Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹የዓለም የነዳጅ ዋጋ ካልጨመረ በስተቀር በምንዛሪ ለውጥ ምክንያት ዋጋ አይጨምርም››

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

የዓለም የነዳጅ ዋጋ ካልጨመረ በስተቀር የአገር ውስጥ የነዳጅ መቸርቸሪያ ዋጋ በብር የዶላር ምንዛሪ ለውጥ ምክንያት ጭማሪ እንደማይደረግበት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው ይህንን የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሁለት ሳምንት በፊት የብርና የዶላር የመግዛት አቅም በማዳከም፣ አንድ ዶላር በ26.9 ብር እንዲሸጥ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ በዚህ የብር የመግዛት አቅም መዳከም የተነሳ የኑሮ ውድነት እንዳይከሰትና ዝቅተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍልና የመንግሥት ሠራተኛ ላይ የኑሮ ውድነት እንዳይኖር፣ እንዴት መከላከል እንደሚቻል የተቀመጠ መፍትሔ ካለ እንዲያብራሩ በአንድ የምክር ቤት አባል ተጠይቀዋል፡፡

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚነስትር ኃይለ ማርያም፣ የብር የመግዛት አቅም እንዲዳከም የተደረገው የአገሪቱን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውጤታማ ለማድረግ መሆኑን በመጥቀስ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የአገሪቱ የግብርና ምርቶች ኤክስፖርት በመጠንም በገቢም እንደሚጨምር ለማበረታታት፣ እንዲሁም ተስፋ መቁረጥ የታየበትን የኤክስፖርት ምርቶች አምራች የሆነውን ገበሬ ለማበረታታት የምንዛሪ ለውጥ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ከዚህ በኋላ ማስቀጠል የሚቻለው በኤክስፖርት ተኮር ኢንዱስትሪ (ማኑፋክቸሪንግ) በመሆኑ፣ ቀድሞ በነበረው የብር ዶላርን የመግዛት ጠንካራ አቅም ዘርፉ እንዳይዳከም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ምክንያት የብር ምንዛሪ ተመን ለውጥ ሲደረግ ከውጭ በዶላር ተገዝተው የሚገቡ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ማኅበረሰቡን እንዳይጎዳ ጥንቃቄ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ከተወሰዱት ጥንቃቄዎች መካከል ከትራንስፖርት ጋር በዋናነት የሚያያይዘው የአገር ውስጥ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በመሆኑ፣ ብር ላይ በተደረገው የምንዛሪ ለውጥ ምክንያት በአገር ውስጥ የነዳጅ ዋጋ ላይ አንድም ሳንቲም እንዳይጨመር መወሰኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ላይ የሚመጣውን ጫና መንግሥት በድጎማ የሚሸፍነው እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የሚስያረዳው የብር የመግዛት አቅም እንዲዳከም በመደረጉ፣ በዶላር ተገዝቶ ለአገር ውስጥ የሚቀርበው የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በምንዛሪ ተመኑ መሠረት እንዳይጨመር መወሰኑን ነው፡፡ ይህም ማለት የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየት የሚጀምር ከሆነ ግን፣ የአገር ውስጥ ነዳጅ መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ አይደረግም ማለት አለመሆኑን ከንግግራቸው መረዳት ተችሏል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነዳጅን አስመልክቶ የተናገሩት ትርጉም የለውም ይላሉ፡፡ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ከውጭ የሚያስገባውን ነዳጅ የሚሸጥበት ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያው ዋጋ ላይ መጠነኛ ትርፍ የታከለበት እንደሆነ፣ ከዚህ የትርፍ ምጣኔ የሚገኘው ገቢ የነዳጅ ፈንድ ተብሎ ወደ ተቋቋመው ተቋም ለዋጋ ማረጋጊያ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት እ.ኤ.አ. ከ2008 ጀምሮ ለነዳጅ የሚያደርገውን ድጎማ በማንሳት መጠነኛ ትርፍ የጣለ መሆኑን የሚጠቁሙት ባለሙያዎቹ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት የዓለም የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ መጠን መርከሱ የነዳጅ ፈንድ የሀብት መጠንን እንዳሳበጠ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ለመጨመርና በአገሪቱ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የገጠመውን ድርቅ ለመቋቋም እንዳስቻለ ያስረዳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የዓለም የነዳጅ ዋጋ በበርሜል 50 ዶላር አካባቢ በመሆኑና በአጭር ጊዜ በዚህ ዋጋ ላይ የተጋነነ ለውጥ ይመጣል ተብሎ ስለማይጠበቅ፣ እንዲሁም መንግሥት አሁንም በአገር ውስጥ የነዳጅ ዋጋ ላይ መጠነኛ ትርፍ የሚያገኝ ስለሆነ፣ በምንዛሪ ለውጡ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ እንዳይጨምር ተወስኗል መባሉ ለሸማቹ ኅብረተሰብ የሚኖረው ትርጉም የተባለውን ያህል እንዳልሆነ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነዳጅ ውጪ እንደ ስኳር፣ ዘይት፣ ስንዴና የመሳሰሉ የፍጆታ ዕቃዎችን መንግሥት እያስገባ ማከፋፈሉን እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ሲባል የተቋቋመው አለ በጅምላ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን አቅርቦትና ሥርጭት በማሻሻል የብር ምንዛሪ ተመን ለውጡ ማኅበረሰቡ ላይ ጫና እንዳይፈጥር እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን በተናገሩበት ወቅት የምክር ቤቱ አባላት ጉምጉምታ ያዘለ ሳቅ በማሰማታቸው በቀጥታ ቴሌቪዥን ይተላለፍ የነበረውን ንግግራቸውን ገታ በማድረግ፣ የጉምጉምታውን ምክንያት ለማወቅ ወደ ምክትል አፈ ጉባዔዋ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ ቢመለከቱም፣ ምክትል አፈ ጉባዔዋ ምክንያቱን ከመጠቆም ይልቅ ፀጥታ እንዲሰፍን ‹‹እንደማመጥ›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸውን እንዲቀጥሉ አድርገዋል፡፡

የፓርላማ አባላቱ ጉምጉምታ ያለው ሳቅ ያሰሙበት ምክንያት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት አለ በጅምላ በአሁኑ ወቅት ሕጋዊነት የሌለው ወይም ከሌሎች ተቋማት ጋር በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እንዲዋሀድ ተደርጎ የኢትዮጵያ ንግድ ኮርፖሬሽን በመባሉ ነው፡፡
 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች