Friday, March 31, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና 5.5 ቢሊዮን ዶላር ያስገኙለት ተቋማት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2006 በጀት ዓመት ከ5.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ በማግኘቱ ለዚህ የውጭ ምንዛሪ መገኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ላላቸው ላኪዎች፣ ገንዘብ አስተላላፊ (ሐዋላ) ኩባንያዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዕውቅና ሰጠ፡፡ ባንኩ ላስገኙለት የውጭ ምንዛሪ ምሥጋናና ዕውቅና የሰጠው ባለፈው ሐሙስ በሸራተን አዲስ ባካሄደው የወጪ ንግድ ቀን ፕሮግራም ላይ ነው፡፡ ባንኩ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ አስገኝተዋል ብሎ ዕውቅና የሰጣቸው ተቋማት 173 ናቸው፡፡ የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ በረከት ስምኦንና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት በዚህ ዝግጅት ላይ በ2006 በጀት ዓመት ባንኩ ላገኘው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ለተባሉት ተቋማት ባስገኙት የውጭ ምንዛሪ ልክ የተለያዩ ደረጃዎች፣ ሽልማቶችና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡ ባንኩ በተለያየ ደረጃ ተሸላሚ ካደረጋቸው ኩባንያዎች ውስጥ ሁለቱን ልዩ ተሸላሚዎች ያደረገ ሲሆን፣ በፕላቲኒየም ደረጃ ደግሞ አምስት ኩባንያዎችን ሸልሟል፡፡ የወርቅ ተሸላሚ ያደረጋቸው ደግሞ አሥር ኩባንያዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወጪ ንግድ ቀን ፕሮግራሙ ላይ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ልዩ ተሸላሚ ያደረገው ሚድሮክ ጎልደን ነው፡፡ ሚድሮክ ጎልድ ተሸላሚ የሆነው ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማስገኘቱ በወጪ ንግድ ከላኪዎች ቅድሚያ ሊይዝ ችሏል፡፡ ከገንዘብ አስተላላፊ ኩባንያዎች መካከል ደግሞ ዌስተርን ዩኒየን ልዩ ተሸላሚ በመሆን ከዕለቱ የክብር እንግዳ የተዘጋጁለትን ሽልማት ወስዷል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት በዕለቱ ተሸላሚ ከሆኑት ገንዘብ አስተላላፊ ኩባንያዎች መካከል ዌስተርን ዩኒየን ሊመረጥ የቻለው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል እንዲንቀሳቀስ ያደረገው የገንዘብ መጠን ከ450 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመሆኑ ነው፡፡ በገንዘብ አዘዋዋሪ ተቋማት መካከል በዌስተር ዩኒየንና በሌሎች ተቋማት መካከል ሰፊ ልዩነት መኖሩንም አሳይቷል፡፡ ከዌስተር ዩኒየን ሌላ በዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ተሸላሚ የሆነው መኒ ግራም የተባለው የገንዘብ አስተላላፊ ተቋም፣ ለባንኩ አስገኝቷል የተባለው የውጭ ምንዛሪ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በፕላቲኒየም ደረጃ ተሸላሚ የሆኑት አምስቱ ኩባንያዎች ደግሞ ለባንኩ ከ40 እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ስላስገኙለት ነው፡፡ በፕላቲኒየም ደረጃ ተሸላሚ ያደረጋቸው አምስቱ ኩባንያዎች ዋርካ ትሬዲንግ፣ በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ፣ ቦሌ አትላንቲክ ኢንተርናሽናል (የገንዘብ አዘዋዋሪ)፣ ኤክስፕረስ መኒ (የገንዘብ አዘዋዋሪ) እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ናቸው፡፡ በወርቅ ደረጃ ተሸላሚ የሆኑት ኩባንያዎች ደግሞ ከ20 እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማስገኘታቸው ነው፡፡ ከ20 እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር አስገኝተዋል ተብለው ከተሸለሙት ኩባንያዎች መካከል ሙለጌ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት፣ አደም ከድር ኮፊ ትሬዲንግና ከማል አብደላ ዓለም አቀፍ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ተጠቅሰዋል፡፡ በዚህ የሽልማት ዘርፍ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተካቷል፡፡ ከገንዘብ አዘዋዋሪዎች ውስጥ ደግሞ መኒ ግራም ተሸላሚ ሆኗል፡፡ በዕለቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አስገኝተዋል ተብለው ከተመረጡት 173 ላኪዎች፣ ገንዘብ አዘዋዋሪዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የያዙት ከአንድ እስከ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ያስገኙ ተቋማት ናቸው፡፡ በዚህ ደረጃ ገቢ በማስገኘት ዕውቅና የተሰጣቸው ተቋማት ቁጥር 67 ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥም ባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ ዜኒት ገብስሸት፣ ኢትዮ ሌዘር፣ ጋፍ ጀኔራል ትሬዲንግና ሼባ ሌዘር ይገኙበታል፡፡ በዚህ ዘርፍ ተሸላሚ ከሆኑ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች መካከል ካህና ጎልደን መኒ የተባሉ የገንዘብ አዘዋዋሪ ኩባንያዎች በ2006 በጀት ዓመት ለባንኩ ከአንድ እስከ ሦስት ሚሊዮን ዶላር በማስገኘት ዕውቅና ሊሰጣቸው ችሏል፡፡ ከሦስት እስከ አምስት ሚሊዮን ዶላር በማስገኘት ደግሞ ከተቀመጡት ኩባንያዎች መካከል የተፈጥሮ ሙጫ ምርት ገበያ ድርጅት፣ ባቱ ቆዳ ማልፊያ፣ አምባሰል የንግድ ሥራዎች፣ አልሳም ኤስፖርት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ አልፋ ትሬዲንግና ፓርትነርሺፕ የተባሉ ኩባንያዎች ይገኙበታል፡፡ ከአምስት እስከ አሥር ሚሊዮን ዶላር በማስገኘት ደግሞ በዕለቱ የተዘጋጁላቸውን ሽልማት መቀበል የቻሉት ሞጆ ታነሪ፣ ኢስት አፍሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ኤስኤ ባገርሽና፣ ሉና ኤክስፖርት የተባሉ ኩባንያዎች ተጠቅሰዋል፡፡ ከአምስት እስከ አሥር ሚሊዮን ዶላር ለባንኩ የውጭ ምንዛሪ አስገኝተዋል ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ በኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ ያስገኛል ተብሎ የሚጠበቀው የቱርኩ አይካ ጨርቃ ጨርቅ ይገኝበታል፡፡ ከአይካ ሌላ ከአምስት እስከ አሥር ሚሊዮን ዶላር አስገኝቷል በሚል ከአገልግሎት ዘርፍ የተሸለመው ሌላው ኩባንያ ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮም ሆኗል፡፡ የወጪ ንግድ ፕሮግራምን በማስመልከት በዕለቱ ንግግር ካደረጉት ውስጥ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ እንደገለጹት፣ በዕለቱ የተዘጋጀው ፕሮግራም ለባንኩ ከፍተኛ ቢሆንም የውጭ ምንዛሪ ያስገኙ ደንበኞቻቸውን ለማበረታታትና ዕውቅና ለመስጠት ነው ብለዋል፡፡ ሌሎችም እንዲከተሏቸውና እንዲበረታቱ እንዲህ ያለው ሽልማትና ዕውቅና ትልቅ እገዛ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ በቃሉ ገለጻ እነዚህ ኩባንያዎች በዓለም አቀፍ ገበያ የአገሪቱን ምርቶችና አገልግሎቶች በስፋት በማስተዋወቅ በዓለም አቀፍ ገበያ ተቀባይነታቸው እያደገ እንዲመጣ አስችለዋል፡፡ ባንኩ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ደንበኞችን በቅርበት እየደገፈና እያበረታታ ይገኛል ያሉት አቶ በቃሉ፣ ባንኩ ለአገሪቱ ዕድገት ወሳኝ የሆነውን ይህንን ዘርፍ ለማሳደግ ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎበታል ብለዋል፡፡ አስቸጋሪ በሆነው የዓለም ገበያ ውስጥ ዘልቀው በመግባት ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን ተወዳዳሪ እንዲሆን ላደረጉት ጥረት ዕውቅና መስጠት ብቻ ሳይሆን ለዘርፉ ዕድገት ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እገዛ ይደረግላቸዋል ተብሏል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የባንኩ ቦርድ ሰብሳቢና በሚኒስቴር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ በረከት ስምኦን፣ መንግሥት የወጪ ንግድ ለአገሪቱ ልማት የሚያበረክተውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዘርፉ የሚበጁ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡ በመሆኑም በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በዓይነትና በመጠን እየተበራከቱ ሊሄዱ በመቻሉ፣ ከወጪ ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡ በ2005 ዓ.ም. በዓለም ገበያ በተፈጠረው የዋጋ መዋዠቅ የአገሪቱ የወጪ ንግድ በተወሰነ ደረጃ ዝቅ ቢልም፣ በ2006 በጀት ዓመት ግን ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ማደጉን ገልጸዋል፡፡ ቡና 11.5 በመቶ፣ የቅባት እህሎች 17.1 በመቶ፣ ሥጋና ሥጋ ውጤቶች 12.6 በመቶ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ደግሞ 8.7 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም አገሪቱ እያገኘች ያለችው የውጭ ምንዛሪ የሚጠበቀውን ያህል ያለመሆኑን ያስታወቁት አቶ በረከት፣ ‹‹አገሪቱ ካላት እምቅ ሀብት አንፃር ሲታይ በዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ያህል እያገኘች አይደለም፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ አገሪቱ ባላት አቅም ለመጠቀም ተጨማሪ ጥረት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ ይህንንም ዳር ለማድረስ በቅንጅት መሥራት ያለበትና ዘርፉን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት የምንረባረብበት ጉዳይ ይሆናልም በማለት ተናግረዋል፡፡ መንግሥት በአገሪቱ የወጪ ንግድ ልማትን ለማስፋፋት የሚያደርገው ጥረት በላቀ ደረጃ የሚተማመነው የውጭ ገበያ ዘልቀው ሊገቡ በሚችሉ አገራዊ ባለሀብቶች ላይ መሆኑን ያስታወሱት አቶ በረከት፣ ይህንን ለማጠናከር መንግሥት እገዛው እንደሚቀጥልና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ አቶ በቃሉ አክለው የወጪ ንግድ ዘርፍ ለአገራዊ ዕድገቱ ያለውን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የሚደረገውን ድጋፍ ለማሻሻል በየጊዜው የሚደረጉ የምክክር መድረኮች አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ገልጸው፣ ከዚህ በኋላም አሠራሩ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ በተለያየ ደረጃ ተሸላሚ ለሆኑ ተቋማት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታደሰ ኃይሌ፣ የንግድ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ያዕቆብ ያላ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ አባልና በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ዓባይ ፀሐዬና የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው ሽልማት ሰጥተዋል፡፡ በፕላቲኒየምና በልዩ ደረጃ ተሸላሚ የሆኑት ኩባንያዎች ደግሞ ከአቶ በረከት እጅ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ የከፈታቸው ቅርንጫፎች ቁጥር 909 ደርሷል፡፡ የባንኩ ሀብት 242.7 ቢሊዮን ብር በላይ ሲደርስ፣ የባንኩ ደንበኞች ቁጥርም 8.8 ሚሊዮን እንደሆነ የባንኩ መረጃ ያመለክታል፡፡ የባንኩ ሠራተኞች ቁጥር ደግሞ ከ22 ሺሕ በላይ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች