በቅርቡ እንደ አዲስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸርና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን፣ በሰፋፊ ግብርና ኢንቨስትመንቶች ላይ የተንሰራፋውን ችግር ለመፍታት ስትራቴጂ ሊያወጣ ነው፡፡
በአቶ ያዕቆብ ያላ የሚመራው የኢትዮጵያ የሆርቲካልቸርና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በደቡብ፣ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች በግብርና ሥራ የተሰማሩ ኩባንያዎች ያለባቸውን ችግሮች ከሰበሰበ በኋላ፣ ማክሰኞ ጥቅምት 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ከኃላፊዎቻቸው ጋር መክሯል፡፡
በውይይቱ ላይ ጎልተው በወጡ ስምንት አንኳር ነጥቦች ላይ መንግሥታዊው ተቋምና የግል ኩባንያዎች መስማማት ላይ የደረሱ በመሆኑ፣ እነዚህን ችግሮች ከመሠረታቸው ለመፍታት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ እንደሚዘጋጅ ተጠቁሟል፡፡
ዋነኛ ተብለው የቀረቡት ችግሮች በጥናት ላይ የተመሠረተ የመሬት አቅርቦት አለመኖር፣ የተላለፉ የኢንቨስትመንት ቦታዎችን በተሟላ ደረጃ ወደ ልማት ማስገባት አለመቻል፣ አስፈላጊ የመንገድ አውታሮች አለመኖር፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የብድር አቅርቦት የተቀላጠፈ አለመሆን፣ የእርሻ ፕሮጀክቶች ዘላቂ የአካባቢና ማኅበራዊ ደኅንነት ያስጠበቁ አለመሆን፣ አስተማማኝ የገበያ ትስስርና የሎጂስቲክስ አገልግሎት አለመኖር፣ ማኅበራዊ ኃላፊነቶችን አለመወጣት፣ ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ሥርዓት አለመኖር ተጠቃሽ ችግሮች ሆነው ጎልተው ወጥተዋል፡፡
ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ በተለይ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ያለው የመሬት ሥሪት በጎሳ መሪዎች የሚተዳደር በመሆኑ፣ መሬት ለማሰተላለፍ እንቅፋት እየሆነ የኢንቨስትመንት ሥርጭቱ ፍትሐዊ እንዳይሆን ማድረጉ ተመልክቷል፡፡
በተለይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደካማ አሠራር በወቅቱ በቀረበው ጥናት ተዘርዝሯል፡፡ ልማት ባንክ ዘርፉ በፋይናንስ ከተደገፈ አዋጭ መሆኑን በቅጡ እንደማይገነዘብ ተወስቷል፡፡ በተለይም በሰፋፊ እርሻዎች ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ብድር በመስጠት የግብርና ኢንቨስትመንት ለመደገፍ የሚሠራ የፖሊስ ባንክ ሆኖ ሳለ፣ አሁን ግን ኃላፊነቱን መወጣት የማይችልበት ደረጃ መድረሱን ተነግሯል፡፡ በተልዕኮው ግራ ስለተጋባና ራሱን ችሎ ስለማይንቀሳቀስ፣ አሁን ያለው የባንኩ አመራር ያለ በቂ ጥናት ወደ ልማት የገባውን ነባሩን አልሚ የሚጎዳ ፖሊሲ ማምጣቱ ተገልጿል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ብድር ማቆም፣ ውል የተገባለትን ብድር በከፊል መቆም፣ ቶሎ ያለመወሰንና የተንዛዛ ብድር አለቃቀቅ አለበት ተብሏል፡፡
የጋምቤላ ክልል ሰፋፊ እርሻ ባለሀብቶች ኅብረት ሥራ ማኅበር ኃላፊ አቶ የማነ ሰይፉ ለሪፖርተር፣ የሆርቲካልቸርና የግብርና ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኝነቱን አሳይቷል ብለዋል፡፡
በአገሪቱ ብዙ የተባለለት የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ፍሬ ከማፍራት ይልቅ በተለያዩ ችግሮች ተተብትቦ እንደሚገኝ፣ ዘርፉ ትክክለኛውን መንገድ ቢይዝ አገሪቱ ከወጪ ንግድ ልታገኝ የምትችለውን የውጭ ምንዛሪ ከማሳደግ በተጨማሪ፣ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥር እንደነበር የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ነገር ግን ዘርፉ እስካሁን ባለቤት አልባ ሆኖ በበርካታ ችግሮች ተተብትቦ የሚገኝ በመሆኑ፣ የሚጠበቅበትን ያህል መጓዝ እንዳልቻለ ሲነገር ቆይቷል፡፡ አቶ የማነ እንደሚናገሩት አሁን ባለው ሁኔታ ቢያንስ ዘርፉ ባለቤት አግኝቷል፡፡
አቶ ያዕቆብ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት፣ ባለሥልጣኑ ከሚመለከታቸው ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ጋር ተናቦ እንደሚሠሩ መግለጻቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡