Wednesday, March 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የገቢዎችና ጉምሩክ የወንጀል ምርመራ ቡድን አስተባባሪ ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጠ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የምሥራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ቡድን አስተባባሪ፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አላከበሩም በመባላቸው ለ24 ሰዓታት ታሰረው እንዲቀርቡ፣ ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡ ትዕዛዙን የሰጠው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል አራዳ ምድብ ችሎት ሲሆን፣ ትዕዛዙን የሰጠው ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ የቡድን አስተባባሪው ታስረው እንዲቀርቡ የታዘዘበት ምክንያት፣ በባልና በሚስት የፍርድ ቤት ክርክር ምክንያት በድርጅት ስም ያለ ንብረት በመታገዱ ምክንያት ነው፡፡ አቶ ፀጉብርሃነ ገብረ እግዚአብሔርና ወ/ሮ ክንዲሃፍቲ ኢታይ የተባሉ ባልና ሚስት፣ በከሳሽ ወ/ሮ ክንዲሃፍቲ አማካይነት በፍርድ ቤት ክርክር ይጀምራሉ፡፡ ክርክሩ በሒደት ላይ እያለ ከሳሽ የክርክሩ ውጤት እስከሚታወቅ ድረስ፣ በአቶ ፀጉብርሃነ ስም የተመዘገቡ ንብረቶች እንዳይሸጡ፣ እንዳይለወጡና ለሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፉ ዕግድ እንዲጣልላቸው ያመለክታሉ፡፡ እንዲታገዱላቸው ያመለከቱዋቸው ንብረቶች በፀጉብርሃን ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም የተመዘገቡ መሆናቸውን ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ ድርጅቱ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ገልባጭ ተሽከርካሪዎችንና የጭነት ተሽከርካሪዎችን በማስመጣት እየሠራ መሆኑንና በፍርድ ቤት ከተያዘው የባልና ሚስት ክርክር ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው በመግለጽ መከራከሩንም የክርክር ሰነዱ ያስረዳል፡፡ በድርጅቱ ስም የተመዘገቡትና በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታገዱት ንብረቶች ሁኔታ ግራ ያጋባቸው የጉምሩክ መጋዘን አስተዳደርና ቁጥጥር የሥራ ሒደት መሪ አቶ አበበ ኃይለ ሥላሴ ለፍርድ ቤት በጻፉት ደብዳቤ እንዳሳወቁት፣ ንብረቶቹ የተመዘገቡት በድርጅቱ ስም ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ንብረቶቹ እንዲታገዱ የሰጠው ትዕዛዝ ግራ የሚያጋባ በመሆኑ፣ ለጊዜው ተሽከርካሪዎቹና ማሽኖቹ ባሉበት መጋዘን ውስጥ ታሽገው የተቀመጡ ቢሆንም ፍትሐዊ የሆነ ውሳኔ ለማስተላለፍ እንዲቻል፣ በድርጅቱ ስም የተመዘገቡትን ተሽከርካሪዎችና ማሽኖችን ማገድ የሚችል ወይም የማይችል መሆኑን አረጋግጦ እንዲልክላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን በሰጠው ውሳኔ ድርጅቱ ንብረቶቹን ለማስለቀቅ ከፈለገ ሦስት ሚሊዮን ብር በሞዴል 85 አስይዞ እንዲያስለቅቅ፣ አለበለዚያ ግን ንብረቱ እንደታገደ እንዲቆይ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የንብረት ዕገዳውና እንዲሁም በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሠራተኞች የድርጅቱ የሒሳብ ሰነዶች በግዳጅ የተወሰዱት፣ የድርጅቱ መሥራችና ከፍተኛ ባለድርሻ የሆኑት አቶ ፀጉብርሃነ በሌሉበት መሆኑን፣ ጠበቆቻቸው ለፍርድ ቤቶቹ ያመለከቱባቸው ሰነዶች ይገልጻሉ፡፡ አቶ ፀጉብርሃነ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የምሥራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ቡድን በተገኙበት እንዲያዙ ከፍርድ ቤት መያዣ በማውጣቱ ፍርድ ቤት ሄደው መጠየቃቸው ተጠቁሟል፡፡ ለምን ታስረው እንዲቀርቡ እንደተፈለገ አቶ ፀጉብርሃነ ፍርድ ቤቱን ሲጠይቁ፣ የወንጀል ምርመራ ቡድኑ አስተባባሪ ቀርበው እንዲያስረዱ ፍርድ ቤቱ ያዛል፡፡ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ቢሰጥም ሊቀርቡ ባላመቻላቸው፣ ለጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ታስረው እንዲቀርቡና እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ አስተባባሪው ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ይዞ ማቅረብ እንዳልቻለ ፖሊስ በማመልከቱ፣ በድጋሚ ለጥር 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አቶ ፀጉብርሃነ ድርጅታቸው ልማታዊ ድርጅት መሆኑን ጠቁመው፣ ያለምንም ምክንያት የድርጅቱ ንብረት መታገድ ለኪሳራ እየዳረጋቸው መሆኑንና ለበርካታ ዓመታት የገነቡት መልካም ስም መጥፋቱን በመግለጽ፣ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ለኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት በተለይ በስም ጠቅሰው ያቀረቧቸው ዳኞች የሰጡት ትዕዛዝ፣ ሕግን የሳተና ሌላውን አልሚ የሚያስደነግጥ በመሆኑ አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንዲወስድባቸው፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ደግሞ ሠራተኞቻቸው ሕገወጥ በሆነ መንገድ የድርጅታቸውን የሒሳብ ሰነድ ከሕጋዊ መረካከቢያ ቅጽ ውጪ፣ ሠራተኞችን በማስፈራራት በመውሰዳቸው እንዲጠየቁና ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች