Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቆዳና ሌጦ ግብይቱ በሕጉ መሠረት አለመሻሻሉ ሕጋዊ ነጋዴዎችን እያማረረ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተንዛዛና ኋላ ቀር የንግድ ግብይትን ያስቀራል ተብሎ የታመነበት የጥሬ ቆዳና ሌጦ ግብይት አዋጅ ከፀደቀ አንድ ዓመት ቢያስቆጥርም፣ በሕገወጦች እየተፈጸመ ያለውን ግብይት ሊያስቆም ባለመቻሉ ነጋዴዎችን ያማረረ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ባለፈው ረቡዕ የተከበረውን የልደት (ገና) በዓልን ተንተርሶ በተለያዩ የገበያ ሥፍራዎች ተዘዋውሮ ለመታዘብ እንደቻለው ልማዳዊው የጥሬ ቆዳና ሌጦ ግብይት በነበረበት አሠራር የቀጠለ ሲሆን፣ በተሻሻለው ሕግ መሠረት ብዙም የተለወጠ ነገር አለመስተዋሉን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት የወጣው ሕግ ግን የቆዳና የሌጦ ግብይቱን ለማከናወን ፈቃድ በተሰጣቸው ግለሰቦችና ተቋማት እንዲካሄድ የሚደነግግ ነው፡፡ ሆኖም በአዲስ አበባ ዋና ዋና የገበያ ማዕከላት ውስጥ አንዱ በሆነው የሾላ ገበያ በነበረው የበዓል ገበያ ላይ የንግድ ፈቃድ አውጥተው የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ጥቂት ሲሆኑ፣ ብዛት ያላቸው ግለሰቦች በቆዳና ሌጦ ግዥ ተሰማርተው ሲገበያዩ መዋላቸው ታይቷል፡፡ የአዋጁን ድንጋጌ ተከትሎ ፈቃድ አጥውተው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የሚገልጹ ነጋዴዎች ለሪፖርተር እንዳመለከቱት፣ ያለፈቃድ የሚንቀሳቀሱት ነጋዴዎች ዋጋ በመስበር ችግር እየፈጠሩባቸውና ለኪሳራ እየዳረጓቸው ነው፡፡ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነጋዴ፣ ‹‹ችግሩ ፈቃድ እንደሌላቸው እየታወቀ በቆና በሌጦ ግብይት ውስጥ የገቡት ነጋዴዎች ምንም ዕርምጃ ስለማይወሰድባቸው፣ ቤት ተከራይተንና ታክስ እየከፈልን በምንነግደው ነጋዴዎች ላይ የዋጋ ጫና እየፈጠሩብንና ጉዳት እያደረሱብን ነው፤›› ብለዋል፡፡ እንደ እኚሁ ነጋዴ ገለጻ የገና በዓል በተከበረበት ታኅሳስ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. የበግ ቆዳ በ50 ብር ሲገዙ የዋሉ ሲሆን፣ ‹‹ፈቃድ የሌላቸው›› የተባሉ ነጋዴዎች እስከ 60 ብር ድረስ እየገዙ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ በተመሳሳይም የፍየል ቆዳ በ25 ብር ሲገዛ የበሬ ቆዳ እንደየክብደቱ በኪሎ አምስት ብር ሲገበያዩ ውለዋል፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት ተከብሮ በዋለው የመውሊድ በዓል የበግ ቆዳ በ60 ብር ሲገበያዩ እንደዋሉም ሕጋዊ ነጋዴዎቹ አስረድተዋል፡፡ የተሻሻለው አዋጅ የጥሬ ዕቃውን ጥራት ለመጠበቅና ግብይቱን በሕጋዊ መንገድ እንዲከናወን የመገበያየቱ ሥራ በአንድ የተከለለ ማዕከል እንደሚሆን ቢያስቀምጥም፣ በሾላና በተለያዩ የከተማዋ የገበያ ሥፍራዎች ግን ግብይቱ ሲካሄድ የነበረው ከአዋጁ መንፈስ ውጪ ነበር ተብሏል፡፡ በተለይም በመኖሪያ ቤቶች፣ በዋና ዋና ጎዳናዎችና በእግረኞች መንገድ ላይ የግዥና ሽያጭ ሥራው ሲከናወን እንደዋለ ለማስተዋል ተችሏል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ከንግድ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ችግሩ ቢኖርም የሕጉ ድንጋጌዎች ገና የሚፈለገውን ለውጥ አላመጡም፡፡ ሚኒስቴሩ ሕጉን ሙሉ ለሙሉ ለማስፈጸም የዝግጅት ሥራ እያከናወነ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ‹‹የተሻሻለውን ሕግ በአግባቡ ለማስፈጸም የዝግጅት ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ አዋጁ ከተሻሻለ አንድ ዓመት ቢያስቆጥርም በምንፈልገው መንገድ ግብይቱ እየተካሄደ ነው ማለት አይቻልም፤›› በማለት የሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አማከለ ይማም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አሁን እየታየ ያለው የተዘበራረቀ የግብይት ሥርዓት ከገበያ ቦታ መከለልና የግብይት ሥርዓቱን ከመቆጣጠር አንፃር ክልሎች ገና ወደ ትግበራ ባለመግባታቸው የተፈጠረ ክፍተት ያለ መሆኑም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ መመርያዎቹና ደንቦቹ ተጠናቀው በተለይ በክልል መንግሥታት በኩል ወደ ትግበራ ሲገባና የንግድ ሥርዓቱን ወደሚፈልገው ሥርዓት ሲመለስ፣ በግብይቱ ውስጥ ያለ ሕጋዊ ፈቃድ የሚንቀሳቀሱት ተዋንያኖችን ሙሉ በሙሉ እንደሚያስወግድ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች