Thursday, March 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለተፈጠረው የስኳር እጥረት አንደኛው ምክንያት ጅንአድ መሆኑ ተጠቆመ

ለተፈጠረው የስኳር እጥረት አንደኛው ምክንያት ጅንአድ መሆኑ ተጠቆመ

ቀን:

በሔኖክ ረታ

– ጅንአድ ችግር አጋጥሟል ከተባለ ተጠያቂነቱ የጋራ ነው ብሏል

በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማና በሌሎችም የክልል ከተሞች ለተከሰተው የስኳር እጥረት መንግሥታዊው የሸቀጦች ጅምላ ንግድና አከፋፋይ ድርጅት (ጅንአድ) አንደኛው ምክንያት መሆኑ ተገለጸ፡፡ ሰሞኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ባዘጋጀው የመስክ ጉብኝት በመተሐራና በወንጂ/ሸዋ ስኳር ፋብሪካዎች ከ157,574 ኩንታል በላይ ስኳር ተከማችቶ መገኘቱን ምክንያት በማድረግ፣ የፋብሪካዎቹ ኃላፊዎች ጅንአድ ምርቱን በፍጥነት ባለማጓጓዙ የተፈጠረ ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘነበ ይማም በስኳር ኮርፖሬሽን በምክትል ዳይሬክተር የሚመራ የምርት ክትትልና አቅርቦት ክፍል መኖሩን ተናግረው፣ ይህ ክፍል በሚሰጠው የምርት ማንሳት ሒደት መሠረት ምርቱ እንደሚነሳ ከገለጹ በኋላ በቅርቡ ምርቱ ተነስቶ ቦታውን ሊለቅ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ከ298,000 ኩንታል በላይ ስኳር መመረቱን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ከዚህ ውስጥ 72,000 ኩንታል በፋብሪካው የማከማቻ ክፍል ውስጥ መከማቸቱንና የጭነት ተሽከርካሪዎችን በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ ማምረት የጀመረው የወንጂ/ሸዋ ስኳር ፋብሪካም በማከማቻ ክፍሉ 85,574 ኩንታል ስኳር እንደሚገኝ የገለጹት የክምችት ክፍል ተጠሪ አቶ ታምራት ሙልደጆ፣ ለመጫን የሚመጡት ተሽከርካሪዎች ቁጥር በቀን ከ12 ወደ 23 ከፍ ቢልም በከፍተኛ መጠን የጨመረውን የአዲሱን ፋብሪካ ምርት ለማከማቸት የቦታ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችልም አሳስበዋል፡፡ ታህሳስ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በ24 ሰዓት ውስጥ 7,221 ኩንታል ስኳር ማምረቱ በፋብሪካው ታሪክ የመጀመሪያ መሆኑን የገለጹት የፋብሪካው የንብረት ክፍል ኃላፊ አቶ ዳዲ በቀለ፣ ይህ መጠን በቀን ይመረታል ተብሎ ይጠበቅ ከነበረው 6,000 ኩንታል ስኳር ጋር ሲነፃፀር በጣም አስደሳችና አበረታች በመሆኑ በዚሁ እንደሚቀጥል በመግለጽ፣ ምርቱ ከማከማቻ ክፍሉ አቅም በላይ እንዳይሆን ጅንአድ ቶሎ ቶሎ ማንሳት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ጅንአድ በበኩሉ በታቀደው መሠረት ስኳር ከየፋብሪካዎቹ እየተጓጓዘ መሆኑን አስታውቆ፣ በ45 ቀናት ሊነሳ ከታቀደው 395,000 ኩንታል ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ መነሳት መጀመሩን ገልጿል፡፡ ‹‹እስከ ጥር 30 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚዘልቀው 29ኛው ዙር ምርት የማንሳት እንቅስቃሴ በእኛ በኩል በዕቅዱ መሠረት እየሠራን ነው፤›› የሚሉት የጅንአድ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገመዳ አለሚ ናቸው፡፡ ፋብሪካዎቹ ምርታቸውን የሚያከማቹበት ቦታ እስከማጣት የሚያደርሳቸው ምንም ምክንያት እንደማይኖርና ይህ በራሱ ለጅንአድ ደስታ እንጂ ችግር ሊሆን እንደማይችልም ገልጸዋል፡፡ በዋናነት ለክልል ከተሞችና አነስተኛ ድርጅቶች ጅንአድ ስኳር በማከፋፈል ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ለአዲስ አበባ ከተማና ለትላልቅ ድርጅቶች የስኳር ማከፋፈሉን ሥራ ወስዶ የሚሠራው ራሱ ስኳር ኮርፖሬሽን በመሆኑ፣ በመጓጓዝ ላይ ተከስቷል የሚባል ችግር ካለ ተጠያቂነቱ የጋራ ሊሆን ይገባል ሲሉም አስታውቀዋል፡፡ ጅንአድ ከ20 በላይ የከባድ ጭነት ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ማኅበራትን በኮንትራት እያሰማራ መሆኑን የሚገልጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ እስካሁንም ከየፋብሪካዎቹ የተነሳው ስኳር በድርጅቱ የክምችት ክፍል ውስጥ እንደተቀመጠም ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...