Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  በሕግ አምላክበከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች በዋስ የመለቀቅ መብት  ከሕገ መንግሥቱ አንፃር...

  በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች በዋስ የመለቀቅ መብት  ከሕገ መንግሥቱ አንፃር እንዴት ይታያል?

  ቀን:

  በታምራት ኪዳነ ማርያም

  በተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 434/97 ዓ.ም. ማናቸውም ከአሥር ዓመት በላይ በሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል የተከሰሰ ሰው በዋስ የመለቀቅ መብት እንደሌለው ይደነግጋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(6) ላይ ቃል ለቃል እንደሚከተለው ተደንግጓል፤ “የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት አላቸው፡፡ ሆኖም በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ላለመቀበል ወይም በገደብ መፍታትን ጨምሮ በቂ የሆነ የዋስትና ማረጋገጫ እንዲቀርብ ለማዘዝ ይችላል፡፡” ከዚህ ላይ በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት እንዳላቸውና ነገር ግን ፍርድ ቤቶች በሕግ የተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎችን መሠረት በማድረግ የዋስትና መብትን ሊነፍጉ ወይም የተለዩ ገደቦችን በማስቀመጥ መብቱን ሊፈቅዱ እንደሚችሉ ነው፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ ለፍርድ ቤቶች (ለዳኞች) ሁኔታዎችን በማመዛዘን ዋስትና መብትን መከልከል እንዲችሉ ሥልጣን ከመስጠቱ በስተቀር ፓርላማ በሕግ (በአዋጅ) ዋስትና መከልከል እንዲችል ሥልጣን ሰጥቶታል ወይ የሚለው በራሱ አነጋጋሪ አከራካሪና የሕገ መንግሥትን ትርጉም የሚሻ ነው፡፡

  በሌላ በኩል ፓርላማው በአዋጅ ዋስትና ለመከልከል በሕገ መንግሥቱ ሥልጣን ተሰጥቶታል አልተሰጠውም የሚለው አነጋጋሪ ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከአሥር ዓመት በላይ በሚያስቀጣ ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች በሙሉ በዋስትና እንዳይለቀቁ የሚከለክል ሕግ ፓርላማው ማውጣቱስ ከራሱ ከሕገ መንግሥቱም ሆነ ሕገ መንግሥቱን ለመተርጎም ከሚያገለግሉት ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ስምምነቶች፣ ሕግጋትና ሰነዶች አኳያ እንዴት ይታያል ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡

  ሕገ መንግሥታዊ ሰብዓዊ መብቶች የሚገደቡት በመጀመርያ ነገር ሕገ መንግሥቱ ሲፈቅድ ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 19(6) ላይ ለዳኞች ሁኔታዎችን በማመዛዘን ዋስትና መከልከል ወይም በገደብ መፍቀድ እንዲችሉ ሥልጣን ከመስጠቱ ባሻገር፣ ለፓርላማ ዋስትና ሙሉ ለሙሉ በሕግ መከልከል የሚችልበት ሥልጣን ሰጥቶታል ወይ የሚለው አከራካሪ ነው፡፡ በሌላ አባባል ፓርላማው ለዳኞች ዋስትና የመፍቀድና የመከልከል ሥልጣናቸውን ሲጠቀሙ ምን ምን ሁኔታዎችን ማየት እንዳለባቸው የሚያመለክት ሕግ ከማውጣት ባለፈ ፓርላማው ራሱ በአዋጅ (ፍርዱ ሰጥቶ) ለአንዳንድ ወንጀሎች ሙሉ ለሙሉ ዋስትና መከልከል ይችላል ወይ የሚለው በቅጡ መታየት ያለበት ነው፡፡ ይኼንን በሚመለከት የኢትዮጵያ ሕግ አካል ተደርጎ የሚቆጠረውና እንዲያውም ራሱ ሕገ መንግሥቱን ለመተርጎም የሚያገለግለው ኢትዮጵያ ያፀደቀችው የዓለም አቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብት ስምምነት አንቀጽ 9 (3) ማናቸውም በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው ባስቸኳይ ዳኛ ጋር የመቅረብ መብት እንዳለውና አግባብ ባለው ጊዜ ውስጥ ለፍርድ ሊቀርብ እንደሚገባ ወይም መለቀቅ እንዳለበት፣ እንዲሁም ፍርድ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ሰዎች በእስር እንዲቆዩ በደፈናው በሕግ ሊደነገግ እንደማይገባና ነገር ግን ሲለቀቁ ዋስ እንዲያቀርቡ ሊደረግ እንደሚቻል ይደነግጋል፡፡ ይኼንን ቃል ኪዳን ስምምነት የመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው በስምምነቱ የተቋቋመው አካል እ.ኤ.አ በዲሴምበር 16 ቀን 2014 በሰጠው አስገዳጅ ትርጉም (ጄነራል ኮሜንት) (ገጽ 12 ላይ) ከላይ የተጠቀሰው የስምምነቱ አንቀጽ 9(3) በአንድ የወንጀል አንቀጽ የተከሰሱ ሰዎች በዋስ እንዳይለቀቁ በሕግ በጥቅሉ (በጅምላ) መከልከልን እንደማይፈቅድና ዳኞች ግን እያንዳንዱን የጉዳይ ዓይነትና የተከሳሹን ሁኔታ እያመዛዘኑ ዋስትና መፍቀድ ወይም መከልከል እንደሚችሉ አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም አዋጁ ከአሥር ዓመት በላይ በሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሰዎችን በደፈናው በጅምላ ዋስትና መንፈጉ ኢትዮጵያ ያፀደቀችውን ስምምነት የሚጥስ ነው በማለት መደምደም ይቻላል፡፡ ይኼ ስምምነት ደግሞ ሕገ መንግሥቱን ለመተርጎም የሚያገለግል ሰነድ እንደመሆኑ መጠን የአዋጁን የዋስትና ክልከላ ሕገ መንግሥታዊነት በእጅጉ አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡

  ሕገ መንግሥታዊ ሰብዓዊ መብቶችን በሕግ መገደብ የሚቻለው የተወሰኑ ሁኔታዎች ሲሟሉ መሆኑን ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ በመጀመርያ ነገር ሕግ አውጪው ሰብዓዊ መብቶችን ለመገደብ የሚችለው በቂና አሳማኝ ምክንያት ወይም ግብ ሲኖረው ብቻ ነው፡፡ በመቀጠልም ሕግ አውጪው ያለመውን ግብ ለማሳካት መብቱን ከመገደብ ውጪ ሌላ አማራጭ ሳይኖረው ሲቀር ነው፡፡ ሦስተኛ ነገር ገደቡ የሚያስገኘው ጠቀሜታ ከሚያደርሰው ጉዳት ጋር ተመዛዛኝ ሲሆን ነው፡፡ እንዲሁም የገደቡ ስፋትና ጥልቀት በተቻለ መጠን መስፋት የለበትም፡፡

  በቅድሚያ ሕግ አውጪው ከአሥር ዓመት በላይ በሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች የዋስትና መብት እንዳይኖራቸው ለመከልከል ተቀባይነት ያለው አጥጋቢ ምክንያት አለው ወይ የሚለውን እንመልከት፡፡ ከአዋጁ (የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 434/97 ዓ.ም) እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚ አዋጅ ቁጥር 438/97 ዓ.ም. ሆነ ከሕጉ በቀላሉ ለመረዳት የሚቻለው በከባድ የሙስና ወንጀል (ከአሥር ዓመት በላይ በሚያስቀጣ) የተከሰሱ ሰዎች የዋስ መብት እንዳይከበርላቸው በሕግ የተከለከለበት ምክንያት ሙስናን ውጤታማ በሆነ ሁኔታ (በብቃት) ለመዋጋት ዝግጁ የሆነ ኅብረተሰብ ለመፍጠርና በቁጥጥር ሥር ለማዋል ነው፡፡ ሰዎች በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰው በዋስ ከተለቀቁ በኋላ ቢሰወሩ ወይም ባይጠፉም ነገር ግን ዳኝነት እስከሚሰጥ ድረስ ጊዜ ስለሚወስድ እንደልባቸው ነፃ ሆነው ከተንቀሳቀሱ (በተለይ ሰዎቹ በትክክል ወንጀሉን ፈጽመው ከሆነ) ለሌላው ኅብረተሰብ ሙስና መፈጸም በሕግ የሚያመጣው የከፋ ውጤት የለም የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በመፍጠር ሙስና ሊስፋፋ ይችል ይሆናል፡፡

  በአጠቃላይ ሕግ አውጪው ሙስና በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዳይስፋፋና እንዲጠፋ መፈለጉና ይኼንን ዓላማ አድርጎ መነሳቱን ነጥለን ስንመለከተው መብት ለመገደብ የተሰጠ አጥጋቢ ወይም በቂ ምክንያት አለ ልንል እንችላለን፡፡

  በሁለተኛ ደረጃ ሕግ አውጪው ሙስና እንዳይስፋፋ ያለመውን ግብ ለማሳካት ንፁሃንና አጥፊ ተጠርጣሪዎችን ሳይለይ የሁሉንም የዋስትና መብት በአዋጅ ከሚነፍግ ይልቅ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም የሚችልበት ሁኔታ አለ የለም የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ሕግ አውጪውን የሚያሳስበው በሙስና ከሚጠረጠሩ ተከሳሾች ውስጥ ወንጀሉን በትክክል የፈጸሙት በዋስትና ተለቀው ጉዳዩ ገና ከሁለትና አራት ዓመት በኋላ ውሳኔ እስከሚያገኝ ድረስ እንደልባቸው በኅብረተሰቡ መካከል ሲንቀሳቀሱ መጥፎ አርአያ ይሆናሉ የሚል ከሆነ ምንም እንኳን ሥጋቱ ተገቢ ቢሆንም፣ ይኼንን ሥጋት ለማስወገድ ንፁሁንና አጥፊውን ቀላቅሎ የሁሉንም የዋስትና መብት ከመደንገግ ይልቅ ፍርድ ቤቶች ብቃትና ውጤታማነታቸውን ጨምረው በተለይ የሙስና ጉዳዮችን ቶሎ ቶሎ አይተው ውሳኔ እንዲሰጡ ማስቻል የሚችልበት አማራጭ አለ፡፡

  የፍርድ ቤቱን በጀት መጨመር፣ ተጨማሪ ዳኞች መሾም፣ የዳኞች ደመወዝ መጨመር፣ የፀረ ሙስና ጉዳይ የሚመለከቱ ችሎቶችን ማብዛት ወዘተ የመሳሰሉ አማራጮችን በመውሰድ የተጠርጣሪዎቹም የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት ጭምር ማክበር በቶሎ ፍትሕ መስጠትና በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፎችን ማባረር እየተቻለ፣ አጥፊነታቸውን ያልተረጋገጠውን ተጠርጣሪዎች በሙሉ ዋስትና መንፈግ በፍፁም አግባብነት ሊኖረው አይችልም፡፡ እንዲሁም ከተጠረጠሩት ተከሳሾች መካከል በትክክል ሙስናውን የፈጸሙ ሰዎች በዋስ ከወጡ በኋላ የዘረፉትን ገንዘብ ሊያሸሹ ወይም በገንዘቡ እየነገዱበት መጥፎ አርዓያ ሊሆኑ ይችሉ የሚል ጥርጣሬ ካለም ምንም እንኳን ይህም ተገቢነት ያለው ሥጋት ቢሆንም፣ አሁንም ንፁሁንና አጥፊውን ሳይለዩ ሁሉንም ተጠርጣሪ ዋስትና ከመንፈግ ይልቅ የተጠርጣሪዎቹን ንብረት በተመጣጣኝ ሁኔታ ማስከበርና እንዳያሸሹ በሕግ ማገድ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩልም አልፎ አልፎ አንዳንድ ተጠርጣሪዎች ከሚጠብቃቸው ቅጣት ለማምለጥ ሊሰወሩ ወይም ከአገር ሊኮበልሉ ይችላሉ የሚል ሥጋት ካለም አንደኛ ነገር የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓታችን ቁጥር 67 እና ከላይ እንደተጠቀሰው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19 (5) ለዳኞች በዋስ ቢለቀቅ ይጠፋል ወይም ማስረጃ ያጠፋል ተብሎ ለሚጠረጠር ተከሳሽ ዋስ እንዲከለክሉ ሥልጣን የሚሰጥ በመሆኑና ዓቃቤ ሕግም ይኼንን ጠቅሶ በመከራከርና በማሳመን ማስከልከል የሚችልበት አማራጭ እያለ ሕግ አውጪው ከአሥር ዓመት በላይ በሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ሁሉም በዋስትና እንዳይለቀቁ መከልከሉ ተገቢነት የለውም፡፡ በአጠቃላይ ሕገ መንግሥታዊ ሰብዓዊ መብቶች ሊገደቡ የሚችሉት የታሰበውን ግብ ለማሳካት መብቶቹን ከመከልከል ውጪ ሌላ አማራጭ በማይኖርበት ጊዜ ብቻ ቢሆንም የሙስናን ወንጀል በሚመለከት ግን ሕግ አውጪው የፍርድ ቤቶችን ብቃት፣ ቅልጥፍናና ውጤታማነትን የመጨመርና ችሎቶችንና ዳኞችን የማብዛት አማራጮችን መጠቀም እየቻለና ዓቃቤ ሕግ ይጠፋሉ ተብሎ በሚገባ የሚጠረጠሩ ተከሳሾን ብቻ መርጦ በዳኞች ፊት ተከራክሮ ዋስትና ማስከልከል እንዲሁም ንብረት ማስከበር የሚችልበት አማራጭ እያለ በአዋጅ ሁሉንም ተከሳሾች ዋስትና መንፈጉ ከዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ስምምነቶችም ሆነ ከሕገ መንግሥቱ ያፈነገጠ ነው፡፡

  በሦስተኛ ደረጃ የገደቡን ተመጣጣኝነት ስንመርምር ሕግ አውጪው ከአሥር ዓመት በላይ በሚያስቀጣ ሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን በሙሉ ንፁሃንና አጥፊውን ቀላቅሎ ሁሉንም ዋስትና መከልከሉ በዜጎች ላይ በጣም ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ገደብ ነው፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የሙስና ተጠርጣሪዎች ዋስትና ተከልከለው ጉዳያቸው ለዓመታት ሲታይ ከቆየ በኋላ በነፃ ይሰናበታሉ፡፡ እነኚህ ሰዎች ነፃ ቢባሉም በእስር ያባከኑት ጊዜ ሊመለስላቸው አይችልም፡፡ የደረሰባቸው እንግልት፣ ጉስቁልናና የሞራል ውድቀት ሊመለስ አይችልም፡፡ በቤተሰቦቻቸውም ላይ የደረሰው ተመሳሳይ ጉዳትና እንግልት ሊካስ አይችልም፡፡ ስለዚህ በሙስና የተጠረጠሩት ተከሳሾች ገና ለገና ሊጠፉ ይችላሉ ብሎ የሁሉንም መብት ከመከልከል ይልቅ ሕግ አውጪው ዳኞች ተገቢ ሆኖ ካገኙት ተጠርጣሪው በዋስ ቢለቀቅም ከአገር እንዳይወጣ፣ በየቀኑ ወይም በተወሰነ ጊዜ ለፖሊስ ወይም ቀበሌ ሪፖርት እንዲያደርግ፣ ከተወሰነ ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ ርቆ እንዳይሄድ ወዘተ መከልከል የሚችሉበትን ድንጋጌ ማውጣት ሲችል ሁሉንም ተከሳሾች ዋስትናቸውን ሙሉ ለሙሉ መገደቡ ተመጣጣኝነት የጎደለው ነው፡፡ በአንዳንድ የበለፀጉ አገሮች እንደሚደረገው ቢያንስ ተከሳሹ እግር ላይ የት እንዳለና ከተፈቀደለት ኪሎ ሜትር ርቆ ሲሄድ ለፖሊስ የሚጠቁም ብራስሌት ማሰር የሚቻልበት ሕግ በማውጣት የተከሳሾችን በዋስ ነፃ ሆኖ የመንቀሳቀስ መብት ሙሉ ለሙሉ ሳይሆን በከፊል ብቻ በመገደብ የታሰበውን ሙስናን የማዳከም ግብ ማሳካት ሲቻል፣ ሕግ አውጪው ግን ከአሥር ዓመት በላይ በሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን መብት ሙሉ ለሙሉ መገደቡ ተመጣጣኝነት የሌለው ነው፡፡ ስለዚህም ሕጉ ተሽሮ በምትኩ ዳኞች ከአሥር ዓመት በላይ በሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል የተከሰሰን ሰው የሚጠፋ ወይም ማስረጃ የሚያጠፋ ለመሆኑ ተጨባጭ ግምት ካለ አመዛዝነው ዋስትና እንዲከለክሉ፣ እንዲሁም ዋስትና ሲፈቅዱ ተገቢ ሆኖ ካገኙት ተከሳሹ ከአገር እንዳይወጣ፣ ከተወሰነ ርቀት በላይ ርቆ እንዳይሄድ፣ ወይም እግሩ ላይ ያለበትን ቦታ የሚያሳውቅ ብራስሌት እንዲታሠር ገደብ ሊያስቀምጡ ይችላሉ በሚል ቢሻሻል የተሻለ ነው፡፡ ለጊዜው ግን የገደቡ ሕገ መንግሥታዊነት በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጽሕፈት ቤት በኩል እንዲታይ አቤቱታ ሊቀርብ ይገባል፡፡ እንዲሁም የፍርድ ቤቶችን ቅልጥፍናና ውጤታማነት ለመጨመር ተጨባጭ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸውን ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ ፍርድ ቤቶች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነቶች አለባቸው፡፡ አገሪቱ በሚመለከታቸው ዓለም አቀፋዊ አኅጉራዊ አካላት አማካኝነት ስምምነት ባለማክበር ብትጠየቅ ወይም ቢወሰንባት ተገቢ ስለማይሆን፣ የተጠቀሱት አካላት ተገቢውን ግዴታቸውን ቢወጡ መልካም መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይችላሉ፡፡

   

   

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...