Wednesday, November 30, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ይድረስ ለሪፖርተርበምንዛሪ ለውጡ የተመታውን ሕዝብ መታደግ የመንግሥት ግዴታ ነው

  በምንዛሪ ለውጡ የተመታውን ሕዝብ መታደግ የመንግሥት ግዴታ ነው

  ቀን:

  መንግሥት የአገሪቱን የወጪ ንግድ ለማበረታታትና ለማደፋፈር በማለት የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ ካደረገ ወዲህ የአገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ የወትሮው ክራሞት ተረብሿል፡፡ የተፈጠረውን አጋጣሚ የተመረኮዙ ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጪዎች፣ ከተለመደው የገበያ ዋጋ ያፈነገጠ ሒሳብ ሲጭኑ ከርመዋል፡፡ በየሚዲያው ‹‹ምክንያት አልባ›› የዋጋ ጭማሪ ወዘተ. እየተባለ ሲደሰኮር ሰንብቷል፡፡ ምክንያት ግን ነበረው፡፡ ያውም መንግሥት ያመጣው ምክንያት፡፡

  መንግሥት የምንዛሪ ለውጡን ለማድረግ ሲነሳ ዝግጅት አድርጎ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በፓርላማ ሲናገሩ መስማቴ አስገርሞኛል፡፡ ዝግጅቱ ምን እንደነበር አብራርተው ቢናገሩ በወደድን ነበር፡፡ በተዋረድ የሚገኙ ባለሥልጣናት በየቀበሌውና በየአዳራሹ እየተገኙ ዋጋ መጨመር እንደማይገባው ቢያንስ ለመጪዎቹ ሦስት ወራት የዋጋ ጭማሪ መደረግ እንደማይገባው ሲናገሩ፣ ነጋዴው ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ያደረገው እንጂ ዋጋ ለመጨመር የሚያገበቃ ምክንያት እንደሌለ ለማሳመን ሲጣጣሩ ለማየት ተገደናል፡፡

  የምንዛሪ ለውጡ ባመጣው አጋጣሚ ምክንያት ለተፈጠረው የዋጋ ጭማሪ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችና የመንግሥት ኃላፊዎች ለየቅል ሲናገሩም አድምጠናል፡፡ የአገሪቱ የወጪ ንግድ እንዲስፋፋ ወይም እንዲጎለብት የሚለውን አባባል ባለሙያዎቹ ቢቀበሉትም ብዙም የማያጠገብ ትንታኔ መሆኑን ግን ሲገልጹ ሰምተናል፡፡ ይኸውም አገሪቱ ምርት በአብዛኛው የግብርና ምርት ላይ የተመሠረተ እንደመሆኑ መጠን ምርት ካልጨመረ በቀር መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ማድረጉ ብዙም የሚያመጣው ፋይዳ እንደሌለ እንሰማለን፡፡ የለም የግብርናው ምርት በውጭ ምንዛሪ ለውጡ ይነቃቃል በማለት መንግሥት መሞገቱን አላቆመም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ለውጥ ላይ ጥገኛ የሆነው የአገሪቱ የንግድ ሚዛን በዚህ መንገድ ሁልጊዜ ሊታሽ እንደማይችል፣ ይልቁንም አገሪቱ በመሠረታዊነት መፍጨርጨር የሚገባት የወጪ ንግዷን ሊያዳብሩ በሚችሉ፣ አምራችነቷን በሚያስፋፉ፣ ተወዳዳሪነቷን በሚያጠናክሩ ሥራዎች ቀድማ በመገኘት በዓለም አቀፍ ገበያው ውስጥ ደህና ተስትፎ ማድረግ ስትጀምርና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ብዛት ያለው ምርት ሲኖራት የውጭ ምንዛሪ ችግሩም አብሮ እንደሚስተካል የሚያምኑ አሉ፡፡

  በዚያም ተባለ በዚህ የምንዛሪ ለውጡ የተረጋጋውን የገበያ እንቅስቃሴ ማወኩ ግልጽ ነው፡፡ ትክክለኛው ጊዜ ስለመሆኑም አጠራጣሪ ነው፡፡ በዚህ መካከል ሕዝብ በመንግሥት ዕርምጃና በነጋዴው የዋጋ ጭማሪ ሳቢያ ተጎጂ ቢሆንም ከሁለቱም ወገን የሚከላከልለት፣ አንጀቱን የሚያርስ መፍትሔ ማግኘት አልቻለም፡፡

  ከዕለት ምግብ ጀምሮ የትኛውም ሸቀጥ አስገምጋሚ የዋጋ ጭማሪ እያሳየ ይገኛል፡፡ የመንግሥት ዕርምጃ ግን እየዞሩ ሱቅና መጋዘን ማሸግ ሆኗል፡፡ ይህ ጊዜያዊ መፍትሔ ነው፡፡ ያውም እዚህ ግባ የማይባል ውጤት የሚያስገኝ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በእኔ እምነት መንግሥት ነጋዴውን ማሸነፍ የነበረበት ተገቢውን የምርት ዓይነትና መጠን ገበያ ውስጥ በማስገባት ነበር፡፡ የምርት ዕጥረት ባለበት ምርት በማቅረብ የዋጋ ንረትና ውድነት ይረግባል እንጂ ሌባና ፖሊስ በመሯሯጥ የሚቃለል ችግር አይኖርም፡፡

  መንግሥት ዋናው ትኩረቱም ምርት በተገቢው መጠንና ጊዜ ገበያው ውስጥ እንዲገኝ በማድረግ ነገን አስበው፣ ዕጥረት ሲኖር ዋጋ ይጨምራል በሚል ምክንያት የምርት ዕጥረት የሚደብቁ ግለሰቦች መቼም የከተማውን ምርት በሙሉ ደብቀው የሚያቆዩበት አቅምና ችሎታው አይኖራቸውም፡፡ አንዲት መደብር በማሸግ እጥረት ሊፈጥሩ ሲሉ፣ ዕቃ ሊያሸሹ ሲሉ እያሉ ማምታትም ከዋናው ጉዳይ መሸሽ ያስመስላል፡፡ ዋናው ጥያቄ ምርት አይመረትም ቢመረትም እንደሚፈለገው መጠን አይደለም የሚለውን አምኖ በመቀበል ይህንን ችግር መቅረፉ ነው መፍትሔው፡፡

  ከውጭ የሚገባውንም በተገቢው ቁጥጥርና ክትትል ወደሚፈለገው ገበያ መውጣትና ለተጠቃሚው መድረሱን ማረጋገጡ ይህን ያህል ከባድ ሥራ አይደለም፡፡ በመሆኑም መንግሥት የወሰደው የምንዛሪ ለውጥ ዕርምጃ ያስገኛል የተባለውን ያህል ጥቅም ጉዳቱንም በዚያው ልክ ባናጣጥል ተገቢ ነው፡፡ ከዚህም በላይ የተባባሰ ችግር እንዳይፈጠር መቆጣጠሪያ ስልቶችን በማበጀት የገበያውን አካሄድ ከሥር ከሥሩ እየተከታተሉ እንዲያገግም መጣጣር እንጂ፣ መንግሥት የ15 በመቶ ጭማሪ ማድረጉ በተሰማ ቅጽበት የጥቁር ገበያው የምንዛሪ ተመን ከ27 ብር ወደ 34 ብር እንዲያድግ መንገዱን የጠረገው እኮ መንግሥት ነው፡፡ ቀድሞ ነገር ለጥቁር ገበያ መፈጠርም የአገሪቱ የዶላር እጥረት ሰበብ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለዚህም እንደ ጥቁር ገበያው ሁሉ የሸቀጦችም ጥቁር ገበያ እንዳይፈጠር ለማድረግ ካስፈለገ ምርትን በተመጣጣኝ መንገድ ማቅረብ መቻል ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ በየሱቁ በራፍ ፖሊስ እያሠማሩ የሚመጣ ለውጥ አይኖርም፡፡ 

  (ዓለም ፀሐይ ይስሃቅ፤ ከአዲስ አበባ)

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...