Tuesday, June 18, 2024

ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ የተቃጣው ሽብር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሰሞኑ የዓለም ልዩ ዜና፣ የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃንን ሰፊና ልዩ ሽፋን የገዛው ርዕሰ ጉዳይ የ‹‹ሻርሊ ኤብዶ›› ሳምንታዊ መጽሔት ጽሕፈት ቤት ጥቃትና የጋዜጠኞቹ እልቂት ነው፡፡ ሰበር ዜናው ራሱ ገና ተወርቶ አላለቀም፡፡ ታሪኩም ገና መቋጫው አልታወቀም፡፡ ፈረንሣይ ገና ብሔራዊ ሐዘን ላይ ናት፡፡ ለጊዜው የሌላው ዓለም ዜና ሁሉ የኤር ኤሽያ የ160 ሰዎች እልቂት፣ የተቀሩት መቶ ሰዎች አስከሬንና የብላክ ቦክስ ፍለጋ፣ ሪፐብሊካኖቹ በሁለቱም ምክር ቤቶች የበላይነት ያገኙበት የአሜሪካ የአዲሱ ኮንግሬስ ወሬ፣ የኢትዮጵያ አምስተኛው ምርጫ የመራጮች ምዝገባ መጀመር ዜና፣ እነዚህ ሁሉ የ‹‹ሻርሊ ኤብዶ›› የየአገር ቤቱ የግርጌ ማስታወሻዎች ናቸው፡፡ ‹‹ሻርሊ ኤብዶ›› ማለት ሳምንታዊ ሻርሊ ማለት ነው፡፡ “Hebdo Phebdomadaire” ጉራጅ ነው፡፡ ሳምንታዊ ማለት ነው፡፡ ሻርሊ ራሱ ከኮሜዲ (አስቂኝ) ባህርይ የተወሰደ ነው፡፡ በአጠቃላይና ባጭሩ ሻርሊ ኤብዶ ማለት የፈረንሣይ ሳምንታዊ ጋዜጣ ነው፡፡ ሳምንታዊው ሻርሊ ግን ወትሮ የሚታወቀው ዓይነት ‹‹የተለመደ›› ጋዜጣ አይደለም፡፡ የፌዝ፣ የቧልት፣ የስላቅ፣ የአሽሙር፣ የልግጫ ጋዜጣ ነው፡፡ ለእኩልነት፣ ለአርነትና ለወንድማማችነት አገር ለፈረንሣይ ቀልድ፣ ቧልትና ፌዝ ሐሳብን ለመግለጽ ነፃነት ሌላ መልክና ቆዳ ነው፡፡ ቤት ያበላሻል የሚባል አይደለም፡፡ የማኅበራዊ ኑሮን ፖለቲካዊ ሕይወትንና ኢኮኖሚያዊ ትዳርን አስልተውና አሽተው የሚያዩበት ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት አንድ ልክ ነው፡፡ በየሳምንቱ ረቡዕ ታትሞ የሚወጣው ይህ ጋዜጣ ቅርፅና መልክ ብቻ ሳይሆን ‹‹ዓላማ››ውም ይኼው ነው፡፡ ማኅበራዊ ሕይወትንና ፖለቲካን እያላገጠ ያሳያል፣ እያጋለጠ ያሾፋል፡፡ በዚህ ላይ ግራ መንገደኛ ነው፡፡ በካርቱኖቹ፣ በሪፖርቶቹ፣ በስላቁና በቀልዱ ጽንፈኛ ቀኞችን፣ አጥባቂዎችን፣ እምነትን፣ ሃይማኖትን፣ ፖለቲካን፣ባህልን ይዳፈራል፣ ይዘረጥጣል፡፡ ይኼ ሁሉ ግን የሚሆነው ይህን ሁሉ የማድረግ መብት ለወግና ለይስሙላ ሳይሆን ባህሉና እስትንፋሱ ነው በሚባል አገር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ስለጋዜጣው የሚባል ‹‹ክፉ›› ነገር ቢኖር ሳምንታዊ ሻርሊ ያበዛዋል ነው እንጂ ሐሳብን በመግለጽ ነፃነት ስም የሚነግዱ የጠላቶቻችን መሣሪያዎች አይባልም፡፡ እንዲያውም የንግግርና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን ዳር ድንበር ሰፋ ያደረገ፣ የውኃ ልኩን ያሳደገና የነፃነት ‹‹አስፋው ወሰን›› እየተባለ ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ እንደዚያ ባለ ፈረንሣይን በመሰለ አገር እነአሜሪካ እንኳን በእንዲህ ያለ ጉዳይ ስሙን ሲጠሩት ስሜትን ጭምር የሚነዝር ነገር ያለው አገር ነው ፈረንሣይ፡፡ የጋዜጦች ‹‹ጫጫታ›› እና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ‹‹ጩኸት›› የሐሳብ ነፃነት ያለ ማስመሰያ ለቱልቱላውና ለክብረ በዓላዊ ባህርይው ብቻ የሚፈለግ ውሸት አይደለም፡፡ እውነት ነው ሳምንታዊው ሻርሊ ሲበዛ ያበዛዋል፣ ሲበዛም ይቀብጣል የሚባለው፡፡ ይህ ሁሉ ግን ምዕራባዊው ዓለም ከሚታገሰው በላይ አይደለም፡፡ እዚያው ፈረንሣይ ውስጥ የማይወዱትና የሚጠሉት መዓት ናቸው፡፡ የሚጠሉትም ጭምር ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነቱን ሲበዛ ይወዱለታል፡፡ የዕለታዊ ሻርሊ ቅብጠት ግን ከዚህ በፊት እ.ኤ.አ. ለኖቬምበር 2011 የቦምብ ጥቃት ጭምር ዳርጎታል፡፡ የቦምብ ጥቃቱ ካደረሰው ቃጠሎና ውድመት በላይ ያስከተለው አደጋ ግን በአጠቃላይ በሰብዓዊ መብቶችና በፈረንሣይ ዲሞክራሲ ላይ ያስከተለው አደጋ ይበልጣል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011ም ሆነ አሁን ባለፈው ሳምንት የሳምንታዊውን መጽሔት ጋዜጠኞች ለእልቂት የዳረገው ጥቃት ለዓለም ታላላቅ መሪዎችና ለታላላቅ የመገናኛ ብዙኃን ዋነኛ ትኩረት ሆኗል፡፡ የዚህ ምክንያት ለዚህ የእልቂት ዓለም የአሥርና የአሥራ ሁለት ሰው ሞት አዲስ ነገር ሆኖ አይደለም፡፡ የዲሞክራሲ እሴቶች፣ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት መርህና የዲሞክራሲ ሥርዓት የመሠረት ንጣፍ ላይ የተደረገ ጥቃት ማለት ግን ጉዳዩን የሁሉም ደንታና የማንም ቁጣ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ለዚህ ነው ባልተለመደ ሁኔታ ፈረንሣይ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ሐዘን ከተቀመጠችባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች አንዱ በዚህ ጉዳይ ላይ ሲሆን ‹‹ያማረባት››፡፡ የተባለው የመላው ዓለም መሪዎች የንግግር ነፃነትን፣ ሐሳብን የመግለጽ መብት ቅዱስነትን እየተማፀኑ ሐዘናቸውን ሲገልጹና ለቅሶ ሲደርሱ ድምቀት ያገኙት፡፡ አንገላ መርከል፣ ዴቪድ ካሜሩን፣ ባራክ ኦባማ ለጥቅስ የበቃ ንግግር አድርገዋል፡፡ በተለይ ባራክ ኦባማ ፈረንሣይ ኤምባሲ ድረስ ሄደው መዝገብ ላይ ፈርመዋል፡፡ የፈረንሣይና የዓለም የመገናኛ ብዙኃን ብዕርና እርሳስ እየያዙ የተጠቂውን መጽሔት ምሥል እያተሙ ጉዳቱ የኛው ነው፣ ጥቃቱ በነፃነት ላይ ነው ብለዋል፡፡ በሚቀጥለው ረቡዕ የሚወጣው የሳምንታዊው ሻርሊ ዕትም 20 ጊዜ በልጦና በዝቶ በአንድ ሚሊዮን ኮፒ እንዲታተም የእኛ ጉዳይ ነው ብለው ቃል ገብተዋል፡፡ መሪዎች ጥቃቱ አሸባሪነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሸባሪነት በገዛ ራሱ ምክንያት ብቻ መወገዝ እንዳለበት፣ ሰዎችን በነሲብ የሚያጠቃው ሽብር በትግል ባህርይው የሰዎችን መብት መከበር የዳጠ በመሆኑ የዲሞክራሲ አማራጭ ሊሆን እንደማይችል አስረግጠው ተናግረው ኮንነዋል፡፡ እውነታቸውን ሆነም አልሆነም የሚፈርዱት በቀድሞ ተግባራቸውና በሚመጣው የባህርይ አረማመዳቸው ነው እንጂ፣ ይህንን ሽብርተኝነት ለመታገል የሚወሰደው ዕርምጃ ሁሉ የገዛ ራስንም የሕግ አስከባሪነት፣ የውኃ ልክ የሚያስገምት ስለመሆኑ አለመርሳታቸውን በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡ የእኛን በመሰለ አገር ቢሄዱት አገር አለ የሚያሰኝ እንዲህም ይደረጋል እንዴ ብሎ በእንግድነት ጥያቄ የሚያስነሳ ትርዒትም ታይቷል፡፡ ትርዒት ሲባል የታይታ፣ የውሸት፣ ሆን ተብሎ የተሠራ ማስመሰያ አይደለም፡፡ ፍራንስዋ ኦላንድ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የተኩዋቸውና ለወደፊትም ለሚመጣው ምርጫ ተቀናቃኝ የሚሆኗቸውን ኒኮላ ሳርኮዚን ነው፡፡ እንደ እዚህ አገር ፋሽንና ቋንቋ እንዲሁም ‹‹የጨዋታ ሕግ›› ቢሆን ሁለቱ በአቋም ‹‹የማይደራረሱ›› ናቸው፡፡ ፍራንስዋ ኦላንድ ሶሻሊስት ናቸው፡፡ ሳርኮዚ ደግሞ መሀል ቀኝ መንገደኛ ናቸው፡፡ ሁለቱም የፈረንሣይ ሚዲያ በተለይም አላስቆም አላስቀምጥ የሚለው የገመና አውጪው የጥቃት ሰላባዎች ናቸው፡፡ አገባ ፈታ፣ ያለ ጋብቻ ከሴት ጋር ይኖራል እያሉ ከመዳፍ በላይ ቁም ስቅላቸውን የማየት ግዴታ ያለባቸውና እንዳለባቸው የሚያውቁ ሰዎች ናቸው፡፡ የሳምንታዊው የቧልትና የሽሙጥ መጽሔት ሻርሊ ኤብዶ ዋና መሥሪያ ቤት የኤዲቶሪያል ቦርድ ስብሰባ ላይ እያለ ከጋዜጠኞችና ከፖሊሶች ጋር በጠቅላላ አሥራ ሁለት ሰዎች ሲገደሉና አገር ብሔራዊ ሐዘን ሲያውጅ፣ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ኦላንድ ከዚህ የበለጠ የአገር ጉዳይ ከዚህ የበለጠ የአገር ግዳጅ የለም ብለው ሳርኮዚን ቤተ መንግሥት ጠርተው አማከሯቸው፡፡ ሳርኮዚም ኤሊሴ ቤተ መንግሥት በር ላይ በክብር ቆመው በክብር መግለጫ ሰጡ፡፡ ጉዳዩን በጥሞና ለሚመለከት የፖለቲካ ታዛቢ እንዲህ ያለ ጉዳይ መቀመጫውን ፓሪስ ያደረገው ከዩኔስኮ ጠቅላይ መምርያ ወይም ከዋናው መሥሪያ ቤት የወጣ የተመዘገበ የታሪክ ቅርስ እንጂ፣ የአገር ወግና ማዕረግ እንዲሁም ፖለቲካ ሊባል አይችልም ብሎ ያስባል፡፡ ምክንያቱም እንደ ‹‹እባብ ለእባብ›› ካብ ለካብ ብቻ የሚተያዩት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ የሚዲያ ውጤቶች ያሉበት አገር ውስጥ አስገራሚ በመሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ሌላው ቢቀር በሚዲያው በኩል በንግግርና ሐሳብን በመግለጽ ነፃነት በኩል ያለው ሥጋ ወይም ዘር ከልጓም ስቧቸው መኖራቸውን ሲያሳዩ አታዩም ይባላሉ፡፡ በብዙ ምክንያት ‹‹ጂ ስዊ ሻርሊ›› ቢሉ ኤምባሲ ሄደው ፈርሙ ቢባሉ ሌላ ያልተጠበቀ ነገር ሊባርቅባቸው ይችላል ተብሎም ይታሰባል፡፡ የሚገባው ሰው ላይኖርም ይችላል ተብሎም ይተቻል፡፡ በጋዜጦኞችና በሚዲያ ሠራተኞች ላይ የሚደርስ እንዲህ ያለ ጥቃት የመጨረሻው ዓይነት ሳንሱር ነው ተብሏል፡፡ እናም የሐሳብና የመረጃ በነፃ መንሸራሸርን ቀስፎ መያዝ የሚችል ዕርምጃ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ነገር ፓሪስ ላይ ተሰማ ማለት በመላው ዓለም ባለ ጋዜጠኝነት ላይ የተሠራ ወንጀል ነው ተብሎ የሚወገዘውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የግብር ይውጣ ጉዳይ፣ ለአንደበት ወግ ያህል ብቻ የሚነገር የአገር ዲሞክራሲ የራሱ እስትንፋስ ሳይሆን፣ የውስጥ ጌጡ እንዳይሆን ማረጋገጥ እንጂ፣ ‹‹እኔም ጉዳተኛ ነኝ›› ማለት የሁሉም አገር የሁሉም የሚዲያ ውጤት፣ የሁሉም ጋዜጠኛ፣ የሁሉም ሰው የውስጥ ሰቆቃ ጩኸት መሆን አለበት እየተባለ ነው፡፡ እንዲህ ሲባልም ከልብ መሆን አለበት እየተባለ ነው፡፡ ምክንያትም አለ፡፡ በሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች መካከል መበላለጥ የለም፡፡ የአንዱ ነፃነት ወይም መብት ከሌላው አይበልጥም፡፡ ሁሉም አጣማጅ አቻ ናቸው፡፡ አቻና እኩል ናቸው፡፡ የአንዱ እኩልነት ከሌላው እኩልነት አያይልም፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ ከዚህ እኩል ሌላም እውነት አለ፡፡ የፕሬስና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት የሌሎች ነፃነቶችና መብቶች ፊታውራሪ ነው፡፡ በጋዜጠኞች መብት ላይ የሚፈጸም ደመ ነውጠኛነት በሌሎች ሰዎች መብቶችም ላይ ጭምር የሚሠራ ወንጀል ነው የሚባለውም በዚህ ምክንያት ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህን ጉዳይ ከልብ መሆኑን ለማስረዳት ጥቂት ቀረብ ያለ አንድ የአገር ምሳሌ ይወሳል፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ሰው በጣም ተርቦ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ ሊሰርቅ ሰው በረት ይገባል፡፡ ባለቤቱ ነቅቶ ሌባ መግባቱን ያውቃል፡፡ ሌባውም የተነቃበት መሆኑን አውቆ ይሸሻል፡፡ ባለቤቱና ያ ሌባ አሳዳጅና ሯጭ ይሆናሉ፡፡ ባለቤቱ ግን በሰውየው ላይ ሊደርስበት አልቻለም፡፡ ይህን ጊዜ ‹‹በቴዎድሮስ ሞት፣ በሞቱ አትላወስ፤›› ብሎ በሕግ ይማፀናል፡፡ ሰውየው እንደተባለው ይቆማል፡፡ ባለቤቱም ሰውየው ሲቆምለት ተጠግቶ አመቻችቶ በጦር ይወጋዋል፡፡ ወድቆ አድሮ ዕርዳታ አግኝቶ ድኖ ለአፄ ቴዎድሮስ አቤት ይላል፡፡ የጉዳዩን ዝርዝርና እውነቱን አንድም ሳያስቀር ይናገርና፣ ‹‹ምንም በጠገበ ጉልበቱ ሮጦ ቢያሳድደኝ ሊደርስብኝ አልቻለም፡፡ በቴዎድሮስ ሞት በሞቱ አትላወስ ቢለኝ የፈለገኝ ለሥርዓት እንጂ ለጉልበት ወይም ለግድያ አይደለም ብዬ ስምዎን ሰምቼ በስምዎ ተዳኝቼ ቆምኩ፤›› ብሎ አቤት አለ፡፡ ቴዎድሮስ ይህ ሁሉ እውነት ስለመሆኑ አረጋግጠውና የተከራካሪውን ሰው እምነት አግኝተው፣ ‹‹እንግዲያው የወጋኸው እኔንና ስሜን ነው፡፡ እናም የምፋረድህ እኔ ነኝ፤›› ብለው ዳኝነቱን ትተው ከሳሽ ሆኑ ይባላል፡፡ ዓለም በሙሉ ‹‹ሳምንታዊ ሻርሊ እኛ ነን፡፡ ሁላችንም ሳምንታዊ ሻርሊ ነን›› የሚለው በእንዲህ ዓይነቱ ምክንያት ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ምክንያት ብዙዎቹ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በመንግሥታቱ ድርጅት ዩኔስኮ አጋፋሪነት ሐሳብን በመግለጽና በንግግር ነፃነት ላይ ልዩ አቋም ይዘው ይታገላሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ በንግግር ነፃነት መገልገልን ምክንያት አድርገው ከዚያም በላይ ቂም ይዘው በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ጥቃት የሚያደርሱትን ይዘመትባቸው ዘንድ ዓለም ወስኗል፡፡ እንዲያውም በጋዜጠኝነት ላይ በንግግር ነፃነት ላይ የሚሠራ ወንጀልና ጥፋት ክስ በይርጋ የማይታገድ ይሆን ዘንድ መላው ዓለምና እያንዳንዱ አገር ተግቶ እንዲሠራ የሕግ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ከራርሟል፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት በየዓመቱ የሚከበር፣ ሳይጠየቁ መቅረትን የሚታገል ቀን ሰይሟል፡፡ ይህ ሁሉና ከላይ የተገለጸው ሁሉ እውነት በመሆኑ፣ ሁሉንም እውነት ለመናገር ግን አንድ ሌላ ጉዳይ መነገር እንዳለበት አቋም ተይዟል፡፡ በዚህ ረገድ ‹‹ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል›› ብሎ መፈክርም ሆነ ፍርኃት ሊበግረው የማይገባ አንድ መነገር ያለበት ጉዳይ አለ ነው የተባለው፡፡ በጋዜጠኞቹና በሚዲያው ተቋም ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ሽብር ነው፡፡ የዚህ ድርጊት ዝርዝር ፍሬ ነገርና ምሥል ሁሉ የአሸባሪነትን የታወቀ ፖለቲካዊ ኪሳራና የአድህሮት ባህርይ እንደገና መልሶ መላልሶ የሚያረጋግጥ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡ አሸባሪነት የሚፈጥረው ፍርኃት ግን የመንግሥታት (የተባበሩትም ሆነ የተናጠልና የየቅል መንግሥታት) እንዳሻ መሆኛና መፈንጫ ሰበብ መሆን የለበትም፡፡ አሜሪካ መስከረም 1 ቀን 1994 ዓ.ም. የደረሰው አደጋ የሽብር አደጋ ነው፡፡ የአሜሪካን ማንነትና ምንነት የቀየረው ግን ከሽብሩ ጥቃት ይልቅ በሽብሩ ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ነው፡፡ ‹‹የፀረ ሽብርተኝነት ጦርነት›› የፓትርዮቲክ አክት (ሕግ) በአሜሪካ በወዳጅም በጠላትም የታወቀ ካፒታሊስታዊ ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ ጦርነት አወጀ፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ አሜሪካ በአንድ የተለያዩ በታወቀ የዘር/የሃይማኖት የሕዝብ ክፍል ላይ ቅስቀሳ ተብሎ ይወቀሳል፡፡ ጠላትህ እሱ ነው ብሎ ጃስ ማለቱ ሁሌም ይነገራል፡፡ የመላውን ዓለም ሕዝብም ‹‹እየው ፊትህ ቁጭ ብሏል ሁለት ዓይነት መንገድ›› ብሎ በማስፈራራት አንዱን ምረጥ በማለቱ መላውን ዓለም የማገድ የአሜሪካ የውክልና ጦርነት መጀመሩም በስፋት ተነግሯል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በሳምንታዊው ሻርሊ ላይ አደጋና ወንጀል የፈጸሙበትን ሁለት ግለሰቦች ጨምሮ በአሜሪካ ላይ የሽብር ጥቃት ያደረሱት ግለሰቦች፣ እንዲሁም የእነዚህንና የሌሎችን ልብ መርታት የቻለው ድርጅት (ድርጅቶች)ን አምጦ የወለደው የሥር ምክንያት ዋናው ተረስቶ እንኳን መፍትሔ ጥያቄ እንኳን ያልቀረበበት ጉዳይ መሆኑ ነው የሚተነተነው፡፡ እነ አሜሪካ እውነት ነው ስለሰብዓዊ መብት ይናገራሉ፡፡ ከአገራዊ ጥቅም ጋር ይገናዘባል እንጂ ስለሰብዓዊ መብትም ይቆረቆራሉ ይባላል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ይነሳ ከተባለ ግን ከአገራቸው በወረራና በሠፈራ ተባረው፣ በቁራሽ መሬት ላይ የራሳቸውን ሉዓላዊ አገር የማቋቋም ትንሽዬ ፍትሕ አጥተው ለብዙው ዓለም አቀፋዊ (ሃይማኖታዊ) አሸባሪነት ምክንያት የሆኑት የፍልስጤም ሕዝቦች ጉዳይ አሁንም ድረስ የዓለም ታላቁ የሰብዓዊ መብት ጥያቄ መሆኑ በስፋት ይነገራል፡፡ በዚህ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ጉዳይ የአሜሪካና የአውሮፓ ተጠያቂነት አለበት ይባላል፡፡ እነዚህን የሳምንታዊ ሻርሊ ጋዜጣ ሁሉት ‹‹እብዶች›› አምጦ የወለደው በፈረንሣይ በአገራቸው ውስጥ በራሱ አሽቀንጥሮ የሚያፈናጥራቸው አገራዊ ሁኔታ፣ የአሜሪካና የአጋሮቿ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦረኝነትና ጣልቃ ገብነት፣ ወዘተ ናቸው የሚል ስሞታም አለ፡፡ ይህን የመሰለ ጉዳይ እያለ በንግግር ነፃነት መሠረታዊ ግንባታ ላይ ስለተሠራ ወንጀል ብቻ መናገር ሳይሆን ሁሉም እውነት መናገር አለበት የሚሉ ድምፆችም ይሰማሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ከምንም ነገር በላይ ክብደትና ትኩረት የሚሰጠው ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት በጉልበተኞች እጅ መውደቅ የለበትም የሚለው ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -