Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቤቶች ኮርፖሬሽን ሠራተኞች የምደባና ደመወዝ አከፋፈል ሁኔታ አሳስቦናል አሉ

የቤቶች ኮርፖሬሽን ሠራተኞች የምደባና ደመወዝ አከፋፈል ሁኔታ አሳስቦናል አሉ

ቀን:

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሠራተኞች ተቋሙ ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲነት ወደ ኮርፖሬሽን በመቀየሩን ምክንያት፣ ከከፍተኛ ኃላፊዎች ውጪ ላሉ ሠራተኞች ምደባ አለመካሄዱና ተሠርቷል በተባለው አዲስ መዋቅር መሠረት የደመወዝ ክፍያ አለመፈጸሙ እንዳሳሰባቸው ገለጹ፡፡

የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በአዋጅ ቁጥር 1022/2009 ፈርሶ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 398/2009 ወደ ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሲቀየር፣ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ መብትና ግዴታዎች በማፍረሻ አዋጁ መሠረት ለኮርፖሬሽኑ የተላለፈ ቢሆንም፣ በሥር ሠራተኞች ላይ ተፈጻሚ እንዳልሆነ ሠራተኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሠራተኞቹ ተቋሙ በአጠቃላይ ከ1,500 በላይ ሠራተኞች እንዳሉት ጠቁመው፣ ወደ ኮርፖሬሽን ተቀይሮ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/1984 መሠረት እንዲተዳደር ሲወሰን፣ አዲስ መዋቅር መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ እያንዳንዱ ሠራተኛ ሦስት ሦስት አማራጮች ተሰጥተውት ቅጽ እንዲሞላ የተደረገ ቢሆንም፣ የሥራ ድልድል የተደረገው ግን ከዋና ሥራ አስፈጻሚ እስከ ቡድን መሪ በሚገኙ 100 ለማይሞሉ ኃላፊዎች ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከሥራ አስፈጻሚው እስከ ቡድን መሪ ያሉ ኃላፊዎች ተቋሙ ወደ ኮርፖሬሽን መቀየሩና ኤጀንሲው ተቋቁሞበት የነበረው አዋጅ ቁጥር 555/2000 መፍረሱ ከተረጋገጠበት ሰኔ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በአዲሱ በጀት ዓመት ሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም. አንስቶ በአዲሱ መዋቅርና የሥራ መደብ ደመወዝ እንደሚከፈላቸው አስረድተዋል፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች በተለይ የተቋሙን ዋና ዋና ሥራዎች በኤክስፐርትነት እየሠሩ የሚገኙት በኮርፖሬሽኑ ቢሆንም፣ ክፍያ የሚፈጸምላቸው ግን በቀድሞው ኤጀንሲው ሰነድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሕግ የተቋቋመ ድርጅት በሕግ መፍረሱ እየታወቀና ማንኛውም አሠራር፣ ግዴታና መብት በአዲሱ ስያሜ እየተፈጸመ የሠራተኞቹ ምደባና ደመወዝ ላይ ልዩነት ለምን እንደተፈጠረ ግራ መጋባታቸውን ሠራተኞቹ ተናግረዋል፡፡

የበላይ ኃላፊዎችን ሲጠይቁ በተደጋጋሚ የሚሰጣቸው ምላሽ ‹‹ጥናቱም ሆነ ምደባው ተጠናቋል፡፡ በሁለትና በሦስት ሳምንታት ውስጥ ይፋ ይሆናል›› እየተባሉ አራት ወራት ያስቆጠሩ መሆናቸውንና ተገቢ ምላሽ እየተሰጣቸው እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ አዲሱ መዋቅር ፀድቆ ተግባር ላይ የዋለው ከአዲሱ በጀት ዓመት ጀምሮ በመሆኑ፣ በሚመደቡበት የሥራ ድርሻ ላይ ሲቀመጡ ክፍያ ሊፈጸምላቸው የሚገባው ከበጀት ዓመቱ መጀመርያ አንስቶ መሆኑን የጠቆሙት ሠራተኞች ይህ የማይሆን ከሆነ መብታቸውን በሕግ ጭምር ለማስከበር የሚንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ድርጅቱ ወደ ልማት ገብቶ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድርና አትራፊ ሆኖ እንዲቀጥል የወሰደው ዕርምጃ ተገቢ ቢሆንም፣ በአስፈጻሚነት የተመደቡ ኃላፊዎች ግን ሒደቱን አዝጋሚ እያደረጉት እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ የሚመለከተው የመንግሥት አካል በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መብታቸውን እንዲያስከብርላቸውና ወደ ታለመለት የሥራ ድርሻ በመግባት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ሠራተኞቹ የገለጹትና የሚያነሱት ሥጋትና ጥያቄ ትክክል መሆኑን በማረጋገጥ ምላሽ የሰጡት፣ በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ሰርቪስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይለ ብርሃን ዜና ናቸው፡፡ አቶ ኃይለ ብርሃን እንደሚሉት፣ ተቋሙ ከኤጀንሲነት ወደ ኮርፖሬሽን ከተቀየረ በኋላ አዲስ መዋቅር ተሠርቷል፡፡ ‹‹መዋቅሩ እንደተጠናቀቀ ኃላፊዎች መመደብ ስለነበረባቸው ሠራተኞቹ እንደገለጹት ምደባ ተደርጓል፡፡ ሠራተኞቹም የኮርፖሬሽኑ ባልደረባ ሆነዋል፡፡ ነገር ግን የተቋሙ ሠራተኞች ከ1,500 በላይ በመሆናቸውና የእያንዳንዱ ሠራተኛ የሥራ ልምድ፣ የትምህርት ዝግጅትና የብቃት ሁኔታ ተጠንቶና ተመርምሮ መመደብ ስላለባቸው ጊዜ ሊወስድ ችሏል፡፡ ያም ቢሆን ኮሚቴ ተቋቁሞ በማጥናት ለማኔጅመንት አስረክቧል፡፡ ይህ በጣም አድካሚና ጊዜ የሚወስድ ሥራ ነው፡፡ ይህ ጥናት ተጠንቶና ምደባ ተካሂዶ ሠራተኛው በአዲሱ ምደባ መሠረት ደመወዝ እስከሚከፈለው ድረስ፣ እየተከፈለው ያለው በኤጀንሲው ያገኘው የነበረውን ደመወዝ ነው፤›› ሲሉ አቶ ኃይለ ብርሃን ተናግረዋል፡፡ አሁን የሚጠበቀው የማኔጅመንቱ ውሳኔ ብቻ መሆኑን የገለጹት አቶ ኃይለ ብርሃን፣ በዚህ ቀን ነው ማለት ባይችሉም በቅርብ ቀን ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የክፍያ አፈጻጸምን በሚመለከት ለበላይ ኃላፊዎች የተፈጸመው ከተመደቡበት ቀን ጀምሮ መሆኑን አስታውሰው፣ የቀሪ ሠራተኞች የክፍያ ጊዜ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው የሚለው ገና እንዳልተወሰነ አስረድተዋል፡፡ አዲሱ መዋቅር የተጠናው የመጀመርያ ዲግሪን መሠረት አድርጎ በመሆኑ በዲፕሎማ፣ በሰርተፊኬትና በሌሎች ማስረጃዎች ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ሠራተኞች ዕጣ ፈንታን በሚመለከት የተጠየቁት አቶ ኃይለ ብርሃን፣ እነሱን በሚመለከት ‹‹ምን ይደረግ?›› የሚለው አንዱ ጊዜ የፈጀ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው፣ ገና ምንም የተወሰነ ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ምደባው ግን በአጭር ጊዜ ተፈጻሚ እንደሚሆን አረጋግጠዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...