Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአሥር ቢሊዮኑ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር ሲመነዘር

አሥር ቢሊዮኑ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር ሲመነዘር

ቀን:

ዓምና መስከረም ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ሲከፈት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ካደረጉት ንግግር አሥር የቢሊዮኑ ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር ቀልብ የሳበና ለወጣቶችም የሥራ ዕድል በዚያው ዓመት ይፈጠርበታል ተብሎ የታሰበ ነበር፡፡

ተወካዮች ምክር ቤት እንዳጸደቀውም ከተማ ከገጠር ሳይል በየአስተዳደሩ ባሉ መዋቅሮች ሥራ አጥ የሆኑና ከዚህ ቀደም በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ብድር ያልወሰዱ ሦሰት ሚሊዮን ያህል ወጣቶች ብድሩን አግኝተው ወደ ሥራ ለመግባም ተመዝግበዋል፡፡

ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 34 ባሉት ክልል ውስጥ ከሆኑት ሥራ አጦች አሥረኛን ያቋረጡ፣ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ሙያዎች የሠለጠኑ ወጣቶች ይገኙበታል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የአሥር ቢሊዮኑን ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር መጽደቅ ተከትሎ ከዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን በአዲስ አበባ በየወረዳው ከተመዘገቡት ወጣቶች አንዱ እንደነገረን፣ ገንዘቡን በአጭር ጊዜ አግኝቶ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተስፋ ሰንቆ ነበር፡፡ ብሩ የተያዘውም ለ2009 በጀት ዓመት በመሆኑ እንዲህ 2010 ዓ.ም. ጥቅምት እስኪገባም ብድሩን ሳያገኝና ሥራ ሳይጀምር እቆያለሁ ብሎ አልገመተም ነበር፡፡ 

እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ሆኖበታል፡፡ ወደ ሥራው ለመግባት ከአምስት የኢንተርፕራይዝ አባላቱ ጋር መንቀሳቀስ ከጀመረና ወረዳቸው በተደራጁበት የምግብ ዝግጅት መስክ የሚፈልጉትን ግብዓት ገዝቶ እስኪያስረክባቸው የነበረው ቅደመ ዝግጅት  ከአምስት ወራት በላይ ወስዷል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ማንኛውም ከአሥር ቢሊዮኑ ብር ተጠቃሚ ለመሆን የሚመጣ ሁሉ ማሟላት የሚገባውን አሥር መሥፈርት ለማሟላት ላይ ታች ማለት ነበረባቸው፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም ከነበረውና ዋስ ለማቅረብ አቅቶን ተስፋ በመቁረጥ ከተውነው  አሠራር የአሥር ቢሊዮኑ ብር ተዘዋዋሪ ብድር የተሻለ ነው፡፡ የእርስ በርስ ዋስትና [አምስት የኢንተርፕራይዝ አባላት እርስ በርሳቸው የሚገቡት] በመሆኑ በዚህ በኩል ያለው ችግር ተቃሏል›› የሚለው ወጣት፣ የነዋሪነት መታወቂያ፣ ከዚህ ቀደም ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ያለመበደራቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ፣ የጋብቻ ሁኔታ ሠርተፍኬት፣ ቅድሚያ ክፍያ ማስቀመጥ፣ የትምህርት ማስረጃ ማሟላትና ከወረዳው ጥቃቅንና አነስተኛ የድጋፍ ደብዳቤ ማምጣት፣ ንግድ ፈቃድ ማውጣት የሚሉትን ተጨምሮ አሥሩን መሥፈርት ማሟላት ጊዜ የወሰደ መሆኑን ይገልጻል፡፡

በየተቋማቱ ሄዶ በአጭር ጊዜ ውስጥ የምስክር ወረቀት ማግኘትም ሆነ ደብዳቤ ማጻፍ ቀላል አልነበረም፡፡ ወጣቱ እንደሚለው፣ እሱና ጓደኞቹ ያለመታከት ከአምስት ወራት በላይ በመመላለስና ከየኃላፊዎች ጋር በመሟገት ለሥራው ከሚያፈልጋቸውና ከጠየቁት 300 ሺሕ ብር ባሳለፍነው ሳምንት የ150 ሺሕ ብር ግብዓት ተገዝቶ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ብዙ የሚያውቃቸውና ከእነሱ እኩል ብድር መጠየቅ የጀመሩ ወጣቶች ግን መሀል ላይ ሒደቱን ማቋረጣቸውን ይናገራል፡፡

አሥሩን መሥፈርት ለማሟላት በየተቋማቱ ያለው አሠራር ቀልጣፋ አለመሆን፣ አንዱ የሚያውቀውን አንዱ አለማወቁ፣ ብድሩን ከማግኘት አስቀድሞ የኢንተርፕራይዙ አባላት በሚጠይቁት ብድር ልክ አሥር በመቶ ማግኘት አቅቷቸውና ከወረዳ ክፍለ ከተማ ያሉ ምልልሶች ተስፋ አስቆርጧቸው ሒደቱን ያቋረጡ መኖራቸው ከታዘባቸው ችግሮች መሃል መሆኑን ነግሮናል፡፡

የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ እንደሚሉትም፣ በገንዘቡ ለመጠቀም በገጠርም በከተማም ሦስት ሚሊዮን ሥራ አጥ ወጣቶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 1.02 ሚሊዮን ያህሉ በሁሉም ክልሎች ከሚገኙ ከተሞች ናቸው፡፡ እነዚህ ተመዝግበዋል ማለት ግን ሁሉም ወደሥራ ገብተዋል ወይም ብድር አግኝተዋል ማለት አይደለም፡፡

ከአሥር ቢሊዮኑ ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር በከተማም በገጠርም በአጠቃላይ 4.716 ቢሊዮን ብር ወደታች ወርዷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ለከተማ ሥራ አጥ ወጣቶች የወረደው ደግሞ 1 ቢሊዮን 379 ሺሕ 342 ብር ከ63 ሳንቲም ነው፡፡

ከወረደው ምን ያህሉ ለወጣቶች ደርሶ ጥቅም ላይ ውሏል? የሚለውን ጥያቄ አስመልክቶ አቶ ዘነበ እንደገለጹት፣ ገንዘቡ በተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀ በኋላ ወደ ተግባር ለመለወጥ ጊዜ ወስዷል፡፡ ሥራ አጥ ወጣቱን መመዝገብ፣ መለየትና ሥልጠና መስጠት፣ ሥልጠና ወስደውም ኢንተርፕራይዝ መመሥረት በራሱ ጊዜ ወስዷል፡፡ ወደ ተጨባጭ ተግባሩ ለመግባት በነበረው ሒደት መዘግየት ቢኖርም ገንዘቡ ከተለቀቀ በኋላ ግን ክልሎች ወጣቱን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ሆኖም የወጣቶቹ ዝግጁነትና የታየው የክልሎች የማስፈጸም አቅም ውስንነት ሥራው በፍጥነት እንዳይከናወን አድርጓል፡፡

ብሩን በመልቀቅ በኩል ችግር እንደሌለ ያስታወሱት አቶ ዘነበ፣ ከተለቀቀው 4.716 ቢሊዮን ብር ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው ሲታይ ግን መዘግየት እንዳለ ተናግረዋል፡፡

በገጠርም በከተማም ከተመዘገቡት ሦስት ሚሊዮን ወጣቶች 1.8 ሚሊዮን ዜጎች ከወረደው 4.716 ቢሊዮን ብር ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ዜጎች 800 ሺሕ ያህሉ ከአሥር ቢሊዮኑ ብር ተዘዋዋሪ ብድር ያገኙ ናቸው፡፡ አንድ ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ ዕድሜ ሳይገደብ በመደበኛ አካሄድ መጥተው የተጠቀሙ ናቸው፡፡

አጠቃላይ በከተማና በገጠር ከወረደው 4.716 ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ የዋለው ወይም የተሠራጨው 2 ቢሊዮን 181 ሚሊዮን 679 ሺሕ 777 ብር ነው፡፡ ይህም የወረደው ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ያሳያል፡፡

አሥር ቢሊዮኑ ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር ለ2009 በጀት ዓመት የተያዘ ቢሆንም፣ ወደ ሥራ ሲገባ ከወሰደው ጊዜ አንፃርና ከተፈጠረው የአሠራር ክፍተት አኳያ ገንዘቡን ሙሉ ለሙሉ በበጀት ዓመቱ ለታለመለት ተግባር ማዋል አልተቻለም፡፡ ይህም አንድ ተግዳሮት መሆኑን አቶ ዘነበ ይናገራሉ፡፡

የመመዝገብ፣ የማደራጀት የማሠልጠኑን ሥራ ጨምሮ፣ ወጣቱ ለተበደረው ስምንት ከመቶ ወለድ የሚከፍልበት ብር ቢሆንም መንግሥት እንደ ዕርዳታ ወይም ችሮታ የሰጠው አድርጎ የቆጠረበትን የተሳሳተ አመለካከት መለወጡም ጊዜ ወስዷል፡፡

በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም እንደ ዋና ችግር ይነሳ የነበረው ከባለሀብት ብር ተበድሮ ወለድ መክፈልም አሁንም አልተቀረፈም፡፡ ቅድሚያ መቆጠብ ያለባቸውን አሥር በመቶ ከባለሀብት ወስደው ይቆጥቡና የተወሰነ ወለድ ለባለሀብቱ የመስጠት አዝማሚያ ታይቶም ነበር፡፡ ባለሀብቱ ምንም የሌለውን መረዳት አሊያም አበድሮ ሠርተው ሲያገኙ ያበደረውን እንዲከፍሉት ማለትም ዘመድና ቤተሰቦች እንደሚያደርጉት ማድረግ ሲገባው፣ ወጣቱን ውል አስገብቶ የሚያበድርበት ዝንባሌ ብዙም ባይሆን መታየቱ ሌላው ችግር ነበር፡፡ ከወጣቶች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ለመወያየትና ችግሩን  ለማጥራት ጊዜ የወሰደ ሲሆን፣ ገንዘቡም ቶሎ እንዳይለቀቅ ሌላው ምክንያት ነበር፡፡

ተቀናጅቶ ያለመሥራት ከተስተዋሉ ችግሮች ይጠቀሳል፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ላይ 123 ሚሊዮን ብር ወርዶ 21 ሚሊዮን 100 ሺሕ ብቻ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በከተማዋ 107 ኢንተርፕራይዞች ቢመሠረቱም፣ ሁሉም ኢንተርፕራይዞች ብድሩን አግኝተዋል ማለት አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ የወረደውን ገንዘብ አሟጦ መጠቀሙ ላይ ክፍተት መስተዋሉን አስመልክቶ በተደረገ ግምገማም በከተማዋ ተቀናጀቶ ያለመሥራት ችግር ብሩን በአግባቡ ጥቅም ላይ ከማዋል ማገዱ ተገልጿል፡፡

አፋር 206 ሚሊዮን እንዲሁም ጋምቤላ 20 ሚሊዮን ወርዶላቸው ሙሉ ለሙሉ ሳይጠቀሙት ቀርተዋል፡፡ ለዚህም የመዋቅር ለውጥ እንደ ችግር ይነሳል፡፡ ለምሳሌ በጋምቤላ በተለያዩ ጊዜያት የመዋቅር ለውጥ በመደረጉ ከፌዴራል የወረደው 20 ሚሊዮን ብር ጥቅም ላይ አንይውል አድርጓል፡፡ አፋርም መዋቅሩን አሟልቶ ወደ ሥራ ቶሎ ባለመግባቱ የተለቀቀለትን ብር አልነካውም፡፡

ሶማሌና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጥሩ አካሄድ ቢኖራቸውም የተለቀቀው ገንዘብና የተጠቀሙት ሲታይ ብዙ ሥራ እንደሚጠብቃቸው ያሳያል፡፡

ከ2008 ዓ.ም. ማብቂያ ጀምሮ 2009 ዓ.ም. ውስጥም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ላይ ያለመረጋጋት ነበር፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ብድሩን ለወጣቶች ለማድረስ ችግር ፈጥሮ ነበር? የሚለው ጥያቄም የሚነሳ ነው፡፡

አቶ ዘነበ እንደሚሉት፣ በኦሮሚያ የነበረውን ችግር በጥልቅ ተሃድሶ ገምግመው የአመራር ለውጥ በማድረግ የሄዱት ርቀት ጥሩ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የገጠማቸው በኪራይ ሰብሳቢነት አንደኛ ዘርፍ ማለትም በቀድሞ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የሚባለው የፈጠረው እክል ነው፡፡ ኦሮሚያ ላይ የገጠመውና ወጣቱ ሆ ብሎ እንዲነሳ መንስኤ የሆነውም በአካባቢው የተፈጥሮ ሀብትና አቅሙ እያለ ይህን ሀብት የተወሰነ  ባለሀብት ብቻ ሲጠቀምበት ማየቱና ሥራ ዕድል ስላልተፈጠረለት ነው፡፡

አመራሩ የወሰደው ዕርምጃም፣ የተፈጥሮ ሀብት ለልማት ሲሰጥ ለተወሰነ ጊዜ ሆኖ የመነሻ ጥሪት ማፍሪያ በመሆኑና ጥቃቅንና አነስተኛ ስትራቴጂ ላይ የተቀመጠውን የጣሰ በመሆኑ የፈጠረውን ኢፍትሐዊ አሠራር ለማስተካከል ነው፡፡ አንድ ባለሀብት የተፈጥሮ ሀብት ላይ ብቻ ሳይሆን ሼዶች ላይም ቢሆን በቦታው መቆየት የሚችለው አምስት ዓመት ብቻ  ስለሆነም ክልሉ በጥቂት ባለሀብት የተያዘውን የተፈጥሮ ሀብት አብዛኛው ኅብረተሰብ እንዲጠቀምበት አድርጎ ሥራውን መሥራት ችሏል፡፡

የአማራ ክልል ሲታይ፣ ከዚህ በፊት ከየዩኒቨርሲቲው ተመርቆ የሚወጣውን ወጣት ወደ ሥራ ማስገባቱ ላይ ትልቅ ክፍተት ነበር፡፡ አሁን በአንድ ጊዜ ከ34 ሺሕ በላይ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁትን በየሙያቸው አደራጅቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርጓል፡፡ ቅጥር ላይም ብዙ ዓመት የሥራ ልምድ የሚጠይቀውን ዝቅ አድርገው ወጣቱ ሥራ እንዲይዝ አድርገዋል፡፡

‹‹ከዚህ በፊት የነበረው ሲታይ ወጣቱን ትኩረት አድርገን ያልሠራንበት፣ ለወጣቱ የገባነውን ቃል ያልፈጸምንበት ነበር፡፡ በንግድ፣ በአገልግሎት፣ በኮንስትራክሽን፣ በከተማ ግብርና እንደሚሠራ ተናግረን ወደ ሥራው አላስገባነውም ነበር፡፡ ውስጡ ሌላ ችግር ቢኖረውም ዓይቶ ዓይቶ ቁጣውን ገለጸ›› የሚሉት አቶ ዘነበ፣ አሁን ሁለቱም ክልሎች ችግሮችን በመፍታት የሄዱት ርቀት መልካም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ደቡብም በተወሰኑ አካላት የተያዘውን የተፈጥሮ ሀብት ሕጋዊ መስመርና አሠራር ተከትሎ ለወጣቱ የሚተላለፍበት መንገድ ላይ እየሠራ ነው፡፡

በ2009 በጀት ዓመት ለሥራ አጥ ወጣቶች ይውላል ከተባለው አሥር ቢሊዮኑ ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር ግማሽ ያህሉ እንኳን ጥቅም ላይ አልዋለም፡፡ ቀሪው ገንዘብ ክልሎችና ከተሞች የተሰጣቸውን ብር ሲጨረሱ የሚለቀቅ ቢሆንም፣ ክልሎችና ከተሞች ከተለቀቀላቸው ገንዘብ አንፃር ለወጣቱ ያሠራጩት ጥቂቱን ነው፡፡

ኦሮሚያ ለመጨረሱ ምልክት እያሳየ ሲሆን ሌሎቹ ክልሎች ግን ብዙ ርቀት ይቀራቸዋል፡፡ በየክልሎችም ወጣቶች ከገንዘብ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ከዚህ ቀደም በነበሩ መድረኮች ተናግረዋል፡፡

ኤጀንሲው በ2009 በጀት ዓመት ለ1.8 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 72 ከመቶ ያህሉ ወጣቶች፣ ከ60 እስከ 70 በመቶው ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ በመላ አገሪቱም ከ40 ሺሕ በላይ ኢንተርፕራይዞች ወደ ሥራ መግባታቸውንም የኤጀንሲው መረጃ  ያሳያል፡፡

በ2009 ዓ.ም. ጥቅም ላይ ይውላል ተብሎ ከነበረው አሥር ቢሊዮን ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር በከተማና በገጠር የተሰራጨውና ጥቅም ላይ የዋለው

በከተማና በገጠር

ተጠቃሚ

ክልል

የተለቀቀ በጀት (በሚሊዮን ብር)

የተሰራጨ (በሚሊዮን ብር)

የተቋቋሙ ኢንተርፕራይዞች

ኦሮሚያ

1,376,331.04

1,376,331,044

15,937

ደቡብ

753,101,225

79,409,077

20,288

አማራ

1,339,500

582,765,488

2,907

ትግራይ

212,000

82,240,702

270

አዲስ አበባ

123,000

21,100,00

107

ድሬዳዋ

27,500

21,985,887

155

ሐረር

10,600

6,663,697

48

ቤንሻንጉል ጉሙዝ

44,200.00

32,283,882

381

ጋምቤላ

20,000.00

 

 

ኢትዮ ሶማሌ

604,000

 

 

አፋር

206,000

 

 

ድምር

4,716,232

2,181,679,777

40,093

 

ምንጭ፡- የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...