Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበብሮድካስት ሚዲያዎች መካከል የአጥቂና የተከላካይነት አዝማሚያ መኖሩ ተገለጸ

በብሮድካስት ሚዲያዎች መካከል የአጥቂና የተከላካይነት አዝማሚያ መኖሩ ተገለጸ

ቀን:

በኢትዮጵያ የብሮድካስት ባለሥልጣን ፈቃድ ተሰጥቷቸው እየሠሩ ያሉ ብሮድካስት ሚዲያዎች፣ በመካከላቸው የአጥቂና የተከላካይነት አዝማሚያ መኖሩ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርዓይ አስገዶም ረቡዕ ጥቅምት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፣ በሚዲያዎች መካከል የመከላከልና የማጥቃት ዘመቻ ተጀምሯል፡፡

‹‹አንዱ ዘመቻ የሚያደርግበት፣ ሌላኛው ደግሞ ተጠቅቻለሁ ብሎ የሚከላከልበት ነው፤›› ብለዋል፡፡ የያዘውን መሣሪያ ተጠቅሞ ውጊያ ውስጥ የገባ ሚዲያ አለ ብለዋል፡፡

በሚዲያዎች መካከል ያለው ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት አገሪቱን ጥላሸት እየቀባ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህን ጽንፍ የያዘ አዝማሚያ በመግራት ወደ ትክክለኛው መንገድ የማምጣት ሚና መንግሥት ይጫወታል ብለዋል፡፡

የመንግሥትም ሆነ የግሉ ሚዲያ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠለት ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ቢኖረውም፣ በዚያው ልክ ግዴታውን በመወጣት ረገድ ውስንነቶች እንደሚታዩበት ጠቅሰዋል፡፡ ሚዲያ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ማጋለጥ ብቻ ሳይሆን ሀቅን ለሕዝብ አሳውቆ መንግሥት ከስህተቱ እንዲታረም የማድረግ ግዴታም አለበት ያሉት አቶ ዘርዓይ፣ ባለፈው ዓመት ጀምሮ በአገሪቱ ከተከሰተው ቀውስ ጋር ተያይዞ የሚታይ የአዘጋገብ ክፍተት እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

ቀውስና አለመረጋጋት ከተፈጠረ በኋላ በርካታ ሚዲያዎች ግዴታቸውን ከመወጣት ይልቅ ከዚህ በተለየ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደሚስተዋሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተሻሉ የሚባሉም ጆሮ ዳባ ብለው (የመንግሥትም ሆነ የግል) የማየት፣ ከዚህ በከፋ ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ሊንዱ የሚችሉ ዘገባዎችን የሚሠሩ በርከት ያሉ ሚዲያዎች ተስተውለዋል፤›› ብለዋል፡፡

ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ሊያጋጩ የሚችሉና ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ዘገባዎች ቀላል በማይባሉ የመንግሥት ሚዲያዎች፣ አልፎ አልፎም በግል ሚዲያዎች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል፡፡ አብዛኛው ሚዲያ ደግሞ በሶሻል ሚዲያ የሚራገበውን መረጃ ትክክለኛ ይሁን አይሁን ሳያጣራ የመጠቀም ድርጊትም እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ‹‹አልፎ አልፎ አንዳንድ የመንግሥት ሚዲያዎች ከመንግሥት ፈቃድ ካገኙ ብቻ የሚሠሩበት፣ ፈቃድ ካላገኙ ግን የሚደበቁበት ጊዜ ተፈጥሯል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹እየተከሰተ ያለው አደገኛ አዝማሚያ ስለሆነ መድረክ ፈጥረን ዘላቂ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ አገር አቀፍ ሽፋን ላላቸው ሚዲያዎች ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የታሰበውን ያህል ስኬታማ ሊሆን እንዳልተቻለ ጠቁመዋል፡፡

መብታቸውን ተጠቅመው ሕዝብን ለማገልገልና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመከላከል በትጋት የሚሠሩ ሚዲያዎችን ባለሥልጣኑ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ጠቁመዋል፡፡

ይህን ያህል አደገኛ አዝማሚያ በሚዲያዎች እየታየ እያለ እስካሁን ድረስ ዕርምጃ እንዳልተወሰደም አቶ ዘርዓይ ገልጸዋል፡፡ ዕርምጃ ሊወሰድ ያልቻለበት ምክንያቶችንም ሲጠቅሱ የመጀመርያው ጉዳይ የችግሩ ምንጭ ሚዲያው ሳይሆን ሌላ የተደበቀ ጉዳይ በመሆኑ፣ ሁለተኛው ደግሞ ሁሉም ሚዲያ በአመለካከት ረገድ ችግር ያለባቸው ስለሆነ ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ሚዲያው የሚስተካከልበትን ሥራ ማከናወን ይሻላል የሚል አቋም በመያዙ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሚዲያው በኩል ችግር እንዳለ እየተጠቀሰ በመሆኑ ለምንድነው የሚዲያ ካውንስሉ በእናንተ ድጋፍ ተቋቁሞ እንዲሠራና ይህንን መሰል ችግሮች እንዲፈቱ አላደረጋችሁም? የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ለተቋቋመው የሚዲያ ካውንስል አለመግባባቶችና የሕግ ክፍተቶች በመኖራቸው እስካሁን በሁለት እግሩ ሊቆም አልቻለም፤›› ብለዋል፡፡ ይህም ቢሆን ግን መሥሪያ ቤታቸው የሚዲያ ካውንስል እንዲቋቋም አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትሩ በቅርቡ የተወሰኑ ሚዲያዎች ያስተላለፉት ዘገባ ስህተት እንደሆነና ይህንንም መንግሥት በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ይህን በተመለከተ አቶ ዘርዓይ፣ ‹‹ሚኒስትሩ የሰጡትን አስተያየት እኔም ሰምቼዋለሁ፡፡ የሰጡት አስተያየት የግል አስተያየት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የሰጡት አስተያየት ትክክል ይሁን አይሁን አከብረዋለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ማንኛውም ሚዲያ በሚያጠፋበት ጊዜ መቼ፣ ማን፣ ምን፣ በማን እንደሚቀጣ ሕግ አለ፡፡ በአዋጅ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት አሉ፡፡ እነሱም ብሮድካስት ባለሥልጣንና ፍርድ ቤት ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

በሚዲያዎች በኩል ትክክለኛ ዘገባን በወቅቱ በማድረስ በኩል ክፍተት እንዳለ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ሚዲያዎች ትክክለኛ መረጃ ከሆነ ማንንም ባለሥልጣንና ኃላፊ ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ መዘገብ አለባቸው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

መሥሪያ ቤታቸው የሁሉንም ሚዲያዎች የሞኒተሪንግ ሥራ ሠርቶ ያጠናቀቀ በመሆኑ፣ በቅርቡ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት እንደሚገለጽ ጠቁመዋል፡፡ ይህም ትልቅ የማስተማሪያና ወደፊት ስህተት እንዳይደገም የማድረጊያ መድረክ ሊሆን እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተከሰተው አለመረጋጋት ምክንያት ሚዲያዎች ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ መዘገብ፣ ትክክለኛ መረጃ በትክክለኛው ሰዓት ለሕዝቡ ማድረስ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡  

በአሁኑ ጊዜ በብሮድካስት ባለሥልጣን ፈቃድ ተሰጥቷቸው በሥራ ላይ የሚገኙ የብሮድካስት ሚዲያዎች ቁጥር 20 ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...