Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹የክለቦች ድምፅ የመወሰን ሥልጣን ያለው ጉባዔው እንጂ ፌዴሬሽኑ አይደለም››

‹‹የክለቦች ድምፅ የመወሰን ሥልጣን ያለው ጉባዔው እንጂ ፌዴሬሽኑ አይደለም››

ቀን:

ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመጀመርያውን ጠቅላላ ጉባዔ ባለፈው ሳምንት (ጥቅምት 11 ቀን 2010 ዓ.ም.) በቢሾፍቱ አድርጓል፡፡ በጉባዔው ለውይይት ከቀረቡ አጀንዳዎች መካከል አትሌቶች የሚዳኙበት የሥነ ምግባር ደንብና ክለቦች በጉባዔ ድምፅ ይኑራቸው፣ አይኑራቸው የሚሉ ሁለት አጀንዳዎች አከራክረዋል፡፡ ይሁንና ጉባዔው የሥነ ምግባር ደንቡን ጨምሮ ክለቦች በጠቅላላ ጉባዔ ድምፅ ሊኖራቸው አይገባም የሚለው በድምፅ ብልጫ ይሁንታ አግኝቷል፡፡ የሥነ ምግባር ደንቡን የአትሌቶች ተወካዮች ሲቃወሙት፣ ክለቦች በጉባዔ ድምፅ ይኑራቸው የሚለውን ደግሞ ኦሮሚያና አማራ ሲደግፉት ደቡብ በድምፀ ታቅቦ በአብላጫ ድምፅ ውድቅ ተደርጓል፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ማርያም ጋር ደረጀ ጠገናው ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በኃይሌ ገብረ ሥላሴ የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኃላፊነቱን ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ አሳክቼዋለሁ የሚላቸው ክንውኖች እንዴት ይገለጻሉ?

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ገብረ እግዚአብሔር፡- እኔን ጨምሮ የፌዴሬሽኑ አመራሮች የመጀመርያ ሥራችን ያደረግነው በፌዴሬሽኑ አፋጣኝ ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ጊዜ የሚፈልጉትን ደግሞ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ በመያዝ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ቅድሚያ ከተሰጠው የመጀመርያው አበረታች መድኃኒቶች (ዶፒንግ) ሲሆን፣ ሌላው ከውድድር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ብለን ከለየናቸው ደግሞ የፌዴሬሽኑ አጠቃላይ ተቋማዊ መዋቅር ተጠቃሽ ነው፡፡ አሠራሮችን አስመልክቶ በአመለካከት ደረጃ ክፍተቶች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ እነዚህን ስፖርቱን ለማሳደግ በሚጠቅም መልኩ መስመር ለማስያዝ ተሞክሯል፡፡

ሪፖርተር፡- አመለካከት ሲሉ እንዴት?

ገብረ እግዚአብሔር፡- በዋናነት በቀድሞውና በአዲሱ ሥራ አስፈጻሚ መካከል ስፖርቱን በሚመለከት የአስተሳሰብ ልዩነቶች ነበሩ፡፡ ይህም ሲባል የሠራተኞችን አቅም፣ በአቅምና በዕውቀት ከመጠቀም አንፃር መሠረታዊ የሚባሉ የአስተሳሰብ ማስተካከያዎች ተደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከእርስዎ አነጋገር መረዳት የሚቻለው ቀደም ሲል የነበረው መዋቅር በአዲስ መልክ ለማዋቀር ዕቅድ የያዛችሁ ይመስላል?

ገብረ እግዚአብሔር፡- እንደዚያ የሚል ነገር የለም፣ ከነበረው ጠንካራውን ጎን እያጎለበትን በክፍተቱ ላይ ደግሞ ማሻሻያዎች aY d Sport ማድረግ ካልሆነ ከዜሮ የሚባል አሠራር የለም፡፡ በዋናነት ተቋሙ ቀድሞ ይዞት የነበረው የሰው ኃይል፣ ስፖርቱን ለማሳደግ ያዘጋጃቸው ማኗሎችና ጥናቶች እንዲሁም ተቋሙ ከሚፈልገው አቅምና ከተቀመጡ ሕገ ደንቦች ጋር በማጣጣም ለማስኬድ ነው የተሞከረው፡፡

ሪፖርተር፡- አመራሩ በተጨባጭ ሊጠቀስ የሚችል ለውጥ አምጥተናል የሚላቸውን ቢገልጹልን?

ገብረ እግዚአብሔር፡- ለአትሌቲክሱ እጅግ አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረው የዶፒንግ ጉዳይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሥራት ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ በአስተዳደራዊ ሥራዎችና ሌሎችም በርካታ ሊጠቀሱ የሚችሉ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ከአሠልጣኞች፣ ከአትሌቶች፣ ከማናጀሮችና ከማናጀር ተወካዮች ጋር የአትሌቲክሱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በሚመለከት ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ ከክለቦችና ክልሎችም ጋር ተመሳሳይ ውይይቶች ተደርገው መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ሌላው የክለቦችና ክልሎች አደረጃጀት በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ከፌዴሬሽኑ ሙያተኞች ወደ ሁሉም ክልሎች ተልከው ጥናትና ግምገማ አድርገዋል፡፡ ከምልመላ፣ ከውድድርና ከአደረጃጀት ተያይዞ ሊኖራቸው ስለሚገባው ቁመና ታይቷል፡፡ ከክፍተቱ በመነሳትም መፍትሔውስ? የሚለው ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ወደ ታች የሚወርድ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ጭምር መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው ሳምንት የመጀመርያውን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በቢሾፍቱ አድርጋችኋል፡፡ ከጉባዔተኛው አንዳንዶቹ አመራሩ ቃል በገባው መሠረት እየሠራ አይደለም፡፡ ለመጥቀስ ያህል ከሙያተኛ ምደባ፣ ከአትሌቶች ምልመላና ሥልጠና እንዲሁም ከማስፈጸም አቅም ውስንነት አንፃር የቀረቡ በርካታ ቅሬታዎች ነበሩ፤

ገብረ እግዚአብሔር፡- ይህ አመራር ወደ ፌዴሬሽኑ ከመጣ ጀምሮ የነበሩና ሲንከባለሉ የመጡ ክፍተቶቹን ለማጥበብ ሞክሯል፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት ከአሠራር ጋር ተያይዞ ማንም ሰው ቅሬታ ማቅረብ እንዳለበት ተቋሙ ያምናል፡፡ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ሥራ ላይ ለማዋልም እየሠራን ነው፡፡ ከባለ ድርሻ አካላት ግብዓቶችን ወስደናል፣ እየወሰድንም ነው፡፡ ነገር ግን ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ እጅግ በጣም ውስብስብ ችግሮች አሉ፡፡ ከነዚህ መካከል በደንቡም በዓለም አገር አቋራጭ፣ በዓለም ሻምፒዮናና በኦሊምፒክ በሚደረጉ ምርጫዎችና ሙያተኛ ምደባ፣ ምልመላና ዝግጅትን ምሳሌ አድርገን ብንመለከት ጥቃቅን ክፍተቶች ካልሆኑ በስተቀር በደንብና መመርያው መሠረት እንዲሄድ ተደርጓል፡፡ ደንብና መመርያው ምናልባት ተጥሏል ሊያስብል የሚችለው ወቅታዊ ብቃት የሚለው ካልሆነ፣ ያን ያህል እንደ ክፍተት ተቆጥሮ ለወቀሳ የሚያበቃ ነገር የለም፡፡ ግን መወቀስ የለብንም እያልኩ አይደለም፡፡ ወቀሳው ምክንያታዊ በሆነ መልኩ መሆን ይኑርበት ነው፡፡ ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ወይም ለዓለም አገር አቋራጭ ምርጫ በአገር ውስጥ ወይም በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ደረጃ ውስጥ ገብቶ ማጠናቀቅ ብቻውን መስፈርት መሆን በቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ለዚያም ነው ወቅታዊ ብቃት የሚል ነገር ቀደም ብዬ የተናገርኩት፡፡ በዝግጅት ጊዜ በአሠልጣኞች የሚቀርቡ ሪፖርቶች መመዘኛ የሚሆኑበት አግባብም እንዳለ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ አመራር ወደ ኃላፊነት በመጣ ማግሥት በተደረገው የለንደኑ ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሙያተኛ ምደባ፣ አትሌት ምርጫና ምልመላ ላይ ከደንብና መመርያ ውጪ ሠርቷል የሚሉ አሉ፡፡ ለምሳሌ የክልል አሠልጣኞች በኮታ የተመደቡበት አጋጣሚ ከመኖሩም በላይ ለምርጫ በሚል በአገር ውስጥ በተደረጉ ውድድሮች ላይ ያልተሳተፉ አትሌቶች በዕውቅናቸው ብቻ ለብሔራዊ ቡድን የተመረጡበት አሠራር ነበር፡፡

ገብረ እግዚአብሔር፡- አሁን ያለው አመራር የፌዴሬሽኑን ኃላፊነት ከተረከበ ገና አንድ ዓመት እንኳን እንዳልሞላው ይታወቃል፡፡ በዚህ የአገልግሎት ጊዜ ውስጥ ደግሞ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት፣ የዓመታት ችግር ሆኖ ሲንከባለል የመጣውን ችግር በአንድ ጊዜ ለማስወገድ መሞከር ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን የተጠቀሱት የአሠራር ክፍተቶች አልነበሩም የሚል መከራከሪያ ማቅረብ አልፈልግም፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሩ እንዳለ ሆኖ አቅምንና ዕውቀትን መነሻ ያደረገ ምደባ ማድረግ ችግሩ ምንድነው? በለንደኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ወቅት የክልል አሠልጣኞች ኮታ በሚል ለብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝነት የተመደቡ ነበሩ፡፡ ይህ እንዴት ይታያል?

ገብረ እግዚአብሔር፡- ከፌዴሬሽኑ ደንብና መመርያ ውጪ የተደረገ ምደባ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብ ያቀረበው ጥያቄ ለዚህ ማረጋገጫ አይሆንም?

ገብረ እግዚአብሔር፡- ክለቡ ጥያቄ ማቅረቡ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ችግሩ የተነሳው ከመደበኛው የአሠልጣኞች ምደባ ጋር ተያይዞ አይደለም፡፡ ፌዴሬሽኑ ለሁሉም የውድድር ርቀቶች ከያዛቸው መደበኛ አሠልጣኞች በተጨማሪ ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ አሠልጣኞች በፌዴሬሽኑ ወጪ በአሠልጣኝነት እንዲካተቱ ያደርጋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የታሰቡት የሴት አሠልጣኞች ሥራ ላይ ስለነበሩ በምትካቸው ዕድሉ ለምን ለክልሎች አይሰጥም? በሚል፣ ነገር ግን ከነዚህም አትሌቶችን ለብሔራዊ ቡድን ያስመረጡ የሚለው እንደ መስፈርት እንዲታይ ተደርጎ የትግራዩ አሠልጣኝ እንዲመጣ ተደረገ፡፡ ይኼ ነው ኮታ ተብሎ የተወሰደው እንዴት የሚሉ ካሉ የምርጫ መስፈርቱን መመልከት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በለንደን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ፌዴሬሽኑ በአሠልጣኝነት ከያዛቸው አሠልጣኞች ይልቅ ማናጄሮችና የማናጀር ተወካዮች እንዲሁም የሴት አትሌቶች ባሎች ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ ከዝግጅት እስከ ውድድር ቦታ ድረስ የጎላ ድርሻ እንደነበራቸው ታይቷል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ አንዳንዶቹ አሠልጣኞች ይህንን በይፋ ተናግረዋል፡፡ የሆቴልና የትራንስፖርት ወጪያቸውም በፌዴሬሽኑ መሸፈኑ ተነግሯል፡፡ ይህንንስ እንዴት ይገልጹታል፣ ደንብና መመርያውስ ይፈቅዳል?

ገብረ እግዚአብሔር፡- ለዚህ ጥያቄ አሁንም መልሴ ሲንከባለል የመጣውን ችግር በአንድ ቀን ጀምበር መቅረፍ አይቻልም፡፡ እውነት ነው በነበረው ሁኔታ በብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ወቅት፣ በአትሌቶች የባል ጣልቃ ገብነት፣ የሚስት ጣልቃ ገብነት፣ የማናጀሮችና የማናጀር ተወካዮች ጣልቃ ገብነት ነበር፡፡ ችግሩ በጣም ከመስፋፋቱም በላይ ሥሩን ለመበጣጠስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ እነዚህ አካላት ከፌዴሬሽኑም በላይ በአትሌቶች ተቀባይነት ያላቸው ሆነዋል፡፡ ይህን ነው ፌዴሬሽኑ በአንድ ቀን ጀምበር መፍታት እንዳለበት የሚጠበቀው፡፡ በመሆኑም እዚህ ላይ ማለት የምንፈልገው ፌዴሬሽኑ ይህን ሁሉ ሥር የሰደደ ችግር በአንድ ቀን ጀምበር ቆርጦ ከመጣል ይልቅ ምርጫ ያደረገው ስፖርቱም ሳይጎዳ ጊዜ ወስዶ ማስታመም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከደንብና መመርያ አንፃር ትክክል ነው?

ገብረ እግዚአብሔር፡- ትክክል እንዳልሆነ ይሰማኛል፡፡ ትክክለኛው ወደ አሠራሩ ለመግባት ግን ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ማስታመም የመረጥነው ለዚህ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ አሁንም ራሱ ያወጣውን ደንብና መመርያ እየጣሰ ነው ለማለት አያስችልም?

ገብረ እግዚአብሔር፡- ችግሩን ማስታመም መጣስ ከሆነ ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ለንደን ያመራው የአሠልጣኞች ቡድን ኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ለአገሪቱ ከሰጠው ኮታ በላይ ነበሩ?

ገብረ እግዚአብሔር፡- እውነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ስሜት ፈጥረናል ስትሉ ነበር፡፡ እውነት ግን በለንደኑ የአትሌቲክስ ልዑክ የተባለው ብሔራዊ ስሜትና የቡድን ሥራ ነበር ማለት ይቻላል?

ገብረ እግዚአብሔር፡- ሙሉ ለሙሉ ክፍተቱን ከሥሩ ነቅለነዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በጣም ብዙ ችግሮች ነበሩ፡፡ በተወሰነ መልኩ የችግሩን ስፋትና መጠን በመቀነስ ደረጃ ግን ብዙ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ምልክቶችም ታይተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቢሾፍቱ በተካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በአንድ ቀን ስብሰባ ከስድስት ያላነሱ መመርያና ደንቦች ለውይይት ቀርበው የጉባዔውን ይሁንታ አግኝተዋል፡፡ እንዲህ በተቻኮለ አግባብ የሚወጣ መመርያና ደንብ ውሎ አድሮ ችግር እንደሚኖረው ከአንዳንድ የጉባዔ ተሳታፊዎች ሲቀርብ ተደምጧል፡፡

ገብረ እግዚአብሔር፡- ፌዴሬሽኑ መመርያና ደንቦቹን ጭምር ለሚመለከታቸው አካላት የላከው ከ15 ቀናት በፊት ነው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ጉባዔተኛው አጀንዳዎቹን በደንብ ተመልክቶ ተዘጋጅቶባቸው እንዲመጣ በማሰብ ነው፡፡ ተጨማሪ አጀንዳ ካለ፣ መሰረዝ ያለበት ካለም በተመሳሳይ ጉዳዩን በደንብ ተዘጋጅቶበት እንዲመጣ ነው፡፡ አንድም ክልል በዚህኛው አጀንዳ ጥያቄም ሆነ ቅሬታ አለኝ ብሎ ያቀረበ የለም፡፡ እርግጥ ነው የአሠልጣኞች ማኅበር፣ የአዲስ አበባ ክለቦች ተወካይና የዳኞች ማኅበር አጀንዳ እንዲያዝላቸው ጠይቀዋል፡፡ እነሱ ያቀረቡት አጀንዳው በመመርያ ይመለሳል በሚል ውድቅ ተደርጓል፡፡ በዋናነት ግን የውሳኔው ባለቤት ጉባዔው ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ ጉዳይ እንዴት ሊጠየቅ ይችላል?

ሪፖርተር፡- ከቀረቡት ደንቦችና መመርያዎች መከካከል የአትሌቶችና ሙያተኞች ሥነ ምግባር ደንብ ይጠቀሳል፡፡ በሥነ ምግባር ደንቡ አንድ አትሌት ፌዴሬሽኑ በሚያዘጋጃቸውና በሌሎችም ተመሳሳይ የሽልማት አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት የማይገኝ ከሆነ በትንሹ ‹‹የስድስት ወር ዕገዳ ይጣልበታል›› የሚል ይገኝበታል፡፡ የአትሌቶች ተወካዮች ረቂቅ ደንቡን ተቃውመውታል፡፡ ነገር ግን በድምፅ እንዲያልፍ ተደርጓል፡፡ ያስኬዳል?

ገብረ እግዚአብሔር፡- የሥነ ምግባር ደንብ እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ መድረስ እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ግን ደንቡ መኖር የለበትም ብለው የሚከራከሩ አካላት የሥነ ምግባር ደንብ ለመጣስ ያሰቡ ካልሆኑ ደንቡ እንደ ደንብ ቢቀመጥ ጉዳቱ ምንድነው?

ሪፖርተር፡- ጉዳዩ የዕውቅና ጉዳይ ሆኖ ሳለ አስገዳጅ ማድረግ ማስፈራራት አይሆንም?

ገብረ እግዚአብሔር፡- አንተ ሌላ ተልዕኮ ወይም ተያያዥ ፍላጎት እስከሌለህ ድረስ የሥነ ምግባር ደንብ ቢኖር በግሌ ጉዳቱ አይታየኝም፡፡ ምክንያታዊ መሆን ያስፈልጋል፡፡ የሥነ ምግባር ደንቡ በምክንያት ከሆነ የፈጣሪ ቃል አይደለም፡፡ በግሌ የአሸናፊነትና ተሸናፊነት ጉዳይ አድርጎ የመውሰድ ጉዳይ ካልሆነ ችግር ያለው አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- በሥነ ምግባር ደንቦች ውስጥ የዕድሜ ልክ ዕገዳ የሚደረግባቸው አሉ፤

ገብረ እግዚአብሔር፡- ድርጊቱን ለመፈጸም ፍላጎቱ እስከሌለኝ ድረስ ዕድሜ ልክ አይደለም፣ ስቅላት የሚል ነገር እንኳን ቢኖር ግድ አይሰጠኝም፡፡ በእርግጥ ሌባ ስለሌለ በሬን ከፍቼ ልደር የሚሉ ካሉ እንደተባለው የሥነ ምግባር ደንቡ ላያስፈልግ ይችል ይሆናል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የማስፈጸም አቅም ውስንነት ካልሆነ ያለው የሥነ ምግባር ደንብ ተግባር ላይ ከዋለ በቂ ነው የሚሉ አሉ?

ገብረ እግዚአብሔር፡- አትሌቶቹም ሆነ ፌዴሬሽኑ ተበታትነው ይቅሩ እየተባለ ካልሆነ እስከዛሬ በነበረው ፌዴሬሽኑ፣ ለአንድ አትሌት ሁሉን የጉዞ ቅድመ ሁኔታ አሟልቶለት ኤርፖርት እየተጠቀመ የለም አልመጣም የሚል አትሌት እንዳለ መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም፡፡ ታዲያ እንዴት ነው ለዚህ ሕግ የማያስፈልገው? በግሌ በጣም ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በጉባዔው ሌላው አከራካሪ የነበረው በአንድ ክልል ቢያንስ ከአምስት በላይ ክለቦች ካሉ አንድ ድምፅ እንዲኖራቸው ከኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቀረበው አጀንዳ ይጠቀሳል፡፡ አጀንዳው ተቃውሞ የገጠመው በዋናነት ከታዳጊ ክልሎች ነበር፡፡ ምክንያት ይኖረዋል?

ገብረ እግዚአብሔር፡- ክለብ ያሏቸው ክልሎችን ድርሻ እየወሰድን መኖር አለብን ያለ ክልል አለ ብዬ አላምንም፡፡ አጀንዳው የተቃወሙት ሲሉ የነበረው በሆነ አጋጣሚ የክለብ ባለቤት የሆኑ ክልሎች እንዳሉ ሁሉ፣ እኛ ደግሞ በአጋጣሚ ይህን ዕድል አጥተነዋል፣ አብቁን እኛም እናንተ የደረሳችሁበት ደረጃ እንድንደርስ አግዙን ነው፡፡ እስከመቼ? የሚለው በፌዴሬሽኑ በኩል ድክመት እንዳለ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አትሌቲክሱ በተለይም በአሁኑ ወቅት ትልቅ የኢንቨስትመንት አማራጭ እየሆነ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚና ለስፖርቱም ዕድገት ሲባል ክለቦች ድምፃችንን ማሰማት የምንችልበት ዕድል ይሰጠን ሲሉ አያስፈልጋችሁም፤ በእኛ በኩል መብታችሁም ሆነ ድምፃችሁ ይሰማል ማለት ለስፖርቱ ዕድገት ይበጃል?

ገብረ እግዚአብሔር፡- እዚህ ላይ የነበረው አደረጃጀት ይለወጥ ከሆነ ጥያቄው ሊያስኬድ ይችላል፡፡ አደረጃጀቱ በክልሎች መሆን የለበትም ማለት ከሆነም እንደዛው፡፡ ያለው አደረጃጀት ይለወጥና የጠቅላላ ጉባዔው ባለቤቶች መሆን ያለባቸው እነማን ናቸው? የሚለው በዝርዝር ይቀርብ ከሆነ እንደጥሩ መውሰድ ጉዳት ያለው አይመስለኝም፡፡ ግን አሁን ባለው የጉባዔ አደረጃጀት ሁሉም ክልሎች የምንሠራው ለአገሪቱ አትሌቲክስ ነው እስካሉ ድረስ እየተነሳ ያለው ጥያቄ ለምን የሚያስብል መሆኑ አይቀርም፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ክለቦች ድምፅ አይገባቸውም? ይገባቸዋል? ለሚለውን መወሰን የሚችለው ጉባዔው ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ የሚያስፈጽመው ጉባዔው በሰጠው አቅጣጫ መሠረት በመሆኑ ለወደፊቱ ጉባዔው ካመነበት ያንን ለማስፈጸም የፌዴሬሽኑ ችግር አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ መሀል በሚፈጠር ውዝግብ ውጤት ቢጠፋ ተጠያቂው ማን ነው?

ገብረ እግዚአብሔር፡- በዋናነት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሆኖ፣ በተዋረድ የሚመለከታቸው አካላት ናቸው፡፡ እርግጥ ነው ክልሎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግና ማገዝ ተገቢ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ጊዜ ገደብም ሊቀመጥ ይገባል፡፡ ክልሎች ለክለቦችና ለሚሠሩ ክልሎች ዕውቅና መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ ፌዴሬሽኑም ከሽልማት ጀምሮ ከፍተኛውን ጥቅም እየሰጠ ያለው ለሚሠሩ ክልሎችና ክለቦች ነው፡፡ ወደ ድምፅ ከመጣን መታየት ያለበት ከአደረጃጀት አኳያ መሆን ይኖርበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...