሰል ስም ማውጣትም የተለመደ ሆኗል፡፡ ነባር የአገር ስሞችም በአሁኑ አያያዝ ከከተማና ከአገር ወጥተው የሚያልቁበት ጊዜ እየቀረበ ይመስላል፡፡ (በዚህ አገር የማይመዘገብ ጉድ ስለሌለ ነው እንጂ የሚገርመው ደግሞ ይህንን የሚያግዝ፣ የሚያበረታታና ‹‹ሽልማት›› የሚሰጥ የመንግሥት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤት መኖሩ ነው) ይህ ዓይነቱ የውጭ ምርኮኝነት መፍረስና በማንነቱ የሚኮራ በአገር ውስጥ ምርት ንቁ ተጠቃሚ የመሆን (ጉድለቶችን የመጠቆምና እንዲሻሻል ግፊት የሚያደርግ) ኃላፊነት የሰረፀው ዜጋ መፍጠር መቻል አለብን፡፡ ዛሬ ከአጭበርባሪነት ብዙም የማይለየውን ነጋዴነትን ሥልጡን ለማድረግ፣ የውጭ ትርኪ ምርኪ ሸቀጥ ወኪል በመሆንና ኢትዮጵያዊ ስም እያስያዙ የውጭ ሸቀጥ በማሻሻጥ የሚመካውን ባለሀብት አገራዊ እይታ ልናስታጥቀው፣ የሚበጁ የሥራ አማራጮች ልናሳየው፣ ልናማክረው፣ ከዘመናዊ የሥራ አመራር ዕውቀት ጋር ሀብቱን እያስተባበረ ወደ ጎሉ ሥራዎች እንዲገባ ልናግዘው ያሻል፡፡ በዚህ አቅጣጫና በአጠቃላይ ከድህነት ጋር በሚደረገው ትግል ውስጥ ሊቃውንትና ዩኒቨርሲቲዎች ‹‹ምርምር ሁሉ ቀጥታ ከተግባር ጋር ላይተሳሰር ይችላል›› ብሎ መከራከር ይቀርና ጎትጓች እስኪመጣ ቢጠብቁ አሳፋሪ ነው፡፡ የአገሪቱ ችግሮች ሁሉ መወያያ፣ መመራመሪያና መፍትሔ መፍለቂያ፣ የሥልጠናና የምክር ድጋፍ መገኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህን ትልቅ ድርሻ ሳያሟሉ ስለአገር ፍቅር እንዴት ሊወራ! የተሻለ የሥራና የገቢ ዕድል ወዳለበት አገር ሄዶ መሥራት ነውር የለውም፡፡ ከእኛ የተሻሉ አገሮች በሥራ አጥነት ማስተንፈሻ የሚጠቀሙበት ነው፡፡ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ጎረቤቶቻችን ለሥራ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ መንግሥትም ከውጭ የሥራ ዕድሎች ጋር ባህልና ሕግ ነክ መረጃዎችና የምክር አገልግሎቶች ተሟልተው የሚገኙበትን ሕጋዊ መንገዶች ማመቻቸት ይኖርበታል፡፡ በውጭ በሚሠሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በአግባቡ ለመከላከልና ለመጠየቅ አለመቻል አስጊ (ወይም ሆስታይል) ሁኔታዎች ሲኖሩም ከማሳወቅ እስከ ጉዞ ማገድና ዜጎችን እስከ መጥራት የሚደርስ ዕርምጃ አለመውሰድ ሊያስጠይቅ መቻል አለበት፡፡ የሚያስጠይቅ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ ወደ ውጭ አገር የሚወጣው/የሚሰደደው ሥራ ያጣ ብቻ አይደለም፡፡ ‹‹ፖለቲካዊ›› ምክንያታችንን እንተወውና አብዛኛው አውሮፓና አሜሪካ መሄድን ገነት የመግባት ያህል አድርጎ የማየት ምርኮኛ ነው፡፡ የተማረው ባለሙያ ሳይቀር ሄዶ ‹‹ኩሊ›› ለመሆን በዲቪ ተራ ከወጣቱ ጋር ሲሻማ ይታያል፡፡ ቤት ሸጦ ተበድሮ ይነጉዳል፡፡ የውሸት ባልነትና ሚስትነት በብዙ ሺሕ ብሮች ይሸጣል፡፡ በአሜሪካ ኤምባሲ ላሉ የውስጥ ‹‹ጉዳይ አሳኪዎች›› የሰባ ጉቦ ይከፈላል፡፡ ያንንም ከፍሎ ቀልጦ የሚቀር አለ፡፡ የአሜሪካ ኤምባሲም ከፍተኛ ከፍያዎች አበጅቶ ያራቁታል፡፡ ቪዛ ጠይቆ እምቢ ወይም እሺ ለመባል ብቻ በአሁኑ ተመን መቶ ስድሳ ዶላር ያስከፍላል፡፡ በውድ ወጪ ወደ ‹‹ገነት›› አሜሪካ ከገባ በኋላ ሐበሻ አፈር ድሜ እየጋጠ ዕዳ መክፈል ይጀምራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አሜሪካ፣ እንኳን እዚያው የተለፋበትን ይቅርና ከውጭ ጥሪት እየሳበ የማስረገፍ ብርታት ያለው ጮሌ ሥርዓት ነው፡፡ በመዓት አምሮቶች ከቦ፣ ከአዲስ መጥ ቁሳቁሶች ጋር አኗኗርን በማስተካከል እሽቅድድም ውስጥ ጠልፎ፣ በገናና በአዲስ ዓመት የሸቀጥ ግዥ ጎርፍና በዱቤ የቤት ግዥ፣ ወዘተ ውስጥ እዚያው አቅልጦ ለማስቀረት የሚታገል ሥርዓት ነው፡፡ በማይሻሻለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ተመርምሮም ይሁን በመቆየት ብዛት በሄደበት አገር ለምዶና ኑሮዬ ብሎ የቀረ ጥቂት አይደለም፡፡ መልመድ አቅቶት በቁጭት የሚብከነከን አገሬ ልግባ ብሎ መጥቶ ተመልሶ የሚሄድም አለ፡፡ እዚያው ሆኖ ለቤተሰብ ቀለብ የሚቆርጥና ወላጆቹን ጠርቶ ‹‹ዓለም በማሳየት›› የምኞታቸውንና የምኞቱን የሚያደርስም አለ፡፡ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ግን ከዚህ በላይ አርቆ ማለምን ትጠይቃለች፡፡ በውጭ ካሉ ኢትዮጵያውያን በኩል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢንቨስትመንትና በልማት እገዛዎች ከበፊቱ የተሻለ ተሳትፎ እየታየ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የዳያስፖራው ጉዳይ የከፍተኛ መድረኮች የውይይት ርዕሰ ጉዳይም ሆኗል፡፡ በእንዲህ ያሉ ወይይቶች ውስጥ በተለይ ከሁሉም በላይ በመንግሥት በኩል መመቻቸት ስላለባቸው ነገሮች በጣም ብዙ ተብሏል፡፡ የሚባለውም እውነት ነው፡፡ ትክክል ነው፡፡ እነዚህ መድረኮች ግን ብዙ ጊዜ ራሱን ዳያስፖራውን የሚመለከተውን ዋነኛ ጥያቄ አይዳስሱትም፡፡ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ዕድገት ላይ የሚያበረክቱት የአስተዋጽኦ መጠን በመንግሥት አቀራረብና እንክብካቤ መለካት አለበት ወይ? በውድም በግድም እየተጎተጎቱና ጫና እያሳረፉ ለአገር ዕድገት መዋደቅ የአገር ወዳድነት ኃላፊነት ነው፡፡ ከቅንጦት ከመቆጠብ በላይ ተቸግሮ እየኖሩ ገንዘብ መቋጠርን፣ የቋጠሯትንም ገንዘብ አትራፊ በሆነ ሥራ ውስጥ አሰማርቶ ማባዛትን፣ አገር ቤት ያለው መንግሥት ይድላም ይጎርብጥም ትርፍን ወደ አገር ቤት እያፈሰሱ (ለቀለብ ሳይሆን) ለሥራ መክፈቻነት ማዋልን፣ ከዚህም ባለፈ የሚበጁ የሥራ ዓይነቶችን፣ ቴክኖሎጂዎችን፣ ምርምሮችንና የአሠራር ጥበቦችን እያነፈነፉና እየቀዱ ወደ አገር ቤት ማሸጋገርን ከእስያውያኑ ብንማር ከፍተኛ የዕድገት ኃይል መሆን እንችላለን፡፡ ይህንን ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት የመጀመሪያው ፈተና እዚያው ባሉበት መከፋፈልን አሸንፎ ከመያያዝ (ከመተባበር) ይጀምራል፡፡ በአገር ቤት ያለውም የእንግዳ ተቀባይነት ዝና አገራዊ ጥቅምን ማስተዋል፣ የገባው መሆን አለበት፡፡ ይህም ደርሶ ሂያጁን (ደርሶ ተመላሹን) በማራኪ አገልግሎቶችና ገበያዎች አስተናግዶ (የቱሪዝም ማስታወቂያ አድርጎ) ከመስደድ/ከመሸኘት አንስቶ ሥራ ሊከፍት የመጣውን የውጭ ባለሀብት ገብቶ እንዲቀር ሥራ ለማስፋፋት ትርፉን እንዲያውልና ሌላ ሥራ ከፍቶ እንዲጠራና እንዲስብ እስከማድረግ ይሰፋል፡፡ ይሁን እንጂ ለኮሪያውያኑ ሚንግ ዩንግ ሆስፒታል 90 ሸሕ ካሬ ሜትር ቦታ (አዲስ አበባ) በነፃ ሰጥቶ ዩኒቨርሲቲ ሊሠራ ላቀደው ተስፋ ድርጅት በ14 ሚሊዮን ‹‹በሊዝ ቦታ መሸጥ›› እና ሌሎች አገር በቀል የግል ኮሌጆች በኪራይ ሲሰቃዩ ዝም ብሎ ማየት ግን የጤና አይደለም፡፡ ሰብዓዊ ዕርዳታ ነፍስ ከማደንና እነ ፉርኖ ዱቄትን ከማስለመድ ባሻገር በዕርዳታ ምርኮኝነት ውስጥ ከትቶ ውስጣዊ የመፍጨርጨር ጥረታችንን አፍዝዞት ኖሯል፡፡ ከኮንትሮባንድ ገቢ ሸቀጦች ጋር ተጋግዞ የውስጥ ምርትን ማለትም የእህል፣ የዘይት፣ የደረቅ ምግብ፣ የብርድ ልብስና የአልባሳትን ዋጋ ህልውናና የማደግ ዕድል ሲያደቅ ቆይቷል፡፡ በደርግ ጊዜ ከተሜዎች ሲሻሙባቸው የነበሩ ለስላሳ ባለፀጉር ብርድ ልብሶች፣ ብስኩቶች፣ በኋላም ከአሜሪካ የበረሃ ማዕበል ዘመቻ ተርፎ በዕርዳታ ተራግፎ የነበረው የታሸገ ምግብ ሁሉ፣ የፈረንጅ አኗኗር አምሮታችንን የማባባስና ለውጭ ገበያ የማዘጋጀት ሚና ነበራቸው፡፡ የንግድ በሩ በምዕራባዊ ሸቀጦች በተበረገደ በአጭር ጊዜ ውስጥም እነሆ ከውጭ የማናስገባው የዕቃ ዓይነት የለም፡፡ አልጋ፣ ሙሉ ሶፋና መደርደሪያ ሳይቀር ከውጭ እንገዛለን፡፡ እነዚህን መሰሎችን ጣጣዎች ለማሸነፍ አንድ ዋና መሣሪያ ትርጉም ያጣውና የደነበዘው አገር ወዳድነታችን በዛሬው ፈጣን ዓለም ያለንን የጥቅምና የዕድገት አቅጣጫዎች በሚያሳውቅ ንቃት ነፍስ ዘርቶ እንዲሠራ ማድረግ ነው፡፡ ዕድገትን ከፈለግን ለአዲስ ነገር ፈጣንና ቅርብ የሆነውን አዲስ ትውልድ፣ አገራዊ ጥቅምን አሳውቆና በአዲሱ ሳይንስና ጥበብ አብስሎ በዛሬው የተራመደ ዓለም ውስጥ ማታገል የግድ ነው፡፡ አገራዊ ሕዝባዊ የፈጠራና የጥበብ ሀብትን ከመሬት ማንሳት ሌላው አቅጣጫ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ትንሿን ነገር ወደ ሥራና ወደ ገቢ ምንጭ የመለወጥ፣ አዲስ ነገር የመቅለብ፣ አትራፊና አክሳሪ አዝማሚያዎችን ፈጥኖ የመለየትና የመለኝነት ልምምድ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችና ግለሰቦች አሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በመርካቶ አዲስ ከተማ ስርጓጉጥና ሽረንቁላ ውስጥ ያለው አስታዋሽና አልሚ ያጣ የዕደ ጥበብ፣ የፈጠራና የኩረጃ ጥሬ አቅም ተዝቆ የሚያልቅ አይደለም፡፡ የሥዕላ ሥዕል፣ የቆዳ፣ የብረታ ብረት፣ የቅልመት ሥራዎች፣ ውዳቂ ዕቃዎችን ስብስቦ ቀጥቅጦና ጠጋግኖ ለአገልግሎት ማብቃት፣ የውጭ ቁሳቁሶችን በግርድፍ ዕደ ጥበብ አስመስሎ መሥራት፣ ዘመናዊ የተባሉ የውጭ ጫማዎችንና አልባሳትን ቀልቦ ከውጭ በማይለይ ጥራት ማቅረብ፣ ወዘተ መርካቶ ያልያዛቸው የለም፡፡ ይህን መሰሉ የፈጠራና የመቅዳት ችሎታ በሙያ ሥልጠና፣ በተሻለ መሣሪያ፣ በመረጃ፣ በቴክኖሎጂ ተደራጅቶ ወደ መሥራት ቢሸጋገር የአገር ውስጥ የፈጠራ ባለቤትነትን አክብሮ ፈጠራን በማትጋት፣ በሠለጠኑት አገሮች ከሚገማሸረው የጥበብ ሀብት ላይ ጨልፎ በመውሰድ መካከል ያለውን ልዩነት በጤናና በዘመናዊ የንግድ ሥራ ሥነ ምግባርንና ጥበብን ባጣጣመ መልክ ቢገራ፣ በኢንዱስትሪ ልማት ውስጥ ታምር ሊሠራ ይችላል፡፡ የሀገረሰብ የቤትና የቁሳቁስ አሠራር አካባቢያዊ የአየር ንብርትንና ጥሬ ዕቃን መሠረት የደረገ ዕድገትን እየተጠባበቀ ነው፡፡ የቀርከሃ ልማትና ጥበብ እንደ እስያኑ ቢተጋ ከተራው ሰው እስከ ባለፀጋው ቤት ድረስ ሥር ሊሰድ፣ የደን ጭፍጨፋንም ሊያስታግስ የሚችል ነው፡፡ የሀገረሰብ አልባሳት የሽመና ጥንቅርና አዘገጃጀት መዳበር፣ አልፎም የውጭ ገበያን ሊማርኩ የሚችሉበት ዕድል ገና አልተነካም ማለት ይችላል፡፡ የተጀማመረው ዘመናዊ የዲዛይን ሥራ ከሽመና ጥንቅር ጥናትና ሙከራ ጋር መተሳሰርን ይፈልጋል፡፡ በፈትል አልባሳት ጥበብ የበለፀገ ሀብት ካላቸው እንደ ህንድ ካሉ አገሮች ትምህርት መውሰድም ለዕርምጃ ይበጃል፡፡ ሽመናንም ሆነ ሎሎችን ሥራዎች በተሻለ የአመራረት ሁኔታ ውስጥ ለማስገባት የሚደረገው መንግሥታዊ ጥረትም ገና ብዙ ርቀት መሄድና መስፋፋት ይኖርበታል፡፡ የገጠሩን ሕዝብ ምርት ዓይነት ብዙ ከማድረግና የምግብ ምንጩን ከማስፋት ጐን ለጐን የፈረንጅ ጣፋጭና ነጭ (ገለባ የለሽ) ምግቦችን የሚያበልጠውን ‹‹ዘመናይ›› አመለካከት ማቃናት፣ ከጤናማ አመጋገብ አኳያ ለፈረንጅ ሳይቀር የሚተርፈውን ቃጫ የምግብ ባህላችንን (ቆሎ ንፍሮ/አሹቅ፣ ቀንጎሎ/በቆልት እሸት፣ ቅይጥ እንጀራ፣ በሶ፣ ቅንጬ፣ በፉርኖ ዱቄት ላይ ያልተመሠረተ ገንፎ፣ አጥሚትና ዳቦ፣ ወዘተ) የተሻለ እንድናከብርና እንድናበለፅግ የማስቻል እንቅስቃሴ በራሱ አንድ የልማት ፈርጅ ነው፡፡ ሀገረሰባዊ የምግብና የመጠጥ ባልትናን ወደ አነስተኛ ኢንዱስትሪ ማሳደግም ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ለምሳሌ ለረዥም ጊዜ ድፍድፍ ሆኖ ከሚቆየውና ተበጥብጦ ወዲያውኑ ሊጠጣ ከሚችለው የደረቆት ጠላ በመነሳት፣ የአልኮል ልኩ በተመጠነ ኢንዱስትሪ ነክ አመራረት ደራሽ የጠላ ድፍድፍ (Instant) እያሸጉ ለገበያ ማቅረብና በጠላ ዝግጅት ላይ ያለውን ድካም ማቅለል ይቻላል፡፡ የሴት እኩልነትም እየተሳካ የሚመጣው እንዲህ ያለውን የሴት ጉልበት ጨራሽ ሥራ፣ ፋብሪካ ገብ በሆነ አመራረትና ቴክኖሎጂ በማቃለል ነው፡፡ አብዛኛው ሕዝብ የሚጠቀምበትን የሀገረሰብ ሕክምና (የሥራ ሥርና የቅጠል እንዲሁም የማዕድን ውኃ ፈውስ) የማጥናትና የማዘመኑ ተግባርም ከዚሁ ማዕዘን ሊተኮርበት የሚገባ አካባቢ ነው፡፡ በአገር ውጤቶችና በማንነት እያፈኑ በሥራ ንቀትና በባዶ ኩራት እየተቆነኑ የትም አይደረስም፡፡ ከጃፓኖች፣ ከቻይናዎች፣ ከኮሪያዎች ግስጋሴ ጀርባ ያለው ችግርን አሸንፎ የመውጣት፣ የመቆጠብ፣ የመለኝነትና የአገር ፍቅር ብርታት የሕዝብ ጥንካሬ ሚስጥርና አስተማሪነቱ እዚህ ላይ ነው፡፡ አነሰም በዛ በእነዚህ ሕዝቦችና መንግሥታት ላይ የታየው ቅልጥፍናና ጮካነትም ከሕዝቦቹ አስተናነፅ ጋር ይሳሳባል፡፡ አንድ መንግሥት በሚያስተዳድረው ሕዝብ ላይ ጥሩም መጥፎም ለውጥ ሊያሳድር እንደሚችል ሁሉ፣ ራሱም መንግሥቱ የኅብረተሰቡ ድክመትና ጥንካሬ መታያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥታት ላይ ሲታዩ የነበሩና አሁንም እየታዩ ያሉት ችግሮች በገዢዎች ማንነት ብቻ የሚብራሩ አይደሉም፡፡ የደቀቀና አንገቱን የደፋ ኅብረተሰብን መልቲዎች እንዳሻ እንዲጫወቱበት ይጋብዛል፡፡ ከአኗኗርና ከአመለካከቱ ብክነትን፣ ንቅዘትንና ደንታቢስነትን ለማራገፍ የተነሳ ኅብረተሰብ በአገዛዙ ላይ የሚታዩ መሰል ችግሮችን መዋጋትና ማስወገድ ይቻለዋል፡፡ ሕዝብ አቀፍ የሆነ ለውጥ የማምጣት ጥያቄ ዋና ቁም ነገርም ይኼው ነው፡፡ ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...