Friday, June 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሚዲያው ሥነ ምኅዳር ካልታረመ ጥፋቱ ይበረታል

 በሒሩት ደበበ

 እንደ አገር ከበርካታና የዘመናት  ውጣ ውረድ በኋላ የተስፋ መንገድ የጀመርንበት ጊዜ ላይ እንደምንገኝ መመስከር ከእውነታው የሚያርቀን አይመስለኝም፡፡ ይህ ማለት ግን አሁን  አገሪቱ ሁሉ ነገር  አልጋ በአልጋ ሆኖላታል ማለት እንዳልሆነ መረዳት የሚያዳግት አይደለም፡፡ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሕዝቦች አንድነት እየላላ፣ ግለኝነት እየበዛና የተጀመረው ፈጣን የለውጥ መንገድ እየተደናቀፈ መሆኑ ሲታይ ቆም ብሎ ማሰቢያው ወሳኝ ጊዜ ላይ ለመገኘታችን አንዱ አስረጅ ሆኗል፡፡

      በእርግጥ በአገሪቱ  በዚህም በዚያም የሚታዩት የልማት ሥራዎች ብቻ ሳይሆኑ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ባህል እንዲገነባ የሚረዳ ሕገ መንግሥት (ሊሻሻሉ የሚገባቸው አንቀፆች እንዳሉ ሆነው) በሥራ ላይ  መሆኑ አበረታች እውነታዎች ናቸው፡፡  ይሁንና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ረገድ በአፈጻጸም ሊሻሻሉና ሊጠናከሩ ሲገባቸው  እየኮሰሱ የመጡ አንዳንድ ጉዳዮች በተዳከመ መንገድ እየተንፏቀቁ መሄዳቸው አሳሳቢ የሕዝብ እምቢተኝነትና ሥርዓት አልበኝነት እንዲፈጠር በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ የዚህ መዘዝም እንደ አገር ሰላም እንዲደፈርስ ከማድረግ ባሻገር ባለሀብቱ በቂ ዋስትና እንዲያጣ፣ ብሎም የተጀመረው ልማት እንዲዳክም ግልጽ ምክንያት በመሆን ላይ ነው፡፡ 

      ከዚህ አንፃር የአገራችን የመንግሥትም (የሕዝብም) ሆነ የግሉ ሚዲያ ምን ይጠበቅበታል? ትኩረቱስ ምን መሆን አለበት? አገር ይነስም ይብዛም በፈተና ውስጥ ስትሆንና መደነቃቀፍን የሚያስወግድ ለውጥ  ሲያስፈልግ ሚዲያው ቀና ብሎ ሊጫወተው የሚገባው ሚና ምን መሆን አለበት? የሚለው ቁም ነገር ላይ መነጋገር አስፈላጊና ግድ የሚል እምነት በመያዝ አንዳንድ የግል ዕይታዎችን ለመሰንዘር እወዳለሁ፡፡

አሁን ባላው ተጨባጭ ሁኔታ የአገራችን የሚዲያ ሥነ ምኅዳር ከ25 ዓመታት ወዲህ አዲስ ምዕራፍ መጀመሩ ባይካድም፣ በመጠኑና ልዩ ልዩ አመለካከቶችን  የማስተናገድ አቅሙ እየቀነሰ፣ ሙያተኛውም በብቃትና ተወዳዳሪነት ረገድ እየተዳከመ፣ መስኩ ጠንካራ ማኅበርና ካውንስልም ሳያገኝ  የመንሸራተት ጉዞ ላይ ወድቋል፡፡

በድምሩ የአገራችን መገናኛ ብዙኃን ሥርዓቱንም ሆነ ሕዝቡን በገንቢ ሒስ ሲሳሳቱ የማያርሙ፣ አለፍ ሲልም በውስጣቸው ጭምር አፍጣጭ ገልማጭ ያለባቸው (በተለይ የመንግሥቶቹ)፤ የኤሌክትሮኒክሶቹም በአብዛኛው የእንቶፈንቶ መዝናኛ ዘገባና የውጭው ዓለም ቧልት ላይ የተጠመዱ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ሚዲያዎቻችን በጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ ምግባር፣ በሙያው መርሆዎችና በአገሪቱ ገዥ ሕጎች ላይ ተመሥርተው አለመሥራታቸው ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ የቀደመው የአንድነት፣ የጀግንነትና የአርበኝነት ታሪክን በማቀንቀን አዲሱን ትውልድ ለመቅረፅ  አለመነሳሳታቸውና በወቅታዊው የልዩነት ፖለቲካ ማዕበል ሲላጉ መዋል፣ ማደራቸው ክፉኛ የሚያሳዝን እውነታ ሆኖ ይገኛል፡፡

እንግዲህ በዚህ ጸሐፊ የግል ዕይታ የመስኩ እንቅፋቶችን ምንነት በመግለጽ፣ መፍትሔውን ማመላከት ተመርጧል፡፡ በመሠረቱ በየትኛውም ዴሞክራሲ እየገነባ ባለ አገር እንደሚታየው ሚዲያው በየደረጃው በነፃነት መሥራት ሲችል ነው የዴሞክራሲ ባህል የሚገነባው፣ የግልፅነትና የተጠያቂነት አለት የሚነጠፈው፣ ብሎም ብሔራዊ ችግሮች ሊቀረፉ የሚችሉት፡፡ ለዚህም ሲባል  የአገራችን መገናኛ ብዙኃን (ሚዲያዎች)  ነፃነት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ብቻ ሳይሆን፣ በመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት 590/2000 አዋጅ መሠረትም  የተከበረ  መሆኑ ይታወቃል፡፡ እውነቱ ይህ ይሁን እንጂ ሚዲያው በነፃነት እንዲሠራ፣ በነፃነት እንዲዘግብ፣ በነፃነት እውነትን ለሕዝብና ለመንግሥት እንዳያደርስ በርካታ እንቅፋቶች ያጋጥማሉ፡፡ 

መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ጠባቂ አልሆነም

       በአገሪቱ የሚዲያ ምኅዳር አለመጠናከር ውስጥ አንደኛው ችግር ከመንግሥት አካላት በኩል የሚያጋጥመው ተግዳሮት ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት ሕግ በአንፀባራቂ ቀለም ተጽፎ በሥራ ላይ የዋለ  ቢሆንም  አሁንም በተለይ የመንግሥት ሚዲያው የሥርዓቱ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ እንዲሆን የተፈረደበት መስሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ በየሴክተሩ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ቢቀረፅም በአንድ የፓርቲ ዕዝ ላይ የተመሠረተ የሚመስል የኤዲቶሪያል ኮሚቴና የፖለቲካ ተሿሚ ተፅዕኖ የበረታ መሆኑ መፈናፈኛውን አጥብቦታል፡፡ በዚህም የተነሳ ወጣ ብሎና በነፃነት ሊሠራ የሚችለው ሙያተኛ እየተገፋ ታዛዡና በአድርባይነቱ የደለበው ብቻ ሕግ እየጣሰ (ከሕገ መንግሥቱም ሆነ ከአዋጅ 590/2000 ጋር እየተጋጨ) ለወር ደመወዝ እንዲኖር ተገዷል፡፡

       በኅትመትም ሆነ ኤሌክትሮኒክ ሚዲያው የግሎቹ ጋዜጠኞቹም ሆኑ የሚዲያ ባለቤቶችም አልጋ በአልጋ ሁኔታ ላይ እንዳልሆኑ ይታወቃል፡፡ እየተፍገመገሙም  የኅትመት ወጭን ሽፍነው፣ በመረጃ ክልከላም ውስጥ ቢሆን የቀጠሉ ቢኖሩም ቀላል ቁጥር የሌላቸው በተለያየ ምክንያት ከጨዋታው ወጥተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዘገባቸው በደግና መልካም አፈጻጸሞች ላይ ብቻ እንዲያተኩር (ምንም ዓይነት የዕርምት ሒስ እንዲነሳ የማይፈልጉ) የሚሹና ለዚህም እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ የመንግሥትና የፓርቲ ሰዎች፣ ድርጅቶችና ተቋማት እንዳሉ ቀድሞም የሚታወቅ ቢሆንም ዛሬም በተጨባጭ እየታዩ መሆናቸው ጉዳቱን አብዝቶታል፡፡

        አሁንም በተሃድሶና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ እንረባረብ እየተባለ እንኳን አንዳንዶች የሚዲያ ሙያተኛውንና የመገናኛ ብዙኃኑን ለማስፈራራት የሚሹ፤ ሌሎች ደግሞ ከሚዲያው ጋር ጦርነት ውስጥ በመግባት ለምን ስለእኛ ተጻፈ? ተዘገበ ተነገረ? በሚል ሚዲያውን ለማስፈራራትና ለማሸማቀቅ የሚራወጡ በየመንግሥት አካላቱ ውስጥ ሞልተው ተርፈዋል፡፡ ከዚያም አልፎ ከመርህና ሕግ ውጭ ሚዲያው ይኼን ይዘግብ ይኼን ይተው የሚል የክልል አመራር እየተቀፈቀፈ ከመምጣቱ ባሻገር ማዕከላዊነትንም እየተጋፋ ይገኛል፡፡

      እነኝህን የፀረ ዴሞክራሲ ሥርዓቶች አንጎበር ያለቀቃቸው (ለመንግሥትም ለሕዝብ የማይበጁ) አንዳንድ ጭፍን ካድሬዎችና መንቻካ ሰዎች ለመሆኑ እናንተ እነማን ናችሁ? ብሎ መንግሥት፣ ሕዝቡና ጋዜጠኛው መጠየቅ  ያለባቸው ጊዜ አሁን መሆኑን መገንዘብ  ያስፈልጋል፡፡ ገንቢ ሒስን፣ የሕዝብ ድምፅንና የአገር ፍላጎትን ወደ ጎን ብለው ራሳቸውን ብቻ ለማዳመጥ የሚሽቱ ገዳቢዎችና የደረስንበትን የመረጃ ዓለምነት ያልተገነዘቡ ኃይሎች ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም በላይ አይደላችሁም ማለትም የሚፈልገው አሁን ላይ ነው፡፡ (እዚህ ላይ የዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ተሸካሚ የሚዲያ ባለቤቶችና የሥራ ኃላፊዎችም በጥብቅ ሊወገዙ ይገባቸዋል)፡፡

በመሠረቱ ሳንሱር (ቅድመ ምርመራ) በአገሪቱ ሕግ መሠረት የተከለከለ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከቀድሞው ሥርዓት ጋር አብሮ ወደ መቃብር እንደወረደ ተደጋግሞ ሲነገር ይደመጣል፡፡ ይህ እውነታ በውል  እየታወቀ ዛሬም በሥውር የሳንሱር መቀስ የተጠመዱ ኃላፊዎችና ሹማምንት በየመሥሪያ ቤቱ ታጉረዋል፡፡ ከዚህም አልፎ ይህን ማድረግ የሚዳዳቸው የሚዲያ ኤዲተሮችና ኃላፊዎች በአንካሳ ልብ ውስጥ ሆነው ስለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የሐሳብ ነፃነት ይሰብካሉ፡፡ ሚዲያው በአግባቡ ሙያዊ ኃላፊነቱን እንዳይወጣ በየቦታው የጎን ውጋት ሆነው አላሠራ ያሉትም እነዚህን የመሳሰሉ ወገኖች  በመሆናቸው ፈጥኖ የሚዲያውን ሥነ ምኅዳር አርነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

     በተለይ በየመሥሪያ ቤቱ ለምን ተተቸን? ለምን ተወቀስን? ለምን ስለእኛ ተጻፈ? በሚል ጋዜጠኛውን አላሠራ ብለው የሥራ ሞራሉንና ተነሳሽነቱን የሚፈታተኑት  አምሳያዎቻቸው የሚዲያ ኃላፊዎች ናቸው፡፡ ሚዲያው ሕዝባዊ የሆኑ ጉዳዮችን፣ ሙስናን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን፣ የፍትሕ ዕጦትና በደልን በየተቋማቱ ያሉ ብልሹ አሠራሮችን፣ የኦዲት ችግሮችን፣ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ብክነቶችን ተከታትሎ በሚሠራበት ወቅት ለምን ተጋለጠ? ለምን አደባባይ ወጣ? ሊባል አይገባም ነበር፡፡ እንዲያውም እየተደፋፋረና ጥበቃ እያገኘ ቢሄድ አሁን አገር አንገት ደርሶ አላላውስ ያለው ችግር ሁሉ ገና ከእንጭጩ ንፋስ እየመታው፣ ፀሐይ እየሞቀው በሄደ ነበር፡፡

        ትናንት በሞዴል አርአያነት የተጠቀሱ የመንገድ ፕሮጀክቶች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የስኳር ፕሮጀክቶችና ኮንትራክተሮቻቸው እንዲሁም የሴክተሩ ኃላፊዎች ሁሉ ዛሬ በሙስናና ሕዝብን በመበደል ከመከሰሳቸው በፊት በሐሰት ሪፖርት እያሞካሸ የካባቸው ሚዲያው ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ውሎ አድሮ ሲጋለጥ  እንደ አገርም ሆነ እንደ ሕዝብ ሁላችንንም ያሳፍረናል፡፡ አንገትም ያስደፋል፡፡

እዚህ ላይ በተለይ በመንግሥት ሚዲያው አካባቢ ያለው አሠራርና የሙያተኛው የዘገባ ሥነ ልቦና መርማሪነት የጎደለው መሆኑና ሕዝብ አሳታፊ አለመሆኑ አንዱ ችግር ቢሆንም ዋነኛው ችግር ግን አስፈጻሚው፣ ሕግ አውጭውም ሆነ ሕግ ተርጓሚው ስኬት እንጂ ውድቀትን መዘገብ እንደ ነውር መቁጠሩ የአንበሳውን ድርሻ ተጫውቷል፡፡ የተሠሩ ሥራዎችን ከመጠንና ከቁጥር አኳያ ብቻ እንጂ ከጥራት፣ ከወጪ፣ ከጊዜና ከሕዝብ ተጠቃሚነት የማይመዝነው የሥራ ኃላፊ ሁሉ ለከንቱ ሙገሳና ላልተገባ ፉክክር ሲጠቀምበት የቆየው ሚዲያውን መሆኑም የውድቀቱ መጀመርያ ነበር፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ ሚዲያው የሚፈለግበትን ያህል ኃላፊነቱን አልተወጣም በሚል የገደል ማሚቱ ሆነው የሚጮሁትም እነዚሁ ወገኖች መሆናቸው ነው፡፡

ስለሆነም በቀዳሚነት መንግሥት በውስጡ ላሉ የሥራ ኃላፊዎችን፣ ባለሙያዎችን በተለይም የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን ሰዎችን በማረም ለፕሬስ ነፃነትም ሆነ ለአመለካከት ብዝኃነት መስተናገድ እንዲተጉ ማድረግ አለበት፡፡ ውግንናውም ለሕጋዊ፣ ሚዛናዊና ዴሞክራሲያዊ ሚዲያዎችና ሙያተኞች ሊሆን ይገባል፡፡

 የፕሬስ ሕግጋት ይከበሩ

በመሠረቱ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 (ከተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 19 ልክ) የሐሳብ ነፃነትን በተሟላ መንገድ ዋስትና ሰጥቷል ሊባል ይችላል፡፡ እዚያው ላይ ቅድመ ምርመራና ክልከላም አክትመዋል፡፡ ስለሆነም በሕግ ከተከለከሉት በስተቀር ማንኛውም የሕዝብና የመንግሥት  መረጃ በጋዜጠኞች በተጠየቀበት ጊዜ ሁሉ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል መሰጠት እንዳለበት ይታወቃል፡፡ ይህም በተለይ በመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000 ክፍል ሦስት ላይ አስፈጻሚውና ሁሉም የመንግሥት አካል የተጣለበት ግዴታ አለ፡፡ ይሁንና ዕንባ ጠባቂ ተቋምም ተቋቋመ፣ በኮሙዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት ደረጃ መረጃ የመስጠት ግዴታ አለብን የሚል ብዙኃኑ አመራር ገና አልተፈጠረም፡፡ ከመረጃ ክልከላ፣ ቅሸባና መጎተት ምክንያት የተቀመጠው ገንዘብና የእስር ቅጣትም እስካሁን በአንድም መረጃ ሰጪ ላይ ስለመተግበሩ አልተሰማም፡፡ ታዲያ ሕጉ ለምን ወጣ?

በመሠረቱ የመረጃ ጥያቄዎቹ በደል ከደረሰባቸው፣ ብሶት ካለባቸው ሰዎች የመልካም አስተዳደር የፍትሕ ችግር አጋጥሞናል ከሚሉና በተጨባጭ ማስረጃ ለማቅረብ ከሚችሉ ክፍሎች ሁሉ ሊነሱም ይችላሉ፡፡ ጋዜጠኛውም ሆነ የሚዲያ ተቋሙ የመጀመርያው ኃላፊነት ማጣራትና የሚመለከታቸውን አካላት በሚዛናዊነት ማነጋገር  መሆኑም የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ ውጭም ሚዲያው አስተያየቶችን፣ ሐሳቦችን፣ ምልከታዎችን የመቀበልና የማስተናገድ ኃላፊነትም አለበት፡፡ የለም እውነቱ ይህ አይደለም የሚል ወገን ደግሞ በወጣው ጽሑፍ ላይ ምላሽ የመስጠትና እውነታውን  ለሕዝብ ግልጽ  የማድረግ መብት አለው፡፡ በዚህም የተለያዩ አስተሳሰቦች ይንሸራሸራሉ፣ ሕዝቡም ይተነፍሳል፣ የአገሪቱ ፖለቲካም ውስጡን ለማየት ዕድል ያገኛል፡፡

ይሁንና  የሕግ ተጠያቂነት ነገር ሲነሳ ከመረጃ ሰጪው ወገን ይልቅ ጋዜጠኛውና የሚዲያ ተቋሙ ላይ የመበርታት ነገር ጎልቶ ይታያል፡፡ ማንም ቢሆን ከሕግ በታች መሆኑ ቢታወቅም ታዳጊ በሆነ ዴሞክራሲና ታዳጊ በሆነ ሚዲያ ላይ ከልክ በላይ መዝመት፣ ጋዜጠኛውን መክስስ፣ በማስፈራራት ማሳደድ የአገሪቱን መልካም ገጽታ ከማጠልሸትና የጥላቻ ፖለቲካን በሌላ ፅንፍ ከማጠንከር ውጪ የሚያስገኘው ውጤት የለም፡፡ በእርግጥ ጋዜጠኛውም ቢሆን ሕግን መሠረት አድርጎ (አክብሮና አስከብሮ) መሥራት እንዳለበት እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡

ሚዲያው በችግር ጊዜ አገር ካላዳነ ፋይዳ የለውም

አሁን አገራችን የምትገኝበት ሁኔታ የፖለቲካ ችግር ያለበት ነው፡፡ ያለ ጥርጥር መደማመጥ የተዳከመበት ዜጋው ስለሚጎለብት ልማትና ዕድገት እንኳን ብዙም መጨነቅ የተወበት ፈታኝ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በየአካባቢው የመልካም አስተዳዳርና የለውጥ ፍላጎት መቀስቀሱ የሚጠበቅ ቢሆንም ፍላጎትን በኃይል ለማስፈጽም የተነሳሱ ግለሰቦችና ቡድኖች አለፍ ሲልም የፖለቲካ ኃይሎችና አክቲቪስቶች መኖራቸው የችግሩን አሳሳቢነት ደረጃ ያሳያል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ በሕዝቦች መካካል ልዩነትና ግጭት እንዲፈጠር እየተሞከረ ያለው የፖለቲካ ሴራና መጠራጠር ጎልቶ መታየቱ ሁሉንም ከእንቅልፍ የሚያባንን እንደሆነ ይሰማናል፡፡

እንግዲህ አገር በዚህ ወደ ኋላ በሚመልስ ፈተና ውስጥ ሆና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትንና ፈሪሀ እግዚአብሔርን ብሎም ለዘመናት የተሳሰረ አገራዊ ኅብረትንና አርበኝነትን ማስተማር የማይችል መገናኛ ብዙኃን ካለም አይቆጠርም፡፡ ከዚህም አልፎ በመንግሥት በኩል መታየት ያለባቸው መፍትሔዎችን ያልተመለከተ፣ ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ ከስሜት እንዲርቅ ያላስተማረ፣ በተለመደው መንቻካ ፕሮፓጋንዳ ብቻ የተጠመደ፣ እንዲሁም ሁሉም የዴሞክራሲ ተቋማት ለቆሙለት ዓላማ እንዲሠሩ መጫን ያልቻለና ሰላምን መዘመር የተሳነው ሚዲያ ባይኖርም ተመራጭ ነው፡፡

አሁን በአንዳንድ የአገራችን ሚዲያዎች (ዛሚ ሬዲዮ በተደጋጋሚ፣ የሰሞኑን የኢኤንኤን እንዲሁም ከቀናት በፊት የኦሮሚያ ቲቪ አዘጋገብ፣ ከወራት በፊት የትግራይና አማራ ቴሌቪዥን አካሄዶችን ያጤነዋል) እየታየ እንዳለው አጉል ተወዳጅነትን ለማትረፍ፤ የእርስ በርስ ግጭት ሊቀሰቅስ የሚችል ሐሰተኛና ስሜታዊ መረጃ የማቅረብ ዝንባሌ ፍፁም መታረም ያለበትና አገር በታኝ አካሄድ ነው፡፡ ለዚህም ነው ለዓመታት በዝምታ ባህር ውስጥ ተዘፍቆ ከከረመው የኢፌዴሪ ብሮድካስት ባለሥልጣን አጣዳፊ መግለጫዎችን መስጠት እየጀማመረ ያለው፡፡

ምንም ተባለ ምን ግን በራሳችን ድክመትም ይሁን በመንግሥት ወደ ኋላ መቅረት ያዳከምነው ፕሬስና የዜጎች የሐሳብ ነፃነት ምኅዳርን ለማስፋት፣ ለማጠናከርና አገርን ከጥፋት እንዲያድን ለማድረግ እንነሳ፡፡ ካልሆነ ግን አሁን ባለው አካሄድ ሁሉንም መጨፍለቅ ቢያስቸግርም ሚዲያው ችግርን ያባባሰ እንደሆን እንጂ አገርን ከችግር ሊያወጣ አይችልም፡፡ ያውም ኮንቬንሽናል (መደበኛ) መገናኛ ብዙኃን በማኅበራዊ ድረ ገጽና ፌስቡክ ዥዋዥዌ ውስጥ ገብቶ እየዋኘ መውጫውን ማግኘት ከፈተናም በላይ ፈተና መሆኑም መዘንጋት አይገባም ለማለት እወዳለሁ፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles