የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2006 በጀት ዓመት ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ከ5.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ ይህንን የውጭ ምንዛሪ ያገኘው በባንኩ አማካይነት ምርቶቻቸውን ከላኩ ላኪዎች፣ በባንኩ በኩል ገንዘብ እንዲዘዋወር ካደረጉ የገንዘብ አስተላላፊ (ሐዋላ) ኩባንያዎችና ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ነው፡፡ ለውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ምክንያት ለሆኑት ለእነዚህ ተቋማት ባለፈው ሐሙስ ባንኩ በሸራተን አዲስ ባዘጋጀው የወጪ ንግድ ቀን ዕውቅና በመስጠት ሽልማት ሰጥቷል፡፡ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ አስገኝተውልኛል ብሎ በተለያዩ የመንግሥትና የባንኩ ባለሥልጣናት ሽልማት ያሰጣቸው የግልና የመንግሥት ተቋማት ቁጥር 173 ነው፡፡ ከተሸለሙት ኩባንያዎች መካከል ከላኪዎች ዘርፍ ሚድሮክ ጎልድ፣ ከገንዘብ አስተላላፊዎች ዌስተር ዩኒየን፣ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይገኙበታል፡፡ በምሥሉ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የታደሙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታደሰ ኃይሌ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪና የባንኩ ቦርድ ሊቀ መንበር አቶ በረከት ስምኦን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪና የባንኩ የቦርድ አባል አቶ ዓባይ ፀሐዬና የንግድ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ያዕቆብ ያላ ይታያሉ፡፡ ዝርዝር ዘገባውን በ ቢዝነስና ኢኮኖሚ ገጽ ላይ ይመልከቱ፡፡