ግዙፉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ባገኘው ዋስትና መሠረት ለአዲስ አበባ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ስምንት ቢሊዮን ብር አበደረ፡፡ ባንኩ ብድሩን የሰጠው በአዲስ አበባ የተቀናጀ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮግራም ቀደም ሲል ግንባታቸው ለተጀመሩ ከ140 ሺሕ በላይ ቤቶች ማጠናቀቂያና ዘንድሮ አዲስ ለሚጀመሩ 62,000 ቤቶች በጠቅላላው ለ202,000 ቤቶች መሆኑን፣ የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሩ የአምስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ባለፈው ማክሰኞ ለሕዝብ ተወካዮች ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ 6.3 ቢሊዮን ብር ለአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በቀጥታ እንደሚገባና የተቀረው 1.67 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የሚውል ነው፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በ1997 ዓ.ም. ከተጀመረ ጀምሮ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ዋስትና ለአዲስ አበባም ሆነ ለክልሎች ብድር እየሰጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ የክልል ኮንዶሚኒየም ፕሮጀክቶች ቀድሞ እንደታሰበው ፈላጊ ሊያገኙ ባለመቻላቸው፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በ2002 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ተጨማሪ ግንባታ በክልሎች እንዳይከናወን ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለክልሎችና ለአዲስ አበባ የኮንዶሚኒየም ፕሮጀክቶች በዚህ ዓመት ያበደረውን ሳይጨምር፣ በጠቅላላው 13 ቢሊዮን ብር በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ዋስትና መስጠቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ባንኩ ከሰጠው ብድር ውስጥ ትልቁ ባለድርሻ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በማግኘት የአዲስ አበባ የኮንዶሚኒየም ፕሮጀክት ቀዳሚ ሲሆን፣ የተቀረውን ክልሎች ተከፋፍለውታል፡፡ ይህ 13 ቢሊዮን ብር እስካሁን ተከፍሎ አለመጠናቀቁን ከሚኒስትሩ ገለጻ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውም በዚህ ዓመት የቀድሞው ብድር ሦስት ቢሊዮን ብር እንዲመለስ እየተከታተለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ባለፉት አራት ወራት ውስጥ 843.5 ሚሊዮን ብር ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ክልል፣ ከትግራይና ከአዲስ አበባ አስተዳደር ተሰብስቦ ተመላሽ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ዓመት በመጋቢትና በሚያዚያ ወራት ውስጥ የሚተላለፉ ከ70 ሺሕ በላይ ቤቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ‹‹በ20/80 እና በ10/90 ቤቶች ፕሮግራም ቀድሞ የከፈለ ወይም የበለጠ የከፈለ ዕጣ ውስጥ ይገባል የሚባል ነገር የለም፡፡ ዕጣ ውስጥ ለመግባት መሠረቱ 20 በመቶውን ማሟላት ወይም 10 በመቶውን ማሟላት ብቻ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ግን የቤቱን ዋጋ ሙሉ በሙሉ ከከፈሉት በመነሳት እስከ 40 በመቶ የከፈሉ እንዲወዳደሩ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡