Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  እኔ የምለዉየገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እንካ አትንካ ጨዋታ አይደለም

  የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እንካ አትንካ ጨዋታ አይደለም

  ቀን:

  በልማት ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ብዙ ቢሊዮን ብሮችን ያከሰሩ ፕሮጀክቶች ላይ ምንም ዓይነት መንጫጫት ሳይፈጠር አንድ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ስለተነደፈ በየቤቱ፣ በየመጓጓዣ ሥፍራውና በገበያ ቦታው ብዙ ሕዝብ ተንጫጫ፡፡ መንግሥት የልማት ኢኮኖሚ ስትራቴጂዎቹ አልቀውበት ወደ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እየተንደረደረ ስለሆነ ገና ወደፊት ብዙ እንንጫጫለን፡፡ በዚያን ሰሞን ግብር ጨምሮብን ተንጫጫን፡፡ ዛሬ ልማታዊ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በግብር ከፋዩ ገንዘብ በትላልቅ ሆቴሎች አትምነሽነሹ ተብለው እየተንጫጩ ነው፡፡ ሃያ አምስት ዓመታት ሙሉ ለኢኮኖሚያችን እንደ ባለድርሻ አካል ተንጫጭተን ቢሆን ኖሮ፣ የዛሬዋ ኢትዮጵያ መልክ የተለየ ይሆን ነበር፡፡

  ዛሬ ግድቦቹን በነደፈ አንድ ሰው፣ አሥር የስኳር ፋብሪካዎችን ለመትከል ባቀደ ሁለተኛ ሰው፣ ከአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መስመር ለመዘርጋት በወሰነ ሦስተኛ ሰው፣ አዲስ አበባን በኮንዶሚንየም ቤቶች ለማጥለቅለቅ ባሰበ አራተኛ ሰው፣ አርባ አራት ዩኒቨርሲቲዎችን ለመሥራት ባለመ አምስተኛ ሰው፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማስፋፋት በወጠነ ስድስተኛ ሰው ከአሥር በማይበልጡ ሰዎች ጭንቅላት የተገነባች ኢትዮጵያን ነው ይዘን ያለነው፡፡ ሌሎቻችን በደመነፍስ የምንንቀሳቀስ ነን፡፡ በጣም የሚገርመው እነዚህ ሰዎች የጠቅላይ ሚኒስትርነትና የሚኒስትርነት ባርኔጣ ሳይኖራቸው የመወሰን ሥልጣን ያላቸው ናቸው፡፡

  ግድቦቹ ዘገዩ፣ የስኳር ፋብሪካዎቹ ተንጓተቱ፣ የባቡር መስመሩ ሥራ አልጀመረም፣ ኮንዶሚንየሞቹ ለተመዘገቡት ሰዎች አልተዳረሱም፣ አርባ አራቱ ዩኒቨርሲቲዎች ሳይንሳዊ ዕውቀት የሚያሰርፁና የሚያመራምሩ ሳይሆኑ የመጠለያ ካምፕ መስለዋል፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውጤት ገና አልታወቀም፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እጅ ስለቆረጣጠመ እስኪ ደግሞ በገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እንጫወት አስብሏል፡፡

  የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አነዳደፍ መርሆች አሉት፡፡ አንዱ መርህ ከመንግሥት ወደ ሕዝብ መልዕክት ተላልፎ ሸማቹና አምራቹ በየራሳቸው ላይ በጎ ተፅዕኖ ካለው ለመጠቀም፣ አፍራሽ ተፅዕኖ ካለው ለማለዘብ የራሳቸውን ግብረ መልስና ግላዊ የፖሊሲ ዕርምጃ የሚወስዱበት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ሁለተኛው መርህ ወቅታዊነቱና አንድምታው መጠናት አለበት፡፡ ሦስተኛው መርህ ከሌሎች አማራጭ ፖሊሲዎች የተሻለ መሆኑ መመዘን አለበት፡፡

  ከእነዚህ ሦስት ነጥቦች አኳያ የምንዛሪ መጣኝ ለውጥ ፖሊሲውንና ከፖሊሲው በኋላ የተከሰቱትን ሁኔታዎች እንመልከት፡፡

  የሕዝብ ግብረ መልስ

  መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ለውጡን በመንተራስ ዋጋ በሚያንሩ ላይ ዕርምጃ እወስዳለሁ እያለ ነው፡፡ በንግድ ሚኒስትሩ የሚመራ ግብረ ኃይልም አቋቁሟል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ፖሊሲው ከመነደፉ በፊት አንድምታው ያልታወቀ መሆኑን ነው፡፡

  ምንዛሪ ለውጡ በዋጋ ንረት ላይ የሚያስከትለው ውጤት ትንሽ ነው፣ ትልቅ ነው የሚሉ ክርክሮችም ነበሩ፡፡ አንዳንድ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም ዋጋ ለመጨመር ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለም እያሉ ነው፡፡ የዛሬውን ማወቅ የነገውን ገምቶም ተስፋ ማድረግ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ነው፡፡ በተገበያዮች አላዋቂነት ወይም በመንግሥት ጣልቃ ገብነት የገበያ ጉድለት ይፈጠራል እንጂ፣ በኢኮኖሚ ዓለም ኢኮኖሚያዊ ያልሆነ ምክንያት የለም፡፡ ጉልበት መጠቀምም አይቻልም፡፡

  የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የሕዝብን እንቅስቃሴ በፖሊሲው ግብ መሠረት ለመግራት እንጂ ሙዚየም የሚቀመጥ ሰነድ ስላልሆነ ለአምራቹም፣ ለሸማቹም፣ ለነጋዴውም የግብረ መልስ ፖሊሲ ዕርምጃ የሚወስዱበትን ጊዜ ዓይነትና መጠን መንግሥት ሊወስንላቸውና ሊቆጣጠራቸው አይችልም፣ አቅሙም አይኖረውም፡፡

  ደንበኛ ንጉሥ ነው የተባለለት ሸማች የፖሊሲውን አንድምታ ለማለዘብና ጉዳቱን ለመቀነስ ቁጥብ ሸመታ ከማድረግ ይልቅ ያልቅብኛል ብሎ ከተሻማና ከተሰገሰገበት፣ አንዳንዱም በወፍ ዘራሽ ልማታዊ ኢኮኖሚ ያገኘውን ያልተለፋበት የአጋጣሚ ገቢ እንደ ልቡ ከመነዛዘረ ለነጋዴው የብዝበዛ በር የሚከፍተው ራሱ ነው፡፡ እንደ ሸማችም እንደ አምራችም የገበያ ኢኮኖሚ ሕግጋትን አለማወቅ ጉዳቱ እዚህ ላይ ነው፡፡ 

  ወቅታዊነት

  ኢሕአዴግ ከገባ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የብር ከዶላር ጋር በተለጣፊነት (Pegged) መመነዛዘሪያ መጣኝ ከነበረበት አንድ ዶላር ለሁለት ብር ወደ አንድ ለሰባት በሕግ ተወስኖ፣ ከዓመታት በኋላም እንደገና ተከልሷል፡፡ ይኸው አሁንም በድጋሚ ተከለሰ፡፡ በእነዚህ ዓመታት መሀልም የየአገሮቹን የዋጋ ንረት ተከትሎ በሸቀጦች የገበያ ዋጋ ውጣ ውረድ ምክንያት መመነዛዘሪያ መጣኞቹ በአዝጋሚ ለውጥ በመንፏቀቅ በአንድ ዶላር ሦስት ብር ደርሶ ነበር፡፡ ይህ ሊሆን የቻለውም የመንግሥት ምንዛሪ መጣኝ አወሳሰን ፖሊሲ ከዋጋ ንረት ጋር ቀስ በቀስ እንዲዋዥቅ፣ ተንሳፋፊ የምንዛሪ መጣኝ ሥርዓት (Floating Exchange Rate Regime) እንዲሆን ተደርጎ ስለተቃኘ ነው፡፡

  በጣም ዝቅተኛ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጭ ብቻ ላላት አገር ከዚህ የተሻለ አማራጭም የለም፡፡

  ሃያ ብር በአንድ የአሜሪካን ዶላር ይመነዘር ከነበረና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የስምንት በመቶ የሸቀጦች ዋጋ ንረት ተከስቶ በአሜሪካ ግን የሦስት በመቶ ብቻ የሸቀጦች ዋጋ ንረት ቢከሰት፣ ከስምንት ላይ ሦስት ተቀናንሶ ከዶላር ዋጋ አንፃር የብር ዋጋ ሸቀጦችን በመግዛት አቅሙ በአምስት በመቶ ዝቅ ስለሚል፣ በዋጋ ንረት ንፅፅር የተለካ የዶላርና የብር መመነዛዘሪያ መጣኝ አንድ ዶላር በሃያ አንድ ብር ይሆናል፡፡

  በዚህም ምክንያት አንድ ዶላር የሚያወጣ የአሜሪካ ሸቀጥ ወደ ኢትዮጵያ ለሚያስገባ አስመጪ ሃያ አንድ ብር በመክፈል ስለሚወደድ፣ የአሜሪካ ምርት በኢትዮጵያ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን ያቅተዋል፡፡ አንድ ዶላር የሚያወጣ ሸቀጥ ወደ አሜሪካ የሚልክ ኤክስፖርተር ሃያ አንድ ብር በማግኘት በብር የተለካ ገቢው ስለሚጨምር በርከት አድርጎ ለመላክ ይበረታታል፡፡ በሌላ አነጋገር የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ለአሜሪካኖች በመርከስ የኢትዮጵያ ምርት በአሜሪካ ገበያ ተወዳዳሪ ሲሆን፣ የአሜሪካ ኢምፖርት ለኢትዮጵያውያን በመወደድ በኢትዮጵያ ገበያ የአሜሪካ ምርት ተወዳዳሪ አለመሆን ነው፡፡

  ሆኖም ግን የብር ዋጋ መርከስ በኢምፖርትና በኤክስፖርት ሸቀጦች ዋጋ ላይ ውጤት ይኑረው እንጂ የመርከሱ ምክንያት ሰው ስለፈለገው ብቻ የሆነ ሳይሆን በራሱ ምክንያት የሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሸቀጦች ዋጋ ንረት ከአሜሪካም ሆነ ከሌሎች ከኢትዮጵያ ጋር ተነጋጋጅ አገሮች ሸቀጦች ዋጋ ንረት የበለጠ ቢሆንም፣ የብር ምንዛሪው ግን በራሱ የመንፏቀቅ ለውጥ ከሸቀጥ ዋጋ ንረት ልዩነቱ ጋር ተመጣጣኝ አልነበረም ነበር ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የሸቀጥ ገበያዎችና የምንዛሪ ገበያዎች የየራሳቸው ልዩ ባህሪያት ስላሏቸው ነው፡፡

  ለመሆኑ ልማታዊ አስመጪና ላኪዎች ዓለም በእንደዚህ ዓይነት የገበያ ኢኮኖሚ ገመድ የተሳሰረች መሆኗን ምን ያህል ያውቃሉ? ዘወትር ሲናገሩ የምንሰማው ቡና ቆልተን ብንሸጥ ኖሮ ሲሉ ነው፣ እንግዲህ በራሳቸው ይወጡት እንጂ እኛ ብረት ምጣድ ገዝተን አንስጣቸው ነገር፡፡

  ለማንኛውም ከዚህ በላይ የቀረበው የምንዛሪ መጣኝ ለውጥ ትንታኔ የሚያመለክተው የዋጋ ንረት ለምንዛሪ መጣኝ ለውጥ ምክንያትም ውጤትም  ሊሆን እንደሚችል፣ የምንዛሪ መጣኝ ለውጥም ለዋጋ ንረት ምክንያትም ውጤትም ሊሆን መቻሉን ነው፡፡ ስለዚህም ወቅቱን ያልጠበቀ ፖሊሲ የቀውስ መባባስን የብሔራዊ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትን ይፈጥራል፡፡

  የሸቀጦች አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት ሕዝቡን እያማረረ ባለበት ጊዜ የሚያባብስ የምንዛሪ ለውጥ ፖሊሲ መንደፉ ወቅቱን ያልጠበቀ ነው ያሰኛል፡፡ የዋጋ ንረትን በተመለከተ ምን ጊዜም ቢሆን የመንግሥት ፖሊሲ መሆን ያለበት ተቃራኒ ዕርምጃ በመውሰድ አለዛቢ ልጓም እንጂ፣ የሚራመደው እንዲሮጥ የሚሮጠው እንዲጋልብ ቆስቋሽ መሆን የለበትም፡፡

  ከሌሎች አማራጭ ፖሊሲዎች የተሻለ መሆኑ

  ባለፈው ሰሞን በንግድ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት ልማታዊ ኤክስፖርተሮች ሰፋ ያለ ምክክር አድርገው ነበር፡፡ ዋናው ርዕሳቸውም የኤክስፖርት መጠንን እንዴት ማሳደግ እንደሚችሉ ነበር፡፡ ከእኛ ጉሮሮ ነጥቀው የውጭ ሸማቾችን ለመቀለብ እንደሆነ ሳይገነዘቡ ይቀራሉ ብዬ አልገምትም፡፡

  ኢትዮጵያ ዛሬ ወደ ውጭ የምትልካቸው የግብርና ምርቶች ቡና፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህል፣ የቁም እንስሳት፣ ሥጋ. . . በንጉሡ ዘመንም በደርግ ዘመንም ስትልካቸው የነበሩ ናቸው፡፡ በጣም ግራ የሚያጋባው ነገር ደርግ በመውደቂያው በ1980ዎቹ የግብርና ምርት ከአርባና ከሃምሳ ሚሊዮን ኩንታል በማይበልጥበት ጊዜ እንኳ፣ እነዚህ ምርቶች ወደ ውጭ ከመላካቸው በፊት እኛ አንድ ኪሎ ቡና በሦስት ብር ዋጋ፣ ጥራጥሬውና የቅባት እህሉ በኩንታል ከመቶ ብር ባነሰ ዋጋ፣ ሥጋው በኪሎ ከአሥር ብር ባልበለጠ ዋጋ ገዝተን ከእኛ የቀለብ ፍጆታ የተረፈው ነበር ወደ ውጭ የሚላከው፡፡

  ዛሬ አራት መቶና አምስት መቶ ሚሊዮን ኩንታል የግብርና ምርት እህል ተመረተ እየተባለ ከውጭ ሸማቾች የተረፈውን አንድ ኪሎ ግራም ቡና በመቶ ሃምሳ ብር፣ አንድ ኩንታል ጥራጥሬና የቅባት እህል በሦስት ሺሕ ብር፣ አንድ ኪሎ ሥጋ በሁለት መቶ ብር የውጭ ሸማቾቹ በወሰኑልን ዋጋ ወይም ኤክስፖርተሩ የውጭ ገበያ ካጣ በኋላ፣ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርበውን እየገዛን ነው የምንጠቀመው፡፡ በምንዛሪ ለውጡም ከ23 ብር ወደ 27 ብር አድጎብናል፡፡

  እንደዚህም ሆኖ ኤክስፖርታችን ከጎረቤት አገሮች ጋር ሲነፃፀር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለንፅፅር ያህል የሚከተለውን መረጃ እንመልከት፡፡

  እ.ኤ.አ. በ2015 የአገሮች ኤክሰፖርት ገቢ

     አገር

  የሕዝብ ብዛት በሚሊዮን

  ኤክስፖርት በቢሊዮን ዶላር

  ነፍስ ወከፍ ኤክስፖርት በዶላር

  ኢትዮጵያ

  90

  3.8

  42

  ኬንያ

  45

  5.7

  127

  ግብፅ

  89

  20.9

  235

  ሱዳን

  40

  4.4

  110

  ኡጋንዳ

  38

  2.8

  74

  ታንዛንያ

  51

  5.4

  106

  ዛምቢያ

  14

  6.3

  450

  ናይጄሪያ

  182

  50.7

  279

  ደቡብ አፍሪካ

  55

  85.1

  1547

  ምንጭ፡- ከኢንተርኔት መረጃ የተወሰደ

  በምንዛሪ መጣኝ ለውጥ ፖሊሲው መንግሥት የፈለገው ኤክስፖርተሩ በአንድ ዶላር ሽያጩ ሃያ ሦስት ብር ከማግኘት ይልቅ፣ ሃያ ሰባት ብር አግኝቶ እንዲበረታታና ብዙ ምርት ወደ ውጭ እንዲልክ ነው፡፡

  ሆኖም ግን ነጋዴ ገዢም ሻጭም ስለሆነ የኤክስፖርተሩ ትርፍ ሊጨምር የሚችለው ከሽያጭ ብቻ ሳይሆን ከግዢ ሊሆንም ይችላል፡፡ ከሽያጭ ሊገኝ የታሰበ ትርፍ በአገር ውስጥ የዋጋ ንረት እንደፈጠረ እያየን ስለሆነ፣ ኤክስፖርተሩ ከሽያጭ ሳይሆን ከግዢ ትርፍ እንዲያገኝ የአገር ውስጥ ጥሬ ገንዘብ አቅርቦትን የመገደብና ገቢን የመቀነስ ሌላ አማራጭ ፖሊሲ መጠቀምም ይቻል ነበር፡፡ 

  በውጭ ምንዛሪ ገበያ የብር ዋጋ ሳይረክስ የሕዝቡን ገቢና የመሸመት አቅም ገድቦ የዋጋ ንረትን በመግታትም ኤክስፖርተሩ ከግዥ ትርፍ እንዲያገኝ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን የአክሳሪ ፕሮጀክቶችን ወጪ ለመሸፈን ብዙ ገንዘብ ለሚያስፈልገው መንግሥት ይህ የፖሊሲ አማራጭ አልታየም፡፡

  እዚህ ላይ አስተዋይ አንባቢያን የገቢያችን መጠንና የመግዛት አቅማችን አንሶ ገቢያቸውና የመግዛት አቅማቸው ከእኛ ወደ ሚበልጥ ጎረቤቶቻችን ምርቱም በኮንትሮባንድ እየነጎደ ወጣቱም በኬላዎች አቋርጦ እየፈለሰ እንዴት የገቢ መጠን ይቀንስ ይባላል ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፡፡

  ምርጫው ከሁለት አንድ ነው ወይስ እንደ እስከ ዛሬው በምርታማነት ያልተለካ የውሸት ገቢን አሳድጎ ቀውስ ውስጥ መግባት? ወይ ደግሞ ገቢ ከምርታማነት እንዳይበልጥ ቀንሶ ትክክለኛ ገቢን በማግኘት ዋጋ እንዳይንር ማድረግ ናቸው፡፡ መራጩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡

  ኢኮኖሚክስ ስለገቢ መጠን የሚነግረን አንድ ሀቅ አለ፡፡ ይኸውም ገቢ ከምርታማነት ከበለጠ ላይ ላዩን አገር እያደገች ያለች ቢመስልም ውስጥ ውስጡን ግን እየከሰረች ነው፡፡ በወር ውስጥ የአምስት ሺሕ ብር ብቻ ምርታማ ሥራ እየሠራ መቶ ሺሕ ብር ገቢ የሚያገኝ ሰው ወይም የመቶ ሺሕ ብር ፍጆታ የሚጠቀም ሰው፣ አገሩን የዘጠና አምስት ሺሕ ብር ኪሳራ ውስጥ እየከተተ ነው፡፡

  በአሜሪካ እ.ኤ.አ. የ2008 የገንዘብ ቀውስ ተከትሎ የባንክ ሰዎች ቋሚና የቦነስ ገቢ ከምርታማነታቸው በላይ በጣም አድጓል በማለት አሜሪካኖች፣ ‹እኛ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ ድሆች› ብለው በኒውዮርክ የገንዘብ ገበያ አካባቢዎች ሠልፍ ወጥተው ነበር፡፡ የእኛ አገር የባንክ ሰዎች የሚያገኙት ገቢ ከምርታማነታቸው እኩል ይሆን እንዴ? በሌሎች ዘርፎች ያሉትስ? ‹አንበሶቹ› እየተባሉ በቴሌቪዥን ሚሊዮችን ሲመነዛዝሩ የምናያቸውስ? ከፍተኛ ገቢ የሚያገኘው ሰው ምርታማነትና ዝቅተኛ ገቢ የሚያገኘው ሰው ምርታማነትስ እንዴት ይነፃፀራል? ለጥቂት ሰዓታት የቦርድ ስብሰባ የሚገኝ ገቢ ዓመታት ከሚሠራ ተመራማሪ ገቢ ሲበልጥ ማንኛው ነው ምርታማው  ሰው?

  የአገሪቱ የማደግ ተስፋ የሚለካው ከመቶ ሚሊዮን ዜጎች ምን ያህሉ ምርታማ እየሆኑ ነው? ውስጣቸው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየሰረፀ ነው? ከዓለም አቀፍ መረጃ ጋር እየተዋሀዱ ነው? ምርምር እያደረጉ ነው? በዕውቀት መገበያየት የሚችሉ ኢኮኖሚያዊ ሰዎች እየሆኑ ነው? ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እየመሩ ነው? ስለማኅበረሰቡ ያላቸው ንቃተ ህሊና እየጎለበተ ነው? በሚሉት መለኪያዎች ነው፡፡

  ለሰው ምርታማነት ቅድመ ሁኔታዎች ከሆኑት በከተሞች ሰዋዊ ካፒታል የጀበና ቡና በማፍላት ደረጃ ወርዷል፣ በገጠር ቁሳዊ ቋሚ ካፒታል የሣር ክዳን ቤትን በቆርቆሮ ክዳን ከመተካት አላለፈም፡፡

  የተወሰኑ የከተማ ሰዎች በአገር ቤትም በውጭ አገርም ተሯሩጠው ሰደው አሳደው ባገኙት ጊዜያዊ ገቢ ሉካንዳ ቤቱን ስለሞሉ፣ ቢራ ቤቱን ስላጨናነቁ፣ መኪና ስለነዱ፣ ስለዘፈኑ፣ ስለዘለሉ፣ የውጭ አገር ሸቀጦች ተጠቃሚ ስለሆኑ፣ የማይሠሩበትን ዲፕሎማና ዲግሪ ስለያዙ፣ የበርካታ ከተማ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ስለሆኑ፣ የዋልጌ መዋያ ሥፍራዎች በመብዛት በከተሞች አካባቢ በሚታየው የፍጆታ ወጪ ማደግ፣. . . የዛሬና የወደፊት የአገር ዕድገት አይለካም፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...