Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልግዙፎቹ የቻይና ፊልም ስቱዲዮዎች

ግዙፎቹ የቻይና ፊልም ስቱዲዮዎች

ቀን:

የቻይናዋ መዲና ቤጂንግ ምሽት ላይ ከሚደምቁ ከተሞች አንዷ ነች፡፡ በየጎዳናው በሥራ የተጠመዱ ፍራፍሬ ሻጮች ገበያተኞችን ያስተናግዳሉ፡፡ በቅርብ ርቀት የቻይናን ባህላዊ ምግቦች የሚሸጡ ሰዎች በሠልፍ የሚጠብቋቸውን ተመጋቢዎች ፍላጎት ለማርካት ተፍ ተፍ ይላሉ፡፡ ከተለያዩ አገሮች ቻይናን ለመጎብኘት የተጓዙ በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች የፍራፍሬና ምግብ ገበያው ይጦፋል፡፡ እንደ ዋንፉጂ ያሉ ጎዳናዎች ምሽት ላይ ሞቅ ደመቅ ስለሚሉ በጎብኚዎች ይመረጣሉ፡፡

የበርካታ አገሮች ኤምባሲዎች የሚገኙበት ጎዳና በጎብኚዎች የሚዘወተር ሲሆን፣ የተለያዩ አገሮች ባህላዊ ምግቦችን የሚሸጡ ሬስቶራንቶችም መናኸሪያ ነው፡፡ የምሽት ክለቦችና ባሮችም ለተዝናኞች በራቸውን ክፍት አድርገው ይጠባበቃሉ፡፡ ጎዳና ላይ መጠጥ እያዘጋጁ በፕላስቲክ ብርጭቆ የሚሸጡ መጠጥ ቀማሪዎች ገበያ የደራ ነው፡፡ ብዙዎች በመገናኛ ብዙኃን ተመልክተዋቸው ቻይና ሲሄዱ በዕውን ለመታዘብ ከሚጓጉላቸው ሁነቶች አንዱ በሕይወት ያሉ ጊንጦች ተጠብሰው ለምግብነት ሲቀርቡ ነው፡፡

ዋንፉጂ ጎዳና ጊንጥ ለምግብነት ከሚሸጥባቸው አካባቢዎች በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል፡፡ የምግብ ልማዳቸውና ባህላቸው የሚፈቅድላቸው የተጠበሱ ጊንጦች እየተንቀሳቀሱ ለመመገብ ይደፍራሉ፡፡ ድርጊቱን ለማመን የሚቸገሩ፣ የሚደነግጡ፣ የሚቀፋቸውና ብዙም የማይደነቁም ሰብሰብ ብለው ይመለከታሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በኤምባሲዎች ጎዳና የአገራቸውንና የሌሎች አገሮችንም ምግብ የሚመገቡ ጎብኚዎች ይበዛሉ፡፡ ለማወራረጃ መንገድ ላይ ሞሒቶና ሌሎችም መጠጦች ይሸምታሉ፡፡ በደማቅ የቤጂንግ ምሽቶች የጎብኚዎችን ትኩረት ከሚስቡ መካከል ፊልም የሚቀረፅባቸው ቦታዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ወይም ፊልሞች ሲቀረፁ ያጋጠማቸው ሰዎች በአንክሮ ይከታተላሉ፡፡

በዓለም የፊልም ኢንዱስትሪ እየገነኑ ከመጡ መካከል የቻይና ፊልም ኢንዱስትሪ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ በተለይም የቻይና ፊልሞች የሚስቧቸው ጎብኚዎች ፊልሞቹ ሲቀረፁ መመልከት ያስደስታቸዋል፡፡ ፊልም የሚቀረፅበት ቦታ ተገኝቶ ከስክሪኑ ጀርባ ያለውን ውጣ ውረድ መመልከትን ከፍተኛ ዋጋ ይሰጡታል፡፡ በቻይና ቆይታችን አንድ ምሽት ላይ ያስተዋልነውም ይህንኑ ነው፡፡ በቅርቡ ለዕይታ የሚበቃ ፊቸር ፊልም ቤጂንግ መሀል ላይ ይቀረፃል፡፡ ጥንዶች መኪና ውስጥ ሆነው የሚያደርጉት ንግግር የሚቀረፅበትን ክፍል ነበር የተመለከትነው፡፡

 የፊልሙ አዘጋጅና የተቀሩትም ባለሙያዎች በየተዘጋጀላቸው ወንበር ተቀምጠዋል፡፡ ቀረፃውን የሚረብሽ ድምፅ ሳናሰማ ከበስተኋላቸው ሆነን እንድንከታተል ጋበዙን፡፡ ቤጂንግ የቻይናውያን ፊልም ሠሪዎች ብቻ ሳይሆን የሆሊውድና ሌሎችም ኢንዱስትሪዎች ባለሙያዎች መዳረሻ መሆኗን ገለጹልን፡፡ ቤጂንግ ከተማ ውስጥ ከሚከናወኑ ቀረፃዎች በተጨማሪ ሁዋይሩ የተባለ ግዙፍ ስቱዲዮም የበርካቶችን ቀልብ የሚስብ ቦታ ነው፡፡

ሁዋይሩ ቤዝ ኦፍ ቻይናስ ፊልም ኤንድ ቴሌቪዥን በመባል የሚጠራው የፊልም ስቱዲዮ አንድ ሰፊ መንደር ያክላል፡፡ በውስጡ የተለያየ ዘውግ ፊልሞች የሚቀረፁባቸው ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ መግቢያው ላይ የዝነኛው አኒሜሽን ፊልም ‹‹ኩንግ ፉ ፓንዳ›› ዋና ገፀ ባህሪ የሆነው ፓንዳ ቅርፅ ይታያል፡፡ የፊልምና ቴሌቪዥን መርሐ ግብሮች አርትኦት የሚሠራባቸው ክፍሎችም ይገኛሉ፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2008 እስከ 2012 ከወጡ ከ78 ፊልሞች 36ቱ የተቀረፁት በሁዋይሩ ነው፡፡ ከዓመት ወደ ዓመት በስቱዲዮው የሚሠሩ ፊልሞች ቁጥር ተበራክቷል፡፡ በቻይና ታሪክ የተለያየ ዘመናትን የሚወክሉ ግዙፍ የቀረፃ ቦታዎች መገኘታቸው ለዚህ ምክንያት ሆኗል፡፡ 

መቼቱ ጥንታዊት ቻይና የሆነ ፊልም መሥራት ሲፈለግ በስቱዲዮው ሙሉ መንደር ማግኘት ይቻላል፡፡ የአንድና የሁለት ሰዎች ቤት ብቻ ሳይሆን በርካታ ቤተሰቦች የሚኖሩባቸውን ቤቶች በማስመሰል የተሠሩት ቤቶች በጥንታዊ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች የተሞሉ ናቸው፡፡ ከትንሹ ማንኪያ አንስቶ ለአንድ ቤተሰብ የሚያስፈልጉ መገልገያዎች በአጠቃላይ ይገኛሉ፡፡ ጥንታዊ ቤተ መንግሥትን በማስመሰል የተሠራው ቤተ መንግሥትም የተንጣለለው ሰፊ ቦታ ላይ ነው፡፡ ለፊልም ግብዓት የሚሆኑ የነገሥታት አልባሳት፣ የጦር መሣሪያዎችና ሌሎችም ቁሳቁሶች እንደየአስፈላጊነታቸው ቀርበዋል፡፡

የቤጂንግ የፈጠራ ኢንዱስትሪ ቀዳሚ መዳረሻ በመባል የሚጠራው ስቱዲዮው ውስጥ ተከታታይ ድራማዎች፣ ዘጋቢ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ዝግጅቶችም ተቀርፀዋል፡፡ የጦርነት ምሽግ፣ ታንክና ሌሎችም መሣሪያዎችን በማስመሰል የተዘጋጀው የቀረፃ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ቁሳቁሶች፣ የዕውን እንጂ ለፊልም ተብለው መዘጋጀታቸውን በሚያጠራጥር መልኩ በጥራት የተዘጋጁ ናቸው፡፡

ከተጨናነቁ መንደሮች የናጠጡ ባለሀብቶች እስከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ማግኘትም ይቻላል፡፡ የተጨናነቁ መንደሮችን በሚወክለው የስቱዲዮው ክፍል አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎችን ሕይወት በሚያንፀባርቅ መልኩ የተሠራ ነው፡፡ ሊፈርሱ ያዘመሙ ቤቶችና በተገቢ ሁኔታ ያልተያዘ መንገድ ይገኛል፡፡ በተቃራኒው አላፊ አግዳሚን የሚማርኩ ድልድዮችና ሰው ሠራሽ ሐይቆችን መመልከት ይቻላል፡፡

በስቱዲዮ ውስጥ ከግለሰቦች እስከ ማኅበረሰብ ሕይወት የሚንፀባረቁባቸው ክፍሎች አሉ፡፡ ተመልካች ታክቶ መጎብኘት ካላቋረጠ በስቱዲዮው ዕይታ የሚስቡ ቦታዎች በርካታ ናቸው፡፡ ለእውነት በቀረበ ሁኔታ ዲዛይን የተደረጉት መንደሮች፣ መንገዶች፣ ቤተ መንግሥቶች (በጌት ኦፍ ሔቨንሊ ፒስ ኪነ ሕንፃ አምሳያ የተሠራውን ጨምሮ) ሌሎችም የቀረፃ ቦታዎች ለፊልም ሙያተኞች ምቹ ናቸው፡፡ ከአራት ዓመት በፊት 33  ካርቱን ፊልሞችና የተለያዩ ተከታታይ ድማራዎች ከ1,680 በላይ ኤፒሲዶች ተቀርፀዋል፡፡

ዓምና የቻይናና አሜሪካ ፊልም ሠሪዎች የሁለትዮሽ ውይይት አድርገው ነበር፡፡ የቻይና ፊልሞችን ዓለም አቀፍ ገበያ ለማስፋት መሰል ስቱዲዮዎች ስላላቸው ሚናም ተወያይተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የቻይና ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ለዕይታ ከሚበቁ ፊልሞች ብዙዎቹ የሚሠሩት ሁዋይሩን በመሰሉ ስቱዲዮዎች ነው፡፡ ሁዋይሩ ብቻውን ከ300 በላይ የፊልምና የቴሌቪዥን ቀረፃ ተቋሞች መገኛ ሲሆን፣ ከቤጂንግ ውጪ በሌሎች የቻይና ግዛቶችም ተመሳሳይ ስቱዲዮዎች ይገኛሉ፡፡

ግዙፎቹ የቻይና ፊልም ስቱዲዮዎች

 

ሁዋይሩ፣ ከሚንግ ሥርወ መንግሥት እስከ ዛሬይቱ ቻይና ያለውን ሒደት መመልከት የሚሹ የሚመርጡት ቦታ ነው፡፡ ስቱዲዮው የመንግሥት ሲሆን፣ የተለያዩ የቱሪዝም ድረ ገጾች ቻይና ውስጥ መጎብኘት አለባቸው ከሚሏቸው ሥፍራዎች አንዱም ነው፡፡ ስቱዲዮው የተገነባው ቻይናን ከዓለም የፊልም መዲናዎች አንዷ ለማድረግ ታልሞ እንደሆነ በጉብኝታችን ወቅት ተገልጾልናል፡፡ 

በሰሜናዊ ቤጂንግ ሁዋይሩ ግዛት የሚገኘው ሁዋይሩ ስቱዲዮ በይፋ ሥራ በጀመረበት ወቅት፣ መንግሥት በየጊዜው በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጾ ነበር፡፡ በፊልሙ ዘርፍ ከሁዋይሩ በተጨማሪ በኒንሻ ግዛት የሚገኘው ዘንቤፑ ዌስት ስቱዲዮም ተጠቃሽ ነው፡፡ በእስያ ውስጥ ግዙፍ ከሆኑ ስቱዲዮዎች አንዱ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2012 ‹‹ማን ኦፍ ታቺ›› የተሰኘውና እንደ ኪያኑ ሪቨስ ያሉ የሆሊውድ ከዋክብት የተወኑበት ፊልም የተቀረፀው ነው፡፡ 
የቻይና ፊልሞች ከቻይና ውጭ በሚፈለገው መጠን አይታዩም በሚል አስተያየት የሚሰነዝሩ የአገሪቱ የፊልም ባለሙያዎች፣ እንደ ሁዋይሩና ዌስት ያሉ ስቱዲዮዎች መገንባታቸው ለዘርፉ ዕድገት ቢያግዝም፣ መንግሥት የፊልሞች ይዘት ላይ ምርመራ ማድረጉ ለሥራቸው እንቅፋት መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡
በሰሜን ቻይና የምትገኘው ኒሻን ውስጥ የሚገኘው ዌስት የፊልም ስቱዲዮ፣ ሔላን ተራራ አካባቢ በጎብኚዎች ከሚዘወተሩ ቦታዎች አንዱ ነው፡፡ ለቻይና ፊልም የጀርባ አንጥንት ናቸው ከሚባሉ ስቱዲዮዎች አንዱ ሲሆን፣ እንደ ሁዋይሩ ስቱዲዮ የተንጣለለ ነው፡፡ በተለያየ የቻይና ዘመን የነበረ የቤት አሠራር፣ አለባበስና አኗኗር በስቱዲዮው ይንፀባረቃል፡፡
ስቱዲዮውን በጎበኘንበት ወቅት መቼቱ በጥንታዊት ቻይና ያደረገ ፊልም እየተቀረፀ ነበር፡፡ ተዋንያኑ በአንድ የቻይና ገጠራማ መንደር ውስጥ የሚኖር ቤተሰብን ወክለው ይጫወታሉ፡፡ ስቱዲዮው ውስጥ ፈረሶች፣ ግመሎችና ሌሎችም እንስሳት ስለሚኖሩ፣ ለፊልሙ በሚያስፈልጉበት ወቅት በቀላሉ ይገኛሉ፡፡ ስቱዲዮው ከፊልም ቀረፃ ጎን ለጎን ለቱሪስቶችም የጉብኝት አገልግሎት ይሰጣል፡፡

የቻይናን ባህላዊ አልባሳት ወይም ወታደራዊ ልብስ ለብሰው ፎቶ መነሳት ለሚፈልጉ በርካታ አማራጮች አሉ፡፡ የቻይናውያን አዲስ ዓመት አከባበርን የሚያሳይ ቴአትር የሚያቀርቡ ተዋንያን የስቱዲዮው አካል ናቸው፡፡ ዌስት ውስጥ ባህላዊ የወይን አጠማመቅ ሒደት የሚጎበኝበት ክፍል አለ፡፡ የአገሪቱን ባህላዊ ልብስ ለብሰው ሒደቱን የሚያሳዩ ሰዎች እያንዳንዱን ደረጃ ያብራራሉ፡፡ የጦር መሣሪያዎች በሚጎበኙበት ክፍል ጎራዴና ሌሎችም መሣሪያዎች በባህላዊ መንገድ ሲሠሩ ማየትም ይቻላል፡፡

ስቱዲዮው በቻይናና በሌሎች አገሮችም ተወዳጅነት ያተረፉ ፊልሞች የተቀረፁበት ነው፡፡ ‹‹ዘ ኸርድስ ማን››፣ ‹‹ዘ ሬድ ሶርገም››፣ ‹‹ግሪፍ ኦቨር ዘ የሎ ሪቨር›› እና ‹‹ኤ ቻይኒዝ ኦዲሴ›› ይጠቀሳሉ፡፡ ጎብኚዎች በጋሪ መጓጓዝ ቢፈልጉ ወይም በጥንታዊ የቻይና ቤቶች መኖር ምን እንደሚመስል ለመገንዘብ ቢፈልጉ ስቱዲዮው ፍላጎታቸውን ያሟላል፡፡ ‹‹ዘመንን አሻግሮ ወደ ጥንታዊት ቻይና የሚወስድ ቦታ›› በሚል ዌስት ስቱዲዮ በቱሪስቶች ተገልጿል፡፡

ከ100 በላይ ትልልቅና መጠነኛ ቋሚ ትዕይንቶች (ሲነሪዎች) ያሉት ስቱዲዮው፣ በታዋቂ የፊልም ተዋንያን የተለበሱ የትወና አልባሳት ማሳያ ክፍልም አለው፡፡ ተዋንያን የተገለገሉባቸው ቁሳቁሶችም የጉብኝቱ አካል ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1980ዎቹ ጀምሮ በስቱዲዮው ፊልም ፊልሞች የተቀረፁ ሲሆን፣ የሚወዷቸው ፊልሞች የተቀረፁባቸውን ቦታዎች ፈልገው ፎቶ የሚነሱ ብዙዎች ናቸው፡፡

በደራሲ ዣንግ ዥያንሊግ የተመሠረተው ዌስት ስቱዲዮ በአገሪቱ ከሚጠቀሱ ስቱዲዮዎች አንዱ ሲሆን፣ ሌሎችም የአገሪቱ የግል የፊልም ስቱዲዮዎች ለፊልም ኢንዱስትሪው አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ ስቱዲዮዎቹ አገርና ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ሲዘጋጁ ያስተናግዳሉ፡፡ ከፊልሙ ጎን ለጎን በአገሪቱ ባህልና ቱሪዝም ዘርፍም ጉልህ ድርሻ አላቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...