Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የግል አየር መንገዶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻርተር ሥራ መግባቱ ሥጋት ፈጥሮብናል አሉ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የግል አየር መንገዶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአነስተኛ አውሮፕላኖች የቻርተር በረራ አገልግሎት ለመጀመር ማቀዱ፣ ከፍተኛ ሥጋት እንደፈጠረባቸው አስታወቁ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምቾት ያላቸው በርካታ አነስተኛ አውሮፕላኖችን ገዝቶ በአገር ውስጥና በውጭ የቻርተር በረራ አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንደሆነ በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ዘገባውን የተመለከቱ የግል አየር መንገዶች ባለቤቶችና ሥራ አስኪያጆች፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አስቸኳይ የውይይት መድረክ እንዲያዘጋጅ በደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡ ጥያቄያቸውን የተቀበለው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ባለፈው ዓርብ የግል አየር መንገዶችን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በመጥራት አወያይቷል፡፡ በስብሰባው ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የግል አየር መንገዶች ተወካዮች የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ የቻርተር በረራ አገልግሎት ለመስጠት የነደፈውን ዕቅድ ለህልውናችን ያሠጋናል በማለት አምርረው ተቃውመዋል፡፡ አየር መንገዱ ከአሥር እስከ ሃያ መቀመጫ ያላቸውን 50 ያህል አነስተኛ አውሮፕላኖችን በመግዛት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቻርተር በረራ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ጥናት አጠናቆ ወደ ዝግጅት መግባቱን አስታውቋል፡፡ የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎት ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካፒቴን አማረ ገብረሃና፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳድሮ የሚሠራ ግዙፍ አየር መንገድ ሆኖ ሳለ፣ በአነስተኛ የግል አየር መንገዶች የሚሠራውን የቻርተር በረራ አገልግሎት ለመስጠት ማሰቡ ግርምት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ያለው ጄኔራል አቪዬሽን ዘርፍ ብዙም ድጋፍ የማይደረግለትና በእንጭጭ ደረጃ የሚገኝ ነው፤›› ያሉት ካርቴን አማረ፣ ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቻርተር በረራ አገልግሎት ለመጀመር ያቀደበት ምክንያት ምንድነው? ዓላማው አሁን ያለውን ጄኔራል አቪዬሽን ማጥፋት ነው? ዕቅዱ የአየር መንገዱ ብቻ ነው? ወይስ የመንግሥት?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከሚተዳደሩት ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ትራንስኔሽን ኤርዌይስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ካፒቴን ተረፈ ኃይሌ፣ ትራንስኔሽን ኤርዌይስ መንግሥት በአውሮፕላን መቀመጫ ላይ የጣለውን ገደብ ከ20 ወደ 50 ከፍ ካደረገ በኋላ መደበኛ የአገር ውስጥ በረራ በመጀመር የመጀመሪያው የግል አየር መንገድ መሆኑን አስታውሰው፣ ኩባንያቸው ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የአዋጭነት ጥናት አጥንቶና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ኃላፊዎች ጭምር አማክሮ በአገር ውስጥ በረራ አገልግሎት ያለውን ክፍተት ለመሙላት በማቀድ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ትራንስኔሽን ኤርዌይስ መደበኛ የበረራ አገልግሎት ሊጀምር ነው ሲባል የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዘጋቸውን የአገር ውስጥ የበረራ መስመሮች ሁሉ መክፈት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ አክለውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ 50 አውሮፕላኖች ገዝቶ የቻርተር በረራ አገልግሎት ለመጀመር ማቀዱን በጋዜጣ ማንበባቸውንና ይህም እንዳስደነገጣቸው አውስተዋል፡፡ ‹‹አየር መንገዱ 50 አውሮፕላኖች ገዝቶ ወደ ቻርተር አገልግሎት የሚገባ ከሆነ፣ ከአንጋፋ አየር መንገድ ጋር የመወዳደር አቅም ስለሌለን ተሰናብተን መውጣት ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡ የናሽናል ኤርዌይስ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካፒቴን አበራ ለሚ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተለያየ ጊዜ የሚናገሩት መንግሥት የሚሠማራባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች በግሉ ዘርፍ ሊከናወኑ የማይችሉ ሥራዎችን እንደሆነ ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በግል አየር መንገዶች የሚሠራውን አነስተኛ የቻርተር ሥራ ለመሥራት ማቀዱ አስገራሚ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹አየር መንገዱ እንደ ኩባንያ የፈለገውን ሊሠራ ይችላል፡፡ ነገር ግን እኛ ማወቅ የምንፈልገው የአየር መንገዱ ዕርምጃ በመንግሥት የተደገፈ መሆኑን ነው፡፡ ይህን የምለው እኛ የመንግሥት ፖሊሲ ስላልመሰለን ነው፤›› ያሉት ካፒቴን አበራ፣ ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከእኛ ጋር ታች ወርዶ ቻርተር በረራ የሚሠራ ከሆነ፣ መንግሥት በእኛ ላይ የጣለውን የአውሮፕላን መቀመጫ ገደብ ሊያነሳልን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ ከግል አየር መንገዶች ለቀረቡት አቤቱታዎች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ምላሽ የሰጡት የኮርፖሬት ስትራቴጂ ኮሙዩኒኬሽንና አሊያንስ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሔኖክ ተፈራ ናቸው፡፡ አቶ ሔኖክ በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ ለመሆን መብቃቱን፣ ከአፍሪካ ትልቁ የካርጎ ኦፕሬተር መሆኑን፣ በ110 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ዘመናዊና ግዙፍ የካርጎ ተርሚናል በመገንባት ላይ መሆኑን፣ 84 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን በማገልገል ላይ እንደሆነ ጠቁመው እነዚህ አመርቂ ውጤቶች ሊገኙ የቻሉት ጠንክሮ በመሥራት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አቶ ሔኖክ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገሪቱ እያስመዘገበችው ላለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ፣ በተለይ ለቱሪዝምና ለወጪ ንግድ ዕድገት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚተጋ ተናግረዋል፡፡ እንደ ብሔራዊ አየር መንገድ በአገር ውስጥ ፍትሐዊ የሆነ የአየር ትራንስፖርት በመላው ኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ኃላፊነት እንዳለበት፣ በዚህ ረገድ መንግሥትም ያስቀመጠው አቅጣጫ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም አየር መንገዱ አዳዲስ የአገር ውስጥ የበረራ መስመሮች የሚከፍተው በራዕይ 2025 ባስቀመጠው ዕቅድ መሆኑን፣ ዕቅዱ የተዘጋጀው ከአምስት ዓመት በፊት መሆኑንና ትራንስኔሽን በረራ ሊጀምር ሲል አየር መንገዱ አዳዲስ መስመሮች ከፈተ የሚለው ፍፁም የተሳሳተ አስተያየት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ዓላማችን ፍትሐዊና ተደራሽ የሆነ የአየር ትራንስፖርት በሁሉም ክልሎች እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ በአገር ውስጥ የምንሰጠው አገልግሎት ገበያ መር አይደለም፡፡ የምናስከፈለው ክፍያ የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበ ነው፡፡ ይህ መንግሥት ያስቀመጠልን አቅጣጫ ነው፤›› ያሉት አቶ ሔኖክ፣ አየር መንገዱ አዲስ የቻርተር በረራ አገልግሎት ሊጀምር ነው የሚለው መረጃ ትክክለኛ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹የቻርተር በረራ አገልግሎት ለረዥም ዓመታት ስንሰጥ ቆይተናል፡፡ አሁን ግን ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉ አውሮፕላኖችን ገዝተን አጠናክረን ለመሥራት በዝግጅት ላይ ነን፤›› ያሉት አቶ ሔኖክ፣ አየር መንገዱ ባጠናው ጥናት ከአገሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተያይዞ የቻርተር በረራ አገልግሎት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን፣ የአየር አምቡላንስ አገልግሎት ፍላጎት እንዳለ መታወቁንና አየር መንገዱ የሚታየውን የቻርተር በረራ ፍላጎት ክፍተት ለመሙላት አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዳይሬክተር ጄኔራል ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ ቻርተር በረራ አገልግሎት እንዳይሠራ የሚከለክለው ምንም ዓይነት ሕግ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ብሔራዊ የአየር ትራንስፖርት ፖሊሲ በመዘጋጀት ላይ እንደሆነ ያስታወሱት ኮሎኔል ወሰንየለ፣ አሁን ያለው የአቪዬሽን መስክ የሚገዛው በኢንቨስትመንት ሕግ እንደሆነና የኢንቨስትመንት ሕጉ አየር መንገዱን የአገር ውስጥ ቻርተር አገልግሎት እንዳይሰጥ እንደማይከለክለው አስረድተዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ 50 አውሮፕላኖች ገዝቶ የሚሠራ ከሆነ እኔ ከዘርፉ እወጣለሁ የሚለው ተገቢ አይደለም፡፡ የግል አየር መንገዶች ተፎካክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዋናው ነገር ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ ምቹ የመወዳደሪያ ሜዳ አለ ወይ የሚል ነው እንጂ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህን ይሥራ ያንን አይሥራ ማለት አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡ መንግሥት ብሔራዊ አየር መንገዱን እንደሚደግፍ የተናገሩት ኮሎኔል ወሰንየለህ፣ ይህ የሚደረገው የግል አየር መንገዶችን በመጉዳት እንዳልሆነና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ፍትሐዊ የሆነ የውድድር መድረክ መኖሩን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ከግል አየር መንገዶች የቀረቡ አንዳንድ ጥያቄዎችን ለመንግሥት እንደሚያቀርቡ ቃል ገብተዋል፡፡ የአውሮፕላን መቀመጫ ብዛት ገደብን በተመለከተ በአየር ትራንስፖርት ፖሊሲ ውስጥ ምላሽ እንደሚያገኝ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ የግል አየር መንገዶች በኤርፖርት አገልግሎቶችና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን፣ በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች