Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሞኝ ሲሰምጥ ብልጥ ይንሳፈፋል!

ሰላም! ሰላም! እንዴት ነው መረብና ኑሮ? የመረብ ዘመን አይመስላችሁም መደፋፈሩን ያናረው? እ? እውነቴን እኮ ነው። እንጃ በስንት ፐርሰንት መሆኑን ግን። ጥያቄዬ እኮ እንዲያው ለጨዋታ ለ‘ኦፒኒዬን’ ነው እንጂ፣ ወጋችንን የታዳጊ አገር  የኢኮኖሚስቶች ማኅበር ባናስመስለው ደስ ይለኛል። ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ዶላር በመረብ እያጠመደ ያስተነትናል ብላችሁ እሙኝ። ዳሩ መቼ ቀረልኝ? ጢን ጢን ብሎ ስልኬ አስነጠሰችላችሁ። አውጥቼ ሳይ ‹‹አፋልጉኝ›› ይላል። ‘ማን ማን ጠፍቶት ይሆን?’ አላልኩም። እንዴት እላለሁ? ወገኔ በየአቅጣጫው የጫረው የትስስርና የፍቅር ብርሃን ጠፍቶበት ዓይኑ በቁጭት ጭስ እያደር እያነሰ እያየሁ እንዴት ብዬ።

ወዲያው ወረድ ብዬ ሳነብ፣ ‹‹ቲማቲም፣ ስኳርና ውኃ ያለፉትን ዓመታት ወጣ ገባ ከፍ ዝቅ ሲጫወቱ ከርመው፣ አሁን ከነ አካቴው ከተዳሳሽነት ወደ ምናባዊነት ተሸጋግረዋል። እናም ከምናባዊነት ወደ ቦታቸው ተዳሳሽነት ለመለሰ ወሮታውን እንከፍላለን፤›› ይላል። ገርሞኝ ፈገግ አልኩ። ቢያንስ ከተዳሳሽነት ወደ ምናባዊነት ያልተሸጋገረ ጥርስ አለኛ። ምን ማለታችሁ ነው። ይህን ስለው የባሻዬ ልጅ ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ? ‹‹ጥርስህ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር አልያም በልተው በማይጠግቡ ነጋዴዎች እጅ አለመሆኑ በጀህ፤›› ነበር ያለኝ። ጎበዝ ምኔ በማን እጅ ነው የሚለውን አደራ እየተጠራጠራችሁ፡፡ እሺ?

እናላችሁ ሰሞኑን ከአንዲት ምስኪን እናት ጋር የቪትስ ዋጋ ሳነፃፅር ነበር የሰነበትኩት። እሳቸው የዶላር ነገር ግራ ገብቷቸዋል። ከዶላር በላይ ግን የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ አበሳጭቷቸዋል። ‹‹እነዚህ ሲያዩዋቸው ጨርቅ የለበሱ የሚመስሉ ቪትዞች ይሰነብታሉ ግን?›› ይሉኛል ዓይን ዓይኔን እያዩ። ‹‹አይ እማማ። በጥሩ ሁኔታ ካልተያዘ እንቁላልስ መች ይሰነብታል?›› እላለሁ ‘ትቼዋለሁ’ እንዳይሉኝ ሰግቼ። ‹‹እሱስ ልክ ነው…›› ብለው ሲቆዝሙ ‘ለማን ለምን’ መኪኖቹን እንደሚገዙ አወጣጣቸው ጀመር። ‹‹ይኼውልህ ትንሹ ልጄ ገና ኮሌጅ እንደገባ ‘ማሪዋና’ ነው የሚሉት? … ብቻ ጭሳጭስ ለምዶ ይህቺን አከለ። ተው ብል ማን ሰምቶኝ። ሽቅብ ያዩሃል የዘንድሮ ልጆች። እያደር ስሜቱ ሁሉ ቀዘቀዘ። ትምህርቱን ተወው። ያልወሰድኩበት ሐኪም ያልወሰድኩት ፀበል የለም። አሁን ምን እንደነካው ሳላውቅ ተለውጦ ሁለት ‘ቪትስ’ ግዢልኝና እያከራየሁ ልደግ አለኝ። ድንግሊቷ ፀሎቴን ሰማች። ይኼው ውጭ ያሉ ወንድሞቹን ሙሉልኝ ብዬ ካንተ ጋር እንከራተታለሁ…›› ሲሉኝ የምለው ጠፋኝ።

‹‹የወለደ …›› ብዬ ብቻ ዝም። እንዲህ ብዬ ሳቀረቅር፣ ‹‹ምነው ግን ልጄ ካልጠፋ ነገር የትውልዱ መጠመጃ ጭሳጭስ ሆነ?›› ብለው አፈጠጡብኝ። ያቅሜን ያህል ተጣጥሬ ሻል ባለ ዋጋ ያልተጫሩና ያልተኮረኮሙ ሁለት ቪትሶች አጋዝቻቸው ስንለያይ አንጀቴ ተንቦጫቦጨ። ሄጄ ለባሻዬ እንደ ወትሮው ውሎዬን ሳጫውታቸው፣ ‹‹በአገር የመጣ ነው አንበርብር…›› ብለው ይባስ ቅስሜን አያነክቱት መሰላችሁ? ‹‹ታደያ ምነው አገር አልሰማው? አገር አላወራው?›› ስላቸው፣ ‹‹ገመና እንዴት ይወራል አንበርብር? ያውም የልጅ? ምንም ቢሆን ሥጋ ሥጋ ነው። ስንቱ ነው በልጁ የተገኘ? ነፃነትና ልቅነት መለየት እስኪያቅተን ተቀላቅለውብን ስንቱ ነው የሚሸነግልበትና የሚሸልምበት ያጣ? ጥርሱን ነክሶ ልጁን በቁም የቀበረ? ስንቱ?›› እያሉ አላቆም አሉ። ይኼን ብሶት ማጠራቀም ትተን ሳይቃጠል በቅጠል የምንዘምትበት ጊዜ ቅርብ ይሆን? ወየው በሆነ!

እንዲሁ ስገረም፣ ነፍሴ ስትገነዝ፣ ስቆጣ፣ ስለዝብ፣ ሳሻሽጥ፣ ሳለዋውጥ፣ ሳከራይ እየዋልኩ ፀጉሬ ማደጉን አላስተዋልኩም። ማንጠግቦሽ፣ ‹‹ኧረ ሽፍታ መሰልክ ተቆረጠው፤›› ስትለኝ እንደማያዋጣኝ ገባኝ። ይገርማችኋል ማንጠግቦሽ ፀጉሬና ፂሜ ከፍ ሲልና በጣም ሲያድግ ተመሳሳይ አነጋገር አትጠቀምም። እንደ ነገሩ መዘዝ መዘዝ ሲል፣ ‹‹ምነው አንበርብር ይኼን ፂምህን እኔ እያስታወስኩህ ባትላጨው?›› ነው የምትለው፡፡ በጣም ሲያስቀይማት ግን ‘ሽፍታ’ የሚለውን ቃል አውቃ ትጠቀማለች። እኔ ደግሞ በሽፍታና በኪራይ ሰብሳቢነት እንዳልታማ በእጅጉ የማደርገውን ጥንቃቄ አሳምራ ታውቃለች። መቼም በደካማ ጎናችሁ አንዴ አለመገኘት ነው። ነገሩን ካነሳሁት አይቀር ስስ ብልታችን በዝቶ እሱን እየነካኩ እንዳሻቸው የሚቀልዱብን መብዛታቸውንም ልጠቁም። እኛም ታዲያ፣ ‹‹አንዱን በቴስታታ አንዱንም በካልቾ ነበር ልማዳችን፣ ሚስት አገባንና ልጆች ወለድንና ፈሰሰ ሐሞታችን›› ብለን እጅ ሰጠን። ታዲያ እንዳልኳችሁ ማንጠግቦሽ ‘ሽፍታ’ የሚባለውን የማልወደው ቃል ስለተጠቀመች እጅ ሰጥቼ የዘወትር ፀጉር ቆራጭ ደንበኛዬ ጋ ስሄድ ‹‹መብራት የለም›› ብሎ ጥፍሩን ሲቆርጥ ደረስኩ።

ዛሬማ በመቀስም ቢሆን አስመድምጄው አድራለሁ እንጂ እንዲህ ሆኜ አልመለስም እያልኩ በጄኔሬተር ኃይል ነፍስ ወደ ዘራ ‘ሞል’ ዘው። ምን እንደነካኝ አላውቅም። ፀጉር ቤት ፈላልጌ አገኘሁና  ‹‹ፓንክ››  አልኩት ቆራጩን። በሦስት ቁጥር መድምዶኝ ሲያበቃ ጨርሻለሁ ብሎ ሰላሳ ዓይነት ቅባት ቀባብቶ ውረድ አለኝ። የደንበኛዬ እጅ ይግደለኝ እያልኩ ማጠሩን ብቻ ዓይቼ ሒሳብ ስል ‹‹ሁለት መቶ ብር›› ተባልኩኝ፡፡ ‹‹የባህታዊ ፀጉርም ይኼን ያህል አይከፈልበት?›› ከማለቴ ‘ቶንዶሱ ሪል የጃፓን ስሪት፣ ቅባቶቹን ቀጥታ ከአሜሪካ የምናስመጣቸው፣ ወንበሩ የጣሊያን’ ተባልኩ። እኔም የአንድ ፈረንጅ አገር ፀጉር እስካበቅል ምን አደርጋለሁ ብዬ ከፍዬ ወጥቼ ሄድኩ እላችኋለሁ። ከአካባቢያችን እያሳደደ የሚጫወትብን መብራት እንደሆነ መቼ አጣነው አትሉም!

በቀደም አንድ ባለተሳቢ ሳሻሽጥላችሁ ሻጩ ደንበኛዬ ትኩር ብሎ ቀለበቴን እየተመለከተ፣ ‹‹ትዳር እንዴት ነው?›› ብሎ ጠየቀኝ። ‹‹አሸወይና ነው ወርቅ ሚስት አለችኝ፤›› አልኩት። አንዳንዴ ከጥያቄው በፊት የተዘጋጁ መልሶች ችግር ይፈጥራሉ እኮ። ለካስ ዕድሜው ከእኔ ከጎልማሳው የማያንሰው ደንበኛዬ አራተኛ ጣት ባዶ ኖሯል። ምን ብዬ ጨዋታዬን ልቀጥል። ‹‹ይገርምሃል ከጓደኞቼ ሁሉ ሳላገባ የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤›› አለኝ። ‘ግድ የለም ሁሉም በጊዜው ይሆናል’ ብዬ ሌላ የተዘጋጀ መልስ ከመመለስ ለጥቂት ተረፍኩ። አንዳንዱ  ባለማግባቱ የሚበሳጨውን ያህል ሌላ በምንም ሲበሳጭ አላየሁማ። ‹‹ምነው አልክ?›› አልኩት ብዙም እንዳልደነቀኝ ነገር ሆኜ።

‹‹ዕድሜ ለጓደኞቼ። መማሪያ ሆኑኛ። አንድ ሁለቱ ይሻላሉ እንጂ ሰባቱ የሚኖሩት ኑሮ ሲዖል በለው። ነጋ ጠባ ጭቅጭቅ ነው። ዘመኑ እንደምታየው ስለእኩልነት የሰበከውን ያህል ስለአንተ ትብስ አንቺ አይሰብክም። እና እኔ ይኼን እያየሁ ምን ተማምኜ ላግባ? ያውስ በመሸበት ማደር በቀለለበት ዘመን…›› ሲለኝ ከልቤ አዘንኩ። ኋላ ሥራዬን ጨራርሼ ኮሚሽኔን ተቀብዬ ከባሻዬ ጋር ስንጫወት ይኼው ደንበኛዬ ያለኝን ብነግራቸው፣ ባሻዬ አንገታቸውን ወዝወዝ አድርገው ‘ዋ’ ብለው ቀሩ። ‹‹ምነው?›› ስላቸው፣ ‹‹ያለሙያቸውና ፍጥረታቸው ገብተው የተደናገሩ ከበሮ መቺዎችን እያየ ስንቱ ከበሮውን ትራስ አደረገው? ስንቱ ዛሬ ታይተው በነጋታው በፈረሱ ትዳሮች የእጮኝነት ተስፋው ፈረሰ? ለአገር ለወገኑ ስንት ዓላማና ዕቅድ ያለው ከእሱ በፊት የነበሩትን እያየ ስንቱ ሐሞቱ ፈሰሰ? ስንቱ ሰላማዊ ትግል ሸሸ? ስንቱ ፖለቲካን እንደ ዓይነ ምድር ተፀየፈ?›› ሲሉኝ  አዝማቹን እየደጋገምኩ አጀብኳቸው። ኧረ ስንቱ ስንቱ?!

በሉ እንሰነባበት። እንቅልፍም እንደ ዘመኑ ሰው ሰዓቱን ጠብቆ አልገኝ እያለ ሲያስቸግረኝ ሁሌ እንደማደርገው የባሻዬ ልጅ ዘንድ እደውላለሁ። ‹‹ለቀጠሮ የምናጠፋው ካርድ ብቻ ቢደመር አንድ የቢራ ፋብሪካ ያስከፍተን ነበር እኮ?›› እለዋለሁ ስንገናኝ። በዘመነ ትራንፎርሜሽን መንደሮች ሁሉ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክነት በሚቀየሩበት በዚህ ጊዜ እንዴት የቢራ ፋብሪካ ትመኛለህ እንዳትሉኝ ብቻ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቢራ በቧንቧ በነፃ ካልታደለ አገሩ በእንቅልፍ ዕጦት የዝንጀሮ መጫወቻ እንደሚሆን የሚታየኝ እኔ ብቻ ነኝ ማለት ነው። እውነቴን እኮ ነው። ‹‹የአሥር ሳንቲም ቆሎ ኮርሸም አደርግና፣ አንድ ጣሳ ውኃ ጭልጥ አደርግና ተመሥገን እላለሁ ኑሮ ይባልና›› ብሎ የገጠመው ሰውዬ ዛሬ አግኝታችሁት ብትጠይቁት፣ እንኳን ጣሳ የሚሞላ እፍኝ ውኃ ጥበቃ አንድ ጠርሙስ ቢራ ብሎ ቢያሻሽለው እንደሚመኝ ያስረዳችሁ ነበር። ተፈጥሮን በቁጥጥር ሥር ማዋል ብሎ ተዓምር ታዲያ ከዚህ በላይ ምን አለ? ተፈጥሮ የለገሰንን ውኃ የገብስ ጭማቂ ሲያስንቀው ማለቴ ነው።

እና ከባሻዬ ልጅ ጋር የባጥ የቆጡን እያወራን በመሀል አንድ ተረት ተረተ። ከፍ ዝቅ ሄድ መለስ የሚለውን ነገረ ሥራችንን አስታኮ፣ ‹‹የሾተላይን ልጅ የገበታ ውኃ ይወስደዋል›› ብሎ ተከዘ። ተረቱ ተመቸኝ። የተመቸኝ ከዚህ ሁሉ የልማትና የትራንስፎርሜሽን ልፍለፋ በኋላ ለገበታ ውኃ መቸገራችን ብቻ ሳይሆን፣ የገበታ ውኃ  የኢንዶኔዥያ ጎርፍ አንገላቶ የማይገለውን ነፍስ እዚህ ፀጥ እያደረገው ማየቴ ነው። አሃ እኛና እነሱ? በቀላል አማርኛ ነገር ሳላንዛዛ ‘እኛና እናንተ’ የሚለው ውስጤ ገባ። ማመሳሰል ለምትወዱ ደግሞ ‘በግል ወይስ በጋራ?’ በሚል ዜማ መጫወት መብታችሁ ነው እያልኩ ስብሰለሰል፣ ከውስጤ የሆነ ድምፅ ተሰማኝ፡፡ ቅዥት ሳይሆን ጭንቀት የያዘው የሚመስል ግን የሚሰማ ድምፅ፡፡ ምንድነው አትሉኝም? ነገራችን ሁሉ ‘ቀልቀሎ ስልቻ፣ ስልቻ ቀልቀሎ’ ስለሆነ የግላችንና የጋራችን አልለይ አለ እኮ? ማን ነበር ሞኝ ሲሰምጥ ብልጥ ይንሳፈፋል ያለው? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት