Friday, September 22, 2023

መኢአድና አንድነት የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ፖለቲካዊ ነው በማለት ተቃወሙ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ታኅሳስ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. የመላው ኢትዮጵያ አድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በውስጣቸው ያለውን ችግር እንዲፈቱ በማለት፣ የአንድ ሳምንት ጊዜ መስጠቱ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው በማለት ፓርቲዎቹ ተቃወሙ፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና በሰጡት መግለጫ ለሁለቱም ፓርቲዎች ታኅሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ቦርዱ ባወጣው መግለጫ ላይ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታውሰው፣ አሁንም በተሰጣቸው ጊዜ ችግሮቻቸውን ፈትተው ወደ ምርጫ እንዲገቡ የጊዜ ገደብ ያስቀመጠ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ቦርዱ ዕርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ ባለፈው ዓርብ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ውሳኔውን ‹‹ፖለቲካዊ ውሳኔ›› በማለት ተችተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አክለውም፣ ‹‹ውሳኔው የተላለፈው በሕግ አግባብ ቢሆን ኖሮ ፍርድ ቤት የወሰነውን ውሳኔ ሽሮ ቦርዱ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ አያስተላልፍም ነበር፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ‹‹የፓርቲው ከፍተኛ የሥልጣን አካል ጠቅላላ ጉባዔው በመሆኑ የምርጫ ቦርድ ተወካዮች በተገኙበት በጠቅላላ ጉባዔው የተካሄደውን ምርጫችንን ማፅደቁን ቦርዱ እያወቀ፣ የውስጥ ችግራችሁን ፍቱ የሚለው አባባል ምንም ዓይነት የሕግ መሠረት የሌለው ነው፤›› በማለት አክለው አብራርተዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም የመኢአድ ሥራ አስፈጻሚ ይህን ሕገወጥ ውሳኔና ሽረባ ለአባላቱ ለማስረዳትና ውሳኔ ለመስጠት እንዲቻል የፓርቲውን ላዕላይ ምክር ቤትና የመጨረሻ የሥልጣን አካል የሆነው ጠቅላላ ጉባዔ አባላት ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ለጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ስብሰባ ጠርቷል፤›› በማለት መኢአድ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶ ለአባላቱ እንደሚገልጽ አስታውቀዋል፡፡ በተመሳሳይ የአንድነት ፓርቲ ተጠባባቂ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አሥራት አብርሃ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹ውሳኔው ፖለቲካዊ ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ገዥው ፓርቲ በምርጫ ቦርድ በኩል እየታገለን ነው ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ አንድነት ይህን ለመታገል ለጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቷል፤›› በማለት አቶ አሥራት አንድነትም ከመኢአድ ጋር ተመሳሳይ ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል፡፡ አቶ አሥራት አክለውም፣ ‹‹ይህ ጠቅላላ ጉባዔ ተጠራ ማለት ችግሩ ይፈታል ማለት አይደለም፤›› ብለው ምክንያቱን ሲገልጹ፣ ‹‹አንድነትን ከምርጫው የማስወጣት ፖለቲካዊ ውሳኔ የተወሰነ ነው የሚመስለው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ቀጣይ ዕርምጃዎችን በተመለከተ አቶ ማሙሸት፣ ‹‹አሁን ውሳኔ ባልተሰጠበትና ባልተከለከልንበት ጉዳይ ላይ ይኼ ነው ለማለት አንችልም፤›› ሲሉ፣ አቶ አሥራት በበኩላቸው፣ ‹‹ከዚህ በኋላ ለምናስተላልፈውና ለምንወስነው ፖለቲካዊ ውሳኔ ሕዝቡ ከጎናችን እንዲቆም ጥሪ እናስተላልፋለን፤›› በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -