Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የትግራይ ክልል ለወጣቶች ከተመደበለት 562 ሚሊዮን ብር ውስጥ 105 ሚሊዮን ብር ብቻ መጠቀሙን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፌዴራል መንግሥት ያለውን የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የአሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ በጅቶ ለክልሎች እያከፋፈለ ቢሆንም፣ ከዚህ ውስጥ የትግራይ ክልል 562 ሚሊዮን ብር እንደተመደበለት ተገልጿል፡፡ ከዚህ ውስጥ ክልሉ እስካሁን ድረስ 105 ሚሊዮን ብር ብቻ መጠቀሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የትግራይ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረሚካኤል መለስ ዓርብ ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የተበጀተው ገንዘብ የሚለቀቀው በሁለት ዓመት በመሆኑ ባለፈው ዓመት 205 ሚሊዮን ብር የፌዴራሉ መንግሥት እንዳላከና መጠቀም የተቻለው 105 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹እኛ ባለፈው ዓመት ይላክልናል ብለን ያቀድነው 265 ሚሊዮን ብር ቢሆንም፣ 205 ሚሊዮን ብር ተለቆልናል፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ለወጣቶች የተከፋፈለው 105 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው ተብሏል፡፡

 የክልሉ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለወጣቶች የሥራ ፈጠራ የሰጡት ብድርና የፌዴራሉ መንግሥት የለቀቀው ገንዘብ ተደምሮ በጠቅላላው፣ ባለፈው ዓመት ለ63,475 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፤›› ብለዋል፡፡

ወጣቶች በፌዴራል መንግሥት የተመደበውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ሊጠቀሙ ያልቻሉበት  ምክንያት ሕጉ የተደራጁ ወጣቶች በአንድ የሥራ መስክ ብቻ እንዲሰማሩ ስለሚያስገድድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በኅብረት ተደራጅተው የሚመጡ ወጣቶች የሚያቀርቡት የቢዝነስ ዕቅድ የተለያየ በመሆኑ፣ ብድሩን ለመስጠት ትልቅ እንቅፋት እንደሆነም አቶ ገብረ ሚካኤል ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች ከፌዴራሉ በጀት ይልቅ የደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በሚሰጠው የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱን ሲያብራሩም፣ የደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ የብድር አሰጣጥ ሕግ ወጣቶች ከተደራጁና ማስያዣ ካላቸው የተለያየ ዕቅድ ቢኖራቸውም ብድር ስለሚፈቅድ በቀላሉ ብድር እንደሚለቀቅላቸው አብራርተዋል፡፡ የፌዴራሉ የወጣቶች ፈንድ ጨምሮ ከክልሉ በተመደበው የሥራ ዕድል ፈጠራ በጀት 63,475 ወጣቶች ባለፈው ዓመት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተገልጿል፡፡

ባለፈው ሳምንት የክልሉ ምክር ቤት ባደረገው ጉባዔ በ2010 ዓ.ም. በጀት ዕቅድ ላይ ውይይት መደረጉ ተጠቁሟል፡፡ በዚህ መሠረት በ2010 ዓ.ም. የክልሉን አጠቃላይ ኢኮኖሚ በ11.3 በመቶ ለማሳደግ መታቀዱን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ የእርሻው ዘርፍ 36.7 በመቶ፣ ኢንዱስትሪው 24.4 በመቶ፣ የአገልግሎት ዘርፉ 38.9 በመቶና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ 24.4 በመቶ የዕድገት ድርሻ እንዲኖራቸው መታቀዱንም አስረድተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የተያዘውን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ድርሻ ወደ 6.5 በመቶ ከፍ የሚልበት ግብ መቀመጡንም አስታውቀዋል፡፡

‹‹ዕቅዱን ለማሳካት በማክሮ ኢኮኖሚው ዕድገት ደረጃ በወጪ ንግድ ላይ በማተኮር የውጭ ምንዛሪ በብዛት እንዲገኝ የእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ ትልቁን ድርሻ እንዲይዝ ያደርጋል፤›› ብለዋል፡፡ የቁጠባ መጠንንም በ28.5 በመቶ ለማሳደግና ብክነትን ዝቅ ማድረግ ከታቃዱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዕቅዶች ውስጥ እንደሚመደቡ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች